ኤርምያስ 26-36

የእውነትና የወንጌል ጠላቶች ብዙ ጊዜ በሕዝቡ መካከል የሚገኙ የሃይኖት መሪዎች መሆናቸው አሳዛኝ የሆነ እውነታ ነው። ይህ ኢየሱስ በኖረበት ዘመንም እውነት ነበር። ተራ የሆኑ ሰዎችና ኃጢአተኞች ኢየሱስን ሲወዱ፥ ለእግዚአብሔር ቅርብ ነን ይሉ የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ግን ኢየሱስን በመጥላት ሰቅለው ገደሉት። ይህ በኤርምያስ ሕይወትም እውነት ነበር። ኤርምያስ የእግዚአብሔርን ቃል፥ ሊመጣባቸው ስላለው ፍርድ ለሕዝቡ በድፍረት በተናገረ ጊዜ ካህናቱና ነቢያቱ ሊገድሉት ሞከሩ። ለእግዚአብሔር እንደሚናገሩና እውነተኛውን የእግዚአብሔርን አምልኮ እንደሚጠብቁ በአፋቸው ቢናገሩም እንኳ ሕዝቡን ከእውነት በማራቅና እውነት የሚናገሩትን በማሳደድ ተግባር ላይ የተሰማሩ የሰይጣን መሣሪያዎች ነበሩ።

ይህ ነገር ዛሬም ቢሆን ዘውትር የሚታይ ነው። እጅግ ክፉ የምንለው ነቀፋና ትችት የሚገጥመን ከሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ሳይሆን ከራሳችን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊሆን ይችላል። እንዲህ ባለው ጊዜ ዝም ልንልና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ልንኖር እንደሚፈልጉት ሆነን ለመኖር እንፈልጋለን። ይህን በማድረጋችንም የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት እናቆምና ለእግዚአብሔር ለመሥራት ለሚፈልጉ ሰዎች ዕንቅፋት መሆን እንጀምራለን። የሌሎች ሰዎችን ነቀፋ መስማትና ከዚያም መማር ያለብን መቼ እንደሆንና ሌሎች ምንም ቢሉ ወይም ቢያስቡ፥ የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና መታዘዝ ያለብን መቼ እንደሆነ ለመለየት ከፍተኛ መንፈሳዊ ብርታትና ጥበብ ያስፈልገናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሃይማኖት መሪዎች አንተን ወይም ቤተ ክርስቲያንህን በቃል ወይም በሌላ አካላዊ ጉዳት በሚያስከትል ሁኔታ እንዴት እንዳሳደዱ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ይህንን ያደረጉት ለምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሪዎች ሳይቀሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለውጥ እንዳይመጣ የተከላከሉባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንዲያደርጉት የሚፈልገውን ነገር በሚያውቁበትና ሌሎች መሪዎች ይህን እንዳያደርጉ በሚቃወሟቸው ጊዜ መስጠት የሚገባቸው ትክክለኛ ምላሻቸው ምንድን ነው?

ሌሎች መሪዎች በሐሰት በሚከሱን ጊዜ መስጠት የሚገባን ምላሽ ምንድን ነው? በመጀመሪያ፥ ራሳችንን ማዋረድና የሚባለውን ነገር በጥንቃቄ ልንሰማ ያስፈልጋል። ክሱ፥ በአብዛኛው ውሸት ቢሆንም እንኳ ብዙ ጊዜ ግን ውሸት በውስጡ የተወሰነ እውነት ሊኖረው ይችላል። ሌሎች ከሚሉት ውስጥ እውነት የሆነው የትኛው ክፍል ነው? ልንናዘዘውና ልንለውጠው የሚገባ ነገር አለን? ሁለተኛ፥ በቃላት የሚያጠቃንን ሰው መልሶ ከማጥቃትና ለሌሎች ከማማት መፋጠብ ይኖርብናል። ትክክል የሆነውን ነገር ለሌሎች ለማሳየት፥ እግዚአብሔርን መለመን አለብን? ሦስተኛ፥ ስለ እኛ የተሳሳተ ነገር ያወራውን ሰው ሁልጊዜ እንደምንወደው ማረጋገጥ አለብን። የታዘዝነው ጠላቶቻችንን እንድንወድ ነው። ይህም ማለት በበቀልና የሌሎችን መልካም ስም ማጕደፍ የለብንም ማለት ነው። አራተኛ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሕይወታችንን ከመረመርን በኋላ ትክክለኛ ለሆነው ነገር ጸንተን በመቆም፥ የሌሎች አመለካከት ሳያስፈራን ልንኖር ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 26-35 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ኤርምያስ የተጋፈጣቸውን የተለያዩ ስደቶች ዘርዝር። ለ) በኤርምያስ ላይ ስደት ያስከተለው ማን ነበር? ሐ) ኤርምያስ ለአይሁድ ሕዝብ የሰጠው የማበረታቻ ተስፋ ምን ነበር?

1. በኤርምያስ ላይ የደረሰው ግጭት (ኤርምያስ 26-29)

ኤርምያስ 26-29 የኤርምያስ መልእክቶች በአይሁድ ሕዝብ፥ በተለይም በሃይማኖትና በፖለቲካ መሪዎች ዘንድ እንዴት ተቀባይነት እንዳልነበራቸው የሚያሳዩ ታሪካዊ ምሳሌዎች ናቸው።

ሀ. የኤርምያስ ከካህናትና ከሐሰተኞች ነቢያት ጋር ግጭት (ኤርምያስ 26) 

ኤርምያስ ቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም ቅጥሮች እንደሚደመሰሱ በድፍረት በተናገረ ጊዜ ካህናትና ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡና በአገር ሽማግሌዎች ፊት ከሰሱት። ዳሩ ግን በጊዜው የነበሩት ባለሥልጣናት የኤርምያስን የመከላከያ መልስ ከሰሙ በኃላ ሕዝቡ ኤርምያስን እንዲገድሉ ከመፍቀድ ታቀቡ። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ኦርዮ የተባለ ሌላ እውነተኛ ነቢይ ለእግዚአብሔር በመታዘዙ ተገደለ። እግዚአብሔር የአንዱን ነቢይ ሕይወት (የኤርምያስን) ሲያተርፍ፥ ሌላውን (ኦርዮ) ደግሞ እንዲሞት መፍቀዱን መመልከት የሚያስገርም ነው። ማን መኖር ግን ደግሞ መሞት እንዳለበት የሚወስነው እግዚአብሔር እራሱ ነው። ሁለቱም ጻድቃን ነበሩ። እግዚአብሔር ሁለቱንም መጠበቅ ይችል ነበር። በዚህ ፋንታ ግን እግዚአብሔር አንዱ ነቢይ እንዲሞት ሌላው ደግሞ እንዲተርፍ አደረገ።

ለ. ኤርምያስ ከሐሰተኞች ነቢያት ጋር የነበረው ግጭት (ኤርምያስ 27-29)

አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በባቢሎኑ ናቡከደነፆር የባርነት ቀንበር ሥር እንደሚወድቁ በተግባራዊ ምሳሌ ለማሳየት፥ በሬዎች በእርሻ ሥራ ላይ ሲሆኑ የሚጫንባቸውን ቀንበር በራሱ አንገት ላይ አደረገ። ኤርምያስ ሕዝቡ ለባቢሎናውያን ቀንበር በመገዛት በይሁዳ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ፥ ይህንን ከተቃወሙ ግን እንደሚሞቱ ወይም በይሁዳ እንደሚማረኩ ነገራቸው። ኤርምያስ የሚናገረው ውሸት እንደሆነና ሕዝቡ ባቢሎንን እንዲቃወሙ የሚገፋፉት ካህናት ሐሰተኞች ነቢያት ስለመሆናቸው ተናገረ። ኤርምያስ፥ እስከ አሁን ድረስ ናቡከደነፆር ያልወሰዳቸው የቤተ መቅደስ ዕቃዎችም ወደ ባቢሎን እንደሚወስዱ ለካህናቱ ነገራቸው።

ኤርምያስን ከተቃወሙት ሐሰተኞች ነቢያት አንዱ ሐናንያ ነበር። ሐናንያ ኤርምያስ ያደረገውን የእንጨት ቀንበር በመስበር በሁለት ዓመት ውስጥ ናቡከደነፆር ከቤተ መቅደስ የወሰዳቸው ዕቃዎች በምርኮ ከተወሰደው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮአኪም ጋር ይመለሳሉ በማለት ተናገረ። ከዚህ በኋላ ኤርምያስ ሊሰበር የማይችል የብረት ቀንበር በአንገቱ ላይ በማድረግ፥ ሊመጣ ያለው የባቢሎን ምርኮ ቀንበር ሊሰብሩት የማይችሉት እንደሆነ አመለከተ። ከዚያም ኤርምያስ በአንድ ዓመት ውስጥ ሐናንያ እንደሚሞት አመለከተ። ይህ ትንቢት ኤርምያስ እንደተናገረ በዓመቱ ውስጥ በመፈጸም፥ ኤርምያስ እውነተኛ ነቢይ እንደሆነ አረጋገጠ።

እንደ ሐናንያና ሺሚያ ያሉ ሐሰተኞች ነቢያት ለተማረኩት አይሁድ ከምርኮ ፈጥነው እንደሚመለሱ ስለነገሯቸው በሄዱበት አዲስ ምድር ተረጋግተው አልተቀመጡም ነበር፤ በስደተኝነት ይኖሩ ነበር። ስለዚህ ኤርምያስ በግዞት ላይ ላሉት ሰዎች እግዚአብሔር እነርሱን ወደ ከነዓን ከመመለሱ በፊት የምርኮው ዘመን 70 ዓመት እንደሚወስድ በመጥቀስ ደብዳቤ ጻፈላቸው። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ስላልተዋቸው አሁንም ለእነርሱ መልካም ዕቅዶች ነበረው። ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በባቢሎን ምድር ተረጋግተው በመቀመጥ በእርሻና በአገሪቱ ንግድ በመሳተፍ፥ የተለመደ ሕይወት መግፋት እንዳለባቸው ነገራቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ ከሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ያደረገውን ትግል ከሚገልጹት ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ መሪነት ምን ትምህርት ልንማር እንችላለን?

2. ኤርምያስ ለአይሁድ ያስተላለፈው የማበረታቻ መልእክት (ኤርምያስ 30-33) 

አብዛኛዎቹ የኤርምያስ ትንቢቶች ስለሚመጣው የኢየሩሳሌም ጥፋት የሚናገሩ ቢሆኑም፥ ከምርኮው በኋላ ለሚኖሩ አይሁድም የማበረታቻ መልእክት ለማስተላለፍ ይፈልግ ነበር። እግዚአብሔር ጨርሶ እንደማይተዋቸው ኤርምያስ ለሕዝቡ ነገራቸው። ሊቀጣቸው እንጂ ፈጽሞ ሊያጠፋቸው አለማቀዱንም አረጋገጠላቸው።

ኤርምያስ «የመከራ ጊዜያት» ተብሎ የሚጠራ እጅግ አስጨናቂ ጊዜ እንደሚኖር ይናገራል። ይህንን የመከራ ጊዜ ምሁራን «የያዕቆብ መከራ» ብለው ይጠሩታል። ይህ ጊዜ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ስለ ሁለት የተለያዩ ጊዜያት የሚናገር ነው። የመጀመሪያው፥ በባቢሎናውያን ስለተፈጸመው የጥፋት ጊዜ ሲሆን፥ ሁለተኛው ግን፥ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ጥፋት ስለሚደርስበትና በመጨረሻው ዘመን ስለሚቀሰቀስ ሌላ የጦርነት ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡ በእነዚህ ጊዜያት እንዲያልፍ ሲፈቅድም እንኳ ፈጽሞ እንደማያጠፋቸው ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። ይልቁንም እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል። ከምርኮ ወደ ተስፋይቱ ምድር ይመልሳቸዋል። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ከአይሁድ ፈጽሞ አይወስድባቸውም። እንደገና ታላቅ ደስታና ሐሤት የሚያደርጉበት ዘመን ይመጣል። እስራኤልና ይሁዳ በመባል የተከፈለው የያዕቆብ ቤት እንደገና አንድ ይሆናል።

ደግሞም እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን ያደርጋል። ይህ ቃል ኪዳን ለእስራኤል ሁሉ ይሆናል። ይህ ቃል ኪዳን እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩ ጊዜ እግዚአብሔር ከሰጣቸው ቃል ኪዳን ይበልጣል።

የዚህን ቃል ኪዳን ልዩ ተስፋዎች ተመልከት፡-

ሀ. ሕጉ በድንጋይ ጽላት ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ ልብና አእምሮ ውስጥ ይጻፋል። ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ስለሚያውቁ ስለ እርሱ ማስተማር አያስፈልግም። ሰዎች ሁሉ ውጫዊ በሆኑ ሕግጋት አማካይነት ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ ከመገደድ ይልቅ ከልባቸው የሚታዘዙ ይሆናሉ። 

ለ. እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ይኖራል። ያለፈው ነገር ይረሳና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ይኖራቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ አዲስ ቃል ኪዳን በኢየሱስ መምጣትና በእርሱ ባመንን ጊዜ በከፊል የተፈጸመው እንዴት ነው? ለ) የዚህ ቃል ኪዳን የተወሰነ ክፍል ገና ወደፊት የምሆነውና ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና በሚመለስበት ጊዜ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

የይሁዳ ከምርኮ መመልስ እርግጠኛ እንደነበር ለማሳየት፥ እግዚአብሔር ኤርምያስን በተወለደበት ምድር መሬት እንዲገዛ ነገረው። ኤርምያስ ሕዝቡ እንደሚማረኩ ቢያውቅም እንኳ ገንዘቡን ለዚህ ዓላማ ማዋሉ፥ ከምርኮ ወደ ይሁዳ ስለ መመለሳቸው በተናገረው ትንቢት ማመኑን የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነበር።

በኤርምያስ 33 ነቢዩ አንድ ተጨማሪ የተስፋ ቃል ይናገራል። ከዳዊት ግንድ ጻድቅ የሆነ ቍጥቋጥ ወይም ጻድቅ ንጉሥ እንደሚነሣና ይህም ንጉሥ ሕዝቡን ሁሉ እንደሚገዛ ይናገራል። ይህ ንጉሥ የይሁዳ ነገድ አንበሳ የሆነውና በእስራኤልና በዓለም ሁሉ ላይ ለመንገሥ እንደገና የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 

3. ለእግዚአብሔር ታማኝ በሆኑና በእግዚአብሔር ላይ ባመፁ መካከል የተደረገ ንጽጽር (ኤርምያስ 34-36) 

ትንቢተ ኤርምያስ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የኖሩ ሰዎችና እግዚአብሔርን ለመከተል ፈቃደኞች ያልሆኑ ሰዎች የተነጻጸሩበት ነው።

እግዚአብሔርን ለመከተል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የመጀመሪያ ምሳሌ ሆኖ የቀረበው የሴዴቅያስና የእስራኤል መሪዎች ምሳሌ ነው። ባቢሎን ከኢየሩሳሌም ጋር በምትዋጋበት ጊዜ ሴዴቅያስ የአይሁድ ባሪያዎች በሙሉ ነፃ መሆናቸውን አወጀ፤ ይህም ተፈጸመ። ይሁን እንጂ ባቢሎናውያን እያፈገፈጉ መሄድ የጀመሩ በሚመስልበት ጊዜ፥ ሕዝቡ የተስፋ ቃላቸውን በሙሉ በማፍረስ ወዲያውኑ ሰዎችን በባርነት መግዛት ጀመሩ። ስለዚህ እግዚአብሔር በመሪዎችና በሀብታሞች ሰዎች እንደሚፈርድባቸውና ሰይፍ፥ መቅሰፍትና ድርቅ እንደሚመጣባቸው ተናገረ።

ከእነዚህ መሪዎች በተቃራኒ የምናገኘው «ሬካባውያን» የሚባሉትን ቡድን ነው። ሬካባውያን ከቄናውያን ጋር የሚዛመዱ ዘላን ነገዶች ነበሩ። ከእነዚህ ነገዶች አንዳንዶቹ የሚኖሩት በእስራኤላውያን አጠገብ ሲሆን፥ ለእነርሱም ወዳጆቻቸው ነበሩ። በዋናነት የሚታወቀው የሬካባውያን ጎሳ ወገን ኢዮናዳብ ነበር (2ኛ ነገሥት 10፡15-31 ተመልከት)። ኢዮናዳብ የአክዓብን የዘር ግንድ ለማጥፋት ከኢዩ ጋር የሠራ ሰው ነበር። ኢዮናዳብ የራሱን የዘር ግንድ ንጹሕ አድርጎ ለመጠበቅ ከነበረው ፍላጎት የተነሣ ቤተሰቦቹ በሙሉ ገበሬዎች እንዳይሆኑ፥ ቤት እንዳይሠሩና ወይን እንዳይጠጡ ከለከለ። ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ እንኳ የእርሱ ዝርያዎች እነዚህን ሕግጋት ይከተሉ ነበር። ኤርምያስ እንኳ ጥቂት ወይን በሰጣቸው ጊዜ ለመጠጣት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። የእነርሱ መታዘዝ ከእግዚአብሔር ጋር በገቡት ቃል ኪዳን ላይ ካመፁት ከመላው ሕዝብ ጋር በተነጻጻሪነት ቀርቧል። ስለዚህ እግዚአብሔር ሬካባውያንን አከበረ፤ ዘራቸው ሁልጊዜ ከምድር እንደማይጠፉም ተናገረ።

ኤርምያስ የጠቀሰው ሦስተኛ ምሳሌ ንጉሥ ኢዮአቄምን ነበር። ያሳደገው አባቱ ጻድቅ ሰው ቢሆንም እንኳ ንጉሥ ኢዮአቄም ክፉ ነበር። ኤርምያስ የመጀመሪያ መጽሐፉን የጻፈው ባሮክ በተባለው ጸሐፊ አማካይነት ነበር። ያ መጽሐፍ ለሕዝቡ በተነበበ ጊዜ፥ ሚክያስ መጽሐፉን ወስዶ በምድሪቱ ላሉት ለሌሎች ባለሥልጣናት አነበበው። ይህ ነገር ንጉሡን እንደሚያስቆጣው ስላሰቡ ኤርምያስና ባሮክ እንዲሸሽጉ ከመከሩ በኋላ እነርሱ መጽሐፉን ለንጉሡ አቀረቡ። ንጉሡም የመጽሐፉ ጥቅልል ከተነበበ በኋላ አቃጠለው። ኤርምያስም እንዲታሠር አዘዘ፤ በመጨረሻ ኤርምያስ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀለለ ሌላ ጥቅልል ጻፈ። በኢዮአቄም ላይ የተናገረው ትንቢት ግን እጅግ ከባድ ነበር። ኢዮአቄም በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ አንድም ዝርያ አንደማይኖረውና አስክሬኑም እንደማይቀበር ተነበየ። ይህ በንጉሡ ላይ የመጣ ከባድ ፍርድ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አብዛኛው ሕዝብ እግዚአብሔርን በማይታዘዝበት ጊዜ እንኳ እግዚአብሔርን ስለ መታዘዝ ከእነዚህ ሦስት ምሳሌዎች ምን እንማራለን? ለ) ከእነዚህ ምዕራፎች የተማርሃቸው ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: