መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን ይላል?

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ ዳባ

በአንዳንድ ሰዎች አስተሳሰብ ግብረ ሰዶማዊ መሆን እንደ ቆዳችን ቀለም እና ቁመታችን ሁሉ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ሥነ-ሕይወታዊ (biological) ክስተት ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የግብረ ሰዶማዊነት ተግባር ኃጢአት መሆኑን በግልፅ እና በማያሻማ መንገድ ያስተምራል (ዘፍጥረት 19፡1-13፤ ዘሌዋውያን 18፡22፤ 20፡13፤ ሮሜ 1፡26-27፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡9)፡፡ ይህ ክፍተት፣ ብዙዎችን ማቆሚያ ወደሌለው ክርክር፣ ንትርክ እና አልፎ ተርፎም ጥላቻ መርቷል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን እንደሚል ስንመረምር በግብረ ሰዶማዊነት ባህሪ እና በግብረ ሰዶማዊነት ዝንባሌ መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት፣ ኃጢአትን በተግባር በማድረግ እና በኃጢአት መፈተን መካከል እንዳለው አይነት ልዩነት ነው፡፡  የግብረ ሰዶማዊነት ባህሪ ኃጢአት ነው፤ ሆኖም ግን መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ኃጢአት መፈተን በራሱ ኃጢአት እንደሆነ በጭራሽ አይናገርም፡፡ በአጭር አነጋገር፣ ከፈተና ጋር የሚደረግ ትግል ወደ ኃጢአት ሊመራ ይችላል፤ ነገር ግን ትግሉ ራሱ ኃጢአት አይደለም፡፡

ሮሜ 1፡26-27፣ ግብረ ሰዶማዊነት እግዚአብሔርን የመካድ እና ያለመታዘዝ ውጤት እንደሆነ ያስተምራል፡፡ ሰዎች በኃጥአትና ባለማመን መኖር ሲቀጥሉ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ውጭ ያለ ሕይወት ከንቱ እና ተስፋ-ቢስ መሆኑን ያሳያቸው ዘንድ ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ይሰጣቸዋል። ከእነዚህ አስነዋሪ ምኞቶች መካከል አንዱ ደግሞ ግብረ ሰዶማዊነት ነው፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡9 ግብረ ሰዶማዊነትን የሚፈጽሙ እና በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር የፈጠረውን ሥርዓት የሚጥሱ በእግዚአብሔር ፍርድ ስር እንደሆኑ ያውጃል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ለአመጽ፣ ስካር፣ ሌብነት እና ሌሎች ሃጢአቶች ከሌላው ሰው ይልቅ ይበልጥ ተጋልጭ ሆነው ሊወለዱ እንደሚችሉ ሁሉ ለግብረ ሰዶማዊነትም ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ይህ ጉዳይ፣ ግለሰቡ ለኃጢያተኛ ምኞቱ (ተጋላጭነቱ) በመሸነፍ ለፈጸመው ኃጢአት ሰበብ ሊሆን አይችልም፡፡ ለንዴት ሃጢአት ተጋላጭ የሆነ ሰው በሚገጥሙት ተንኳሽ ሁኔታዎች ሁሉ ላይ ተጋላጭነቱ ንዴቱን በተግባር የመግለጥ መብት እንደማይሰጠው ሁሉ በግብረሰዶም ሃጢአት ተጋላጭ ሆኖ መወለድም በዚህ ኃጢአት ባህሪ ውስጥ ለመኖር እንደምክንያትነት መቅረብ አይችልም፡፡

በቀላሉ የምንሳብበት ኃጢአት ምንም ይሁን ምን፣ በዚያ ኃጢአት ለመኖር ፈቅደን ስናበቃ ከእግዚአብሔር ጋር የሰመረ ሕብረት እንዳለን ልናስብ ከቶ አይገባም፡፡ ጳውሎስ የቆሮንቶስ አማኞች ኢየሱስን ለመከተል ከመወሰናቸው በፊት ያደርጓቸው የነበሩትን የኃጢአት አይነቶች ዘርዝሯል፤ በዚያ ዝርዝር ውስጥ ከሰፈሩት መካከል ግብረ ሰዶማዊነት አንዱ ነው፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 6፡11፣ “ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል” ይላል፡፡ ይህ ማለት፣ አንዳንድ የቆሮንቶስ አማኞች ከመዳናቸው በፊት ግብረ ሰዶማዊነትን ይለማመዱ ነበር ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን፣  የትኛውም ኃጢአት ከኢየሱስ ደም የማንጻት ኃይል በላይ ሊሆን አይችልምና ነጽተዋል፡፡ ይህን መንጻት ካገኙ በኋላ፣ በቀደመው ኃጢአታቸው ጸንተን መኖር አልተገባቸውም፡፡

በግብረ ሰዶማዊነት ኃጢአት መሳብ ማለት እግዚአብሔር በከለከለው ምኞት መሳብ ማለት ነው፤ የኃጢአት ምኞት ዞሮ ዞሮ ስሩ ከሆነው ከኃጢአታዊ ማንነታችን ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ምኞታችንን የማድረግ ሃጢአታዊ ዝንባሌያችን ያለንበትን አለምና ድርጊቶቻችንን በተዛባ መንገድ እንድንመለከታቸው ሊያደርገን ይችላል፡፡ ሀሳቦቻችን፣ ፍላጎቶቻችን እና ዝንባሌዎቻችን ከዚህ ሃጢአታዊ ዝንባሌያችን ተጽእኖ ውጪ ሊሆኑ አይችሉም። ከዚህ የተነሳ፣ ግብረ ሰዶማዊነት ሁል ጊዜ ወደን እና ፈቅደን በምርጫችን የምናደርገው ተግባር ላይሆን ይችላል፤ ከዚህ ሃጢአታዊ ተፈጥሯችን የሚመነጭ አስገዳች ምኞት ሊሆንም ይችላልና፡፡  የተመሳሳይ ጾታ ወሲባዊ ዝንባሌ የዚህ የወደቀው (አሮጌው) ተፈጥሮ መገለጫ ነው፡፡

በኃጢያት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ኃጢአተኞች (ሮሜ 3፡23) እንደመሆናችን፣ በድክመቶች፣ ፈተናዎች እና በኃጢአት ግፊቶች ውስጥ ተወጥረን ነው የምንኖረው። ይህ ዓለም የሰዶማዊነት ኃጢአት ልምምድን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ኃጢአታዊ ማባበያዎች እና ማሰናከያዎች  የተሞላ ነው፡፡

የሰዶማዊነት ፈተና ከጊዜ ወደጊዜ የበርካቶች ፈተና እየሆነ መምጣቱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ፈተና ውስጥ ያሉ ሰዎች ከዚህ ፈተና ለመላቀቅ የአመታት ትግል ያደረጉ መሆናቸውንም ሲገልጹ ይሰማል፡፡ ሰዎች እንዴት ወይም ምን ሊሰማቸው እንደሚገባቸው በመወሰን ላይ ቁጥጥር ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም፣ ፈተናው ከስሜት አልፎ ተግባራዊ እንዳይሆን ራሳቸውን መግዛት ይችላላሉ (2ኛ ጴጥሮስ 1፡5-8)፡፡ ሁላችን፣ ፈተናን የመቃወም ሀላፊነት አለብን (ኤፌ. 6፡13)። ሁላችንም፣ “በአእምሮአችን መታደስ መለወጥ” አለብን (ሮሜ 12፡2)፡፡ “የሥጋችንን ምኞት ላለመፈጸም” ሁላችን “በመንፈስ መመላለስ” አለብን (ገላትያ 5፡16)።

በመጨረሻም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊነትን ከሌላ ከማንኛውም ኃጢአት ይልቅ “ታላቅ” ኃጢአት እንደሆነ አይገልጽም፡፡ ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፡፡ ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ አመጽ ነው (1ኛ ዮሐንስ 3፡4)፡፡ በየትኛውም አይነት ኃጢአት ውስጥ ብንኖር ያለ ክርስቶስ ከሆንን በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ነን፡፡ ለአመንዝራው፣ ጣዖት አምላኪው፣ ነፈሰገዳዩ እና ሌባው የተዘረጋች የእግዚአብሔር የምሕረት እጅ ለግብረ ሰዶሙም እንዲሁ እንደተዘረጋች ነች፡፡ ለድነታቸው በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ለሚታመኑ ሁሉ እግዚአብሔር ግብረ ሰዶማዊነትን ጨምሮ በሌሎች ኃጢያቶች ላይ ድልን ሊሰጠን ቃል ገብቶልናል (1ኛ ቆሮንቶስ 6፡11፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17፣ ፊልጵስዩስ 4፡13)።

1 thought on “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን ይላል?”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading