ትንቢትን ማጥናት ቀላል አይደለም። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ሌሎች የሰጡትን ትርጕም ለመመርመር ረጃጅም ሰዓታትን የሚጠይቅ ነው። በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን አብዛኛዎቹን የነቢያት መልእክቶች ለመተርጐም በምሁራን ዘንድ አጠቃላይ ስምምነት ቢኖርም፥ ሆኖም ግን በአይሁድ ታሪክ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ተፈጻሚነት ያላገኙትን ትንበያዎች ለመተርጎም ትልቅ ልዩነት ታይቶአል። ምሁራን፡- እነዚህ ትንበያዎች ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ቀደም ሲል በአይሁዳውያን ተፈጽመዋል ወይስ በቤተ ክርስቲያን ልምድ ውስጥ በመንፈሳዊ ሁኔታ ተፈጽመዋል? ወይንስ ደግሞ በቀጥታ የሚፈጸሙበትን መጪውን ጊዜ እየተጠባበቁ ናቸው? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ያልተፈጸሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በመረዳት ረገድ ከፍተኛ ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች አሉ፡-
1. ትንቢቶቹን መረዳት የሚቻለው እንደተጻፉ በቀጥታ ነው ወይስ በተምሳሌታዊ መንገድ? አንዳንድ ምሁራን ወደፊት ስለሚመጣው ጦርነት፥ ስለተባበረው የእስራኤል መንግሥት ዳግም መመሥረት ወይም ወደፊት ስለሚሠራው ቤተ መቅደስ የሚናገሩ ትንቢቶች ሁሉ በተምሳሌታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ይገምታሉ። እነዚህ ነገሮች መፈጸም ያለባቸው በቀጥታ ለአይሁድ ሕዝብ ሳይሆን፥ ለቤተ ክርስቲያን ነው ይላሉ። እነዚህ ትንቢቶች እግዚአብሔር አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያመጣቸው የአንድነት፥ የሰላም ወይም ዘላለማዊ የሆነ አምልኮ መግለጫዎች ናቸው የሚል እምነት አላቸው።
ሌሎች ምሁራን ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጐም አጥጋቢ ነው ብለው አያምኑም። ቀጥተኛ የሚመስሉትን ትንቢቶች (ለምሳሌ፡- ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራት የተነገረው ሕዝቅኤል 40-48) ተምሳሌታዊ አድርገን መውሰድ ከጀመርን ትንቢትን እንዴት እንደምንተረጕምና እንደምናዛምድ እንዲሁም ልንረዳው የሚገባን በቀጥታ ይሁን በተምሳሌት የምንወስንበት መመዘኛ አይኖረንም ይላሉ። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ አመጣጥ፥ በቤተ ልሔም ስለ መወለዱ፥ ወደ ግብጽ ስለ መሸሹ፥ ስለ ሞቱና ትንሣኤው የተነገሩ ኣብዛኛዎቹ ትንቢቶች በብሉይ ኪዳን በተነገሩበት አኳኋን በቀጥታ መፈጸማቸውን ይጠቁማሉ፤ ስለዚህ አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ቀጥተኛ አይደሉም፤ የምንረዳቸውና የሚፈጸሙትም በተምሳሌታዊ ሁኔታ ነው ለማለት የምንችልበት ግልጽ መሠረታዊ ምክንያት የለንም ይላሉ። እነዚህ ምሁራን ትንቢቶችን መጀመሪያ ከተጻፉትና መልእክቱ የተጻፈላቸው አይሁድም ከተረዱበት መንገድ ጋር በእጅጉ ተቀራራቢ በሆነ አኳኋን መተርጐምን ይመርጣሉ። ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል 40-48 በግልጽ የሚያስተምረው ስለ እስራኤል ሕዝብ መመለስ፥ ስለ ምድሪቱ መከፋፈል፥ ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራትና ስለ መሥዋዕት አቀራረብ ነው። ስለዚህ ይህ ሁሉ በመጨረሻው ዘመን ልክ እንደተነገረው ይፈጸማል ብለው ያምናሉ።
2. በእግዚአብሔር የወደፊት ዕቅድ ውስጥ እስራኤል ያላት ስፍራ፡- በብሉይ ኪዳን ዘመን አይሁድ ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደነበሩ ምሁራን በሙሉ ይስማማሉ። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በዚህ ዘመን ያለች የእግዚአብሔር ሕዝብ ማኅበር እንደሆነች ያምናሉ፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የወደፊት ዕቅድ ውስጥ ስላላቸው ስፍራ ምሁራን ኣይስማሙም። እግዚኣብሔር ለአይሁድ ወደፊት ሊፈጽምላቸው ተስፋ የሰጣቸው ልዩ ዕቅድ አላውን? ወይስ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረው የልዩነት ግድግዳ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ፥ በብሉይ ኪዳን ስለ አይሁድ የተነገሩ ትንቢቶች ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን መፈጸም ያለባቸው ናቸው? ከእንግዲህ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች እንጂ በሥጋ የአብርሃም ልጆች የሚባሉ የሉም ማለት ነውን? (ገላትያ 3፡29፤ 4፡28-31፤ ሮሜ 9፡8)።
የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፡- ገላትያ 3፡29፤ 4፡28-31፤ ሮሜ 9፡8። ጥቅሶቹ ስለ እውነተኞች አይሁድና ስለ እውነተኞች የአብርሃም ልጆች ምን ይላሉ?
አንዳንድ ምሁራን እግዚአብሔር በሥጋ የአብርሃም ልጆች ከሆኑ እስራኤላውያን ጋር የነበረው ዕቅድ ያከተመ ይመስላቸዋል። አሁን የሚሠራው አይሁድና አሕዛብ ከሚገኙበት ቤተ ክርስቲያን ጋር ብቻ ነው ይላሉ። ስለዚህ እስራኤልና ይሁዳ እንደገና እንደሚዋሐዱ፥ ምድራቸውን ወደፊት እንደሚያገኙ ወይም ወደ ምድራቸው እንደሚመለሱ ወዘተ. የተነገሩት ትንቢቶች ቤተ ክርስቲያንን በሚያመለክት መንገድ በተምሳሌት መተርጐም አለባቸው ይላሉ።
15ኛ ጥያቄ. ሮሜ 11፡25-32 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ለእስራኤል ነገድ የተለየ ዕቅድ እንዳለው የሚያስተምሩ ናቸው ወይስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ኣንድ ናቸው? መልስህን አብራራ።
ሌሉች ምሁራን እግዚአብሔር የአብርሃም የሥጋ ዝርያ ለሆኑት አይሁድ አሁንም ቢሆን ዓላማ አለው ይላሉ። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ ከነዓን ምድር፥ ከኢየሩሳሌም የዳዊት ልጅ እንደሚገዛቸው፥ ወዘተ. ልዩ በሆነ መንገድ የሰጣቸው የተስፋ ቃል ወደፊት በቀጥታ ይፈጸማል። ስለዚህ እነዚህ ምሁራን ያልተፈጸሙ ትንቢቶች የሚፈጸሙት በተምሳሌት ለቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፥ በቀጥታ ለእስራኤል ሕዝብ እንደሆነ ይናገራሉ።
ስለ እነዚህ ጉዳዮች ያለን ቅድመ አስተሳሰብ እነዚህን ያልተፈጸሙ ትንቢቶች በምንተረጕምበት ሂደት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ልብ ልንል ያስፈልጋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች በትንቢት መጻሕፍት አተረጓጐም ረገድ በከፍተኛ ደረጃ የሚለያዩት በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ባላቸው የተለያየ ግንዛቤ ነው። ይህ ነገር ክርስቲያኖች በመሆናችን ወይም ባለመሆናችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር አለመሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በሁለቱም አመለካከቶች ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረው ነገር እነርሱ እንደሚያስቡት ብቻ እንደሆነ የሚያምኑ ጠንካራ የክርስቲያን ምሁራን አሉ። ሆኖም ስለ ሁለቱ አመለካከቶች ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ማግኘት አስፈላጊ ነው። የትኛው አመለካከት የበለጠ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሚመስልና ያንንም ያልነው ለምን እንደሆነ ለራሳችን መወሰን አለብን። ነገር ግን እነዚህን ጉዳዮች በሚመለከት ከእኛ የተለየ ግንዛቤና አተረጓጐም ካላቸው ጋር በመቻቻል ለመኖር መዘጋጀት አለብን።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሚቻል ከሆነ፥ ከተለያዩ የክርስትና እምነት ክፍሎች ከሆኑና በሚገባ ከተማሩ ሰዎች ጋር በመነጋገር ስለ መጪው ጊዜ ምን እንደሚያስቡ ተረዳ። የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች እንዴት መተርጐም እንዳለባቸውና እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለወጠነው የወደፊት ዕቅድ ያላቸው አስተሳሰብ ምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ስለ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ያላት እምነት ምንድን ነው? ለምን? የቤተ ክርስቲያንህን መጋቢ ወይም ወንጌላዊን ጠይቅ።
ምሁራን አብዛኛዎቹን ያልተፈጸሙ ትንቢቶች በመተርጐም ረገድ ይረዳቸው ዘንድ እያንዳንዱን ትንቢት ለመረዳት የሚጠቅም ሰፋ ያለ መሠረት ጥለዋል። በአጠቃላይ ሰዎች ትንቢቶችን ለመተርጐም የሚጠቀሙባቸው መሠረቶች ሦስት ዓይነት ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመለካከቶች ትንቢቶችን በተምሳሌታዊ ሁኔታ የሚተረጕሙበት ሁኔታዎች ናቸው። እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንንና እስራኤልን እንደ አንድ የእግዚአብሔር ሕዝብ አድርገው የሚቆጥሩና እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያንና ለእስራኤል አንድ እንጂ የተለያየ ዕቅድ የለውም የሚሉ ናቸው።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመለሰው ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ነው የሚለው አመለካከት (ድኅረ ሺህ ዓመት ወይም ፖስት-ሚሌኒያሊዝም)፡- ይህም አመለካከት እግዚአብሔር አንድ ሕዝብ ብቻ እንዳለው ያምናል። ያም ሕዝብ በብሉይ ኪዳን እስራኤል የተባለው ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በመባል ይጠራል። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል የገባው ቃል ኪዳን የተፈጸመው በቀጥታ ለእስራኤል ሳይሆን፥ በመንፈሳዊ መንገድ ለቤተ ክርስቲያን ነው። ወንጌል በዓለም ሁሉ ስለሚስፋፋ ዓለም በሙሉ በክርስትና እምነት ትለወጣለች። ክርስቶስ መጀመሪያ ሲመጣ የተጀመረው የእግዚአብሔር መንግሥት ዓለምን ሁሉ እስኪያጠቃልል ድረስ ይስፋፋል። ከዚያም ለረጅም ጊዜ በምድር ላይ ሰላም ከሰፈነ በኋላ ክርስቶስ ይመጣል። ሰው ሁሉ ከተነሣና ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ዘላለማዊ ወደሆነው መንግሥተ ሰማያት ወይም ገሃነም ይገባል። ኢየሱስ አንድ ሺህ ዓመት እንደሚነግሥ የተነገረው ቃል ተምሳሌታዊ ሲሆን፥ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገበት ጊዜ ጀምሮ ለዘላለም ሊነግሥ እስከሚመለስበት ድረስ ያለው ወቅት ነው። ከአንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ይህ አመለካከት የታወቀ ነበር። ብዙ ክርስቲያኖች ክርስትና በፍጥነት በማደግ ዓለምን ሁሉ ያጠቃልላል ብለው ያስቡ ነበር፤ ከጦርነቶቹ በኋላ ግን ይህ አመለካከት እስከዚህም የታወቀ አልነበረም። ማስታወሻ፡፡ ሚሊኒየም የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ የክርስቶስ ሺህ ዓመት መንግሥት ማለት ነው (ራእይ 20፡1-6)።
የውይይት ጥያቄ. ሀ) ማቴዎስ 24፡14 ተመልከት። ወንጌል በዓለም ሁሉ ሊዳረስ የሚችልባቸው አንዳንድ መንገዶች አሉን? ለ) አብዛኛው ሕዝብ ክርስቲያን የሚሆንበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል?
2. በምድር ላይ የአንድ ሺህ ዓመት መንግሥት የሚባል ነገር የለም የሚለው አመለካከት (አሚሌኒያሊዝም)፡- እነዚህ ክርስቲያኖች እስከ ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ መልካምና ክፉ በምድር ላይ ይኖራሉ ይላሉ። ክርስቶስ በአካል በምድር ላይ የሚነግሥበት ጊዜ ከቶ አይኖርም። የክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥት ጉዳይ ተምሳሌታዊ ነው። ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ በመንፈሱ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ነግሦአል፤ ከሞቱና በሰማይ ከእርሱ ጋር ካሉ ቅዱሳን ጋር ነግሦአል። በመጨረሻው ዘመን በምድር ላይ ሁኔታዎች ሁሉ ይከፋሉ። ክሕደት ይጨምራል። ከዚያም ክርስቶስ በክብሩ ይመጣና ጠላቶቹን ሁሉ ያሸንፋቸዋል። የሞቱት ይነሡና ይፈረድባቸዋል። ከዚያም በኋላ ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ወይም በገሃነም ውስጥ ለዘላለም ይገባል። እስራኤልና ቤተ ክርስቲያን አንድ ስለሆኑ በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል የተሰጡት ተስፋዎች ሁሉ በመንፈሳዊ ረገድ ለቤተ ክርስቲያን ይፈጸማሉ። ይህ እስካሁን ድረስ በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ነው።
3. ክርስቶስ ከሺሁ ዓመት መግሥት በፊት ይመጣና በምድር ላይ ለአንድ ሺህ ዓመት ይነግሣል የሚለው አመለካከት (ቅድመ ሺህ ዓመት ፕሪሚሌኒያሊዝም)፡- ይህ አመለካከት እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን በቀጥታ ለመውሰድ የሚፈልግ ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ቃል ኪዳኑም ለእነርሱ ሊፈጽምላቸው የሚገባ ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ያለው ዕቅድ ለቤተ ክርስቲያን ካለው ዕቅድ የተለየ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን መጨረሻ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንደሚመጣ ያምናሉ። ከዚያም ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ ከእርሱ ጋር ይኖራሉ። በምድር ላይ ግን ታላቅ የመከራ ጊዜ ይጀምራል። የእግዚአብሔር ቍጣም በሰዎች ሁሉ ላይ ይፈስሳል። ቀጥሉ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ጋር ተመልሶ የክፋት ኃይላትን በማሸነፍ በምድር ላይ ለአንድ ሺህ ዓመት ይነግሣል። ይህ ዘመን ታላቅ ሰላምና ብልጥግና የሰፈነበት ይሆናል። የአዳም መርገም ከፍጥረት ሁሉ ላይ ይወገዳል። ክፋት እንዳይሠለጥን በክርስቶስ ይታገዳል። በዚህ አንድ ሺህ ዓመት እስራኤል ከፍ ያለ ድርሻ ታበረክታለች። ምሁራን እንግዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ ነው እጅግ የተለያየ አሳብ ያላቸው። ሆኖም ግን ከእስራኤል ሕዝብ አብዛኛው ያምንና በተስፋይቱ ምድር ይሰበሰባል፤ እስራኤልና አሕዛብም ይፈረድባቸዋል። በዚህ ጊዜ ለእስራኤል የተሰጡ የተስፋ ቃሉች በአንድ መንገድ ይፈጸማሉ። ከሺህ ዓመት በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የሚካሄድ ጦርነት አለ። ክርስቶስ የክፋትን ኃይላት ሁሉ ያሸንፋል። ባልዳኑት ሰዎች ላይ የመጨረሻ ፍርድ ይሰጣል፤ እነርሱም ወደ ገሃነም ይገባሉ። ከዚያም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይፈጠርና ዘላለማዊነት ይጀመራል።
በሦስተኛው አመለካከት ውስጥ ሦስት መጠነኛ ልዩነቶች አሉ። አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖች ከታላቁ መከራ በፊት ይነጠቃሉ ይላሉ። ሌሎች ክርስቲያኖች መነጠቅ የሚሆነው በመከራው ዘመን መካከል ነው ሲሉ፥ የቀሩት ደግሞ ክርስቲያኖች በታላቁ የመከራ ዘመን ውስጥ ካለፉ በኋላ ይነጠቁና በምድር ላይ ለመግዛት ወዲያውኑ ከክርስቶስ ጋር ይመለሳሉ ብለው ያምናሉ።
የአተረጓጐም ችግር የሌለበት አመለካከት የለም። ለዚህ የጥናት መጽሐፍ አዘጋጅ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ስለ ሺህ ዓመቱ መንግሥት የሚያስተምረው የመጨረሻው አመለካከት ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ይታየዋል።
ከእነዚህ ሦስት አመለካከቶች የምንቀበለው የትኛውም ይሁን ብዙዎቹን ትንቢቶች የምንረዳበትን መንገድ ይወስናል። በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ እስካሁን ወዳልተፈጸሙ ትንቢቶች ላይ በምንደርስበት ጊዜ፥ ተርጓሚው እነዚያን ትንቢቶች አስቀድሞ ከወሰነው አመለካከት ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ ይሞክራል።
የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን ሦስት ኣመለካከቶች አጥና። ሀ) የምትቀበለው የትኛውን አመለካከት ነው? ለምን? ለ) ሌሎች ክርስቲያኖች ይቀበሉታል የምትለው የትኛውን አመለካከት ነው? ሐ) የእነርሱ አመለካከት ከአንተው የሚለየው እንዴት ነው? መ) {የትንቢት አመለካከቶችን በሚመለከት ስለ እነዚህ ልዩነቶች መከራከር የማያስፈልገው ለምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)