የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንተ ባለህበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ሰው መሪ የሚሆነው እንዴት ነው? የሚመረጠውስ እንዴት ነው? ለ) አንድ ሰው የቤተ ክርስቲያን መጋቢ፥ ሽማግሌ ወይም ወንጌላዊ ለመሆን ሊኖሩት የሚገቡ የተለያዩ መመዘኛዎችን ዘርዝር።
አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሊኖረው ከሚገባ እጅግ ጠቃሚ ነገሮች አንዱ፡- የሚሠራው ሥራ እግዚአብሔር ሊያደርገው የሚፈልገው ነገር ለመሆኑ ማረጋገጥ አለበት። ይህን ማረጋገጥ ብዙ ጊዜ «የእግዚአብሔር ጥሪ» ብለን እንጠራዋለን። የቤተ ክርስቲያን መሪ የሚሠራው ሥራ እግዚአብሔር እንዲሠራ የሚፈልገው ጉዳይ መሆኑን፥ እግዚአብሔር በሰጠው ስጦታ እንደሚሠራና ሥራውንም የሚያከናውነው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሆኑን ማወቁ አስፈላጊ ነው። የሚያሳዝነው ግን ከመሪዎቻችን መካከል አብዛኛዎቹ ለመምራት በእግዚአብሔር ስለ መጠራታቸው ምንም የሚሰማቸው ነገር የለም። ለመሪነት የምትሾማቸው ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ነው የሚያስቡት። በቤተ ክርስቲያን አመለካከት የመሪነት ብቃት ዋና መመዘኛ ሆኖ የሚቀርበው ሰውዬው ከትክክለኛ ትውልድ መምጣቱ፥ ከፍተኛ ትምህርት ያለው መሆኑ ወይም መሪ ለመሆን ያለው ትክክለኛ ማኅበራዊ ከበሬታ ነው። አንዳንድ ቦታ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክብር ለማግኘት ወይም ሥራ ለመቀጠር የሚያስችል ስለሆነ መሪ ለመሆን ይፈልጋሉ።
አንድ መሪ የሚያደርገው ነገር እግዚአብሔር እንዲያደርገው የመረጠውን ተግባር ስለመሆኑ በጥልቀት የማይሰማው ከሆነ በአመራሩ ላይ ወዲያውኑ ችግሮች ይፈጠራሉ። በስግብግብነትና በራስ ወድነት ሀብትና ክብርን ለማካበት ሲል ይመራል። አንድ የተሻለ ሥራ በተሻለ ክፍያ በሚያገኝበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የአመራር ተግባር ይተዋል። አንድ ሰው እግዚአብሔር እንደጠራው ይህ ውስጣዊ ግንዛቤ ከሌለው፥ በስደት ጊዜ ጸንቶ ከመቆም፥ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚመጣውን አብዛኛውን ስደት ከመቀበልና አመራሩን ከመቀጠል የመሪነት ሥራውን ይተዋል።
እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የነበሩትን ነቢያት ለነቢይነት አገልግሎት የጠራቸው ግልጽ በሆነ ሁኔታ ነበር። እነርሱ መርጠው የገቡበት አልነበረም። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ነቢያትን ለመጥራት ትልልቅ ራእዮችን ይሰጥ ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ፥ ሕዝቅኤል)። ብዙውን ጊዜ ግን የነቢያት ጥሪ ቀላል ነበር። እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን ሰዎች ለመጥራት የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀም ነበር። ዋናው ነገር እግዚአብሔር አንድን ሰው መጥራቱ ሳይሆን፥ ቤተ ክርስቲያንና ሰውዩው ራሱ፥ እግዚአብሔር ለዚያ አገልግሎት እንደጠራው መረዳታቸው ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር ሳይጠራቸው ወይም ስጦታ ሳይኖራቸው በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ በሚቀመጡበት ጊዜ ምን ዓይነት ችግሮች ተፈጥረው አይተሃል? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ የተሻሉ መሪዎችን ለመምረጥ ምን ማድረግ የምትችል ይመስልሃል?
ኤርምያስ የአገልግሎት ጥሪውን የተቀበለው በወጣትነቱ ነው፤ ይሁንና በጥሪው ለ40 ዓመታት አገልግሎት ዘመኑ ተመርቶበታል፤ የደረሰበትንም ስደት እንዲቋቋም ረድቶታል።
የውይይት ጥያቄ፥ ከእግዚአብሔር ጥሪ አለህን? ከእግዚአብሔር ጥሪ አለኝ ካልክ፥ አንድ የተለየ ነገር ታደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራህ የተረዳህበትን መንገድ ግለጽ።
የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 1-6 አንብብ። ሀ) የኤርምያስን ጥሪ ግለጽ። ለ) በኤርምያስ ምዕራፍ 1 የምትመለከታቸው ሁለት ራእዮች ምን ይመስሉሃል? ሐ) እስራኤላውያን በጥፋተኛነት የተከሰሱባቸውን የተለያዩ ኃጢአቶች ዘርዝር። መ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ተለይተው የተጠቀሱት የመሪዎች ኃጢአቶች ምንድን ናቸው?
1. የኤርምያስ ጥሪ (ኤር. 1)
ኤርምያስ እግዚአብሔር እንደጠራው ያውቅ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ እግዚአብሔር ኤርምያስን ለነቢይነት የመረጠው ገና በማኅፀን ሳለ መሆኑን ነግሮት ነበር። ኤርምያስ እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ ገና ወጣት ስለነበረ ለመሪነት እንደማይበቃ አስቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን እኔ ከአንተ ጋር ነኝ በማለት፥ እድሜ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ እንደገና አረጋገጠለት። ኃይል የሚመጣው ከኤርምያስ እድሜ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ከመናገሩ ነበር። የመንግሥታትን መደምሰስ የመተንበይ ችሎታ ለኤርምያስ የሰጠው ያ የእግዚአብሔር ቃል ነበር።
በኃጢአታቸው ምክንያት በይሁዳ ሕዝብ ላይ ፍርድ የሚመጣበት ጊዜ መኖሩን ገና ከጅምሩ እግዚአብሔር ለኤርምያስ ነግሮት ነበር። እንዲሁም የሰው ተቃውሞ የሚገጥመው ቢሆንም እንኳ እግዚእብሔር እንጂ ሰውን መፍራት እንደሌለበት ኤርምያስን አስጠንቅቆት ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙውን ጊዜ መሪዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን የሚፈሩባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ይህ ነገር በአንተ ሕይወት የደረሰው እንዴት ነበር?
እግዚአብሔር ለኤርምያስ ለመልእክቱ ምልክት የሚሆኑት ሁለት ራእዮች ሰጥቶት ነበር፤ እነርሱም፡-
ሀ. ስለ ለውዝ ዛፍ በትር ያየው፡- በዕብራይስጥ የለውዝ በትርና «መጠበቅ» የሚሉት ቃላት አንድ ዓይነት ይመስላሉ። የዚህ ራእይ ትርጕም እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ይጠብቃል፤ እርሱ አልተኛም ማለት ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ፍርድን ለማምጣት ቀርቦ ነበርና እግዚአብሔር እንደተናገረው ይፈጸም ዘንድ ቃሉ ይጠብቃል ማለት ነው።
ለ. በሰሜን አቅጣጫ ስላየው የሚፈላ ድስት ራእይ፡- ይህ ራእይ የሚያመለክተው በባቢሎን አማካይነት ስለሚመጣው የሰሜን ሠራዊት ጦርነት ነበር። እግዚአብሔር ይሁዳን ያጠቁ ዘንድ አሕዛብን እያንቀሳቀሰ ነበር። እግዚአብሔር በወሰነ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ የሆነው ድስት በኃጢአታቸው ምክንያት የይሁዳን ሕዝብ ለመቅጣት ይፈስሳል።
2. የኤርምያስ የመጀመሪያ መልእክት፡- የይሁዳ ሕዝብ እምነት ማጣት (ኤርምያስ 2፡1-3፡5) የመረጣቸውን እግዚአብሔርን ያለ አንዳች ምክንያት እንደተዉት ኤርምያስ ለሕዝቡ ነገራቸው። በሞኝነታቸው ሌሉችን የድንጋይና የእንጨት አማልክት በመምረጥ የጣዖት አምልኮ ያዘወትሩ ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ፍርድን ለማምጣት ወሰነ።
3. የኤርምያስ ሁለተኛ መልእክት፡- ተመለሱ ወይም የእግዚአብሔርን ፍርድ ተቀበሉ (ኤርምያስ 3፡6-6፡30) ይሁዳም ልክ እንደ እስራኤል ስለሆነች እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ተመሳሳይ ፍርድ ሊያመጣ ተዘጋጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይሁዳ ለባለዋ እንዳልታመነች ሚስት ለእግዚአብሔር ያላትን ታማኝነት የተወች ቢሆንም፥ ሕዝቡ ንስሐ ቢገቡና መንገዳቸውን ቢለውጡ እግዚአብሔር ይሁዳን ይቅር ለማለት አሁንም ፈቃደኛ ነበር። ቢመለሱና መንገዳቸውን ቢለውጡ፥ እግዚአብሔር ተገቢ የሆኑ እረኞችን (መሪዎች) ይሰጣቸዋል። ኢየሩሳሌምና ይሁዳም ለእግዚአብሔር ክብርን ያመጣሉ። ንስሐ ካልገቡና ካልተመለሱ ግን ምድሪቱን ሙሉ በሙሉ የሚደመስስ ኃይል ከሰሜን ይመጣል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ የኤርምያስ መጽሐፍ ምዕራፎች ምን ማስጠንቀቂያዎችን መውሰድ እንችላለን? ለ) ቤተ ክርስቲያንህን ስለ ኃጢአትና ኃጢአት ስለሚያስከትላቸው ነገሮች፥ እንዲሁም ስለ ንስሐ አስፈላጊነት ለማስተማር እነዚህን ምዕራፎች እንዴት ትጠቀምባቸዋለህ?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)