ትንቢትን ለመተርጐም የሚጠቅሙ መመሪያዎች

በብሉይ ኪዳን ውስጥ 17 የትንቢት መጻሕፍት እንዳሉ ተመልክተናል። ይህ ማለት ከብሉይ ኪዳን መካከል ብዙዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት በነቢያት ነው ማለት ነው። እነዚህ ነቢያት እኛ በምናስተውለው በተለመደው መንገድ አልነበረም ነቢይነታቸው፤ ነገር ግን ለነበሩበት ትውልድ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ነበሩ። የትንቢት መጻሕፍት ስለ ወደፊት ሁኔታዎች እንደሚናገሩ ከማሰብ ይልቅ መልእክቶች (ስብከቶች) እንደሆኑ መቊጠሩ ይመረጣል። ብዙውን ጊዜ ነቢያት የእስራኤልን ሕዝብ በሚመለከት ከዚህ ቀደም እግዚአብሔር በታሪካቸው ውስጥ ስላደረገው ነገር ይናገሩ ነበር። አብዛኛው መልእክታቸው በዘመናቸው የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ስለነበሩበት ሁኔታ የሚናገር ነበር። ስለ ወደፊት ሁኔታዎች የሚናገረው የመልእክታቸው ክፍል ጥቂቱ ብቻ ነበር። እነዚህ ታሪካዊ ድርጊቶች ለመጀመሪያዎቹ ሰሚዎች ወደፊት የሚፈጸሙ ቢሆኑም፥ ዛሬ ግን ለእኛ ያለፉ ታሪኮች ናቸው፤ ስለዚህ ከነቢያት መጻሕፍት መካከል እስካሁን ድረስ ያልተፈጸሙ ትንቢቶች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

ብዙ ሰዎች የነቢያትን መጻሕፍት በተሳሳተ መንገድ የሚተረጕሙት ስለ እነርሱ ያላቸው አስተሳሰብ በዚህ ዓይነት የተሳሳተ ስለሆነ ነው። ለዚህም ጉዳይ ምቹ ሁኔታ የፈጠረው ስለ ወደፊት ሁኔታ ለማወቅ ከፍ ያለ ጒጒት ያላቸው ብዙ ክርስቲያኖች በመኖራቸው ነው። እነዚህ የትንቢት መጻሕፍት ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ግልጽ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚሰጡ ይገምታሉ። የትንቢት መጻሕፍት ሕይወታቸውን እንዴት መለወጥ እንዳለባቸውና ለእግዚአብሔር ክብር እንዴት እንደሚኖሩ የሚያሳዩ ከመሆን ይልቅ፥ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ግምታዊ ሙከራ ለማድረግ የሚጠኑ መጻሕፍት ይመስሏቸዋል። ይህ አመለካከት ከመጠን ያለፈ ግምታዊ ነገር ውስጥ እንድንገባና የተሳሳቱ ትርጕሞችን እንድንሰጥ ያደርገናል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ክርስቶስ በዚህ ዓመተ ምሕረት፥ በዚህ ቀን ይመጣል በማለት ይናገራሉ። ወይም ከመንግሥታት መሪዎች መካከል አንዱን «እርሱ ሐሰተኛው ክርስቶስ ነው» ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊት ሁኔታዎች ሲናገር ግልጽ ያልሆነውን ያህል ግልጽ ለማድረግና ራሳቸውን ደስ ለማሰኘት ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ በመግባት ትርጓሜ ለመስጠት ይሞክራሉ። ይህን በማድረጋቸውም ብዙ ጊዜ ይሳሳታሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በነቢያት መጻሕፍት ላይ የዚህ ዓይነት አመለካከት ሲንጸባረቅ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የሚያደርጉት ትንበያ (ቅድመ ምልከታ) ምን ዓይነት ነው? ሐ) የተሳሳተ ትንበያ ወይም ትርጕም ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች በዓለም ፊት ያላቸውን ገጽታና አመለካከት የሚያበላሸው እንዴት ነው?

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ መሆናችን መጠን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነቢያት መጻሕፍት የሚሰጡ ከእውነት የራቁና የተሳሳቱ አተረጓጐሞች የሚያስከትሏቸውን አደገኛ ሁኔታዎች ተረድተን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሰዎች ኢየሱስ የሚመጣው በዚህ ቀን ነው እያሉ ሲናገሩ ይህ ሌሎች ክርስቲያኖችን ይረብሻቸዋል። በክርስትና ሕይወት ውስጥ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆኑ እንደ መመስከርና ማስተማር የመሳሰሉ ነገሮችን እንዲዘነጉ በማድረግ በእምነታቸው ሰነፎች ያደርጋቸዋል። እንዲሁም ከእውነት የራቀ አተረጓጐም በዓለም ፊት የቤተ ክርስቲያንን ስም የሚያጎድፍ ነው። የኢየሱስ ወንጌል በኃይል እንዲነገር መንገድ ከመክፈት ይልቅ ወንጌልን መሳለቂያ ያደርገዋል። ኢየሱስ በቅርብ ይመጣልና መዘጋጀት ያስፈልጋል በሚለው አሳብ ላይ የሚሳለቁ ብዙ ሰዎች አሉ። ምክንያቱም ክርስቲያኖች ትንቢትን በተሳሳተ መንገድ ተጠቅመው ኢየሱስ በዚህ ቀን ይመጣል የሚል ቃል በመናገራቸው ነው። ከማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይልቅ በተሳሳተ መንገድ የመተርጐም ዝንባሌ ያላቸው የነቢያት መጻሕፍት ናቸው። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡-

1. አብዛኛዎቹ የነቢያት መጻሕፍት፥ በተለይም የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ – ዳንኤል) የተከታታይ መልእክቶች ስብስብ ናቸው። መጻሕፍቱ ግልጽ በሆነ አስተዋጽኦ ተቀናብረው የተጻፉ አይደሉም፤ ስለዚህ በመጻሕፍቱ ውስጥ እየጐለበተ የሚሄድ የሃሳብ ሂደት ስለማናገኝ መልእክቱን መረዳት አስቸጋሪ ነው።

2. ብዙውን ጊዜ መጻሕፍቱ በተናጠል ያሉና ተያያዥነት የሌላቸው መልእክቶችን ያካተቱ ስለሆኑ አንድ ስብከት ወይም መልእክት የት ቦታ እንደሚጠቃለልና ሌላው የት እንደሚጀምር ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ነቢያቱ መጻሕፍቱን በጻፉበት ጊዜ የምዕራፍና ቍጥር ክፍፍል እንዳልነበረ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የምዕራፍ ክፍፍል ሰዎች ለመጻሕፍቱ አስተዋጽኦ ለማበጀት ያደረጉት ሙከራ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጸሐፊው ባቀረበው መልእክት ወይም ስብከት አንጻር ሳይሄዱ ይቀራሉ። በዚህም ምክንያት የመልእክቱን ተዛማጅነትና የአሳብ ሂደት እናጣለን።

3. አብዛኛዎቹ መልእክቶች የሰፈሩት በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አይደለም። የዚህን እውነትነት በተለይ የምናየው በትንቢተ ኤርምያስ ሲሆን፥ መልእክቶቹ አንድ ንጉሥ ከነበረበት ዘመን ወደ ሌላ ንጉሥ ዘመን ያለምንም የታሪክ ቅደም ተከተል ሲሸጋገሩ እንመለከታለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 1፡1-3፤ 25፡1፤ 26፡1፤ 27፡1፤ 34፡1፤ 36፡1፤ 40፡1-2፤ 45፡1 ተመልከት። ሀ) ኤርምያስ የተነበየው በእነማን ዘመነ መንግሥት ነበር? ለ) ከዚህ ቀደም ከምታውቀው የነገሥታቱ ዘመነ መንግሥት ቅደም ተከተል አንጻር እነዚህን ምዕራፎች በጊዜ ቅደም ተከተል አስፍራቸው።

4. ብዙውን ጊዜ እነዚህ ትንቢቶች በተሰጡባቸው ጊዜያት የተፈጸሙትን ታሪካዊ ድርጊቶች አናውቅም። ብዙዎቹ ትንቢቶች (መልእክቶች) በዘመኑ ለተፈጸሙ ለተወሰኑ ታሪካዊ ድርጊቶች ምላሽ ይሆኑ ዘንድ የተሰጡ ነበሩ (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 9)። ነገር ግን ለአብዛኛዎቹ ትንቢተች ያ ድርጊት ምን ግንኙነት እንደነበረው አናውቅም። ስለዚህ ትንቢተቹን በሚመለከት ግልጽ የሆነ ታሪካዊ ሥረ መሠረት የለንም።

5. አብዛኛዎቹ ትንቢተች የተሰጡት በተራ ቋንቋ ሳይሆን በግጥም መልክ ነው። በጥንት ዘመን ጸሐፊዎች በዚህ መንገድ መጻፍ ይመርጡ የነበረው ሰዎች መልእክቱን ለማስታወስ ይቀላቸው ስለነበረ ነው። (ለምሳሌ፡- የመልእከት ወይም የስብከት ቃላትን ከማስታወስ ይልቅ የመዝሙር ቃላትን ማስታወስ ይቀላል።) ስለዚህ ነቢያት ብዙ ጊዜ የጻፉት በርካታ ተምሳሌታዊውን መግለጫዎችን በመጠቀም በግጥም መልክ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ተምሳሌታዊውን ቋንቋ ከቀጥተኛ ትንቢታዊ አነጋገር መለየት አስቸጋሪ ነው።

6. መልእክቱ በመጀመሪያ ለደረሳቸው ሰሚዎች ግልጽ ቢሆንም እንኳ መልእክቱ በተሰጠበትና እኛ በምንኖርበት ዘመን መካከል የብዙ መቶ ዓመታት ልዩነት ስላለ በባህላችን ማለትም በሃይማኖታዊ፥ በታሪካዊና በልማዳዊ ዘይቤያችን በጣም የተለያየን ስለሆንን እነዚህን ትንቢቶች የመተርጐም አስቸጋሪነት እየጨመረ ይሄዳል። 

የትንቢት መጻሕፍትን ለመተርጐም የሚጠቅሙ መመሪያዎች 

አንድን የትንቢት መጽሐፍ ክፍል በትክክል ለመተርጐም በምትሞክርበት ጊዜ የሚከተሉትን መመሪያዎች አስታውስ፡-

1. የትርጕም አካሄዱን ለመረዳት ክፍሉን በጥንቃቄ አጥና። ትንበያ ከሚመስል ቍጥር አትጀምር። ይልቁንም ክፍሉን በሙሉ አንብብ። ያንን የተለየ ክፍል ለመረዳት በዙሪያው ያሉ አሳቦች ይረዱህ እንደሆነ ለመመልከት ከክፍሉ በኋላና በፊት ያሉትን ምዕራፎች አንብብ። ከተቻለ የመጽሐፉን አጠቃላይ ትምህርት ለመረዳት መጽሐፉን በሙሉ አንብብ። ቀጥለህ የሚከተለውን ጥያቄ ጠይቅ፡- «ይህ ክፍል ከመጽሐፉ አጠቃላይ ትምህርት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?» 

2. ግልጽ ያልሆኑልህን አሳቦችና ቃላት ዘርዝር። እነዚህ ቃላት ወይም አሳቦች ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትን ወይም ማብራሪያን ተመልከት። ተምሳሌታዊ መግለጫዎች በሚኖሩበት ጊዜ መግለጫዎቹ መጀመሪያ ለተጻፈላቸው ሰዎች ምን ማለት እንደሆነ ተረዳ። ቀጥሎ ከባህልህ ወይም በዚህ ዘመን ካሉ ነገሮች ለዚህ ተምሳሌታዊ መግለጫ አቻ የሆነ ነገር ፈልግ (ለምሳሌ፣ ጦሮችና ሰረገላዎች በዚህ ዘመን ባሉ ጠመንጃዎችና ታንኮች ሊመስሉ ይችላሉ)።

3. መልእክቱ የቀረበው በግጥም መሆኑን ልብ በል። ስለሆነም ትንቢቱን ለመተርጐም ለግጥምና ለቅኔ አተረጓጐም የሚረዱ ሕግጋትን ተጠቀም።

4. የክፍሉን ዋና ዋና አሳቦች (ትምህርቶች) በሙሉ ዘርዝር። በክፍሉ ውስጥ የአሳብ መጐልበት መኖሩን ለማሳየት በሚያስችል መንገድ በዝርዝር ግለጻቸው። 

5. ክፍሉ የተጻፈበትን ጊዜ ታሪካዊ ሁኔታ ለመወሰን ሞክር። ምን በመፈጸም ላይ ነበር? ድርቅ ነበርን? ጦርነት ነበርን? ባቢሎናውያን አይሁድን ይወጉ ነበርን? ከመጽሐፈ ነገሥትና ዜና መዋዕል ስለ ዘመኑ ለማንበብ ሞክር።

እነዚህ ነቢያት በነበሩበት ዘመን በእስራኤል ብዙ ችግሮች እንደነበሩ አስታውስ። የሕዝቡን ሕይወት ያጐሳቆሉ ከፍተኛ ጦርነቶች ነበሩ። በእስራኤልና በይሁዳ መካከል የእርስ በርስ ጦርነቶች ነበሩ። ከሶርያውያን፥ ከአሦራውያንና ከባቢሎናውያን ጋር የተደረጉ ብሔራዊ ጦርነቶች ነበሩ። ከሕዝባቸው አብዛኛው ክፍል በሌሎች ሕዝቦች ተማረኩ። ከግዛታቸው አብዛኛው ክፍልም ተወሰደባቸው። ብዙ ሕዝብ ባህላዊ እምነታቸው የሆንውን አንድ አምላክ እግዚአብሔርን ትተው የተለያዩ ጣዖታትንና የተቀረጹ ምስሎችን ያመልኩ ስለነበር በአይሁድ ሕዝብ መካከል ክሕደት ተስፋፍቶ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ አይሁድ የነበሩበትን ታሪካዊ ሁኔታ ማወቅ ነቢያትንና እነርሱ ያመጡአቸውን ልዩ መልእክቶች አስፈላጊነት ለመረዳት ምን ያህል የሚጠቅም ይመስልሃል?

6. በዚያ ክፍል ውስጥ ነቢዩ ለአይሁድ ሊያስተምር የሞከረውን ዋናውን መልእክት ለማግኘት ሞክር። ትንቢት የሚሰጥበት ዋና ምክንያት ስለ ወደፊቱ ሁኔታ ለሰዎች ለመናገር አይደለም። ይልቁንም ሰዎችን ለማበረታታት፥ ለመገሠጽና ለማስጠንቀቅ ነበር፤ የክፍሉ ዋና መልእክት ይህ ነው። ስለ እግዚአብሔር ምን ያስተምረናል? ስለተቀደሰ አኗኗር ምን ያስተምረናል? እግዚአብሔር ፍርድን ስለሚያመጣበት መንገድ ምን ያስተምረናል? ትንቢቱን ለመረዳት በመሞከር አሳብህ ከመበታተኑ በፊት፥ መልእክቱን ለመረዳትህ እርግጠኛ ሁን። ትንቢት ሁልጊዜ የሚሰጠው በዚያን ወቅት የነበሩትን ሰዎች አኗኗርና አስተሳሰብ ለመለወጥ ነበር። ብዙ ሰዎች ወደፊት የሚሆነውን ነገር እንዲያውቁ ተብሉ የሚሰጥ አልነበረም። የክፍሉ ዋና ትምህርት ብዙ ጊዜ በዚህ ዘመን ላለች ቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ የሆነ መልእክት ነው። ስለዚህ በነቢዩ በኩል እግዚአብሔር ለዚያ ዘመን ሰዎች እንዲደርስ የፈለገው መልእክት ምን እንደሆነ በጥንቃቄ ተመልከት፤ እንዲሁም ለአንተና ለቤተ ክርስቲያንህ እንዲደርስ የፈለገው መልእክት ምን እንደሆነ በጥንቃቄ ተመልከት። ለምሳሌ፣ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርገው ስለሚፈልገው ነገር የተናገሩበት ዋና ምክንያት በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ታሪካቸውን የሚቆጣጠረውንና በቅድስና የሚኖረውን እግዚአብሔርን በማክበር ይኖሩ ዘንድ ነበር። ነቢያት እግዚአብሔር እንዲከበር ይፈልጉ ነበር። በተለይ ደግሞ ትንቢቶቹ በሚፈጸሙበት ጊዜ የነበሩ ሰዎች እንዲያከብሩት ይፈልጉ ነበር። 

7. የነቢያትን መልእክት አይሁድ ለቃል ኪዳኑ ቢታዘዙ ወይም ባይታዘዙ ስለሚሆነው ነገር ከተጻፈባቸው ከኦሪት ዘሌዋውያን፥ ዘኁልቁና ዘዳግም ጋር አወዳድር። ግንኙነታቸው እንዴት ነው? እንዲሁም በታሪክ ውስጥ በኋላ ከታዩት፥ በተለይም ደግሞ በአዲስ ኪዳን ከተገለጡት ትንቢቶች ጋር አወዳድር። እነዚህ ባመዛኙ ቀደም ሲል የተነገረውን ትንቢት ለመረዳትም ይጠቅሙናል። ጊዜው እያለፈ በሄደ መጠን የእግዚአብሔር ቃል የሚሰጠን መረጃ እየጨመረ መሄዱን አስታውስ። ስለሆነም እውቀት በኋለኞቹ መጻሕፍት የበለጠ እየጨመረ መሄዱን ተመልከት።

8. ያ ክፍል የያዘው ትንቢት ምን ዓይነት እንደሆነ ወስን። ነቢያት ብዙ ጊዜ የጻፉባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡-

ሀ. በክስ መልክ የቀረበ መልእክት፡- በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የፍርድ ቤት ችሎት በመካሄድ ላይ እያለ የቀረቡ የሚመስሉ ብዙ ክፍሎች አሉ። እግዚአብሔር እስራኤላውያን የገቡትን ቃል ኪዳን እንዳፈረሱ የሚጠይቅ ዳኛና ዐቃቤ ሕግ ነው። አንዳንድ ጊዜ ፍጥረት ምስክር ወይም ታዛቢ ሆኖ ተጠቅሶአል። እስራኤላውያን ደግሞ ተከሳሾችም ጠበቆችም ነበሩ (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 3፡13-26).

ለ. ፍርድንና ዋይታን የሚያውጅ መልእክት፡- ብዙ ጊዜ እነዚህ ክፍሎች «ወዮ» የሚለውን ቃል የያዙ ናቸው። በእነዚህ ክፍሎች ብዙ ጊዜ ነቢዩ በመምጣት ላይ ያለውን ጥፋት፥ የጥፋቱን ምክንያቶችና የጥፋቱን ዓይነት የሚያመለክቱ ነገሮችን ይናገራል (ለምሳሌ፡- ዕንባቆም 2፡6-8፤ ኢሳይያስ 5፡8-23)።

ሐ. ሊመጣ ስላለው በረከት የሚያውጅ መልእክት፡- የነቢያት አብዛኛው መልእክት ፍርድና ዋይታ ያለበት ቢሆንም፥ በእያንዳንዱ ነቢይ መልእክት ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ተበታትኖ ያለ የበረከት ተስፋ እናገኛለን። እነዚህ በረከቶች ብዙውን ጊዜ «በዚያን ቀን» የሚል ሐረግ አለባቸው። ይህም በረከቱ የሚመጣበትን ያልተወሰነ ጊዜ የሚያመለክት ነው (ለምሳሌ፤- አሞጽ 9፡11-15፤ ሆሴዕ 2፡16-23)።

መ. ስለ ወደፊት ታሪካዊ ድርጊቶች ለመናገር ከፍተኛ ተምሳሌታዊ መግለጫዎችን የሚጠቀሙ ትንቢቶች፡- እነዚህ ክፍሎች ብዙ ጊዜ የአንድን ነገር በተለይም የዓለምን ፍጹም ውድመት የሚያመለክቱ («አፖካሊፕቲክ») ክፍሎች በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ ክፍሎች ራእይና መላእክት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱባቸው ብዙ ተምሳሌቶች አሏቸው። (ለምሳሌ፡- ራእይ 4-22፤ ዳን. 7-12፤ ዘካርያስ 1፡8-14)። እነዚህ ክፍሎች ለመተርጐም እጅግ አስቸጋሪ ስለሆኑ፥ ግምታችን በትርጒሙ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። 

9. የነቢዩ መልእክት ነቢዩ ይኖርበት ለነበረው ዘመን ብቻ የተነገረ ወይም ስለ ወደፊቱ ዘመን ጭምር መሆን አለመሆኑን ወስን። እዚህ ላይ ነቢዩ ሕዝቡን እየወነጀle፥ እግዚአብሔር ለምን እንደሚፈርድባቸው እየነገራቸው ነው ወይስ በኃጢአታቸው ምክንያት ወደፊት ምን እንደሚድርስባቸው እያስጠነቀቃቸው ነው ያለው? 

10. ስለ መጪው ጊዜ የሚናገሩትን ትንቢቶች በምትመመለከትበት ጊዜ፥ የተነገሩት ጉዳዮች ተፈጽመው እንደሆነ ወይም ገና ወደፊት የሚፈጸሙ ስለ መሆናቸው ወስን። ቀደም ሲል እንደገለጽነው፥ በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ትንበያዎች ተፈጽመዋል። በአሦራውያን ወይም በባቢሎናውያን አማካይነት በተከናወነው ምርኮ ወይም እስራኤላውያን ከምርኮ በተመለሱበት ጊዜ ተፈጽመዋል። እንዲሁም አብዛኛዎቹ በክርስቶስ መጀመሪያ መምጫ ጊዜ ተፈጽመዋል። 

11. ወደፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች በግልጽ ስለሚናገሩ ክፍሎች ልናስታውሳቸውና ከሌሎቹ ልንለያቸው የሚያስፈልጉን አራት ዓይነት ትንቢተች አሉ፤ እነርሱም፡-

ሀ. በቀጥታ የተፈጸሙ ቀጥተኛ ትንቢቶች፡- በእነዚህ ዓይነቶቹ ትንቢቶች ፍጻሜው የተለየን ድርጊት የሚያመለክት ሆኖ፥ ልክ እንደ ትንቢቱ ይፈጸማል (ለምሳሌ፡- ሚክ. 5፡2)። 

ለ. ተምሳሌታዊ ትንቢቶች ሆነው በተምሳሌነት የተፈጸሙ፡- የእነዚህ ዓይነተቹ ትንቢቶች ብዙ ጊዜ የሚነገሩት ነቢያቱ ይኖሩበት በነበረው ዘመን ስለተከናወኑት ነገሮች ወይም በቡሉይ ኪዳን ውስጥ ስለተፈጸሙት ነገሮች ነው። ይሁን እንጂ በአንዳንድ መንገዶች በአዲስ ኪዳን የተፈጸሙ ድርጊቶችን በተምሳሌት የሚያሳዩ ናቸው (ለምሳሌ፡- ዘካርያስ 11፡12-13፤ ማቴዎስ 26፡14-15፤ 27፡3-10፤ ሆሴዕ. 11፡1፤ ማቴዎስ 2፡14-15)። ብዙውን ጊዜ እነዚህን ነገሮች መረዳት የሚቻለው ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ መሆናቸውን አዲስ ኪዳን በማረጋገጡ ነው። ከአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የምንለይበት ነገር ቢኖር የትኞቹ ትንቢቶች በተምሳሌታዊ ሁኔታ ወደ ክርስቶስ እንደሚያመለክቱ የሚነግረን መንፈስ ቅዱስ ስለሌለን ትንቢቶችን ከመጠን በላይ ጠልቀን ከማንበብ ልንቆጠብ ይገባል። 

ሐ. ሁለት ትርጒም የነበራቸው ትንቢቶች፡- አንዳንድ ትንቢቶች ለእስራኤላውያን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስለሚፈጸሙባቸው ነገሮች የተሰጡ ሲሆኑም እንኳ ከብዙ ዓመታት በኋላ በተለይም በዘመናት መጨረሻ የሚፈጸሙ ነገሮች ተምሳሌቶች ናቸው። (ለምሳሌ፣ ዳንኤል 11፡21-45 የሚናገረው ስለ አንጾኪየስ ኢጲፋነስ ሲሆን፥ ስለ ሐሰተኛው ክርስቶስም ይናገራል።) 

መ. በአጠቃላይ ሕዝብ ጥፋት ላይ የሚያተኩሩ (አፖካሊፕቲክ) ትንቢቶች፡- እነዚህ ትንቢቶች ብዙ ተምሳሌቶችን የሚጠቀሙ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ለዚህች ምድር ያለው ዕቅድ የሚጠቃለልበትን የመጨረሻ ዘመን ሁኔታን የሚያመለክቱ ናቸው። አብዛኛዎቹን ተምሳሌቶች በትክክል መተርጐም ቀላል ስላልሆነ፥ ስለምን እንደሚናገሩ ለመረዳት ብንችልም እንኳ በተለየ መንገድ የተተረጐሙትን የሌሎች ሰዎችንም ትርጕሞች በመቻቻል ማስተናገድ ይኖርብናል። 

12. አንዳንድ ጊዜ ነቢያት ትንቢትን ሲናገሩ መልእክታቸው የሚያስከትለውን ውጤት ሙሉ በሙሉ አያውቁም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ነቢያት በአንድ ጊዜ የሚፈጸሙ የሚመስሉ ሁለት አሳቦችን በአንድነት ይገልጹ ነበር። ይሁን እንጂ አሳቦቹ ሁለት የተለያዩ ጊዜያትን እንደሚናገሩ እናውቃለን። ለምሳሌ፡- ስለ ክርስቶስ የመጀመሪያና ዳግም ምጽአት በአንድ ጊዜ የሚናገሩ የነቢያት መልእክቶች አሉ። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይህን አልተረዱም ነበር (ለምሳሌ፡- ዘካርያስ 12፡10-14፡21)። 

ይህንን እውነት ለመረዳት በአንድ ከፍተኛና ትልቅ ተራራ ላይ ሆንህ በርቀት የሚታዩ ሌሉች ተራራዎችን እንደምትመለከት አድርገህ አስብ። እጅግ የተቀራረቡና በአንድነት ያሉ በሚመስሉ ሁለት ተራሮች መካከል ትልቅ ሸለቆ ሊኖር ይችላል። ነቢያት በከፍተኛና ትልቅ የጊዜ ተራራ ላይ ሆነው ይመለከቱ ነበር። በዚህ ጊዜ ልክ እንደ ሁለቱ ተራራዎች በአንድ ጊዜ የሚፈጸሙ የሚመስሉትን ሁለት ድርጊቶችን ተመለከቱ፤ ነገር ግን እነዚህ ሁለት ድርጊቶች በ2000 ዓመታት ልዩነት የተፈጸሙ መሆናቸውን እናውቃለን። 

13. በርካታ ትንቢቶች ለመረዳት ግልጽ የሚሆኑት ከተፈጸሙ በኋላ ነው። ስለ ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምድር መምጣት የተነገሩ ትንቢተች በብሉይ ኪዳን ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ወይም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለነበሩ ሰዎች ግልጽ አልነበሩም። እነዚህ ትንቢቶች ግልጽ የሆኑት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ ነበር። አሁንም ገና ወደፊት ሊፈጸሙ ያሉ ትንቢቶች ለእኛ ግልጽ አይደሉም። ከተፈጸሙ በኋላ ግን ወደ ኋላ መለስ ብለን ልንመለከትና በግልጽ ልንረዳቸው እንችላለን። ስለዚህ ይህ ነገር ገና ወደ ፊት ሊፈጸሙ ስላሉ ትንቢቶች ያለንን አስተሳሰብ ላላ አድርገን እንድንይዘው ሊያስተምረን ይገባል። እንዴት እንደሚፈጸሙ አሳብ ሊኖረን ቢችልም እንኳ አፈጻጸማቸው እኛ ከምናስበው ፍጹም በተለየ መንገድ ሊሆን ይችላል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 9 አንብብ። ከላይ በተመለከትናቸው 13 መመሪያዎች በመጠቀም ይህንን ምዕራፍ አጥና። ሀ) በዚህ ክፍል ውስጥ ግልጽ ያልሆኑት ቃላት የትኞቹ ናቸው? ትርጕማቸውን ስጥ። ለ) የምዕራፉን ዋና ዋና ትምህርቶች ዘርዝር። ሕዝቡን ለማበረታታት፥ ለመገሠጽ ወይም ለመምከር የታቀደው እንዴት ነው? ሐ) የምዕራፉ ታሪካዊ ሥረ መሠረት ምንድን ነው? መ) በኦሪት ዘዳግም 28-32 ከተጠቀሱ መርገሞችና በረከቶች ጋር ተመሳሳይነት አለውን? ካለው እንዴት? ሠ) ይህ ምዕራፍ ከየትኛው ዓይነት የነቢያት መልእክት ይመደባል? ረ) የተሰጡት የትንቢት ዓይነቶች የቅርብ ጊዜ ናቸው ወይስ የሩቅ ጊዜ፥ ወይስ የሁለቱም? የሩቅ ጊዜ ከሆኑ ተፈጽመዋልን? እንዴት? የተፈጸሙት በተምሳሌት ነው ወይስ በቀጥታ? ሰ) ከግል ሕይወትህ ወይም ከቤተ ክርስቲያንህ ጋር ልታዛምዳቸው የምትችለውን ትምህርቶች ከዚህ ክፍል ጥቀስ፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: