Site icon

መክብብ 7-12

በሕይወት ውስጥ ሌሎች የሚሰጡንን ቀላል መልሶች ከመቀበል ይልቅ አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ማሰብ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። መጽሐፈ መክብብ አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ያነሣል። ጸሐፊው የሚያስተምረውን ነገር ለመረዳት በጥንቃቄ የተሞላ ጥናት ይጠይቃል። ግልጽ መልሶች ስለሌላቸው ጉዳዮች በጥልቀት ለማሰብ ፈቃደኞች ካልሆንን በስተቀር እምነታችንና መረዳታችን ሁል ጊዜ የላላ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች ቀላል መልሶች የሚሰጡባቸውን፥ በጣም የተወሳሰቡና በጥልቀት ማሰብ የሚጠይቁ ጉዳዮችን ዘርዝር። ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ በመመራትና በጥንቃቄ በማሰብ፥ የተወሳሰቡ ጉዳዮችን በመቀበልና ጥሩ መልሶችን በመስጠት ችሎታቸው የታወቁትን ኢትዮጵያውያን ጥቀስ። ሐ) እንደ መጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ በጥልቀት ለማሰብ የሚፈልጉ ሰዎች እጅግ ጥቂት የሆኑት ለምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ መክብብ 7-12 አንብብ። ሀ) ጸሐፊው «ከንቱ» የሚላቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) ጸሐፊው እነዚህ ነገሮች ከንቱዎች እንደሆኑ የሚናገረው ለምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ፥ ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረግ ግንኙነት ለሕይወት ትርጒም ማግኘት እንደሚቻል ለማንጸባረቅ፥ ጸሐፊው ስለ እግዚአብሔር የሚናገራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

1. መክብብ 7 የሰዎችን የተለመደ አስተሳሰብ የሚቃወሙ የአጫጭር ምሳሌዎች ስብስብ ነው። ሰዎች፡- ከሞት ቀን የልደት ቀን፥ ኃዘን ካለበት የቀብር ሥርዓት ላይ ከመገኘት ደስታ ባለበት በጋብቻ በዓል ላይ መገኘት ይሻላል ይላሉ። ጸሐፊው ግን ይህንን አሳብ ይቃረናል። ምናልባት ይህ የሆነው፥ በደስታ ከምንፈነጥዝበትና በሳቅ ከምናወካበት ጊዜ ይልቅ ወደ ሞት ስንጠጋ በይበልጥ ስለ ሕይወትና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ስለ መጓዝ ስለምናስብ ይሆናል። ምንም እንኳ ሐሤት በምናደርግበት ጊዜ ደስ መሰኘት ቢኖርብንም፥ እግዚአብሔር ያስተምረን ዘንድ ክፉ ጊዜያትንም እንደሚሰጠን ማስታወስ ያስፈልጋል (መክብብ 7፡1-14)። 

2. ሕይወት ሚዛናዊና ቅን ፍርድ የሚገኝባት አይደለችም። ጻድቅ ዕድሜ ሳይጠግብ ይሞታል፤ ኃጢአተኛ ሰው ግን በክፋቱ እየቀጠለ፥ ረጅም ዕድሜ ይኖራል (መክብብ 7፡15)። ጻድቃን ብዙ ጊዜ ይቀጣሉ፤ ኃጢአተኞች ግን ቅጣት ሳያገኛቸው ይኖራሉ (መክብብ 8፡14)። 

3. ትምህርት ማብቂያ የለውም ጥበብንም ሁሉ ማወቅ አይቻልም። በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ ይጠብቀን ዘንድ ጥበብ ያስፈልገናል (መክብብ 7፡19-8፡1)። 

4. የሰው ልብ በኃጢአትና በክፋት የተሞላ ነው (መክብብ 7፡20፤ 9፡3)።

5. ሞት የሀብታምና የድሀ፥ የመሪዎችና የተራ ሰዎች፥ በአጠቃላይም የሰው ልጅ ሁሉ መጨረሻ ነው፤ ዳሩ ግን በሕይወት ዘመንህ ሳለህ ደስ ይበልህ። እግዚአብሔር በሰጠህ ሚስት ደስ ይበልህ። በሥራህ ደስ ይበልህ፤ ሥራህንም በሙሉ ኃይልህ ሥራ። ሞት ይህንን ሁሉ ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣ በማስተዋል ኑር (መክብብ 9፡1-10)። 

6. ጥበብ ከሀብት ይበልጣል (መክብብ 9፡13-11፡6)። ጥበብ ሰውን ከጕዳት በመጠበቅ ረጅም ዕድሜን ያጐናጽፈዋል።

ደግሞም ጸሐፊው የሕይወትን ከንቱነት በማሳየት እግዚአብሔርን በሕይወት ዘመን ሁሉ ከማስታወስ አስፈላጊነት ጋር አወዳድሮ ሚዛናዊ ያደርገዋል። የሚከተሉትን አስተውል፡-

1. ጸሐፊው በሃይማኖት ስም ተገቢ ያልሆነ ቅንዓት እንደማያስፈልግ፥ ይልቁንም የሃይማኖትን ቅንዓት ከተግባራዊ ጥበብ ጋር ሚዛናዊ ማድረግ እንደሚገባ ይመክራል (መክብብ 7፡15-18)። በሌላ አባባል ሚዛናዊነት አትጣ ማለት ነው። የማይገባ የሃይማኖት ቅንዓት ከሌሉች ጋር ላለህ ግንኙነት ዕንቅፋት እንዲሆን ወይም በራስህ ላይ የማያስፈልግ ስደት እንዲያስከትል አታድርግ። 

የውይይት ጥያቄ፥ የማያስፈልግ የሃይማኖት ቅንዓት በሰው ላይ የሚያመጣቸው ተገቢ ያልሆኑ ችግሮች ምንድን ናቸው?

2. ወጣቶች በሕይወት ጣጣዎች ሊጐብጡ አይገባም። ነገር ግን መደሰት ያስፈልጋቸዋል። ዳሩ ግን በሕይወታቸው የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣው ሁልጊዜ ሊያስታውሱ ይገባል (መክብብ 11፡7-10፤ 12፡14)። 

3. ሰው እስከ ሽምግልና ዕድሜው ድረስ በመጠበቅ እግዚአብሔርን ሊያስብና እርሱን ሊያከብር ከመሞከር ይልቅ በወጣትነት ዕድሜው ሊያደርገው ይገባል። ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ለእግዚአብሔር ልንሠራ የምንችልበት ኃይላችን የሚከዳበት ጊዜ ይመጣል። ያኔ ለእግዚአብሔር ለመሥራት ጊዜው እጅግ እንደዘገየ እንረዳለን (መክብብ 12፡1-7)። 

4. ለሕይወት መሠረታዊውና ትርጒም የሚሰጠው ነገር ራስን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ወይም እግዚአብሔርን በመፍራትና ትእዛዛቱን በመጠበቅ መኖር ነው (መክብብ 12፡13)፤ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበት ምክንያት ይህ ነው። ሕይወት ከንቱና ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ነገር የተሞላች ብትመስልም በፈሪሀ-እግዚአብሔር በመኖር ደስታና እርካታ ለማግኘት ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህን የመጽሐፈ መክብብ ምዕራፎች በመጠቀም፥ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉትን ወጣቶች እንዴት ትመክራቸዋለህ? ለ) በሕይወታቸው መጨረሻ፥ ጊዚያቸውን በከንቱ እንዳጠፉ እንዳይሰማቸው ማስታወስ የሚገባቸውን እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ጥቀስ። ሐ) መጽሐፍ መክብብን በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችንና ነጋዴዎችን የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዐቅድ። መ) ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ልታስተምራቸው የምትፈልጋቸውን እጅግ ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version