ኤርምያስ 18-25

እግዚአብሔር ከግለሰቦች ጋር እንደሚሠራ ሁሉ፥ በቡድን ከሰዎች ጋር ወይም ከአብያተ ክርስቲያናት ጋርም ይሠራል፤ በሁለቱም ረገድ የራሱ ዓላማዎች አሉ። በግለሰብ ደረጃ፥ ለሁላችንም ያለው ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስን እስክንመስል ድረስ እያንዳንዳችንን መቅረጽ ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 3፡18)። በአብያተ ክርስቲያናት ደረጃ ደግሞ የእግዚአብሔር ፍላጎት ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቁ የሆነች ቅድስትና ንጽሕት ሙሽራ እንድትሆን ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2)። በግለሰብ ወይም በአብያተ ክርስቲያናት ደረጃ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን በሚፈጽመው ሥራ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን የመምሰሉን ሂደት በማፋጠን ረገድ ልንተባበር እንችላለን። ወይም ደግሞ ይህንን ለውጥ በሕይወታችን ልንቃወም እንችላለን፤ ይህ ሲሆን ግን እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ያደርገን ዘንድ ዋናውን ሥራ የሚሠራው እርሱ ይሆናል። ይህም እግዚአብሔር መልሶ እኛን ከመሥራቱ በፊት በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ችግርና ሥቃይ ጥፋትም ይፈጸማል። እግዚአብሔር ለኤርምያስ ይህንን መመሪያ ለማስረዳት ሸክላ ሠሪን እንዲመለከት ያዘዋል። ሸክላ ሠሪው አንድ ማሰሮ ለመሥራት ሞክሮ ስለተበላሸበት ሙሉ ለሙሉ እንደገና አፍርሶ መሥራት ነበረበት። እግዚአብሔርም እንደዚሁ ይሁዳን ውብ አድርጎ ለመሥራት ፈልጎ ነበር፤ ይሁዳ ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች፤ ስለዚህ በምርኮና በፍርድ እግዚአብሔር ይሁዳን አንድ ቀን እርሱ እንደሚፈልገው እስክትሆን ድረስ ሊሠራት ፈለገ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስን እስክትመስል ድረስ እግዚአብሔር በሕይወትህ የሚሠራባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ከቤተ ክርስቲያንህ ቅድስትና የበለጠ ጠቃሚ እንድትሆን እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚሠራባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) ከዚህ መንፈሳዊ መመሪያ ልንወስዳቸው የሚገባን ማስጠንቀቂያዎች ምንድን ናቸው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 18-25 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ከክፉ ሥራቸው የሚመለሱ ሕዝብ ምን ይሆናሉ አለ? ለ) ክፉ ሥራን የሚሠሩና ከእርሱ የማይመለሱ ሕዝብስ ምን ይሆናሉ? ሐ) በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ምን ይመጣባቸዋል? መ) የተሰበረው ሸክላ ዕቃ የምን ምልክት ነው? ሀ) ጳስኮር በኤርምያስ ምን አደረገ? ረ) ኤርምያስ በእግዚአብሔር ላይ ያቀረበው ስሞታ ምን ነበር? ሰ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተጠቀሱ ልዩ ልዩ ነገሥታትን ጥቀስ። ሸ) ስለ ዳዊት የዘር ግንድ የተነገረው ትንቢት ምንድን ነው? ቀ) ስለ ሐሰተኛ ነቢያት የተሰጠው ትንቢት ምንድን ነው? በ) ስለ ምርኮው ዘመን ርዝመት የተሰጠው ትንቢት ምንድን ነው? 

1. ኤርምያስ በሸክላ ሠሪውና በተሰበረ ጠርሙስ ምልክትነት የሰጠው ስምንተኛ መልእክቱ (ኤርምያስ 18-20)

የሸክላ ሠሪነት ተግባር በኢትዮጵያውያን የተጠላ ቢሆንም በአይሁድ ዘንድ ግን የተናቀ አልነበረም። ይልቁንም የተከበረ ሙያ ነበር። እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በሸክላ ሠሪ እየተመሰለ የቀረበው ለዚህ ነው። እግዚአብሔር ኤርምያስን ሂድና ሸክላ ሠሪውን ተመልከት አለው። ኤርምያስም ሸክላ ሠሪው አንድ የሸክላ ዕቃ በሚሠራበት ጊዜ ሲበላሽበት፥ የተበላሸውንም ዕቃ በማፈራረስ ከዚያው ሸክላ አዲስ ዕቃ ሲሠራ ተመለከተ። እግዚአብሔር ከዚህ ምልክት እስራኤላውያንን ያስተማራቸው ነገር፥ የመጀመሪያው የሸክላ ዕቃ የሆኑት በኃጢአት ምክንያት ቢበላሹ፥ እነርሱን አፍርሶ ሌላ የሸክላ ዕቃ ለመሥራት እንደሚችል ነበር። ይህ ትምህርት ሌሉችንም ሕዝቦች በሙሉ የሚመለከት ነበር። ከኃጢአቱ ንስሐ የሚገባ ማንኛውም ሕዝብ ይድናል፤ በክፋት ሥራው እየቀጠለ የሚሄድ ሕዝብ ሁሉ ግን ይጠፋል። ይሁዳ በክፋት ሥራው እየቀጠለ ከሚሄድ ሕዝብ መካከል የሚመደብ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ሊያጠፋው ተዘጋጅቶ ነበር።

ኤርምያስ የእስራኤልን ሕዝብ መጥፋት ለማመልከት ሌላ ምሳሌያዊ ድርጊት ተጠቅሞ ነበር። ኤርምያስ አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎችን (ሽማግሌዎች) እና ሃይማኖታዊ መሪዎችን (ካህናት) ወደ ሄኖም ሸለቆ ይዞአቸው እንዲሄድ ተነገረው። የሄኖዎ ሸለቆ ከኢየሩሳሌም ቅጥር ክልል ውጭ የሚገኝ ስፍራ ነበር። በዚያ ስፍራ ለበአልና ለሌሎችም አማልክት ሰው እንደ መሥዋዕት ይቀርብላቸው ነበር፡፡ በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር ኤርምያስን ገንቦ እንዲወስድና እንዲሰብር በመንገር፥ የይሁዳ ሕዝብም እንዲሁ እንደሚደመሰሱ አመለከተ። አይሁድ ልጆቻቸውን መሥዋዕት አድርገው ለጣዖት ወይም ለባዕድ አማልክት የሚያቀርቡበት ይህ ስፍራ ከባቢሎን ጋር በሚካሄድ ጦርነት በሚወድቁ ሰዎች ሬሳ ይሞላል። እንዲያውም ወላጆች ልጆቻቸውን እስኪበሉ የሚያደርስ የከፋ ራብ ይሆናል። በኢየሱስ ዘመን ይህ ሸለቆ ቆሻሻ የሚጣልበትና የሚቃጠልበት ሲሆን፥ የገሃነም ምሳሌ ሆኖ ነበር።

ኤርምያስ ይህን መልእክት ከተናገረ በኋላ ከካህናት አንዱ የሆነው ጳስኮር ኤርምያስን መታው። ለአንድ ምሽት በላይኛው በብንያም በር ባለው በእግር ግንድ ውስጥ አሳደረው። ይህም ኤርምያስ ከሕዝቡ በኩል ከሚደርሱበት የስደት ዓይነቶች አንዱ ነበር። ኤርምያስ በእግዚአብሔር ላይ በማጉረምረም፥ ባይወለድ ይሻለው እንደነበር ተናገረ። ዝም በማለት ከስደት ለማምለጥ በሞከረ ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ቃል በውስጡ እያቃጠለው የባሰ ስደት ቢያስከትልበትም እንዲናገር ያስገድደው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሌሎች ሰዎችን ፌዝና ቀልድ ወይም ነቀፋ በመፍራት የእግዚአብሔርን ቃል ያለመናገር ስሜት ተሰምቶህ ያውቃልን? ለ) አንድ ክርስቲያን ለኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንዲኖርና ያለማቋረጥ ወንጌልን ለሌሎች እንዲያካፍል የሚያደርገው ነገር ምን መሆን አለበት? ሐ) በኤርምያስ ላይ የደረሰው ነገር በተፈጸመ ጊዜ ብትኖር ኖሮ ለኤርምያስ ምን ምክር ትሰጠው ነበር?

2. የኤርምያስ ዘጠነኛ መልእክት የይሁዳን ነገሥታት የሚመለከት ነበር (ኤርምያስ 21፡1-23፡8)። 

ኤርምያስ 21 የተፈጸመው ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት በፈጸመ ጊዜ ነበር። ንጉሥ ሴዴቅያስ፥ ኤርምያስ የሚለውን ለመስማት በፈለገ ጊዜ፥ ባቢሎናውያን ወደ ኢየሩሳሌም ሊገቡ እንዳለና ንጉሥ ሴዴቅያስና ሕዝቡ እንደሚቀጡ ተናግሮ ነበር።

እነዚህ ምዕፍራፎች የተጻፉት ከዳዊት ዘር በርካታ ነገሥታት በነገሡበት ዘመን ነበር። ኤርምያስ ከዳዊት ዘር የሆኑትን ነገሥታት በጽድቅ ባለማስተዳደራቸውና እግዚአብሔር እንደፈለገው ባለመግዛታቸው ገሠጻቸው። እነዚህ ነገሥታት በራሳቸው ብርታትና ጥንካሬ ተማምነው ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ደግሞ በነገሥታቱ ላይ ለመፍረድ ተዘጋጅቶ ነበር።

ዳሩ ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ከዳዊት ዘር ጻድቅ ቍጥቋጥ ያስነሣል፤ «እግዚአብሔር ጽድቃችን» ተብሎም ይጠራል። እግዚአብሔርን የሚያከብር ዓይነት ንጉሥም ይሆናል። እስራኤልንና ይሁዳንም ነጻ ያወጣል። በእርግጥ ይህ ከዳዊት የዘር ሐረግ ስለሚወጣው የመጨረሻ ንጉሥ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ ትንቢት ነው። 3. የኤርምያስ አሥረኛ መልእክት በይሁዳ ሐሰተኛ ነቢያት ላይ ያነጣጠረ ነበር (ኤርምያስ 23፡9-40)። ኤርምያስ በየሄደበትና የእግዚአብሔርን እውነት በሰበከበት ስፍራ ሁሉ ከእግዚአብሔር ተልከናል እያሉ ሐሰትን የሚናገሩ የነበሩ በርካታ ሐሰተኞች ነቢያት ነበሩ። በእነዚህ ሐሰተኞች ነቢያት ምክንያት ሕዝቡ መንገዳቸውን እንዲቀይሩ የሚጠይቀውንና ተወዳጅ ያልነበረውን የኤርምያስን መልእክት ከመስማት ታቀቡ። የቃላቸው ሐሰተኛነት ብቻ ሳይሆን ተግባራቸውም ክፉ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሐሰተኞች ነቢያት ላይ ሊፈርድ ተዘጋጅቶ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሐሰተኞች ነቢያት ዛሬ የሚሠሩት እንዴት ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖችን ወደ ስሕተት የሚመሩት እንዴት ነው? ሐ) በእውነተኞችና በሐሰተኞች ነቢያት መካከል ያሉትን ልዩነቶች መነጋገር የምንችልባቸው ነጥቦች ምንድን ናቸው? መ) የሐሰተኞች ነቢያትን ተጽዕኖ ለመቋቋም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

4. የኤርምያስ አሥራ አንደኛ መልእክት የሁለት ቅርጫት በለስ ነበር (ኤርምያስ 24)።

ኤርምያስ ሁለት ቅርጫት ሙሉ በለስ ተመለከተ። ይህ ያመለከተው ሁለት ዓይነት የይሁዳ ሕዝብ መኖራቸውን ነበር። ለመብላት መልካም የሆኑ በለስ የሞሉበት ቅርጫት ወደ ምርኮ የሚወሰዱትን ጻድቃን የይሁዳ ሰዎችን ሲያመለክት፥ በምርኮ በሚሆኑበት ምድር እግዚአብሔር እንደሚጠብቃቸውና አንድ ቀን ወደ ገዛ ምድራቸው ወደ ከነዓን እንደሚመልሳቸው የሚናገር ነበር።

ለመብላት መልካም ያልሆነ በለስ የሞሉበት ቅርጫት የሚወክለው በከነዓን ምድር የሚቀሩ ወይም ወደ ግብፅ የሚሸሹና እግዚአብሔርን የማይወዱ ሰዎችን ነበር። እግዚአብሔር ተስፋ በሰጣቸው ምድር እንዳይደሰቱ በሰይፍ፥ በራብ፥ በመቅሠፍትና በጥፋት ይፈርድባቸዋል። 

5. የኤርምያስ አሥራ ሁለተኛ መልእክት ግዞትና ከምርኮ አገር ስለ መመለስ ነበር (ኤርምያስ 25)። 

ይህ መልእክት የተሰጠው ኢየሩሳሌም በባቢሎን እጅ ለመውደቅ በተቃረበችበት በ605 ዓ.ዓ. ነበር።

ኤርምያስ ለአይሁድ የተናገረው እርሱን ስላልሰሙት ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋና ሕዝቡም እንደሚማረኩ ነበር። በዚህ ስፍራ ግን የምርኮው ዘመን ለሰባ ዓመት ብቻ እንደሚሆንና ከዚያ በኋላ ምርኮው ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመለስ በመናገር ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝቡን ያበረታታቸዋል።

የሰባ ዓመቱ ምርኮ የተጀመረበትን ጊዜ በሚመለከት ምሁራን የተለያየ አሳብ አላቸው። አንዳንዶች ይህ ቊጥር የምርኮውን አጠቃላይ ዘመን የሚወክል ቍጥር ነው ይላሉ። ሌሉች ደግሞ ይህ ቁጥር ትክክለኛ የዓመታት መግለጫ ሆኖ ከ605-539 ዓ.ዓ. ያለውን ጊዜ ማለትም ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰችበትና ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ መግዛት ካቆመበት ጀምሮ አይሁድ እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን የሚያመለክት ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ይህ 70 ዓመት የሚያመለክተው ቤተ መቅደሱ ከተደመሰሰበት ከ586 ዓ.ዓ. ጀምሮ እንደገና እስከተሠራበት እስከ 516 ዓ.ዓ. ድረስ ያለውን የአይሁድ የሃይማኖት በምርኮ ሥር የቆዩበት ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ዳንኤል 9 አንብብ። አይሁድ የሚመለሱበት ጊዜ እንደተቃረበ በተረዳ ጊዜ ዳንኤል ምን እያነበበ ነበር?

የእግዚአብሔር ፍርድ በአይሁድ ላይ ብቻ ሳይሆን በቀሩት አሕዛብም ላይ የሚደርስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመቅጣት ለጊዜው በተጠቀመባቸው በባቢሎናውያን ላይ ይፈርዳል። እንዲሁም በይሁዳ አካባቢ በሚኖሩና ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት በተባበሩ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ይህ ፍርድ ይመጣል። አንድ ጽዋ ወይን አንድን ሰው እንደሚያሰክር ሁሉ የእግዚአብሔር የቍጣ ጽዋ ደግሞ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ጥፋትን ያመጣል። የኤርምያስ የትንቢት ዓይን በቅርብ ጊዜ እነዚህ አሕዛብ አብዛኞቹ በባቢሎንና በሌሎችም አገሮች እንደሚጠፉ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ በሚነሡ ክፉ ሕዝቦችና መንግሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር የመጨረሻ ፍርድ የሚገለጽበትን የፍጻሜ ዘመን ጭምር ተመልከቶ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መንግሥታትና ክፉዎች ሰዎች ሁሉ አንድ ቀን የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደሚቀበሉ በሚያውቁበት ጊዜ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ጸንተው እንዲራመዱ የሚያበረታታቸው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች ወደ ዓለም እንዳይመለሱ ለማስጠንቀቅ እነዚህን (ምዕራፎች እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: