በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚመጣው ከፍተኛ አደጋ ስደት አይደለም። የሐሰት ትምህርትም አይደለም። ትልቁ አደጋ ግን ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖትን ቅርጽ ወይም ሥርዓታዊ አምልኮ ብቻ ይዛ መጓዟን፥ መቀበሏንና የሰዎችን ሕይወት የሚለውጥና በሰዎች አኗኗር ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሃይማኖት አለመኖሩ ነው። በኤርምያስ ዘመን የነበሩ አይሁድ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ ማምለካቸውን አልተዉም ነበር። ለእግዚአብሔር የእንስሳ መሥዋዕት ማቅረባቸውን አልተዉም ነበር፤ ነገር ግን ይህ በየጊዜው የሚፈጸሙት ሥርዓት ብቻ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት አልነበራቸውም። ሕይወታቸው እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የሚመራ አልነበረም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምልኮአቸውን ለመቀበል አልፈለገም፤ በምትኩ ግን ፍርድ እንደሚያመጣባቸው ተናገረ።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ወይም በሌላ ቤተ ክርስቲያን ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? አንዳንድ ማስረጃዎች ስጥ፡፡ ለ) ይህ በግል ሕይወትህ ሊፈጸም የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) አምልኮህ እውነተኛና በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ ልታደርጋቸው የምትችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? መ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ አባላት ላይ እንዳይፈጸም ለማድረግ አንተ ወይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 7-17 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር የአይሁዶችን አምልኮ ያልተቀበለው ለምንድን ነው? ለ) በዚህ ክፍል ውስጥ የታዩትን የይሁዳ ኃጢአቶች ዘርዝር። ሐ) በዚህ ስፍራ ስለ ይሁዳ መሪዎች የተነገረው ምንድን ነው? መ) ኤርምያስ መንፈሳዊ እውነቶችን ለመግለጥ የተጠቀመባቸውን ምልክቶች ዘርዝር።
እነዚህ ምዕራፎች በሚጻፉበት ጊዜ፥ ኢዮስያስ የአይሁድን ሃይማኖት ለማደስ ፈልጎ እንደነበር አስታውስ። ተግባራቸውን ለተወሰኑ ጊዜያት ለመቀየር ችሎ ነበር፤ የሕዝቡ ልብ ግን አልተለወጠም ነበር። ኢዮስያስ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ ወደ ሐሰተኛ ሃይማኖቱ ተመለሰ።
1. የኤርምያስ ሦስተኛ መልእክት ስለ አይሁድ አምልኮ መበላሸት የሚናገር ነበር (ኤርምያስ 7፡1-10፡25)።
አይሁድ የአምልኮ ሥርዓት እየፈጸሙ ቢመላለሱም እንኳ እግዚአብሔር ደስተኛ አልነበረም። እንደ ብዙዎቻችን ሁሉ በአምልኮ የሚያደርጉትን ነገር በሕይወታቸው ከሚለማመዱት ነገር ለይተውት ነበር። እግዚአብሔር ከአምልኮ ሕይወት ይልቅ በአምልኮ ተግባራት ላይ የበለጠ እንደሚያተኩር ይመስላቸው ነበር፤ ስለዚህ ሕይወታቸው እግዚአብሔርን የሚያስከብር እንዲሆን ምንም ጥረት አያደርጉም ነበር። ከሌሎች ጋር በቅድስናና በፍትሕ አይኖሩም ነበር። የዚህ ዓይነቱ አምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የሌለው ከንቱ ነበር። አይሁድ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው ቤተ መቅደስ በመካከላቸው ስለነበር ኤርምያስ የሚናገረው የትንቢት ፍርድ ሊፈጸም ወይም ሊደርስባቸው እንደማይችል አድርገው ያስቡ ነበር፤ ስለዚህ ስለ መልእክቱ ይጠራጠሩ ነበር። ኤርምያስ በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ እንደተጻፈው፥ በዔሊ ዘመን የመገናኛው ድንኳን እንዲደመሰስና ታቦቱ እንዲማረክ እግዚአብሔር እንዴት እንደፈቀደ ማስታወስ ነበረበት (1ኛ ሳሙኤል 4)።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ይፈርስና ይጠፋ ዘንድ እንደማይፈቅድ በሚያስቡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ዘንድ ይህ ተመሳሳይ አመለካከት የሚታየው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ስላለ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በኃጢአት ምክንያት አይቀጣም ለሚሉ ክርስቲያኖች እንዴት መልስ ትሰጣለህ?
የይሁዳ ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና እርሱንም ለመታዘዝ በተደጋጋሚ እምቢ አሉ። ሐሰተኞች አማልክትን የማምለክ ተግባራቸው የበለጠ ግልጽ እየሆነ መጣ። ፍርድ የሚቀበሉበትን ጊዜ ወሰነ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ኤርምያስን ለሕዝቡ ደኅንነት ወይም ከጥፋት ነፃ መውጣት የሚያደርገውን ጸሎት እንዲያቆም ነገረው። ኤርምያስ ባቢሎናውያን ይሁዳን በሚወጉበት ጊዜ ስለሚመጣው ታላቅ ጥፋት ተነበየ።
ኤርምያስ ከተመኛቸው ነገሮች አንዱ፡- የተቀረጹ ምስሎችን ማምለክ ምን ያህል የሞኝነት ተግባር እንደሆነ ማስተማር ነበር። የተቀረጹ ምስሎች ሰዎች ከሚያገኟቸው ከማናቸውም ዓይነት ቍሳቁሶች የሠሯቸው ነበሩ፤ ነገር ግን ምንም ኃይል አልነበራቸውም። ከነዚህ ጋር ሲነጻጸር፥ የማይታየው አምላክ እጅግ ታላቅ ኃይል ነበረው። እርሱ ምድርን የፈጠረ ዘላለማዊ ንጉሥ ነው። ስለዚህ ኤርምያስ የተከተሉትን የሞኝነት መንገድ እንዲመለከቱና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ እስራኤላውያንን ያሳስባቸዋል። እነርሱ ግን በሞኝነታቸው ገፉበት፤ የእግዚአብሔርንም ፍርድ በራሳቸው ላይ አመጡ።
እግዚአብሔር በአብዛኛው ማንን ጥፋተኛ እንደሚያደርግ አስተውል። ለአብዛኛው ጥፋት ተጠያቂ ያደረጋቸው የይሁዳ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች የሆኑ እረኞችን ነበር። ከእግዚአብሔር ምሪትን ስለማይጠይቁ ምናምንቴዎች ነበሩ። የመጨረሻው ውጤት መንጋው በሙሉ ማለትም የእስራኤላውያን መበታተንና መጥፋት ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ መጥፋት የእስራኤልን ሕዝብ መሪዎች ዋና ተጠያቂዎች ያደረገው ለምን ይመስልሃል? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሆንን ለእኛ ምን ማስጠንቀቂያ ይሆነናል ሐ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገቢ ያልሆነ አመራር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ጉዳት ሲያስከትል ያየኸው እንዴት ነው?
2. የኤርምያስ አራተኛ መልእክት ይሁዳ ከእግዚአብሔር ጋር የገባችውን ቃል ኪዳን ስለ ማፍረሷ የሚናገር ነው (ኤርምያስ 11፡1-12፡17)።
እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በሲና ተራራ ላይ የገባውን ቃል ኪዳን የማፍረሳቸው ክስ በብሉይ ኪዳን ነቢያት ልብ ውስጥ መቀመጡ የሚታወስ ነው፤ ስለዚህ ነቢያት ብዙውን ጊዜ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተገለጹት እርግማን መድረሳቸውን ያመለክቱ ነበር። ቃል ኪዳኑን ስላፈረሱ እርግማኑን መጋፈጥ እንደነበረባቸው ኤርምያስ ለሕዝቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል። እንደገና ኤርምያስ ለሕዝቡ መጸለይ እንደማያስፈልገው ተነግሮት ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር መልስ አይሰጥም ነበርና ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ስለማይመልስልን ዛሬ ልንጸልያቸው የማይገባን ጸሎቶች አሉን? አንዳንድ ምሳሌዎችን ዘርዝር።
ኤርምያስ የፍርድ መልእክትን በግልጽ በማወጁ፥ ከሕዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። የገዛ ራሱ ነገድና ከትውልድ አገሩ የሆኑ ሰዎች ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር (ኤርምያስ 11፡18-23)።
ኤርምያስ፥ የይሁዳ ሕዝብ ያዘወትሩት የነበረውን ግልጽ የሆነ ክፉ ድርጊት በመመልከት፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ የተናገረውን ፍርድ ለምን እንዳላመጣባቸው ይጠይቃል። ክፉዎች የሚከናወንላቸው እስከ መቼ ነው? እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደተዋቸውና ያለ እርሱ ጥበቃም ጥፋቱ እንደማይቀር ለኤርምያስ ነገረው።
3. የኤርምያስ አምስተኛ መልእክት ለምንም የማይረባ የወገብ መታጠቂያና በተቀደደ የወይን አቍማዳ ምልክትነት የተገለጠ ነበር (ኤርምያስ 13)።
እግዚአብሔር ሕዝቡ የጥፋት መልእክት እንዲሰሙ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ ለዚያ ጥፋት የሚታይ ምልክት አድርጎ ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ኤርምያስን ይሁዳ እንዴት ዋጋ እንዳጣች ለማሳየት፥ ሁለት ምልክቶችን እንዲያሳይ ኤርምያስን ጠየቀው። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ኤርምያስን ከተልባ እግር የተሠራች ካህናት የሚታጠቋት ዓይነት መታጠቂያ እንዲገዛና እንዲታጠቅ አዘዘው። ይህች መታጠቂያ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ የእግዚአብሔር ካህናት መሆን እንደነበረባቸው የምታስታውሳቸው ነበር (ዘጸአት 19፡6 ተመልከት)። ይህችን መታጠቂያ ወደ ጴራክ ወስዶ እንዲሸሽጋት ተነገረው። ይህች ስፍራ በመቶ የሚቈጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ከኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የምትገኝ ነበረች። ይህ የአሦራውያንና የባቢሎናውያን ክፉ ተጽዕኖ የሚመጣበትን አቅጣጫ የሚያሳይ ነበር። ከብዙ ቀናት በኋላ ኤርምያስ የተበላሸችውን መታጠቂያ ለሕዝቡ እንዲያሳይ ተነገረው። ይህም የእግዚአብሔር ሕዝብ በምድራቸው እያሉ በአሕዛብ ተፅዕኖ መበላሸታቸውን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም በምርኮ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ እንደሚበላሹ የሚያሳይ ነበር። በዚህ ጊዜ ለእግዚአብሔር ያላቸው ጠቀሜታ ያከትማል።
ሁለተኛው ምልክት በወይን የተሞላ አቁማዳ ነበር። በጥንት ዘመን በኅብረተሰቡ ዘንድ ከሚታወቁ ክፉ ነገሮች መካከል አንዱ ሰካራምነት ነበር። ብዙ መሪዎች ሰካራሞች በመሆናቸው ይመኩ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በተለይ መሪዎችን ለየት ባለ መንገድ ሰካራሞች ያደርጋቸዋል። በቍጣው መዓት እንዲሰከሩ ሲያደርግ በእነርሱ መዘጋጀቱን ያሳያል። ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነው ይህ ፍርድ በከፊል የጠላት ወረራ በሚመጣበት ጊዜ፥ ሕዝቡ የሰከሩ በመምሰል ጠላቶቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ለይተው መናገር እስከማይችሉ መድረሳቸው ነው።።
ከዚያም ኤርምያስ ግልጽ በሆነ መንገድ ስለሚመጣው ምርኮ ተነበየ። ንጉሡና የንግሥቲቱም እናት ሳይቀሩ ከሰሜን በሚመጡት በባቢሎናውያን እንደሚማረኩ ተናገረ።
4. የኤርምያስ ስድስተኛ መልእክት ስለሚመጣው ድርቅ የተነገረ ነበር (ኤርምያስ 14፡1-15፡21)።
በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥ በሕዝቡ ላይ ስለሚደርሱ ሦስት ዐበይት የጥፋት ምንጮች በተደጋጋሚ እናነባለን። በዝናብ ዕጥረት ምክንያት የተከሠተ ድርቅ ነበር። ምግብ ባለመኖሩ ምክንያት ደግሞ ራብ ነበር። ራብ የድርቅ ወይም ሰብል ሁሉ የሚደመሰስበትና የእርሻ ሥራ የሚቆምበት የጦርነትም ውጤት ሊሆን ይችላል። በመጨረሻ ሰይፍ ነበር፤ ይኸው ሰይፍ በጠላት ውጊያ የሚመጣ ጥፋት ነበር። እግዚአብሔር ለኤርምያስ የፍርዱ ቀን ስለደረሰ፥ ስለ ሕዝቡ ነፃ መውጣት መጸለይ እንደሌለበት ለሦስተኛ ጊዜ ይነግረዋል። በዚያን ወቅት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ታላላቅ የጸሎት ሰዎች በመሆናቸው የሚታወቁት ሁለቱ ሰዎች ማለትም እስራኤላውያን በሲና ተራራ ፈጽመው እንዳይጠፉ የማለደው ሙሴና ሕዝቡ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው በጠየቁ ጊዜ ሊጸልይላቸው ቃል የገባው ሳሙኤል እንኳ ለሕዝቡ ቢማልዱ፥ እግዚአብሔር አይሰማቸውም ነበር።
ኤርምያስ ሊመጣ ስላለው ጥፋት የተሰማውን ኀዘን ይገልጻል። ዓይኖቹ እንባ አዝለው፥ ልቡም ተሰብሮ ነበር፤ ይህም ሆኖ በእግዚአብሔር ምሕረት ይተማመን ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ ሕዝቡ በመልእክቱ ላይ የሚሰነዘሩትን ተቃውሞ መቀበል ጀምሮ ነበር። እግዚአብሔር ግን ሊያጠፉት ቢፈልጉም እንኳ እርሱ ስለሚታደገው ሊያሸንፉት እንደማይችሉ በመናገር አበረታታው።
5. የኤርምያስ ሰባተኛ መልእክት፡- ሳያገቡ ስለመኖር ተምሳሌትና ስለይሁዳ ጥፋት ነበር (ኤርምያስ 16-17)። እግዚአብሔር ሊመጣ ስላለው ነገር ለመናገር የኤርምያስን ሕይወት ቋሚ ምልክት አድርጎት ነበር። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሚስት እንዳያገባ ወይም ልጆች እንዳይወልድ ነገረው። በአይሁድ ባህል አንጻር ማግባትና ልጅ መውለድ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ስለነበር ለኤርምያስ ይህ ትልቅ ሸክም ነበር። አንድ አይሁዳዊ በሕይወቱ እንዳያጋጥሙት እጅግ ከሚሰጋባቸው ነገሮች ምንም ልጅ ከሌለው ስሙ ስለሚጠፋ (መታሰቢያ ስለማይኖረው) ልጅ እንዳያጣ ነበር፤ ነገር ግን ኤርምያስ ይህንን እጅግ ከባድ ትእዛዝ ፈጸመ። እግዚአብሔር ኤርምያስን ሚስት እንዳያገባ የከለከለው ለሕዝቡ በራሳቸው፥ በሚስቶቻቸውና በልጆቻቸው ላይ ሊመጣ ያለውን ጥፋት ያለማቋረጥ እንዲያስታውሳቸው ነበር።
እግዚአብሔር ለኤርምያስ የነገረው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ እንዳያለቅስና እንዳያዝን ነበር፤ ምክንያቱም የሕዝቡ መሞት የእግዚአብሔር ፍርድ ስለነበር ኤርምያስ እግዚአብሔርን በመቃወም የቆሙ ሰዎች ሲፈረድባቸውና የሚገባቸውን ቅጣት ሲቀበሉ በማዘን በእግዚአብሔር ፍርድ ያለመስማማቱን ማሳየት ስላልነበረበት ነው።
እግዚአብሔር ኤርምያስን በሠርግ ወይም በሌላ የደስታ ጊዜያት እንዳይደሰት ነግሮት ነበር። ይህም በባቢሉን አማካይነት በይሁዳ ላይ ሊመጣ ያለውን የጥፋት ኅዘን በሕይወቱ የሚያሳይ ምልክት ነበር።
ፍርድ መምጣቱ የተረጋገጠ ቢሆንም እንኳ ፍርድን እንደሚያመጣ የተናገረ እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ መመለስም ተናግሮ ነበር። አንድ ቀን የእግዚአብሔር ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች ሁሉ ወደ አገራቸው ይሰበስባሉ።
የውይይት ጥያቄ፡ ኤርምያስ 17፡58 አንብብ። ሀ) ብርታት ለማግኘት በሥጋ ላይ ልንታመን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) ስለ ችሎታችን ወይም ብቃታችን በእግዚአብሔር ላይ እንዴት መታመን እንደምንችል ምሳሌዎችን ጥቀስ። ሐ) ኤርምያስ በሰውና በእግዚአብሔር በሚታመን ሰው መካከል ስላለው ልዩነት የሚናገረው ምንድን ነው?
ኤርምያስ በተለይ በእግዚአብሔር አመለካከት ክፉ ስለሆነ አንድ ሌላ ኃጢአት ይገልጽልናል፤ ይህም እግዚአብሔር ስለ ሰንበት ወይም ቅዳሜ ዕረፍት የሰጠውን ትእዛዝ መጣስ ነበር። የእስራኤላውያን የሰንበት ዕረፍት ቅዳሜ ነበር። በብሉይ ኪዳን ከተሰጡ ዋና ዋና ትእዛዛት መካከል ሰንበትን መጠበቅ አንዱ ቢሆንም፥ እስራኤላውያን ግን ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ ሥጋዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን አስቀድመው ነበር፤ ስለዚህ የሰንበትን ሕግን መጣስ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ትተው በራሳቸው መንገድ መሄዳቸውን ከሚያሳዩ ምልክቶች አንዱ ነበር፡፡
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች የምንማራቸውን ትምህርቶች ዘርዝር። ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ኃጢአት፥ ስለ እግዚአብሔር ፍርድና እግዚአብሔር ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር ምን እንማራለን? ለ) እነዚህ ቊጥሮች ከሚያስተምሯቸው ነገሮች መካከል ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የምንረሳቸው ወይም የማንሰብካቸው የትኞቹ ናቸው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)