የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መጽሐፍ ዓላማ

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፥ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንን ልንረዳባቸው የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። የመጽሐፉ ዓላማ የሚወሰነው መጽሐፉ በሚተረጐምበት መንገድ ነው። ይህን መጽሐፍ በምንተረጕምበት ጊዜ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ሁለት ከፍተኛ ደረጃዎች ይኖራሉ። የመጀመሪያው መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ ዓለማዊ የሆነና ስለ ፍቅር አሳፋሪ በሆነ መንገድ የሚናገር ነው በለሚል ብዙ ክርስቲያኖች ሐፍረት ስለሚሰማቸው ይህንን መጽሐፍ ከማጥናት ይቈጠባሉ። እንዴት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተካተተ በማሰብም ይገረማሉ። ሁለተኛው ከፍተኛ ደረጃ ደግሞ፥ መጽሐፉን ከመጠን በላይ መንፈሳዊ ማድረግና የሚሰጠው ትርጕም ግጥሙ ከያዛቸው ነገሮች ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌለው አድርጎ ማቅረብ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ እያዳንዱን የአነጋገር ዘይቤ ስለ እግዚአብሔርና እርሱ ለእኛ ስላለው ፍቅር የሚገልጽ ነው ብለው እስከ መገመት ይደርሳሉ። ይህም በተርጓሚው አመለካከት ብቻ የሚታይና በእውነታ ላይ ያልተመሠረተ ግምታዊ አተረጓጐምን ወደ መከተል ይመራል። ለመጽሐፉ የምንሰጠው ማንኛውም ትርጒም በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች መካከል ሚዛናዊ ሆኖ መቅረብ አለበት። ይህን የጥናት መጽሐፍ በጻፈው ሰው አመለካከት፥ የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንን ትርጕም በሁለት ደረጃ ማየት ከሁሉ የተሻለ ነው።

1. ለማንኛውም ዓይነት አተረጓጐም ልዩ ክብደት ከመስጠታችን በፊት፥ በቅድሚያ ለመጽሐፉ ታሪክ ልዩ ትኵረት መስጠት አለብን። ታሪኩ የፍቅር መዝሙር ሲሆን፥ በባልና ሚስት መካከል ሊኖር ስለሚችልና መኖርም ስላለበት የግንኙነትና የፍቅር ውበት ምሳሌ ነው። ይህ ፍቅር በመጨረሻ በፍትወተ ሥጋ ግንኙነት ይገለጣል። በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ንጹሕና መንፈሳዊ እንዳልሆነ የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በእግዚአብሔር ፊት መልካም ያልሆነና ልጆችን ለማፍራት ብቻ የሚደረግ ነገር አድርገው ይገምቱታል። ይህ አመለካከት በካቶሊክና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ስለ ጋብቻ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ እንዲሆንና ሳያገቡ መኖርን እንደ ከፍተኛ ብቃት እንዲቈጥሩ አድርጓቸዋል፤ ዳሩ ግን ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት አይደለም።

እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ወንድና ሴት አድርጎ በአምሳሉ ፈጥሯቸዋል (ዘፍጥ. 1፡27)። የጾታ ባሕርያቸውን በመወሰን፥ በጋብቻ ውስጥ በሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ደስ እንዲላቸው አስቀድሞ አቀደ። እርቃናቸውን ባያቸው ጊዜ እንኳ «መልካም» እንደነበሩ ተናግሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፥ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በጋብቻ መጣመር ውስጥ እስከሆነ ድረስ መልካም ነው። ጋብቻ ክቡር ነው (ምሳሌ 18፡22፤ ዕብ. 13፡4። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከለክለው የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ከጋብቻ ውጭ በመፈጸም፥ ክቡር የሆነውን ግንኙነት ማበላሸትን ነው (ዘጸ. 20፡14፤ ዘሌ. 18፡22፤ ማቴ. 5፡27-28፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡13፥ 18)። ሁለት ሰዎች ከመጋባታቸው በፊት የሚያደርጉት ማንኛውም የግብረ ሥጋ ግንኙነትና ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አጥብቆ የተከለከለ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ የተሳሳተ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሰው ልጅ በኃጢአት የመውደቅ ምልክትና በጋብቻ ውስጥ ብቻ የተቀደሰውን ነገር እንደማጥፋት ተደርጎ ተወስዷል (ለምሳሌ፡- ሮሜ 1፡24-32)።

መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በዚህ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባልና ሚስት ደስ ሊሰኙበት እንደሚገባ ይናገራል (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 6፡2-3፤ 7፡10-13፤ 8፡1-3)። የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈቀደው ለተጋቡ ሰዎች ብቻ ነው (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4፡12 ተመልከት)። የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሥጋዊ ፍላጎት ውጤት ከመሆን ይልቅ በባልና ሚስት መካከል ሊኖር የሚገባው የፍቅር ግንኙነት ውጤት መሆን አለበት (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 6፡2-3፣ 7፡10-13)። በባልና ሚስት መካከል የጠለቀ የፍቅር ግንኙነት ከሌለ፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ በባልና ሚስት መካከል እንዲኖር ያቀደው የአእምሮ፥ የመንፈስና የአካል ውሕደት ጭምር ግቡን ሳይመታ ይቀራል። በዚህ ሁኔታ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንስሶች ከሚያደረጉት ነገር ያልተለየ አካላዊ እንቅስቃሴ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ሰዎች የግብረ ሥጋ ግንኙነት በጋብቻ ውስጥ ስላለው ስፍራ ካላቸው አስተሳሰብ ይህ ትምህርት የሚለየው እንዴት ነው? ለ) ይህ ነገር ይሟላ ዘንድ ባሎች ስለሚስቶቻቸው ካላቸው አስተሳሰብ ውስጥ ሊለውጡት የሚገባው ምንድን ነው?

በጋብቻ የተጣመሩ ሰዎች መኃልየ መኃልይን በማንበብ አንዳቸው ለሌላቸው ያላቸው ፍቅር ጥልቅ መሆን እንደሚገባው ቢመለከቱ ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ ነው። 

2. በአንድ በኩል መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ሀ) በእግዚአብሔርና በእስራኤል፥ ደግሞም ለ) በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልጽ ሥዕላዊ ሁኔታ ነው። ለዚህ ነው አይሁዳውያን እንዲረዱት እግዚአብሔር መኃልየ መኃልይን በቡሉይ ኪዳን ውስጥ እንዲጠቃለል ያደረገው።

በብሉይ ኪዳን፥ እስራኤል ብዙ ጊዜ ከሙሽራ ጋር ትነጻጸር ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 50፡1፤ 54፡4-5፤ ሕዝቅኤል 16፡23፤ ሆሴዕ 1-3)። ማንኛውም የጣዖት አምልኮ እንደ ማመንዘር ይታይ ነበር። ለእስራኤላውያን መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ሊኖር የሚገባው የፍቅር ጥልቀት ምሳሌ ነው። አንድ ሰው ይህ ግጥም ሦስት ባሕርያት አሉት የሚለውን አመለካከት ከያዘ፥ ሴቲቱ እስራኤልን፥ እረኛው እግዚአብሔርን የሚወክሉ ሲሆን፥ ሰሎሞን ደግሞ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የሚኖረውን የፍቅር ግንኙነት ለማበላሸት የሚጥረውን ዓለምን ይወክላል። ሴቲቱ ከሰሎሞን ጋር ለመዋሐድ እሺ ብትል ኖሮ በኤኮኖሚ በኩል የሚበጃት ቢሆንም ቅሉ አሻፈረኝ በማለቷ እስራኤል ለእግዚአብሔር ሊኖራት የሚገባውን ታማኝነት የሚያመለክት ነበር። ሌሉች አማልክት ወይም ሕዝቦች የእርሷን ታማኝነት የቱንም ያህል ቢሹም እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ነበረባት።

በታሪኩ ውስጥ ሰሎሞንና ሴቲቱ ብቻ አሉ በሚለው አመለካከት ግን ሰሎሞን የእግዚአብሔር፥ ሴቲቱ የእስራኤል ምሳሌ ናቸው።

አዲስ ኪዳን ይህንን የጋብቻ ተምሳሌት በመጠቀም፥ ክርስቶስ ሙሽራው፥ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሙሽራይቱ እንደሆነች ይናገራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤፌ. 5፡23-33፤ ራእይ 19፡7፤ 21፡2፥ 9-10፤ 22፡17 ተመልከት። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የክርስቶስ ሙሽራ ተብለው የተጠሩት ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) ምድራዊ የሆነው ጋብቻ ከክርስቶስ ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የተነጻጸረው እንዴት ነው?

ብዙ ሰዎች በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት የመጣው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ከሚኖር የጋብቻ ግንኙነት ተምሳሌት የሆነ ይመስላቸዋል፤ ነገር ግን ምድራዊው ጋብቻ በእግዚአብሔር በራሱ መካከል ከነበረው ግንኙነት ተምሳሌት እንደተከሠተ ማሰቡ የተሻለ ይመስላል። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መጽሐፍ ዓላማ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: