የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሌላ መንግሥት የተነሣባቸው በሚመስላቸው ጊዜ ወይም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት ተስፋ የሚቆርጡት ለምንድን ነው? ለ) ክርስቲያን እንዲህ ባሉ ወቅቶች ከተስፋ መቁረጥ ነፃ ይሆንና ይበረታታ ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ማስታወስ ያለበት እውነቶች ምን ይመስሉሃል?
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን፥ ብዙ የተዛቡ ፍርዶችን በምድር ላይ ደጋግመን በምንመለከትበት ወቅት እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ በእርግጥ እግዚአብሔር እየተቈጣጠረ ነውን? በማለት እንጠይቃለን። ምንም የማያውቁ ሰላማዊ ሕዝቦች ከጦር መኮንኖች ይልቅ የሚሠቃዩባቸው ጦርነቶች አሉ። እነዚህ ጦርነቶች ትክክለኞችና ፍትሐዊ አይደሉም። በአንድ ሕዝብ ላይ የሚደርሱና ሌላውን ሕዝብ የማይነኩ የሚመስሉ ድርቅና ራብ ወይም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች በምድር ላይ ይታያሉ። የበለጠ ክፉና ኃጢአተኞች የሆኑ ሕዝቦች ከፍርድ እያመለጡ፥ በሌሎች ሕዝቦች ላይ ግን እጅግ ብዙ ችግር የሚደርስ በሚመስልበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን በእርግጥ እየተቈጣጠረ ይሆንን!? በማለት በትዝብት ሳንጠይቅ አንቀርም።
የእስራኤል ሕዝብም በተመሳሳይ ሁኔታ አጠያያቂ እንደሆነባቸው ጥርጥር የለውም። የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ነበሩ። እግዚአብሔር በዓለም ላይ ካለ ከማንኛውም ሕዝብ ይልቅ ታላቅ እንደሆነ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ እስራኤል ያለማቋረጥ በሌሎች ሕዝቦች ጥቃት እየደረሰባት ትሸነፍ ነበር። ይህ የሆነው እግዚአብሔር ደካማና ሌሎችን ሕዝቦች ለመቈጣጠር የማይችል ስለሆነ ነውን? እግዚአብሔር ከአሕዛብ አማልክት ይልቅ ደካማ ነውን? እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ እንደሚፈርድ ተናግሯል። ይሁዳ ግን በሥነ- ምግባር ረገድ ከሌሎች አሕዛብ እጅግ የተሻለች ነበረች። እግዚአብሔር ታዲያ በይሁዳ ላይ የሚፈርደውና በሌሎች ሕዝቦች ላይ የማይፈርደው ለምንድን ነው? ኢሳይያስ እነዚህን ትንቢቶች በሚናገርበት ጊዜ በእርሱና እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሌሎች አይሁድ አእምሮ ውስጥ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች ተፈጥረው እንደነበር ጥርጥር የለውም።
እግዚአብሔር ጥያቄዎቻቸውን በጸጋ ተቀብሉ አስተናገደ። እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል የተፈጸሙትን ድርጊቶች እየተቈጣጠረ መሆኑን በኢሳይያስ በኩል ለአይሁድ አሳየ። አሕዛብንም በአይሁድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሳይሆን፥ በራሱ ጊዜ በኃጢአታቸውና በክፋታቸው ይፈርድባቸዋል።
እግዚአብሔር በግለሰቦች ላይ በሕይወት አኗኗራቸው መሠረት እንደሚፈርድባቸው ብቻ ሳይሆን፥ መንግሥታትም በአጠቃላይ ቅን ፍርድን በማጕደልና የተለዩ ዜጎችን በመንከባከብ ስለፈጸሙት ድርጊት እንደሚፈርድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። በተለይ የሚፈርድባቸው የራሱ ሕዝብ በሆኑት በአይሁድ ላይ በፈጸሙት ድርጊት ምክንያት ነው። አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነትና ለሕዝባቸው የሚሆነውን የሥነ-ምግባር መሠረት የተዉ አገሮችን ካሉበት ሥልጣን ፈጥኖ ያወርዳቸዋል። በሌላ ጊዜ ይህ ፍርድ በመቶ የሚቈጠሩ ዓመታትን ሊወስድና በክርስቲያኖች የሕይወት ዘመን የማይታይ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር በግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በመንግሥታትም ላይ እንደሚፈርድ እርግጠኞች ነን (ለምሳሌ ኢዩኤል 3)።
የውይይት ጥያቄ፥ መንግሥታትና መሪዎች ራሳቸውን እንዴት እንደሚመሩ፥ ሕግጋታቸው ምን ያህል ትክክለኞች እንደሆኑና ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ-ምግባር መመሪያዎች ጋር እንዴት እንደሚስማሙና በእግዚአብሔር ፊት መልስ እንደሚሰጡ ማወቃቸው ለምን ይጠቅማል?
ዛሬ የምናጠናው በይበልጥ እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ እንደሚፈርድ የሚያሳየውን የትንቢተ ኢሳይያስን ክፍል ነው። እነዚህ ሕዝቦች በኢሳይያስ ዘመን ገናና የነበሩ ናቸው። ስለ እግዚአብሔር የተነገሩት እነዚህ ትንቢቶች ስለተፈጸሙ፥ ዛሬ ከእነዚህ ሕዝቦች አብዛኛዎቹ ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል።
የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 13-23 አንብብ። በእነዚህ ምዕራፎች የተጠቀሱትን ልዩ ልዩ መንግሥታትና እግዚአብሔር የወሰናቸውን ፍርዶች ዘርዝር።
1. በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 13-14፡1-23)
የመጀመሪያው ትንቢት የተነገረበት ሕዝብ የባቢሎን ሕዝብ ነው። ይህ ትንቢት በተነገረበት ወቅት ዓለምን ይገዛ የነበረው ታላቁ የአሦር የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ ከነበሩት ዋና ዋና ከተሞች አንድዋ ባቢሎን ነበረች፤ ስለዚህ በአንድ በኩል፥ በባቢሎን ላይ የተነገረው ትንቢት በአሦር መንግሥት ላይ የተነገረ ነበር። ትኩረቱ በባቢሎን ላይ ስለሆነ ከዚህም የላቀ ትርጕም አለው። በኢሳይያስ ዘመን የነበረው ዓለምን የሚገዛ ዋና መንግሥት አሦር ሆኖ ሳለ ትንቢቱ በባቢሎን ላይ መነገሩ የሚያስደንቅ ነው። እግዚአብሔር ግን ከ150 ዓመታት በኋላ የይሁዳን ሕዝብ በምርኮ የሚያግዘው የባቢሎን መንግሥት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ባቢሎን ርእሰ ከተማ ከመሆኗ በፊት እንኳ እግዚአብሔር ስለ ጥፋቷ ተናግሮ ነበር፡፡ ባቢሎንን የሚደመስሰው የሜዶን መንግሥት እንደሆነም አስቀድሞ ተናገረ።
ኢሳይያስ 14፡12-15 በምሁራን መካከል ከፍተኛ ውዝግብን ያስነሣ ክፍል ነው። ይህ ክፍል ማንን ነው የሚያመለክተው? የባቢሎንን ንጉሥ ብቻ ነው ወይስ ሰይጣንንም ጭምር?
ይህ ክፍል በመጀመሪያ የተጻፈው በሕዝብ ዘንድ እንደ አምላክ ይታይ ስለነበረው ስለ ባቢሎን ንጉሥ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ይህ ክፍል በብዙ መንገድ ሰብአዊ ንጉሥን ብቻ የሚያመለክት አይመስልም። ስለ አንድ ልዩ ሕያው ፍጡር የሚያመለክት ይመስላል። በዘመናት ሁሉ የኖሩ ክርስቲያኖች ይህ ክፍል የሚናገረው ስለ ሰይጣን ውድቀት ነው ብለው የሚያምኑት በዚህ ምክንያት ነው። ሰይጣን «የአጥቢያ ኮከብ» ወይም «ሉሲፈር» ተብሎአል። ይህ ክፍል ስለ ሰይጣን የሚናገር ከሆነ፥ ሰይጣንን ለውድቀት የዳረገው ትዕቢት እንደነበረ መመልከት እንችላለን። ሰይጣን እንደ እግዚአብሔር ለመሆንና በነገሮች ሁሉ ላይ ለመግዛት ፈለገ፤ ስለዚህ ከሰማይ ተጣለ። በራእይ 13፡4 እና 17፡3 ይህ ክፍል በተምሳሌታዊነቱ በዘመናት መጨረሻ በሰይጣን ቍጥጥር ሥር ስለሚሠራው ክፉ መሪ ስለ አውሬው የተጠቀሰ ይመስላል።
የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ ጥቅሶች ትዕቢት በእግዚአብሔር አመለካከት ምን ያህል የከፋ ኃጢአት መሆኑን እንዴት ያሳያሉ?
ስለ ባቢሎን የተነገሩት እነዚህ ትንቢቶች ያለአንዳች ስሕተት እንዴት እንደተፈጸሙ ስናይ እንደነቃለን። ትንቢቱ እንዳመለከተው፥ ዛሬ ባቢሎን የሚባል ከተማ የለም፤ በረግረግ መካከል ያለ ፍርስራሽ ነው። እግዚአብሔር እስከወሰነ ትዕቢተኞች የሆኑ መንግሥታትንና መሪዎችን ለማዋረድ የሚያግደው ምንም ነገር የለም።
2. በአሦር ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 14፡24-27)።
አሦር የመጀመሪያዋ የዓለም ታላቅ መንግሥት እንደነበረችና የሰሜኑን የእስራኤል መንግሥት የደመሰሰች መሆንዋን ታስታውሳለህ። እንዲሁም በኢሳይያስ ዘመን ከፍተኛ የዓለም መንግሥት በመሆን በይሁዳ ሕዝብ ላይ ታላቅ ጥፋትና መከራ አምጥታለች።
ይህ ትንቢት በተነገረ ጊዜ ታላቅ መንግሥት የነበረች ብትሆንም፥ በ150 ዓመታት ውስጥ እንደምትወድቅ እግዚአብሔር ያውቅ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን መንግሥት መውደቅ ለማመልከት በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ልዩ ትኩረት አልሰጠውም።
3. በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 14፡28-32)፡፡
ከይሁዳ መንግሥት የረጅም ጊዜ ጠላቶች አንዱ የፍልስጥኤም መንግሥት ነበር። ፍልስጥኤም በአይሁድ የተያዘችው በዳዊት ዘመነ መንግሥት ነበር። ሆኖም ዕድል ባገኘች ቍጥር፥ ፍልስጥኤም በአይሁድ ላይ በማመፅ፥ ይሁዳን ለማጥቃት ከይሁዳ ጠላቶች ጋር ብዙ ጊዜ ትተባበር ነበር። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔር ፍልስጥኤም በአሦር ስለ መወረርዋና ስለመደምሰሷ ተነበየ።
4. በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 15-16)፡፡
ከጥንት የአይሁድ ጠላቶች አንድዋ ሞዓብ ነበረች። ከዳዊት ዘመን በኋላ በነበረው አብዛኛው ታሪኳ ሞዓብ በእስራኤል ወይም በይሁዳ ቍጥጥር ሥር ነበረች። አጋጣሚ ጊዜ ባገኘበት ጊዜ ሁሉ ግን ታምፅ ነበር። የይሁዳ ጠላቶች ኢየሩሳሌምን ለማጥቃት በተነሡበት ጊዜ ሁሉ ሞዓብ ትተባበር ነበርና እግዚአብሔር ሽንፈቷንና ጥፋቷን አስቀድሞ ተናገረ። ይህ ትንቢት ሞዓብ በባቢሎን መወጋቷንና መሸነፉን የሚያመለክት ቢሆንም እንኳ ዋናው አሳብ ግን በአሦር መንግሥት ስለሚደርስባት ጥፋት የተነገረ ሳይሆን አይቀርም።
5. በደማስቆ ወይም በሶርያ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 17)፡፡
ደማስቆ የአራም ወይም የሶርያ መንግሥት ዋና ከተማ እንደሆነች ታስታውሳለህ። ኢሳይያስ በኖረበት ዘመን፥ በተለይ ደግሞ በአካዝ ዘመነ መንግሥት የሶርያ መንግሥት ከእስራኤል ጋር በመተባበር ይሁዳን ለማጥቃት ውጊያ አካሂዶ ነበር። የሶርያ ሕዝብ የአይሁድ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት ነበሩ (ለምሳሌ፡- 1ኛ ነገሥት 20)። እግዚአብሔር ሶርያ በተለይም ደግሞ ዋና ከተማዋ ደማስቆ በቅርቡ እንደምትደመሰስ ተናግሮ ነበር። ይህም በ732 ዓ.ዓ. አሦራውያን ከተማዋን ባጠፉትና ብዙ ሕዝብ ማርከው በወሰዱበት ወቅት ተፈጸመ። በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ከሶርያ ጋር ተባብረው ነበር። ስለዚህ በዚህ ክፍል በተነገረው ትንቢት ውስጥ የሰሜኑ መንግሥት ተጨምሮ ነበርና እግዚአብሔር እስራኤልም ትደመሰሳለች በማለት ተናገረ።
6. በኩሽ ወይም በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 18)፡፡
በጥንት ዘመን ኩሽ ተብሎ ይጠራ የነበረው ሕዝብ ከገናናው የግብፅ መንግሥት በስተደቡብ ይገኝ የነበረው ነው። ይህች አሁን አገራችን የምትጠራበት ያለችው በጥንታዊ ግሪክም «ኢትዮጵያ» በሚለው ስም ትጠራ ነበር። ይሁን እንጂ የጥንቱ የኩሽ ወይም የኢትዮጵያ ግዛት ከዛሬው የኢትዮጵያ ግዛት ጋር አንድ አይደለም።
የኩሽ ሕዝብ ከይሁዳ እጅግ ርቆ የሚገኝ ሕዝብ ነበር። ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ወደቀ። ይህም ሊሆን የቻለው የኩሽ ምድር ሰዎች ከጠላቶቻቸው ጋር የሚዋጉት ብዙ ጊዜ ከግብፅ ጋር በመተባበር ስለነበረ ነው። እንዲያውም በ715 ዓ.ዓ. ከኩሽ የመጣ ሰው የግብፅ መሪ ሆኖ ነበር። የግብፅ ምድር መጀመሪያ በአሦር በኋላም በባቢሎን እንደተወረረች ሁሉ፥ የኩሽ ምድርም የእግዚአብሔርን ፍርድ የቀመሰችው በዚህ መንገድ ነበር፤ ነገር ግን አንድ ቀን የዚህ ምድር ሰዎች እግዚአብሔርን እንደሚያከብሩና ለእርሱ ስጦታን ይዘው ወደ ጽዮን እንደሚመጡ ኢሳይያስ ተንብዮአል። ይህ ትንቢት መሢሑ ሊገዛ በሚመጣበት በዘላለማዊው ጊዜ መንግሥት እንደሚፈጸም አያጠራጥም።
7. በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 19-20)፡፡
የጥንቷ ግብፅ በጥበቧ፥ በኃይሏና በሥልጣኔዋ የምትታወቅ ነበረች። እግዚአብሔር ሊፈርድባት በወሰነ ጊዜ ግን እነዚህ ሁሉ ከንቱ ሆኑ። እግዚአብሔር አሦራውያንን በኋላም ደግሞ ባቢሎናውያንን በመጠቀም በግብፅ ትዕቢት ላይ ፈረደና አዋረዳት።
እንደገና እግዚአብሔር ወደ መጨረሻው ዘመን የሚያመለክተውን፥ የግብፅን ደኅንነት በሚመለከት አስቀድሞ ተናገረ። ግብፆች ወደ እስራኤል በመምጣትና እግዚአብሔርን በማምለክ ያከብሩታል። ጥንት ጠላቶች በነበሩት በአሦርና በግብፅ መካከልም ሰላም ይሆናል፤ ሁለቱም ከእስራኤል ጋር በመሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ ተብለው ይጠራሉ።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወደፊት አሕዛብ በሙሉ እግዚአብሔርን እንደሚያከብሩና እግዚአብሔርም ከእስራኤል እኩል የተመረጡ ሕዝቦች አድርጎ እንደሚቈጥራቸው እነዚህ ቈጥሮች ምን ያስተምሩናል? ለ) ይህ ነገር ለእኛ ትልቅ ማበረታቻ የሚሆነንና በተስፋ ወደፊት እንድንጠብቀው የሚያደርገን እንዴት ነው?
በኢሳይያስ 20 አሦርን ለመውጋት ከግብፅ ጋር እንዳትተባበር ወይም ተስፋዋን በግብፅና በኩሽ ጦር ላይ እንዳታደርግ እግዚአብሔር ይሁዳን ይመክራታል ምክንያቱም የእነርሱም ጦር ስለሚደመሰስ ነው። ኢሳይያስ ለሦስት ዓመታት እንደ ባሪያ በመልበስና በባዶ እግሩ በመመላለስ ይህንን በተግባር አሳየ።
8. በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 21፡1-10)፡፡
ባቢሎን በሜዶን እንደምትደመሰስ እግዚአብሔር ለሁለተኛ ጊዜ ይናገራል።
9. በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 21፡11-12)፡፡
ኤዶምም ከጥንት የእስራኤልና የይሁዳ ጠላቶች መካከል አንዷ ነበረች። እግዚአብሔር ምሳሌዎችን በመጠቀም፥ በኤዶም ምድር ላይ ጨለማ እንደሚሆን ተንብዮአል። ይህ ኤዶም በአሦርና በባቢሎን ስለ መደምሰሷ የሚናገር ነው። ገና ማለዳ በሚመስልበት ወቅት የአሦር ጥፋት ይመጣል፤ የባቢሎን ምርኮ ጨለማም በእነርሱ ላይ ይሆናል።
10. በዐረብ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 21፡13-17)፡፡
የዐረብ ምድር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሽንፈት እንደሚገጥመውና እንደሚመታ እግዚአብሔር አስቀድሞ ተናገረ። በ732 ዓ.ዓ. አሦራውያን፥ ዲዳናይቶች በመባል ይታወቁ የነበሩትን የዐረብ ነጋዴዎች መውጋት ጀመሩ፤ በኋላም ባቢሎናውያን ይህንኑ አደረጉ።
11. በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 22)፡፡
እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ፍርድን በሚያመጣበት ጊዜ፥ በምርጥ ሕዝቦቹ በአይሁዳውያን ላይ ፍርድን አያመጣም ማለት አይደለም፡፡ ኢሳይያስ ወደ ይሁዳና ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ጥፋቷ እንደቀረበ በመተንበይ ይህንን አስታወሳቸው። እግዚአብሔር እንደ ኢሳይያስ ላሉ ነቢያት ራእይን የሚሰጠው በኢየሩሳሌም ስለነበር ኢየሩሳሌም «የራእይ ሸለቆ» በመባል ተጠርታለች። እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደተናገረው ኢየሩሳሌም፥ አሦራውያን ከሚያመጡት ጥፋት ልታመልጥ ብትችልም፥ ባቢሎናውያን እነርሱን በምርኮ ለማጋዝ ከሚያመጡት ጥፋት ግን አታመልጥም።
12. በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 23)፡፡
የጢሮስና የሲዶና ትንንሽ የከተማ መንግሥታት በጥንት ዘመን የነበሩ ሁለት ትልልቅ ከተሞች ናቸው። የጢሮስና የሲዶና ሰዎች ፊንቄያውያን በመባል ይታወቁ ነበር። በመላው ሜዲተራኒያን ባሕር በመርከብ እየተዘዋወሩ በመነገድ ችሎታቸው የታወቁ ነበር። ጢሮስ ባለጠጋ አገር ሆነች። እንዲሁም ልትጠፋና ልትደመሰስ እንደማትችል ባሰበችው መንገድ የተገነባች ነበረች። የጢሮስ ከተማ አንዱ ክፍል በየብስ ላይ፥ ሌላው ክፍል ደግሞ በውጊያ አንሸነፍም ባሉበት በሜዲተራኒያን ባሕር ደሴት ላይ የተመሠረተች ነበረች። ይህም የጢሮስን ሰዎች በራሳቸው እጅግ እንዲታበዩ አደረጋቸው።
ብዙ ጊዜ ጢሮስና ይሁዳ በሰላም የቆዩ ነበሩ። እግዚአብሔር ግን ጢሮስን በከፍተኛ ትዕቢትና በክፉ የጣዖት አምልኮዋ ምክንያት ጠልቷት ነበር። የበዓል አምልኮ የተጀመረው በጢሮስ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ጢሮስን ሊያጠፋት ወሰነ። በየብስ ላይ ተገንብቶ የነበረው ዋናው የከተማዋ ክፍል በ572 ዓ.ዓ. በናቡከደነፆር ሲደመሰስ፥ በደሴት ላይ የነበረው የከተማዋ ክፍል ደግሞ በ332 ዓ.ዓ. በታላቁ እስክንድር ተደመሰሰ። ስለ ጢሮስ ጥፋት ሕዝቅኤል ከዚህ ይልቅ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ይተነብያል (ሕዝቅኤል 26-28)።
ታላቅ የሆነው የእግዚአብሔር እጅ ማንም ሊያጠፋን አይችልም በማለት ይመካ የነበረውን ይህን ትዕቢተኛ ሕዝብና መሪዎቹን በማዋረድ ታሪክን እንደሚቈጣጠር እንደገና እንዳሳየ እናያለን።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ስለ እግዚአብሔር እንዲሁም ሕዝቦችንና መሪዎችን ስለ መቆጣጠሩ ከእነዚህ ምዕራፎች ምን እንማራለን? ለ) በመንግሥታትና በመሪዎች ቍጥጥር ሥር የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ይህ እውነት የሚያበረታታቸው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር ትዕቢትን የሚጠላው ለምን ይመስልሃል? መ) ዛሬ ሕዝቦች ወይም መንግሥታት ሊታበዩ የሚችሉባቸው መንገዶችን ጥቀስ። ሠ) ብዙ ክርስቲያኖች ሊታበዩ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚታበዩትስ ለምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)