I. ኢሳይያስ የኖረበት ዘመን ታሪካዊ ሥረ-መሥረት፡-
የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 1፡1 እና 2ኛ ነገሥት 15-20 አንብብ። ሀ) ኢሳይያስ ባገለገለባቸው ዘመናት የነበሩትን ነገሥታት ስም ዘርዝር። ለ) የእነዚህ ነገሥታት ባሕርይ ምን ይመስል ነበር? ሐ) በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በእስራኤልና በይሁዳ የተከናወኑ ዋና ዋና ድርጊቶች ምን ነበሩ?
ነቢዪ ኢሳይያስ የኖረውና የሠራው ለብዙ ዓመታት ነበር። መቼ እንደተወለደ ባናውቅም እንኳ የነቢይነት አገልግሉቱን የጀመረው ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት በ740 ዓ.ዓ. ይመስላል፤ የኖረውም እስከ 680 ዓ.ዓ. አካባቢ ይመስላል። ይህ ማለት በነቢይነት ያገለገለው ከ55 ዓመታት በላይ ነበረ ማለት ነው። ኢሳይያስ በዚህ ረጅም ዕድሜው በሕዝቡ መካከል የተካሄዱ የበርካታ ለውጦች ምስክር ነበር። ሕዝቡ በከፍተኛ ደረጃ እግዚአብሔርን የወደዱበትና ደግሞም በግልጽ በእግዚአብሔር ላይ ያመፁበትን ጊዜ ተመልክቷል። በሕዝብ መካከል ከፍተኛ ጥፋትና ደግሞም ከፍተኛ ብልጽግናና ሰላም የነበረበትን ወቅት ተመልክቷል።
1. ዖዝያን፡- የዖዝያን ዘመነ መንግሥት የይሁዳ ሕዝብ ከዳዊትና ከሰሎሞን በኋላ ደርሶበት ወደማያውቀው ከፍተኛ ሥልጣን የደረሰበት ጊዜ ነበር። የግብፅና የአሦር መንግሥታት ደካሞች ስለነበሩ ይሁዳና እስራኤል ከውጭ መንግሥታት ተጽዕኖ ነፃ የሆኑበት ጊዜ ነበር፡፡ በሰሜን በኩል የእስራኤል መንግሥት በዳግማዊ ኢዮርብዓም አመራር ተከናውኖለት፥ ከይሁዳም ጋር በሰላም የሚኖርበት ጊዜ ነበር። በይሁዳ ሕዝብ መካከል ደግሞ መንፈሳዊ መነቃቃት የነበረበት ወቅት ነበር። ዖዝያን እግዚአብሔርን የሚፈራ ንጉሥ ስለነበረ ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ያበረታታ ነበር። ሕዝቡ ይህን ቢያደረጉም እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ኅብረት ጥልቀት እንዳልነበረው ኢሳይያስ ያውቅ ነበር። ኢሳይያስ እርሱና ሕጉ በቅዱሱ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሐን እንዳልነበሩ ባየው ራእይ ተገንዝቦአል። በዝያን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። ዳግማዊ ኢዮርብዓም በ753 ዓ.ዓ. ሲሞት፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ሽኩቻ ይካሄድ ነበር። እስራኤል በ722 ዓ.ዓ. ፈጽማ እስክትጠፋ ድረስ ሥልጣኗ ፈጥኖ እያሽቆለቆለ መሄድ ጀመረ። ዖዝያን በእግዚአብሔር ላይ በማመፁ በለምጽ ስለተመታ በ750 ዓ.ዓ. ዙፋኑን ለልጁ ለኢዮአታም ማስረከብ ነበረበት።
ኢሳይያስ ያደገው በዖዝያን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ በ740 ዓ.ዓ. የሞተውን የታላቁን ንጉሥ የዖዝያንን ሞት ሲመሰክር ምናልባት ኢሳይያስ ወጣት ሳይሆን አይቀርም፤ ለነቢይነትም የተጠራው ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነበር (ኢሳይያስ 6፡)።
2. ኢዮአታም፡- የዖዝያን ልጅ የሆነው ኢዮአታም አብዛኛውን መንግሥቱን ያሳለፈው ከአባቱ ከዖዝያን ጋር ሲሆን፥ በኋለኛው መቶ ደግሞ ከልጁ ከአካዝ ጋር ነበር። በመሠረቱ ኢዮአታም የአባቱን የዖዝያንን መንገድ ቢከተልም፥ በዘመነ መግሥቱ መጨረሻ ገደማ ችግር ተጀመረ። በአሦር ሣልሳዊ ቴልጌልቴልፌሶር የተባለ ንጉሥ በ745 ዓ.ዓ. ሥልጣን ያዘ፤ መንግሥቱንም ወደ ምዕራብ ማስፋፋት ጀመረ። እስራኤልንና ይሁዳን በማጥቃት አሸነፋቸውና ነገሥታትን አስገበረ። የኢዮአታም ልጅ አካዝ በአቋሙ አሞራውያንን ይደግፍ ስለነበር ልጁ አካዝ አብሮት ይነግሥ ዘንድ ሕዝቡ ኢዮአታምን ግድ አሉት።
3. አካዝ፡- አካዝ በሥልጣን ላይ የነበረው ከ736-735 ዓ.ዓ. ነበር፤ እግዚአብሔርን አይፈራም ነበር፤ ይልቁንም የይሁዳን ሕዝብ ወደ ከፍተኛ ክፋት መራ። አካዝ ሥልጣን ላይ በተቈናጠጠ ጊዜ፥ ሕዝቡ ለአሦር መንግሥት ይገብር ነበር፤ ዳሩ ግን እስራኤልና ሶርያ በአሦር ላይ ለማመፅ ወስነው ነበር። በዚህ ዓመፅ የይሁዳ ሕዝብ እንዲተባበራቸው ፈለጉ፤ አካዝ ግን አሻፈረኝ አለ። በዚህ ምክንያት ሶርያና እስራኤል በይሁዳ ላይ ጥቃት ፈጸሙ። አካዝ እነዚህን አገሮች እንዳይፈራቸውና በእግዚአብሔር እንዲታመን ኢሳይያስ ቢነግረውም፥ መልእክት ወደ አሦር በመላክ እንድታድነው ጠየቀ። አሦር ሶርያን በማጥቃት በ732 ዓ.ዓ. ሙሉ ለሙሉ አጠፋቻት። የእስራኤልንም ምድር በአብዛኛው በመውሰድ መንግሥቱን አስገበረች፡፡ የአሦር ንጉሥ በሞተ ጊዜ ግን እስራኤል ከሌሉች ብዙ አሕዛብ ጋር በመሆን ለማመፅ ወሰነች። አሦር በ722 ዓ.ዓ. እስራኤልን በመደምሰስ አብዛኛውን ሕዝብ በምርኮ ወሰደች። ኢሳይያስ የእስራኤልን ጥፋት ያየው በከፍተኛ ኃዘን እንደነበር ጥርጥር የለውም። እስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ቢሆኑም፥ ኃጢኣታቸው ጥፋትን አመጣባቸው። ኢሳይያስ ወደፊት ይሁዳም የሰሜኑ መንግሥት ያደረገውን ይህንኑ ኃጢአት በማድረግ ወደ ምርኮ እንደምትሄድ በተጨማሪ ያውቅ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ሲቀጣቸው ያየኸው በምን መንገድ ነው? ለ) ይህ ቅጣት እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ላይ ታላቅ ሥቃይ የሚያስከትለው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት በራሱ ሕዝብ ላይ ፍርድን ሲያመጣ እርሱን የሚፈሩ ሰዎች ምላሽ ምን መሆን አለበት?
አካዝ አሦር ባደረገችው ነገር በጣም ተደስቶ ነበር። የአምላካቸውን (የጣዖታቸው) ምስል ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በማምጣት፥ ሕዝቡ የአሦራውያንን አምላክ እንዲያመልኩ አዘዘ። ሕዝቡ እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልኩ አልፈቀደላቸውም። ኢሳይያስ ይህ ጉዳይ በእስራኤል ላይ ያመጣውን ዓይነት ፍርድ በይሁዳ ሕዝብም ላይ ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። የትንቢተ ኢሳይያስ መጀመሪያ ክፍል አብዛኛው ምዕራፍ በአካዝ የክፋት ዘመነ መንግሥት የተጻፈ ነው ( ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 9)።
4. ሕዝቅያስ፡- የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን የሚፈራና መንገዱን ከጌታ ጋር ያደረገ ንጉሥ ነበር። ኢሳይያስ ከሕዝቅያስ ጋር በቅርብ ሳይሠራ አልቀረም። እስራኤል ከወደቀችና ሕዝቅያስ ከነገሠ በኋላ ሕዝቡ በቤተ መቅደስ ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ማምለክ እንዳለባቸው ወሰነ። በወደቀው የእስራኤል መንግሥትና በይሁዳ መንግሥት ይኖሩ የነበሩት ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔርን በቤተ መቅደሱ ያመልኩ ዘንድ ጋበዘ። በይሁዳ መንግሥት ውስጥ በርካታ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኣካሄደ። ይሁን እንጂ ከአሦር በኩል በይሁዳ ላይ እንደገና ችግር ተነሣ። ዳግማዊ ሳርጎን የተባለ አዲስ ንጉሥ (ከ722-705 ዓ.ዓ.) ሥልጣን ከያዘ በኋላ፥ ፍልስጥኤምንና (711 ዓ.ዓ.) በአሦር ላይ የተባበሩ ሌሎች ሕዝቦችን ሁሉ ወጋ። በዚህ ነገር እንዳይተባበር ኢሳይያስ ሕዝቅያስን አስጠንቅቆት ነበር። ኢሳይያስ ለሦስት ዓመታት እንደ ባሪያ ያለጫማ በመሄድና ቡቱቶ ለብሶ በመመላለስ ግብፅና ተባባሪዎችዋ እንዴት ለአሦር ባሪያዎች እንደሚሆኑ አሳይቷል። ሕዝቅያስ ለአሦር እንዲገብር ቢገደድም እንኳ ኢየሩሳሌም ጥቃት አልደረሰባትም። ሳርጎን በሞተ ጊዜ ግን ሕዝቅያስ የአሦርን የበላይ ጭቈና አሽቀንጥሮ ለመጣል ተፈተነ። የግብፅ ሕዝብ አሦርን ለመጣል የሚችል የኅብረ-ብሔር ጦር ለማቋቋም የሞከረው በዚህ ጊዜ ነበር። ኢሳይያስ፥ ሕዝቅያስን ወደዚህ ኅብረት በመግባት በግብፅ እንዳይታመን አስጠነቀቀው። ይልቁንም በእግዚአብሔር እንዲታመን አበረታታው። አሦር በሰናክሬም መሪነት ይሁዳን በመውጋት አብዛኛውን የይሁዳ ክፍል ደመሰሰ። ሆኖም ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው፥ እግዚአብሔር የአሦርን ጦር በመደምሰስ (በ701 ዓ.ዓ.) ኢየሩሳሌምን ከጥፋት ጠበቃት።
5. ምናሴ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢሳይያስ አሟሟት ባይነግረንም እንኳ የአይሁድ አፈ-ታሪክ በምናሴ ዘመነ መንግሥት በመሥዋዕትነት መሞቱን ይናገራል። ምናሴ በአብዛኛው የሕይወት ዘመኑ እግዚአብሔርን እንደተወና የጣዖት አምልኮን ሥርዓት እንደገና ወደ ይሁዳ እንዳመጣ ታስታውሳለህ። ኢሳይያስ ይህን በሚመለከት እንደተቃወመው ጥርጥር የለውም። የአይሁድ አፈ ታሪክ እንደሚናገረው፥ ኢሳይያስ በአንድ ውስጠ ክፍት በሆነ የዛፍ ግንድ ውስጥ ከምናሴ በተሸሸገ ጊዜ፥ ምናሴ በመጋዝ ለሁለት እንደሰነጠቀው ይናገራል (ዕብራውያን 11፡37 ተመልከት።)
የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ የኖረበትን ዘመን ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ገጽታ በአንድ ዐረፍተ ነገር ግለጥ። (ኢሳይያስ ስለኖረበት ጊዜ ማወቅ አብዛኛውን ትንቢቶቹን ለመረዳት ይጠቅምሃል።)
እርግጠኛ ለመሆን ባንችልም እንኳ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት፥ ትንቢተ ኢሳይያስ የተጻፈው ቀጥለው በተጠቀሱት ነገሥታት የግዛት ዘመን ቅደም ተከተል ነው፡-
1. ኢሳይያስ 1-6 የተጻፈው በዖዝያንና በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት ነው (740-735) ዓ.ዓ.)፤
2. ኢሳይያስ 7-12 በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተጻፈ ነው (735-715 ዓ.ዓ.)
3. ኢሳይያስ 13-39 የተጻፈው ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት ከመነሣቱ በፊት፥ በሕዝቅያስ የመጀመሪያ ዘመነ-መንግሥት ነበር፤ (715-701 ዓ.ዓ.)፤
4. ኢሳይያስ 40-66 በሕዝቅያስ የኋለኛ ዘመነ መንግሥትና በምናሴ የመጀመሪያ ዘመነ መንግሥት የተጻፈ ነው (701-680 ዓ.ዓ.)።
II. የነቢዪ ኢሳይያስ ሥረ- መሠረት
የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ የሚለውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከትና ስለ ነቢዪ ኢሳይያስ የተጻፉ አንዳንድ እውነቶችን ጥቀስ።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢሳይያስ የግል ሕይወት የሚነግረን ብዙ ነገር የለም፤ ሆኖም ስለ እርሱ የሚከተሉትን መሠረታዊ እውነቶች እናውቃለን፡-
1. ኢሳይያስ የአሞጽ ልጅ ነበር። የአይሁድ አፈ ታሪክ አሞጽ የንጉሥ ዖዝያን አባት የነበረው የንጉሥ አሜስያስ ወንድም ነው ይላል። ይህ ማለት ንጉሥ ዖዝያንና ኢሳይያስ የአጎት ልጆች ናቸው ማለት ነው፤ ስለዚህ ኢሳይያስ የዳዊት ንጉሣዊ ቤተሰብ አካል የነበረ፥ ብዙ መብትና ዕድል የነበረው ሰው ነው። ኢሳይያስ ለንጉሥ አካዝና ሕዝቅያስ በቀጥታ ይናገር የነበረበት ምክንያት ዘመዶቹ ስለነበሩ ይሆናል። ምናልባት በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ ትምህርት የሠለጠነ ሰው ሳይሆን አይቀርም።
2. ኢሳይያስ እንደ እርሱ ነቢይት የሆነች ሴት አግብቶ ነበር (ኢሳይያስ 8፡3)። የኢሳይያስ ሚስት ነቢይት መሆኗን በሁለት የተለያዩ መንገዶች መገንዘብ እንችላለን፤ ይኸውም፡- አንድም ልክ እንደ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ቃል በመናገር በእርግጥ የነቢይነትን ሥራ የምትሠራ ነበረች ማለት ሊሆን ይችላል፤ ወይም ነቢይ ስላገባች ነቢይት ተብላ ተጠርታ ሊሆን ይችላል።
3. ለኢሳይያስ ቢያንስ ሁለት ልጆች እንደነበሩት እናውቃለን። እነዚህ ሁለት ልጆቹ የእርሱን የነቢይነት መልእክት የሚያንጸባርቁ ልዩ የሆኑ ስሞች ነበሯቸው። የአንዱ ልጅ ስም በዕብራይስጥ ማሃርሻላል-ሃሽ-ባዝ ሲሆን፥ ትርጕሙ «ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኮለ» ማለት ነው። ይህ ስም እስራኤላውያን ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው ካልተመለሱ እግዚአብሔር ለሚማርኩአቸው አሕዛብ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው የሚናገር የማስጠንቀቂያ መልእክት ነበር (ኢሳይያስ 8:1-3)። የሁለተኛው ልጅ ስም በዕብራይስጥ ሸአር-ያሹብ ሲሆን ትርጕሙም «ቅሬታዎቹ ይመለሳሉ» ማለት ነው። ይህ ስም እስራኤላውያንን ለማጽናናትና ለማበረታታት የተሰጠ ስም ነበር። እግዚአብሔር እንደሚያስማርካቸው የተናገረ ቢሆንም፥ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ግን ኣልነበረም። ሁልጊዜ ለእርሱ የሆኑ ቅሬታዎች ነበሩት፤ ስለዚህ አንድ ቀን እግዚአብሔር እነዚህን ቅሬታዎች በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ወደ ይሁዳ ሊመልሳቸው ተስፋ ሰጠ (ኢሳይያስ 7፡3)።
አንዳንድ ምሁራን ኢሳይያስ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ልጆች ነበሩት ብለው ያምናሉ። የአንዱ ስም «አማኑኤል» ሲሆን የሌላኛው ስም ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም ይላሉ። [ኢሳይያስ 7፡14፤ 8፡8፥ 10፤ 9፡6]።
4. ኢሳይያስ አገልግሎት የሰጠው ብቻውን ሆኖ አልነበረም። ኢሳይያስ በሠራበት ዘመን ሆሴዕና አሞጽ በሰሜን እስራኤል ያገለግሉ ነበር። ሚክያስ ደግሞ በይሁዳ ገጠር ክፍል ያገለግል ነበር። የሚክያስና የኢሳይያስ መልእክቶች ምን ያህል ተመሳሳይ እንደሆኑ ማየት የሚያስደንቅ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ መልእክቶቻቸው ፍጹም ተመሳሳይ ነበሩ (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 2፡1-4ን ከሚክያስ 4፡1-3 ጋር አወዳድር)። መልእክቶቻቸው የተመሳሰሉት ኢሳይያስ ለይሁዳ መሪዎች የሰጠውን መልእክት ሚክያስ በገጠር ላሉ ሰዎች በድጋሚ ስለተናገረ ሳይሆን አይቀርም።
5. ኢሳይያስ የተነበየው ስለ ሁለቱም ማለት ስለ ደቡቡና ሰሜኑ መንግሥታት ቢሆንም ዋናው መልእክቱ ስለ ይሁዳና እርሱ ስለኖረባት ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ ነበር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)