የመጽሐፈ መክብብ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የማያምኑ ሰዎች በሕይወት ውስጥ ካላቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ጥቂቶቹ ምንድን ናቸው? እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከፍተኛ ጥረት የሚያደርገው ምን ለማግኘት ነው? እርካታ እንደሚሰጠው አድርጎ የሚገምተው ምንድን ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖችም በሕይወት ውስጥ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ነገር መልካም ነው ወይስ ክፉ? መልስህን አብራራ።

ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት የሌላቸው ወይም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የማይስማማ ዓይነት ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች፥ በሰው ሕይወት ውስጥ እጅግ ከፍተኛውና የላቀው ነገር ምን ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? ይህን በሚመለከት ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ሀብት፥ ዝና፣ ሥልጣን፥ ትምህርት፡ ምቹ ኑሮ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በራሳቸው አንዳችም ክፋት ባይኖርባቸውም እንኳ ለሰው ሕይወት እርካታን ለማስገኘት የሚችሉ ግን አይደሉም። የሕይወት ዓላማ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም። የሚያሳዝነው ግን ልክ እንደ ዓለም ሰዎች የሚያስቡ በርካታ ክርስቲያኖች መኖራቸው ነው። ትምህርት ብቻ ካላቸው ደስተኞች የሚሆኑ ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ብዙ ገንዘብ ኖሯቸው:- ቴሌቪዥን፥ ቪዲዮ፥ ቴፕና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ባሉበት ትልቅ ዘመናዊ ቤት የተመቻቸ ሕይወት ለመኖር ያልማሉ። የሌሎች ግብ ደግሞ የአንድ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን መሪ መሆን ነው። በዚህ የሥልጣን ስፍራ በኩል ክብርና ዝናን ለማግኘት ይፈልጋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህን የተለያዩ ነገሮች ለማግኘት የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) እነዚህን ነገሮች መመኘት በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው?

ይህ አዲስ ችግር አይደለም። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ አይሁድም ተመሳሳይ ችግር ነበረባቸው። በዓለም አመለካከት ሀብትን፥ ጥበብን፥ ዝናን፥ ክብርን፥ ወዘተ. ይፈልጉ ነበር። መጽሐፈ መክብብ የሚያሳየው፡ አንድ ሰው እግዚአብሔርን መፈለግ ተቀዳሚ ተግባሩ ካላደረገ በስተቀር እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከንቱ መሆናቸውን ነው። ሕይወት ዋጋ የሚኖረውና እግዚአብሔር በሰጠው ነገር ሁሉ ሰው ደስተኛ ሊሆን የሚችለው፥ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት ለመኖር በሚፈልግበትና በሚሞክርበት ጊዜ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ማቴዎስ 6፡25-34 አንብብ። እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ማስቀደምንና ለዚህ ዓለም ነገሮች አለመኖርን በተመለከት ረገድ እነዚህ ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል?

እግዚአብሔር የለም የምንል ከሐድያን (ኤቲስቶች) ወይም እግዚአብሔር ቢኖርም እንኳ ልናውቀው አንችልም የምንል አግኖስቲኮች ወይም እግዚአብሔር እንደሌለ አድርገን የምንኖር ተግባራዊ አግኖስቲኮች ብንሆን ኖሮ፥ ሕይወት ምን ትርጒም ይሰጠን ነበር? ሰዎች ደስታን ይሰጣሉ የሚሉአቸው እንደ ሀብት፥ ዝና፥ ሥልጣንና ትምህርት ያሉ ነገሮች በእርግጥ ደስታን ይሰጣሉን? መጽሐፈ መክብብ እግዚአብሔር እንደሌለ ለሚቆጠሩ ሰዎች፥ ሕይወታቸው ትርጕም የሌለው እንደሆነ ለማረጋገጥ የተጻፈ ነው። ያለእግዚአብሔር ሰው ባዶና ሕይወቱም ትርጒም የሌለው «ከንቱ» ነው። ብዙ ጊዜ ክርስቲያን ወጣቶች የማያምኑ ሰዎች የሕይወት አኗኗርን ይመኛሉ። የማያምኑ ሰዎች ደስተኛ ሕይወት የሚኖሩ ይመስላሉ። ሀብታምና ነፃ ሆነው፥ ለሕይወት ደስታን የሚሰጥ ብዙ ነገር ያላቸው ይመስላሉ። ሰይጣን አኗኗራቸውን ታላቅ ደስታና ሐሤት ያለበት አስመስሎ ያቀርባል። መጽሐፈ መክብብ ይህ አስተሳሰብ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ይናገራል። ሰው እግዚአብሔርን ለማክበር በመሻትና እንደሚፈርድበት ተገንዝቦ ካልኖረ በስተቀር፥ የልብ ሰላምና እውነተኛ የሕይወት ትርጕም ሊያገኝ አይችልም።

መጽሐፈ መክብብ ለመተርጐም እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዱ ነው። ከዚህም የተነሣ ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፈ መክብብን አያነቡም፤ ሊረዱትም አይሞክሩም። የመጽሐፈ መክብብን ዓላማ እስካልተረዳን ድረስ መጽሐፉን መረዳት አስቸጋሪ ነው። የመጽሐፈ መክብብን ዓላማ ከተረዳን ግን ያለንን ውስጣዊ አሳብ ለመመርመር ከሁሉም የላቀ መጽሐፍ ነው። የዚህን ዓለም ነገሮች ከንቱነት እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን ከመከተል ጋር በማወዳደር ራሳችንን ለመመርመር ይረዳናል። 

የመጽሐፈ መክብብ ስያሜ 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) «መክብብ» ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንድን የኦርተዶክስ ቄስ ጠይቅ። ለ) መጽሐፈ መክብብን በተሻለ ሁኔታ ሊገልጥ የሚችል ሌላ የአማርኛ ቃል ምንድን ነው?

በአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ መጽሐፍ «የኮህሌዝ» ቃላት ወይም «ኮህሉዝ» በመባል ይታወቃል። ይህ ቃል የተገኘው ከመጽሐፈ መክብብ 1፡1 ሲሆን፥ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ «ሰባኪ» ተብሉ ተተርጕሟል። ኮህሌዝ የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን፥ ትርጕሙም አንድን ጉባኤ የሚሰበስብ ማለት ስለሆነ፥ ጉባኤን የሚያስተምር ሊባል ይችላል። ይህ ቃል የጸሐፊው ስም ወይም በጉባኤ ውስጥ እንደ አስተማሪ ሆኖ የማገልገል ተግባሩ ሊሆን ይችላል። ጸሐፊው ጥበበኛ ሰው እንደመሆኑ መጠን ሰዎችን በአንድነት ለመሰብሰብና ጥበብን ለማስተማር ኃላፊነት የነበረው ሰው ሊሆን ይችላል። «ኤክለሲያስተስ» የሚለው የእንግሊዝኛው ርእስ የተገኘው ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን፥ ትርጕሙም «ሰባኪ» ማለት ነው። መክብብ የሚለው የግዕዙ ቃል ትርጕምም «ሰባኪ ወይም አስተማሪ» ማለት ነው። 

የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ 

የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊን ማንነት በሚመለከት ምሁራን ይከራከራሉ። ከመጽሐፉ በግልጽ እንደምንመለከተው ጸሐፊው ታላቅ ጥበብ ያለው ሆኖ፥ ነገር ግን የአይሁድ ሃይማኖታዊያን መሪዎች የሚሰጡትን ቀላል መልስ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበረ ሰው ነበር። በክፍሉ ውስጥ «የዳዊት ልጅ» እንደነበረ የሚናገር ሐረግ እናገኛለን። ይህም በቀጥታ የዳዊት ልጅ ወይም የዳዊት ዘር ነበር ማለት ሊሆን ይችላል። በኢየሩሳሌም የኖረ ንጉሥም ነበር። ስለ መጽሐፉ ጸሐፊ ሦስት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡-

1. መጽሐፉ በተለያዩ ጸሐፊዎች የተዘጋጀ ነው የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አሉ። ይህ የማይመስልና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትነት የሚያምኑ ብዙ ምሁራን የማይቀበሉት አሳብ ነው።

2. አንዳንዶች ደግሞ መጽሐፉን የጻፈው ሰሎሞን ነው ብለው ያምናሉ። ይህ በአይሁድና በክርስቲያኖች ሁሉ ዘንድ የሚታመንበት ታሪካዊ አመለካከት ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የምናያቸውን መመዘኛዎች ሁሉ በተሻለ ሁኔታ የሚያሟላ ሰሎሞን ብቻ ነው ይላሉ። ሰለሞን የዳዊት ልጅና የእስራኤል ንጉሥ ነበር፤ ደግሞም ጥበበኛ ነበረ። ልቡ በባዕዳን ሴቶች ከእግዚአብሔር ርቆ የኮበለለበትና ዓለማዊ ጥበቡ በርካታ የሆኑ የሕይወት መሠረታዊ ነገሮችን እንዲጠይቅ ያደረገው ሰው ነበር። ይህን መጽሐፍ በሕይወቱ ፍጻሜ ለሕይወቱ ትርጒም በመሻት ያሳለፋቸውን ማብቂያ የሌላቸውን ነገሮችና የተጓዘባቸውን መንገዶች ወደኋላ ዞሮ በመመልከት የጻፈው ሊሆን ይችላል። ሰሎሞን በሕይወቱ እውነተኛ ትርጕም የሚኖረው በእግዚአብሔር በማመንና ለእርሱም በመታዘዝ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።

3. አንዳንድ ምሁራን መጽሐፈ መክብብ ሁለት ምንጮች ያሉት ይመስላቸዋል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት አሳቦችና የጥበብ ንግግሮች አብዛኛዎቹ የሰሎሞን እንደሆኑ ጥርጥር የለውም ይላሉ፤ ነገር ግን ከሰሎሞን በኋላ ብዙ ዓመታት ቆይቶ ይኖር የነበረ አንድ ሌላ ሰው፥ ሰሎሞን ለሌሉች ያስተላለፈውን ጥበብ በመጠቀም፥ መጽሐፉን ጽፎት ይሆናል። ጸሐፊው «ኮህሌዝ» የሚለውን ቃል የተጠቀመው በሦስተኛ መደብ ነው፤ ይህም ማለት ከሰባኪው ወይም ከአስተማሪው በቀጥታ የተጠቀሰ ሳይሆን፥ ሌላ ሰው ስለ ሰባኪው የተናገረው ነው። ሰሎሞን መጽሐፉን ጽፎ ቢሆን ኖሮ የሚጠቀመው የራሱን ስም እንጂ ኮህሌዝ የሚለውን ቃል አልነበረም በማለት የማሳመኛ አሳብ ያቀርባሉ። በተጨማሪ መጽሐፈ መክብብ ከሰሎሞን በኋላ የተጻፉትን ሌሎች መጻሕፍት የሚመስል ነው። የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ይዘትም ከሰሎሞን በኋላ የነበረውን ጊዜ የሚያመለክት ነው በማለት ያረጋግጣሉ። እንደ ሌሉች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ አይታወቅም ማለቱ የተሻለ ነው፤ ነገር ግን የሰሎሞንን ጥበብ የሚያንጸባርቅ ነው። መጽሐፉ አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን ከእግዚአብሔር ተለይቶ የኖረና ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ትርጒም የለሽ መሆኑን የተገነዘበ አዛውንት ሁኔታን የሚያንጸባርቅ ነው። 

መጽሐፈ መክበብ የተጻፈበት ዘመን 

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን እንደሆነ ስለማናውቅ የተጻፈበትንም ጊዜ አረጋግጠን መናገር አንችልም። አንዳንዶች ጊዜው ከ400-300 ዓ.ዓ. ነው ቢሉም፥ መጽሐፉ የተጻፈው ቀደም ብሎ ሳይሆን አይቀርም። ጸሐፊው ሰሎሞን ቢሆን ኖሮ፥ የተጻፈው በ940 ዓ.ዓ. ገደማ ይሆን ነበር። ከሰሎሞን በኋላ ይኖር በነበረ ሌላ ጸሐፊ ተጽፎ ቢሆን ኖሮ ደግሞ፥ ጊዜው ከ900-800 ዓ.ዓ. ይሆን ነበር። 

የመጽሐፈ መክብብ አስተዋጽኦ 

1. መግቢያ፡- ከእግዚአብሔር ተለይቶ በምድር ላይ መኖር ትርጕም የለውም(1፡11)።

2. በምድራዊ ሕይወት ጊዜያዊ ነገሮችን መመዘን (1፡12-3፡22)፡-

ሀ. የዓለም ጥበብ ከንቱ ነው (1፡12-28)፤ 

ለ. ምቾት ከንቱ ነው (2፡1-11)፣ 

ሐ. የዓለም ጥበብ ከንቱ ነው(2፡12-23)፤ 

መ. የእግዚአብሔር ጥበብና የእግዚአብሔርን ዓላማ መከተል ለሕይወት ትርጕም ይሰጣል (2፡24-3፡15)፤

ሠ. ሰው ላደረገው ነገር በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ መሆኑን ማስታወስ አለበት (3፡16-22)። 

3. የሰውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መመዘን (4፡1-8፡8)፡-

ሀ. የድህነትና የጭቆና ከንቱነት (4፡1-16)፤

ለ. ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ዋጋ አለው (5፡1-7)

ሐ. የሀብት ከንቱነት (5፡8-17)፤ 

መ. ሰው በእግዚአብሔር ደስ መሰኘት ሲጀምር ለሕይወቱ ትርጉም ያገኛል (5፡18-20)፤ 

ሠ. የሀብት ከንቱነት (6፡1-12)፤ 

ረ. ከእግዚአብሔር የሆነ ጥበብ ወደ ሚዛናዊ ሕይወት ይመራል (7፡1-8፡8)።

4. ዓለማዊ ጥበብን መመዘን (8፡9-12፡7)፡-

ሀ. ዓለማዊ ጥበብ በምድር ላይ በሚታዩ ነገሮች የተወሰነ ነው (8፡9-17)፤ 

ለ. ሰው ሁሉ ሟች ስለሆነ አሁን በሕይወት ሳለ ደስ ሊለው ይገባል (9፡1-12)፤ 

ሐ. በእግዚአብሔር ጥበብ መኖር ለሕይወት ጥቅምን ያስገኛል (9፡13-10፡20)፤

መ. ለወጣት የተሰጠ ምክር (11፡1-12፡7)። 

5. ማጠቃለያ፡- ሕይወት ትርጒም የሚኖረው እግዚአብሔርን ስንፈራና ስንታዘዘው ነው (12፡8-14)።

ማስታወሻ፡- መጽሐፈ መክብብን በአስተዋጽኦ ለመከፋፈል የሚያመች መጽሐፍ አይደለም። ከላይ የተመለከትነው አስተዋጽኦ መክብብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን አብዛኛዎቹን ዐበይት ትምህርቶች ለማጠቃለል የሚሞክር ብቻ ነው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የመጽሐፈ መክብብ መግቢያ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: