አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ሕይወት በመኖሩ ሌሎች ሰዎች ከሚቀበሉት መከራ ያመልጣል ማለት አይደለም። ይልቁንም ድርቅ ወይም ወረርሽኝ ሲኖር የእግዚአብሔር ሕዝብም ብዙ ጊዜ መከራ ይቀበላሉ፤ ደግሞም ይሞታሉ። ኤርምያስ የእግዚአብሔር ነቢይ ቢሆንም እንኳ የኖረው የእግዚአብሔር ፍርድ በይሁዳ ላይ በተፈጸመ ጊዜ በመሆኑ፥ ሌሎች አይሁድ የተቀበሉትን መከራ ተቀብሏል። የምግብ ዕጥረት ሲከሠት ተርቧል፤ አንዳንድ ዘመዶቹ ሞተውበታል፤ ወዘተ። እግዚአብሔር ሌሎች ሰዎች ይቀበሉት ከነበረው መከራ ኤርምያስን አልከለለውም።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች ለጌታ በሚኖሩበት ጊዜ፥ መከራ ሊቀበሉ የሚችሉባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ካለህ ግንዛቤ፥ ሰዎች መከራ እንዲቀበሉ እግዚአብሔር የሚፈቅደው ለምንድን ነው?
ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ በተደረገው ጦርነት ከሌሉች ጋር ከተቀበለው መከራ ሌላ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ አንዳች ፍርሃት ያውጅ ስለነበር፥ በተጨማሪ ሌላ መከራንም ተቀብሏል።
ክርስቲያኖች መከራ ሊቀበሉ የሚችሉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ከዚህ ቀጥሉ በዝርዝር ቀርበዋል፡
1. በሕይወታችን ውስጥ በሚገኙ ኃጢአቶች ምክንያት እኛን ለመቅጣት (ኢዮብ 4፡7-9፤ 8፡20)።
2. በሥርዓት እንድንኖርና አካሄዳችን እንዲስተካከል ለማድረግ (ዘዳግም 8፡3፤ ምሳሌ 3፡11-12)።
3. ልባችንንና ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅርና መታዘዝ ለመፈተን (ዘዳግም 8፡2፤ ኢዮብ 1፡6-12)፥
4. እንደ ድርቅና ሞት ያለ ሥቃይ የምንቀበለው ደግሞ ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት በኋላ ኃጢአት በሞላበት ዓለም ውስጥ የምንኖር ሥጋ ለባሾች ስለሆንን ነው (ኢዮብ 5፡6-7፤ መዝ. (14)፡1-4)።
5. የእግዚአብሔር ባሕርይና ዕቅድ ከእኛ የተሰወረ በመሆኑ፥ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች መከራ የሚቀበሉት ለምን እንደሆነ አናውቅም (ኢዮብ 11፡7፤ መክብብ 3፡1)፥
6. አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ፈንታ ወይም ስለ ብዙዎች መከራ ልንቀበል እንችላለን (ዘዳግም 4፡21፤ መዝሙር (106)፡23)፥
7. እግዚአብሔርን በመምሰል እንድናድግ ስለሚረዳን (ያዕቆብ 1፡2-4፤ ሮሜ 5፡3)።
8. ስለ ክርስቶስ ስም ብለን ስለምንሰደድ (ማቴ. 5፡11-12)፡
9. ሌሉች መከራ በሚቀበሉበት ወቅት ልናጽናናቸው እንድንችል (ቆሮንቶስ 1፡3-5) ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 37-45 አንብብ። ሀ) ኤርምያስ የእግዚአብሔርን ቃል በመናገሩ ምክንያት የደረሰበትን መከራ ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ለኤርምያስ መከራን ባያስቀርለትም እንኳ በስደት ጊዜ እርሱን የጠበቀባቸውን መንገዶች ዘርዝር።
ኤርምያስ 37-45 በ586 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ከመውደቋ በፊት ከወደቀች በኋላ በኤርምያስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸሙ የተለያዩ ታሪኮች የተመዘገቡበት ክፍል ነው።
1. በኢየሩሳሌም ጦርነት በተካሄደበት ወቅት የተፈጸሙ ክሥተቶች (ኤር. 37-39)።
ኢየሩሳሌም ለበርካታ ወራት በባቢሎናውያን ተከብባ ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ኤርምያስ ከባቢሎናውያን ጋር መዋጋት እንደሌለባቸውና ከዚህ ይልቅ ዕርቅ ቢመሠርቱ እንደሚሻል ሕዝቡን ይመክራቸው ነበር። ጦርነቱ በመካሄድ ላይ እያለ የግብፅ ጦር ከባቢሎናውያን ጋር ለመዋጋት በመገሥገሥ ላይ እንደሆነ ተወራ። ይህም ባቢሎናውያን እነርሱን ትተው ከግብፃውያን ጋር ለመዋጋት እንደሚሄዱና ከጥቃት እንደሚድኑ ለሚያስቡ አይሁድ የልብ ልብ ሰጣቸው። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሴዴቅያስ ስለዚህ ጉዳይ ኤርምያስን በጠየቀው ጊዜ ጥፋት ጨርሶ የማይቀር እንደሆነ ነገረው። የባቢሎን ጦር በሄደ በጥቂት ቀናት ውስጥ ኤርምያስ ከኢየሩሳሌም ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኝ ወደ ትውልድ መንደሩ ሄደ። ኢየሩሳሌምን ለቅቆ በሚሄድበት ወቅት ከባቢሉን ጦር ጋር ለመቀላቀል የሚሄድ የባቢሎን ሰላይ ተደርጎ በውሸት ተከሰሰና ተያዘ፤ ወደ ወኅኒም ተጣለ። በኋላ ሴዴቅያስ በዘበኞች ጠባቂዎች ግቢ ውስጥ እንዲቆይ አደረገው።
ቆይቶ ለባቢሎናውያን እጃቸውን እንዲሰጡ ያቀረበው አሳብ አገርን እንደመካድና በአገር ላይ እንደማመፅ ስለተቆጠረበት፥ ባለሥልጣኖች ኤርምያስ መገደል አለበት ብለው ሰጥሞ እንዲቀር በማለት ጭቃ በሞላበት ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት። ኤርምያስ ከዚህ ጕድጓድ እንዲወጣና በግዞት እንዲቆይ ወደ ዘበኞቹ ጊቢ ተመለሰ። በዚህም ነፍሱ እንድትድን ያደረገው ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነበር። ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ እስክትወድቅ ድረስ በግዞት ስፍራ ቆየ። እግዚአብሔር የኤርምያስን ነፍስ ለማዳን ምክንያት ለሆነው አቤሜሌክ ከባቢሎናውያን ጋር በሚደረግ ጦርነት እንደማይሞት ቃል በመግባት ለፈጸመው ድርጊት ብድራት መለሰለት።
ከተማዋ በባቢሎን እጁ ከወደቀች በኋላ ናቡከደነፆር የኤርምያስን ሕይወት በማትረፍ ወደ ቤቱ ተመልሶ ከራሱ ሕዝቡ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት።
2. ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ የተፈጸሙ ድርጊቶች (ኤርምያስ 40-45)
የኢየሩሳሌም ከተማ ስትወድቅ የባቢሎን ጦር አዛዥ ኤርምያስን በነፃ ለቀቀው። ወደሚከበርበትና ጥሩ ኑሮ ወደሚኖርበት ወደ ባቢሎን ሊወስደው ወይም በይሁዳ ውስጥ በፈለገው ስፍራ ሊኖር ምርጫ ሰጠው። ኤርምያስ በይሁዳ ከቀሩ ድሆች ሰዎች ጋር መኖርን መረጠ። ባቢሎናውያን ጎዶልያ የተባለን ሰው በይሁዳ ለቀሩት አይሁድ መሪ አድርገው ሾሙ። ሆኖም በእስማኤል መሪነት ያመፁ ሰዎች ጎዶልያን ገድለው ሸሹ። ሕዝቡም በዚህ ምክንያት ባቢሎናውያን የሚፈጽሙትን ቅጣት እጅግ ፈሩ። ኤርምያስ በይሁዳ ይቆዩ ዘንድ ሕዝቡን ቢመክራቸውም ብዙዎቹ ሳይሰሙት ቀሩ። ኤርምያስን እንደ እስረኛ ይዘው ወደ ግብፅ ሸሹ። እግዚአብሔር በግብፅ የሚኖሩትን አይሁድ ሁሉ እንደሚቀጣና በግብጽ ሕዝብም ላይ ሽንፈትን እንደሚያመጣ ተናገረ።
ስለ ኤርምያስ የምናውቀው የመጨረሻው ነገር ይህ ነው። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፥ አይሁድ ኤርምያስን በድንጋይ ወግረው እንደገደሉት አፈ-ታሪክ ይናገራል። በመሆኑም ዘመኑን ሁሉ በታማኝነት ያገለገለው ነቢይ ታሪክ በዚሁ አበቃ። የእግዚአብሔርን ቃል በግልጽ በመናገሩ ብዙ መከራ ደረሰበት። ይሁን እንጂ እስከሞት ድረስ የታመነ ሆነ። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ ኤርምያስ ከብሉይ ኪዳን ታላላቅ የእምነት ጀግኖች ውስጥ አንዱ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ከኤርምያስ ሕይወት ስለ መሪነት የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 45 የኤርምያስ ጸሐፊ ለነበረው ለባሮክ የቀረበ አጭር ማበረታቻ ነው። በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት የቀረበ አይደለም። ይህ ምዕራፍ የሚያሳየን ኤርምያስ በስደት ውስጥ እንኳ ሳለ፥ የጸሐፊው የባሮክ ጉዳይ ያሳስበው እንደነበረና ሊያበረታታው እንደፈለገ ነው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)