Site icon

የመኃልየ መኃልይ ትርጕም እና አስተዋጽኦ

የመኃልየ መኃልይ ትርጕም

ምሁራን ይህ መኃልየ መኃልይ እንዴት መተርጐም እንዳለበት ለመወሰን ሞክረዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፉን መረዳት ስለሚችሉበት መንገድ ለመስማማት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት መጽሐፉ ሲተረጐም የቆየባቸው አያሌ የተለያዩ መንገዶች አሉ። እንዲሁም ይህን መጽሐፍ መተርጐም እጅግ አስቸጋሪ የሆነበት ሦስት ምክንያቶች አሉ፡-

1. የመጽሐፉ ርእሰ-ጉዳይ የሆነው የሁለት ግለ ሰቦች ፍቅርና በመጽሐፉ ውስጥ የምናየው የቋንቋ አጠቃቀም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖር ያለበት ዓይነት አይመስልም። ስለ ፍትወተ-ሥጋ የሚናገር እንጂ የሥነ-መለኮት ትምህርት እውነቶችን የሚያስተምር አይመስልም። 

2. መጽሐፉን ራሱ ለመረዳት ቀላል አይደለም። በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ቃላት ግልጽ ያልሆኑና ያልታወቁ ትርጒሞች ያሏቸው ናቸው። እንደ እውነቱ መጽሐፉ የሚናገረው ስለ ሁለት ይሁን ወይም ስለ ሦስት ሰዎች ግልጽ አይደለም። አንዳንዶች መጽሐፉ የሚናገረው ስለ ሰሎሞንና ስለ ሱላማጢሲቱ ሴት ፍቅር ነው ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ በታሪኩ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ሦስት ናቸው፤ እነርሱም:- በአንድ በኩል ሴትየዋን ወደ እልፍኙ ሊያስገባት የቃጣው ንጉሥ ሰሎሞን ሲሆን፥ በሌላው በኩል ደግሞ የሴትየዋ የመጀመሪያ ወዳጅ የሆነውና በፍቅሩም ሊማርካት የቻለው ፍቅረኛዋ እረኛ አለ በሦስተኛ በኩል ደግሞ ሰሎሞንን ለማግባት ተቃርባ የነበረችው ነገር ግን መጨረሻ ላይ እረኛውን ያገባችው ሱላማጢሲቱ ሴት ነበረች። የታሪኩም ትርጕም እንደስሜታችን ሊለያይ ይችላል። እዚህ ላይ ሰሎሞን የቀረበው በመልካም ነው ወይስ በክፉ አስተሳሰብ በሚለው ስሜት ላይ የተመረኮዘ ይሆናል ማለት ነው።

3. ታሪኩ የተፈጸመበትን ጊዜና ቦታ አናውቅም። መዝሙሩ የቀረበው ሰሎሞን አንዲትን ሴት በፍቅሩ ለማሸነፍ በመቻሉ እንደ ሠርግ መዝሙር ሆኖ ነውን? ወይስ ሰሎሞን ባሉት ሚስቶቹ ላይ ሌላ ሴት ለመጨመር ባደረገው መከራ የታየበትን ሞኝነት ለመግለጥ ነው?

ይህ መዝሙር የተተረጐመባቸው ስድስት መንገዶች አሉ። የመጀመሪያዎቹን ሦስት የአተረጓጐም መንገዶች የማይቀበሉት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት የማያምኑ ሰዎች ናቸው። እነዚህም ሦስት መንገዶች መጽሐፉን ለመተርጐም ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው። እነርሱም፡-

1. ታሪኩ ልብ ወለድ ሲሆን፥ የተጻፈውም ለእስራኤል ነገሥታት መዝናኛ ይሆን ዘንድ በተውኔት (ድራማ) መልክ እንዲቀርብ ነው። 

2. ታሪኩ የተወሰደው ከከነዓናውያን እምነት ሲሆን፥ በሁለት አማልክት መካከል ስላለ ፍትወተ-ሥጋ ግንኙነት የሚናገር አፈ ታሪክ ነው። 

3. መዝሙሩ የሠርግ መዝሙር ሲሆን፥ የሚዘመረው ለሙሽራዪቱና ለሙሽራው ፍቅር አክብሮት ለመስጠት ነበር። የሚዘመረውም በሠርግ በዓል ላይ ነበር። 

የመጨረሻዎቹ ሦስት የአተረጓጐም መንገዶች ግን በክርስቲያኖችና በአይሁድ ዘንድ የተለመዱ መንገዶች ናቸው፡-

4. አንዳንዶች ይህ ታሪክ ተምሳሌታዊ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ከሰሎሞንና ከሴቲቱ ፍቅር ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ተምሳሌታዊ ትርጕም አዘል ነው። እግዚአብሔር ሙሽራው ለሆነችው እስራኤል ያለውን ፍቅር ለአይሁድ የሚያሳይ ሲሆን፥ ለክርስቲያኖች ደግሞ፥ ከርስቶስ ሙሽራው ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። በታሪክ ውስጥ በጣም የታወቀውና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው አተረጓጐም ይህ ነው። ሆኖም ግን ይህ አተረጓጐም በርካታ ችግሮች አሉት። ሰዎች በይሆናል ታሪኩን በሚተረጕሙበት ጊዜ ከእውነት የራቀ ትርጕም ወደ መስጠት ይመራቸዋል።

5. ይህ አመለካከት ከአንድ ልዩነት በቀር፥ በተራ ቊጥር 4 ከሚገኘው አመለካከት ጋር ይስማማል። መዝሙሩ የሚያንጸባርቀው የሰሎሞንና የሴቲቱ ገጠመኞችን ነው። ታሪኩ በእርግጥ የተፈጸመ ነው። ሆኖም ይህ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገኘበት ዋና ምክንያት ከዚህ ለጠለቀ እውነት ተምሳሌት እንዲሆን ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የመጨረሻው ሰው የክርስቶስ ተምሳሌት እንደሆነ ሁሉ (ሮሜ 5)፣ መልከ ጸዴቅም የኢየሱስ ተምሳሌት ነው (ዕብ. 7)፤ ይህም ታሪክ የሚከተለውን ተምሳሌት ይዞአል፡- ለአይሁድ ሰሎሞን የእግዚአብሔር፥ ሴቲቱ ደግሞ የእስራኤል ተምሳሌት በመሆን በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ያሳያሉ። ለክርስቲያኖች ደግሞ፥ ሰሎሞን የክርስቶስ፥ ሴቲቱ የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችውን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት።

6. የመጨረሻው አመለካከት ታሪኩን እንዳለ በቀጥታ የሚቀበል ነው። በሰሎሞንና በሴቲቱ ወይም በሰሎሞን፥ በሴቲቱና በእረኛው መካከል ያለ የፍቅር ታሪክ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተተበት ምክንያት፥ እግዚአብሔር በጋብቻ ውስጥ በፍትወተ ሥጋ ለሚገለጥ ፍቅር አክብሮት እንዳለው ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር ወንድና ሴት እርስ በርሳቸው በጥልቅ ፍቅር እንዲዋደዱና አንዱ ለሌላው ደስታ ሙሉ በሙሉ ራሱን ይሰጥ ዘንድ እንደሚፈልግ ያሳያል። የጋብቻን ክቡርነትና በጋብቻ ውስጥ የፍትወተ ሥጋ መልካምነትን ያሳያል። 

የመኃልየ መኃልይ አስተዋጽኦ 

ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ለመኃልየ መኃልይ የተለያየ አስተዋጽኦ አላቸው። እነዚህ አስተዋጽኦዎች የጥቅሶቹ አከፋፈልና የተናጋሪዎቹ ማንነት ከአንዱ ትርጓሜ ወደ ሌላው ይለያያል። ይህ የሚያሳየው ይህን ግጥም መተርጐም ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ነው። ከዚህ በታች ሁለት አስተዋጽኦዎች ቀርበዋል። አንዱ አስተዋጽኦ መጽሐፉ ሁለት ዋና ገጸ-ባሕርያት እንዳሉት አድርጎ የሚያቀርብ ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ መጽሐፉ ሦስት ዋና ገጸ-ባሕርያት እንዳሉት አድርጎ የሚያቀርብ ነው። 1ኛ. መጽሐፉ ሁለት ዋና ገጸ ባሕርያት ማለትም ሰሎሞንና ሴቲቱ ብቻ እንዳሉት አድርጎ የሚያቀርበው አመለካከት፡-

1. ሴቲቱ ስለ ወደደችው ንጉሥ የፍቅር መዝሙሯን ትዘምራለች (1፡2-7)፤ 

2. ንጉሡ ከሴቲቱ ጋር ይነጋገራል (1፡8-2፡7)፤ 

3. የፀደይ ወቅት መዝሙር ነው (2፡8-13)፤ 

4. ሴቲቱ ፍቅረኛዋን ትፈልጋለች (2፡14-3፡5)፤ 

5. የንጉሡ የሠርግን ሂደት ያሳያል (3፡6-11)፤ 

6. የሴቲቱ ውበት እንደ አትክልት ስፍራ ነበር (4፡1-5፡ 1)፤ 

7. ሴቲቱ ስለ ፍቅረኛዋ ያደረገችውን ንግግር ያመለክታል፤ (5፡2-6፡3)፤ 

8. ሰውዬው ስለ ፍቅረኛው ውበት ያደረገውን ንግግር ያመለክታል (6፡4-7፡9)፤ 

9. ሴቲቱና ሰውዩው ስለ ፍቅር ያንጸባረቁት ነገር ነበር (7፡10-8፡14)። 

2ኛ. በታሪኩ ውስጥ ሦስት ዋና ገጸ ባሕርያትን ማለትም ሰሎሞን፥ እረኛውንና ሴቲቱን የሚያሳየው አመለካከት፡-

1. ሱላማጢሲቱ ሴት በቤተ መንግሥት አደባባይ 

ሀ. ንጉሡና ሴቲቱ ሲነጋገሩ (1፡2-2፡2)፥

2) ሴቲቱ ስለጠፋባት ፍቅረኛዋ ስትናገር (1፡2-4)፥

3) የቤተ መንግሥቱ ሴቶች ቁንጆይቱን ሲያሞግሷት (1፡4)፥ 

4) ቁንጆይቱ ለቤተ መንግሥቱ ሴቶች ምላሽ ስትሰጥ (1፡5-7)። 

5) የቤተ መንግሥቱ ሴቶች ቆንጆይቱን ሲመክሯት (1፡8)። 

6) ሰሎሞን ቆንጆይቱን ሲናገራት (1፡9-10፥ 

7) ቆንጆዪቱ ለሰሎሞን ስትመልስለት (1፡12-14)። 

8) ሰሎሞን እንደገና ቆንጆይቱን ሲናገራት (1፡15)። 

9) ቆንጆይቱ ለሰሎሞን ምላሽ ስትሰጥ (1፡16-2፡1)፥

10) ሰሎሞን ቆንጆይቱን ሲናገራት (2፡2)። 

ለ. ቆንጆዪቱ አፍቃሪዋን እረኛ ስትፈልገው (2፡3-3፡5) 

2. ሰሎሞን ቆንጆይቱን በፍቅር ለመማረክ ይናገራል 

ሀ. ሰሎሞን ቆንጆይቱን ለመማረክ ያደረገው የመጀመሪያ ሙከራ (3፡6-5፡8) 

ለ. ሰሎሞን ቆንጆይቱን ለመማረክ ያደረገው ሁለተኛ ሙከራ (5፡9-7፡9) 

3. ሱላማጢስቱ ሴት ንጉሥ ሰሎሞንን ሳትቀበል እንደቀረች (7፡10-8፡4) 

4. ሱላማጢሲቱ ቆንጆና እረኛው እንደገና በፍቅር እንደተዋሐዱ (8፡5-14)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version