ኢሳይያስ 1-6

የምንሰብከው ወንጌል በረከትንና ፍርድን በአንድነት አጠቃልሉ የያዘ ነው። ለደኅንነታቸው በኢየሱስ ለሚታመኑና ለእርሱ በመታዘዝ ለሚኖሩ ሁሉ በረከት አላቸው። በኢየሱስ በማያምኑና እርሱን በማይታዘዙት ሁሉ ላይ ደግሞ ፍርድ አለ።

የውይይት ጥያቄ፥ ለማያምን ሰው በምትመሰክርበት ጊዜ በእነዚህ በሁለቱም የወንጌል ገጽታዎች እንዴት እንደምትጠቀም አብራራ።

ይህ ትምህርት በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ተንጸባርቋል። ትንቢተ ኢሳይያስ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ለሚኖሩ ሰዎች የበረከት ቃል ኪዳን የያዘ መጽሐፍ ነው። ደግሞም ከሕዝቡ ብዙዎቹ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በሰበቡ ስለሚቀበሉት አሳዛኝ የሆነ እውነታ የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።

ትንቢተ ኢሳይያስ የሚጀምረው፥ የሚጠቃለለውም ፍርድን ዋና አሳቡ በማድረግ ነው። አይሁድ ሊመጣባቸው ስላለው የፍርድ ቅጣት በማስጠንቀቅ ይጀምራል። ክፉና ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎችን በማስሕንቀቅ ይደመደማል።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 1 የሚጀምረው በፍርድ ቤት ችሎት ፊት እንዳለ ሆኖ ነው። ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ ክስ ይመሠርታል። የገባውን ቃል ኪዳን ባፈረሰው በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ሰማይና ምድር ጭምር ምስክር ሆነው ቀርበዋል (ዘዳግም 4፡26)። አይሁድ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና ቃል ኪዳኑን ለመጠበቅ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ መቅመስ ጀምረው ነበር። በመንግሥት ደረጃ በአሕዛብ መሸነፍ ጀምረው ስለነበር እንደ ሰዶምና ገሞራ ለመጥፋት ደርሰው ነበር።

እግዚአብሔር አይሁድን ወደ እርሱ እንዲመጡ፥ ከእርሱ ጋር እንዲነጋገሩና የኃጢአታቸውን ይቅርታ እንዲቀበሉ ጋብዞ ነበር። ይህ ይሆን ዘንድ ግን መንገዳቸውን መለወጥ ነበረባቸው። ሥነ-ሥርዓታዊ ኣምልኮአቸው ዋጋ አልነበረውም። እግዚአብሔርን በእውነት ለማምለክ፥ ከእነርሱ የሚያንስ ዕድል ከገጠማቸው ሰዎች ጋር በፍትሕ መኖር ነበረባቸው።

የእግዚአብሔርን ፍርድ መቅመሳቸው የማይቀር ቢሆንም እንኳ ክፋት የሚጠፋበትና የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአምላካቸው ጋር ለገቡት ቃል ኪዳን በመታዘዝ የሚኖሩበት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ጊዜ የይሁዳ መንግሥት ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም በጽድቅና በፍትሕ ትሞላለች።

የውይይት ጥያቄ፥ የኢሳይያስ ምዕራፍ 1 ዋና ዋና ትምህርቶችን ዘርዝርና ለቤተ ክርስቲያንህ በማስጠንቀቂያነት እንዴት ሊጠቅሙ እንደሚችሉ አስረዳ።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 የሚያተኩረው «በመጨረሻዎቹ ቀናት» ላይ ነው። በትንቢት ውስጥ ይህ ሐረግ በጣም ጠቃሚ ነው። ይህ ሐረግ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ በሚሠራበት በማንኛውም ጊዜ ስለሚያመጣው ፍርድ ወይም በረከት የሚናገር ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ የሚያመለክተው ግን እግዚአብሔር ለዚች ምድር ያለውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ስለሚፈጽምበት የመጨረሻ ዘመን ነው። ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 የሚጠቅሰው ስለዚሁ የመጨረሻ ዘመን ነው። ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 በዚህ ጊዜ ስለሚፈጸሙ ሁለት ጉዳዮች ይናገራል፡

1. የታላቅ በረከት ጊዜ (ኢሳይያስ 2፡1-5)፡- ይህ የበረከት ጊዜ እግዚአብሔር በምድር መንግሥታታት ሁሉ ላይ በሚገዛበት ወቅት የሚፈጸም ነው። ሰዎች ሁሉ ከተለያዩ መንግሥታት እግዚአብሔርን ለማምለክ ይመጣሉ። እነርሱም ለእግዚኣብሔር ሕግ ታዛዦች ሆነው ይኖራሉ። እርሱ ደግሞ በመካከላቸው እውነተኛና ጻድቅ ፈራጅ ይሆናል። በሕዝቦች መካከልም ዘላቂ ሰላም ይሆናል።

2. የታላቅ ፍርድ ጊዜ (ኢሳይያስ 2፡6-22)፡- የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት አይሁድ የእግዚአብሔርን ታላቅ በረከት ቀምሰውት ነበር። ብዙ ብር፥ ወርቅ፥ ፈረሶች፥ ወዘተ. ነበሯቸው። ነገር ግን ጣዖትን ማምለክና ትዕቢትን የመሰለ ከፍተኛ ክፋትም በመካከላቸው ነበረ። ስለዚህ የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ሲመጣ ክፉ ያደረጉትን ሁሉ ይቀጣል። የእግዚአብሔር ፍርድ የእርሱን ገናናነት በመግለጥ ሕዝቡ እንዲፈሩት ያደርጋል። ሰው መፍራት የሚገባው ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያስጥለው የማይችለውን ሰውን ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን ነው። ኢሳይያስ ምዕራፍ 3 የሚያተኩረው በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ኃጢአት እንዲሁም እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀጣበት ምክንያት ላይ ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ለመፍረድ በሚመጣ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከሁሉ በላይ የሚቀበሉት መሪዎች ነበሩ። በእስራኤል መሪዎች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣል። ለሕዝቡ መውደቅ እግዚአብሔር መሪዎችን እንዴት እንደሚወቅስ አስተውል (ኢሳይያስ 3፡12-15)። በተጨማሪም ይህ ምዕራፍ እግዚአብሔር በመታዘዝ ሳይኖሩ፥ ስለ ውጫዊ ውበታቸው ብቻ ስለሚያስቡና ስለሚታበዩ ሴቶች ኃጢአት አበክሮ ይናገራል። እግዚአብሔር በውበታቸው የታበዩትን እነዚህን ሴቶች ውበታቸው ወደሚረግፍበትና ወንዶቻቸው ወደሚገደሉበት ምርኮ በማፍለስ እንደሚያዋርዳቸው ይናገራል። 

ኢሳይያስ ምዕራፍ 4 እንደገና ተመልሶ የእግዚአብሔር ሕዝብ ቅሬታዎች ለወደፊት ስለሚያገኙት ክብር ይናገራል። በዚህ ክፍል የመሢሑ ወይም የኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ስም ከሆነው «ከእግዚአብሔር ቍጥቋጥ» ጋር እንድንተዋወቅ ተደርጓል። እስራኤል ወደ ቀድሞ ክብርዋ ትመለሳለች፤ ሕዝቡም የተቀደሱ ይሆናሉ። እግዚአብሔር በምድረ-በዳ እንዳደረገው (ዘጸአት 40፡34-38)፥ በመካከላቸው እንደ እሳት ዐምድና እንደ ክብር ደመና ይኖራል።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 5 እንደገና በፍርድ መሪ አሳብ ላይ ተመሥርቶ፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በሚፈርድባቸው ምክንያቶች ላይ ያተኩራል። ኢሳይያስ 5፡1-7 እስራኤል ከወይን ቦታ ጋር ተነጻጽራ የቀረበችበት የፍርድ መዝሙር ነው። በእስራኤል ውስጥ በጣም ከተለመዱና ከታወቁ የእርሻ ሥራዎች አንዱ የወይን ተክል ሥራ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ለመግለጥ ወይንን በምሳሌነት ተጠቀመ። እግዚአብሔር የራሱን ወይን-እስራኤልን በከነዓን ምድር ተከለ፤ ጠበቃት፤ ተንከባከባትም። ነገር ግን እስራኤል የጽድቅ ፍሬ የሆነውን መታዘዝን በማፍራት ፈንታ ኮምጣጣ የሆነውን ያለመታዘዝንና የሐሰተኛ አምልኮን ፍሬ አፈራች። ስለዚህ እግዚአብሔር በወይኒቱ ላይ ይፈርዳል ያጠፋታልም።

በኢሳይያስ 5፡8-30 የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጡትንና በሕዝቡ መካከል ተስፋፍተው የነበሩትን ኃጢአቶች በዝርዝር እንመለከታለን። እነርሱም እያንዳንዳቸው የ «ወዮታ» ቃል የያዙ ስድስት ኃጢአቶች ነበሩ። በድሆች ጉልበት፥ ድካምና ጥረት ያለማቋረጥ ሀብት እያካበቱ የመኖር ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች፥ ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ባለባቸው ኃላፊነት ግድ የሌላቸውና ግብዣ በማድረግ የሚሰክሩ መሪዎች፥ በክፋትና በግፍ ደስ የሚሰኙና እግዚአብሔር በክፉዎች ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ በተናገረው ቃል ላይ የሚሳለቁ፥ እግዚአብሔር መልካም ነው ያለውን ነገር ክፉ ነው የሚሉ ወይም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆኑትን ነገሮች መልካም ነው የሚሉ፥ በጥበባቸው የሚታበዩ፥ እንደዚሁም አዘውትረው የሚሰክሩና ፍርድን የሚያጣምሙ ሰዎች ነበሩ።

ኃጢአት ቅጣትን ያመጣል። በመሆኑም እግዚአብሔር ለእርሱ ባለመታዘዝ የሚኖሩትን ሰዎች እንደሚቀጣ ይናገራል። እግዚአብሔር ታላቅና ኃያል የሆነ ባዕድ ሕዝብን በይሁዳ ሕዝብ ላይ በማስነሣት ያጠፋቸዋል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 6 ስለ ኢሳይያስ መጠራትና ለይሁዳ ሕዝብ የእግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን ስለ መመረጡ ይነግረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ምዕራፎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ የሚመላለሱ ከሆነ ስለሚያጋጥሟቸው ነገሮች የሚያስጠነቅቁት ምንድን ነው? ለ) ሀብታቸውንና ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ስለሚጠቀሙ ሰዎች እነዚህ ምዕራፎች የሚያቀርቡት ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ሐ) እነዚህ ምዕራፎች [ በመከራና በሥቃይ ጊዜያት ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ማበረታቻ የሚሆን የወደፊት ተስፋ የሚናገሩት ነገር ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d