በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚቀርቡ ስብከቶችና ትምህርቶች ውስጥ የሚተላለፉ መልእክቶችን ውጤታማ ከሚያደርጓቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መልእክቶቹ የጠፉትን የማዳንና ክርስቲያኖችን የማስተማር ሚዛናዊነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ስብከቶቻችን በሚያበረታታና ተስፋ በሚሞላ፥ እንዲሁም ስለ ፍርድ በሚናገር መልእክት መካከል ሚዛናዊ መሆን አለባቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16ን በቃልህ አጥና። ሀ) የእግዚአብሔር ቃል ለምን እንደሚጠቅም ዘርዝር። ለ) ለክርስቲያን የእግዚአብሔር ቃል የመጨረሻ ውጤት ምንድን ነው? ሐ) ባለፉት ሦስት ወራት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተሰበኩ ስብከቶችን ወይም አንተ ራስህ ባለፈው አንድ ዓመት የሰበከውን ስብከት አስታውስ። የእግዚአብሔር ቃል የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የሕይወት ክፍሎች (አቅጣጫዎች) በመጠቀም፥ የትኛው መልእክት ለየትኛው ዓይነት ጥቅም እንደታለመ ግለጽ። (ለምሳሌ፡- የደኅንነት መልእክትና ትምህርት)። መ) ብዙ ጊዜ ባለመሰበኩ ምክንያት ትምህርቱን ሚዛናዊ ያላደረገው የትኛው ዓይነት መልእክት ነው? ሠ) የሚሰጠው ትምህርት የበለጠ ሚዛናዊ ይሆን ዘንድ አንተ ወይም ቤተ ክርስቲያንህ ማቅረብ የሚገባችሁ አንዳንድ ርእሰ-ጉዳዮችን ጥቀስ።
ኢሳይያስ፥ እንደ ብዙዎቹ ነቢያት መልእክቱን ሚዛናዊ አደረገው። ነቢዩ አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡን ለክፉና ኃጢአተኛ ለሆነው ሕይወታቸው በብርቱ ሲገሥጻቸው፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሚያጽናናና የሚያበረታታ መልእክት ይነግራቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ነቢያት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በቅርቡ ስለሚፈጸም ፍርድ ያመለክቱ ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ ነቢያት በዓለም ላይ የሚገኝ ክፋት ሁሉ ስለሚደመሰስበትና እግዚአብሔር ስለሚነግሥበት የመጨረሻ ዘመን ይናገሩ ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰብኩና የሚያስተምሩ ሰዎች በብሉይ ኪዳን የነበሩትን ነቢያት ምሳሌነትን ለመከተል በጣም ጠንቃቃዎች መሆን አለባቸው። ስለ መንፈሳዊ ስንፍናውና ስለ ቅድስና ጕድለት የእግዚአብሔርን ሕዝብ መገሠጽ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ሕዝቡ እግዚአብሔርን በመከተሉ ሊመሰገንና ከዚያ በላቀ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር በቅርብ ተሳስሮ እንዲራመድ ሊበረታታ የሚገባውም ጊዜ መኖር አለበት።
ኢሳይያስ ከምዕራፍ 24 እስከ 39 ባለው የመጽሐፉ ክፍል የፍርድና የማጽናኛ ወይም የማበረታቻ መልእክቱን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አቅርቦታል።
የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 24-39 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የፍርድ መልእክቶችን ዘርዝር። ፍርዶቹ ምንድን ናቸው? ለ) በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ የማበረታቻ መልእክቶች ዘርዝር። የተሰጡት የተስፋ ቃሎች ምንድን ናቸው? ሐ) ከኢሳይያስ 36-39 የተገለጹ ታሪካዊ ድርጊቶች ምንድን ናቸው? እነዚህ ምዕራፎች በኢሳይያስ ትንቢት ላይ ተጨማሪ ነገሮችን የሚያክሉት እንዴት ነው?
የትንቢተ ኢሳይያስ አራተኛው ዐቢይ ክፍል ከምዕራፍ 24-35 ነው። እነዚህ ምዕራፎች እጅግ የተለያዩ መልእክቶችንና የወደፊቱን ሁኔታ የሚያመለክቱ ትንበያዎችን ይዘዋል።
1. ኢሳይያስ 24፥ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱን ከመጀመሩ በፊት፥ በምድር ላይ ያለው ዘመን ስለሚያከትምበትና በሩቅ ስላለ የፍርድ ጊዜ የሚናገር መልእክት ነው። እግዚአብሔርን በመቃወም የሚቆሙ ሁሉ፥ ማለት መንግሥታት፥ ነገሥታት፥ አጋንንትም ሳይቀሩ (በከፍታ ያሉ ኃይላት ኢሳይያስ 24፡21) እንደሚደመሰሱ ይናገራል።
የውይይት ጥያቄ፡ ክፉ የሆኑ ሁሉ እንደሚደመሰሱ የተሰጠው ማረጋገጫ፥ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት ይኖሩ ዘንድ ማበረታቻ የሚሆነው እንዴት ነው?
2. ኢሳይያስ 25-27 የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያጽናኑ መልእክቶች ናቸው። እግዚአብሔር የማጽናናት አምላክ ነው፤ ለድሆች መሸሸጊያ የሚሆን ታማኝም ነው። በችግር ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይረዳል። በችግርና በጥፋት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ሰላም የማግኘት ምሥጢሩ አእምሮአችንን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ ነው። እርሱ ውስጣዊ ሰላምና ዋስትናን ይሰጠናል (ኢሳይያስ 26፡3-4 ተመልከት)። አንድ ቀን ሞት ይደመሰሳል። የክፋት መጋረጃ ከምድር ላይ ይወገዳል።
3. ኢሳይያስ 28-31 የፍርድንና የተስፋን መልእክቶች አዋሕዶ ያቀርባል። ሦስት ዐበይት ፍርዶች ታውጀዋል፤ በመጀመሪያ፥ በኤፍሬም ላይ የተደነገገ ፍርድን እናያለን። ኤፍሬም የእስራኤል ሰሜናዊው መንግሥት ሌላ ስም ነው። (ኢሳይያስ 28) ኢሳይያስ እስራኤል ፈጥና እንደምትጠፋ ተነበየ። ኢሳይያስ ሕዝቡን ወደ ክፋት በመሩት በእስራኤል መሪዎች ላይ እንዴት ትኩረት እንዳደረገ አስተውል። ካህናትንና ነቢያትን ስለ ስካር ያወግዛል፤ ነገር ግን የጽዮን የመሠረት ድንጋይ ወደሆነውና ሊመጣ ወዳለው መሢሕ ዳግም ያመለከታል። ሁለተኛ፥ በዳዊት ከተማ ላይ ፍርድ ይመጣል። የዳዊት ከተማ የደቡቡ መንግሥት ዋና ከተማ የሆነችው የኢየሩሳሌም ሌላ ስም ነው (ኢሳይያስ 29-30)። ኢየሩሳሌም ትዋረዳለች እንጂ አትጠፋም፤ ዳሩ ግን ኢየሩሳሌም ልትጠፋ በተቃረበችበት ጊዜ ጠላቶችዋ ይደመሰሳሉ። ይህ የሚያመለክተው የአሦርን ጦር መደምሰስ እንደሆነ አያጠራጥርም (ኢሳይያስ 37)። ኢየሩሳሌም ፍርድ ልትቀበል የነበረችበት ምክንያት ሕዝቡ በከንፈራቸው እግዚአብሔርን እናከብራለን ቢሉ እንኳ እግዚአብሔርን የሚያመልኩት በባዶ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ ስለነበር ነው። እግዚአብሔርን ከልባቸው አያመልኩትም ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝቦች እግዚአብሔርን በእውነት የሚያመልኩበት ጊዜ ግን ይመጣል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እኛ እግዚአብሔርን ከልባችን ሳይሆን በከንፈራችን ብቻ ማምለክ ቀላል የሚሆንልን እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆንህ መጠን ሕዝቡ በከንፈሩ ብቻ ሳይሆን በልቡም ጭምር እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ሦስተኛ፥ ከጠላቶቻቸው ከአሦራውያን ያድኗቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ላይ ከመታመን ይልቅ፥ በግብፅ ላይ በሚታመኑ ሰዎች ላይ ፍርድ ይመጣባቸዋል። አይሁድ የአሦር ጦር ኢየሩሳሌምን ለመውጋት በመጣ ጊዜ በጦርነቱ ይረዳቸው ዘንድ እጅግ ታላቅ ጦርና በርካታ ፈረሶች ያሉትን የግብፅን መንግሥት ለመጠየቅ በጣም ተፈትነው ነበር። እግዚአብሔር ግን ይህንን እንዳያደርጉ በኦሪት ዘዳግም አስጠንቅቆአቸው ነበር። ይልቁንም ነፃ እንዲያወጣቸው በእግዚአብሔር ላይ መታመን ነበረባቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እኛ በእግዚአብሔር ላይ ከመታመን ይልቅ በሌሎች ሰዎች፥ በመንግሥታት ወይም በውጭ ዜጎች እንዴት ልንታመን እንችላለን? ለ) ይህስ በእግዚአብሔር ላይ ስላለን እምነት ምን ይናገራል?
4. የሚመጣው የጽድቅ ንጉሥ (ኢሳይያስ 32)፡- የዓለም ተስፋ ሰብአዊ መንግሥት ወይም ሰብአዊ ንጉሥ አይደለም። እነዚህ ልክ እንደ እኛ ኃጢአተኞችና ደካሞች ስለሆኑ ሁልጊዜ ተስፋ ያስቈርጡናል። ከዚህ ይልቅ ተስፋችን ሊመጣ ባለው የጽድቅ ንጉሥ-በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መሆን አለበት። በእርሱ የጽድቅ ዘመነ መንግሥት እውነተኛ ሰላም ይኖራል።
5. ፍርድና በረከት (ኢሳይያስ 33-35)፡- ቀሪው የዚህ ክፍል ምንባብ ሊመጣ ያለውን ፍርድ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ከተዘጋጁ የወደፊት አስደሳች የተስፋ ቃሉች ጋር አጣምረው የያዙትን ትንቢቶች ያካትታል። ፍርዱ በፍጥነት እንደሚሆን ይናገራል። ይህ የሚያመለክተው የአሦርንና የባቢሎንን ምርኮ ነው፤ ነገር ግን ነፃ የወጡት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በሰላምና በደኅንነት የሚኖሩበትንና ክፋት የሚደመሰስበትን የመጨረሻውን ጊዜ ደግሞ ያመለክታል።
የትንቢተ ኢሳያይስ የመጀመሪያ ዐቢይ ክፍል የሆነው ከምዕራፍ 1-39 ያለው አሳብ የሚጠቃለለው ታሪካዊ በሆነ አቀራረብ ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ ሁለት ዐበይት ታሪካዊ ድርጊቶች ይገኛሉ። በመጀመሪያ፥ አሦር ኢየሩሳለምን የወጋችበት ታሪካዊ ድርጊት አለ። ይህ ለሕዝቡ ሁሉ የኢሳይያስን መልእክት ትክክለኛነትና እውነተኛነት የሚያመለክት ስለሆነ በጣም ጠቃሚ ነበር። ኢሳይያስ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ላይ እንደሚፈርድና ዳሩ ግን ጨርሰው እንደማይጠፉ ተናገረ። አሦራውያን ይሁዳን ሊወጉ በወጡ ጊዜ ከኢየሩሳሌም በስተቀር ሁሉም ከተሞች ፈራረሱ። በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች ወደ አሦር ተጓዙ። እግዚአብሔር ግን ከተማይቱ እንደማትወድቅ የገባውን ቃል አከበረ። ያለምንም የውጭ ጦር እርዳታ ጌታ ራሱ የአሦራውያንን ጦር ደመሰሰ። እርሱ ጠባቂያቸው እንደሆነና በእርሱ ብቻ ሊደገፉ እንደሚገባ እግዚአብሔር ለሕዝቡ አረጋገጠ።
ሁለተኛው ታሪካዊ ክሥተት የሕዝቅያስ ሕመም ሲሆን፥ እርሱም ከትንቢተ ኢሳይያስ ሁለተኛ ግማሽ ክፍል ጋር ያስተዋውቀናል። ሊመጣ ያለው የባቢሎን ምርኮ እርግጠኛ ነገር መሆኑን ያሳየናል። ሕዝቅያስ በታመመ ጊዜ እራስ ወዳድነቱ ዕድሜ እንዲጨመርለት እንዲጸልይ አደረገው። ሕዝቅያስ እስከዚህ ዘመኑ ድረስ እግዚአብሔርን የሚፈራ የመልካም ንጉሥ ሕይወት ምሳሌነት የሞላበት ኑሮ ስለኖረ በዚህ ሕመሙ ወቅት ቢሞት ይሻል ነበር። በስተ እርጅናው የታየው ራስ ወዳድነት ግን የሞኝነት ተግባር እንዲፈጽም አድርጎት ራሱንና ሕዝቡን አዋረደ።
የነበረውን ሀብት በሙሉ ለባቢሎናውያን በማሳየት፥ በሕዝቡ ላይ የወደፊት ጥፋት ጋበዘ። ያደረገው ነገር ቢኖር ስለ ራሱ በስስታምነት ማሰብ፥ እንደማይሞትና በዘመኑ ክፉ እንደማይመጣ በመመኘት መጽናናት ብቻ ነበር። አብዛኛውን የሕይወት ዘመናችንን እግዚአብሔርን ከተከተልን በኋላ እግዚአብሔርን፥ ራሳችንና ሕዝባችንን የማያስከብር ጥበብ የጐደለው ተግባር መፈጸም እጅግ ቀላል ነው።
ክፉው ንጉሥ ምናሴ የተወለደውም በዚህ ጊዜ ነበር። ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ የከፋ ሰው ነበር። ሕዝቅያስ በዚያን ጊዜ ሞቶ ቢሆን ኖሮ ይሁዳ ከዚህ ሁሉ ጥፋት ለማምለጥ በቻለች ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር በታማኝነት ሲጓዙ ቆይተው ድንገት የወደቁና እግዚአብሔርን ቤተሰባቸውንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያሳደቡትን ሰዎች እንዴት አይተሃቸዋል? ለ) ይህ ነገር ለእኛ ማስጠንቀቂያ ሊሆን የሚገባው እንዴት ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)