ኤርምያስ 46-52

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የመንግሥታት መሪዎች በጽድቅና በቅን ፍርድ ይመሩ ዘንድ የሚያበረታታቸውና ሊገነዘቡት የሚገባቸው ነገር ምንድን ነው? ይህ ነገር ብዙ ጊዜ ይሆናልን? ለ) እግዚአብሔር ለሚፈጽሙት ተግባር ሕዝቦችን ተጠያቂ ሲያደርግ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር ሕዝቦችን ሲቆጣጠር ያየኸው እንዴት ነው?

የብዙ መንግሥታት መሪዎች የተሳሳተ ስሜት ወይም እምነት በእግዚአብሔር ተጠያቂ እንደማይሆኑ ማሰባቸው ነው። ስለ ራሳቸው ኃይል ብቻ ያስባሉ። ይህ ኃይላቸው ብዙ ጊዜ ወደ ምግባረ ብልሹነት፥ ኢፍትሐዊነት የሆነ ውሳኔ ወደ መስጠትና በእግዚአብሔር ላይ በግልጽ ወደ ማመፅ ይመራቸዋል። ዓለማዊ መሪዎች የእግዚአብሔርን ሥራ ለመከልከል፥ አንዳንድ ጊዜም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ይፈልጋሉ። ነገር ግን ተጠያቂነት የለባቸውምን? እግዚአብሔር እነርሱንና ሕዝባቸውን በሞላ ተጠያቂ ያደርጋቸዋልን?

እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥ፥ እንዲሁም የአሕዛብና የመንግሥታት ሁሉ ተቈጣጣሪ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። እነርሱ ቢገነዘቡትም ባይገነዘቡትም እግዚአብሔር ሕዝቦችንና መንግሥታትን ሁሉ ይቈጣጠራል። ሳያውቁት ፈቃዱን የሚፈጽሙ አገልጋዮቹ ናቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር በእነርሱም ላይ ይፈርዳል። ስለዚህ መንግሥታት፥ ሕዝቦችና ነገሥታት ከፍርዱ ለማምለጥ ለሰዎች ሁሉ ቅን ፍርድ ማድረጋቸው ብልህነት ነው።

በኤርምያስ ዘመን የባቢሎን ሕዝብ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነበሩ። ከመንገድ የወጡትን ሕዝቦች ለመቅጣት እግዚአብሔር ተጠቅሞባቸዋል። ዳሩ ግን እግዚአብሔር በእነርሱም ላይ ፈረደባቸውና አጠፋቸው። ሌሎች ሕዝቦች፥ እንደ ነጣቂዎች ያሉት፥ የይሁዳን ሕዝብ ለመበዝበዝ በኢየሩሳሌም ውድቀት ተጠቀሙ። ለጊዜው ጥቅም ስለ ማግኘታቸው ብቻ እንጂ እንደሚፈረድባቸው አላሰቡም። ኤርምያስ ግን በብዙ አሕዛብ ላይ ስለሚሆነው የእግዚአብሔር ፍርድ ተነበየ።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 46-52 አንብብ። ሀ) ኤርምያስ የተነበየባቸውን አሕዛብ ዘርዝር። ለ) በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥ የተጠቀሱትን አገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። እነዚህ የጥንት አገሮች በዚህ ዘመን እነማን ናቸው ወይም የየትኛው መንግሥት አካል ናቸው? ሐ) ስለ እነዚህ አሕዛብ ኤርምያስ የተናገራቸውን ዋና ዋና ትንቢቶች ዘርዝር። መ) ከባቢሎን ውድቀት በኋላ በኤርምያስ ላይ የደረሰውን አሳጥረህ ግለጽ።

1. ኤርምያስ በአሕዛብ ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ኤር. 46-51)

የትንቢተ ኤርምያስ የመጨረሻ ክፍል በይሁዳ ዙሪያ ስለነበሩት ስለ አብዛኛዎቹ አሕዛብ የተነገረ ነው። እነዚህ የአሕዛብ መንግሥታት ከጥንት ጀምሮ የነበሩ የአይሁዳውያን ታሪካዊ ጠላቶች ሲሆኑ ብዙ ጊዜ ይሁዳን ወይም እስራኤልን ከሚወርር ጠላት ጋር በመተባበር ጥቃት የሚያደርሱ ነበሩ። ብዙዎቹም በ586 ዓ.ዓ. በተፈጸመው የኢየሩሳሌም መደምሰስ ተሳትፈዋል።

ሀ. ግብፅ (ኤር. 46)

ግብፅ የአይሁድ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጠላት ነበረች። አይሁድን ለ400 ዓመታት በባርነት የገዛችው ግብፅ ነበረች። በአይሁድ ሕዝብ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሁሉ ዓለምን ይገዛ የነበረው ኃያል መንግሥት የግብፅ መንግሥት ነበር። ስለሆነም አይሁድን በሥልጣናቸው ሥር አድርገው ገዙአቸው። ኃይላቸው በሚደክምበትና የአሦርና የባቢሎን መንግሥታት በሚበረቱበት ጊዜ ግብፅ ይሁዳን እንደምትረዳት ተስፋ በመስጠትና በማግባባት በአሦርና በባቢሎን ላይ እንድታምፅ ትመክራት ነበር። የይሁዳ ነገሥታትም የግብፅን ምክር በመስማት ያምፁ ነበር። ይህም በይሁዳ ላይ የአሦርን ወይም የባቢሎንን ጥቃት ይጋብዝባት ነበር። በዚህ ጊዜ ግብፅ ቃሏን በማጠፍ፥ ይሁዳን ታጋፍጣት ነበር። ግብፅ እንደገና የዓለም ኃያል መንግሥት ለመሆን ብትሻም፥ በባቢሎን ቊጥጥር ሥር እንደምትሆን ኤርምያስ ተነበየ። የግብፅ የክብር ዘመን አልፎአልና ናቡከደነፆር ግብፅን ወርሮ ይይዛል።

ለ. ፍልስጥኤም (ኤር. 47) [በዘመናችን ይህ ስፍራ በእስራኤል ውስጥ የሚገኘው የጋዛ ሰርጥ ነው]

የአይሁድ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጠላት የነበረው ሌላው የፍልስጥኤም ሕዝብ ነበር። እንደሚታወሰው በሶምሶን፥ በዔሊ፥ በሳኦልና በዳዊት ዘመን ፍልስጥኤማውያን ያለማቋረጥ ከአይሁድ ጋር ይዋጉ ነበር። ቆይተው ለአይሁድ ቢገዙም፥ ባመቻቸውና ዕድል ባገኙ ጊዜ ሁሉ እያመፁ አይሁድን ለመውጋት ከሌሎች ኃይላት ጋር ይተባበሩ ነበር። ፍልስጤማውያን በይሁዳ ላይ የደረሰውን ጥፋት ግዛታቸውን ለማስፋፋት ተጠቅመውበት ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ እንደሚፈርድና በፍልስጥኤም ላይ ከፍተኛ ጥፋት እንደሚያመጣ ተናገረ። ይህንንም ለመፈም ግብጻውያንን፥ ባቢሎናውያንና ሌሎች መንግሥታትን ተጠቅሟል።

ሐ. ሞዓብ (ኤር. 48) [በአሁኑ ጊዜ ይህች አገር ዮርዳኖስ ናት]

ይሁዳን ከሙት ባሕር በስተምሥራቅ የምታዋስናት ሌላዋ አገር ሞዓብ ነበረች። በመጀመሪያ፥ ይህ ክልል የሮቤል ነገድ ክልል ነበር። ብዙ ጊዜ ለይሁዳ የተገዛች ብትሆንም ዕድል ባገኘች ቍጥር ይሁዳን ከሚያጠቁ ኃይላት ጋር ትተባበር ነበር። ይሁዳ በባቢሎን እጅ በወደቀች ጊዜ ሞዓባውያን ይህን እንዳደረጉ ጥርጥር የለውም። እግዚአብሔር ግን ይህን ክፋታቸውን ስላሰበ ኢየሩሳሌም ከወደቀች በኋላ ብዙም ሳይቆይ፥ የባቢሎን መንግሥት መጣና የሞዓብን መንግሥት አጠፋ።

መ. አሞን (ኤር. 49፡1-6) [የአሁኖቹ ዮርዳኖስና ሶርያ]

የአሞን ሕዝብ የሰፈረው ከሞአባውያን በስተ ሰሜን የጋድ ነገድ ክልል በነበረው ስፍራ ነበር። ይህም ሕዝብ ብዙ ጊዜ ለአይሁድ የተገዛ ቢሆንም፥ ዕድሉን ባገኘ ጊዜ ሁሉ ግን ከማመፅ እንዲሁም ይሁዳንና እስራኤልን ለመውጋት ከሚነሡ ሕዝቦች ጋር ከመተባበር ወደኋላ አይልም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ሽንፈትን እንደሚያመጣ ተናገረ። ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌም ከወደቀች ከብዙ ዓመታት በኋላ በአሞን ላይ ወረራ አካሄደ።

ሠ. ኤዶምያስ (ኤር. 49፡7-22) [በዛሬዋ ግብፅ ያለው የሲና ወሽመጥ ያለበት ስፍራ ነው]

ኤዶምያስ ከሞዓብ በስተደቡብ ትገኝ ነበር። ይህች አገር የዔሳው ዝርያዎች የሚኖሩባት ምድር ስትሆን፥ እነርሱም የአይሁድ ሕዝብ ክፉ ጠላቶች ነበሩ። በማከታተል የአይሁድን ሕዝብ እንደ እሾህ ያለማቋረጥ ይወጉ ነበር። በገደላማ ስፍራዎች ይኖሩ ስለነበር ማንም ሊያጠቃን አይችልም ብለው ያስቡ ነበር። እግዚአብሔር ግን ኤዶምያስን እንደሚደመስስ ተናገረ። በመጀመሪያ ናቡከደነፆር፥ በኋላ ደግሞ ዐረቦች ኤዶምያስን ደመሰሱ።

ረ. ሶሪያ (ኤር. 49፡23-27) [የአሁኗ ደማስቆ]

በዋና ከተማዋ ስም በደማስቆ የምትጠራው ሶርያ የአይሁድ ሕዝብ ጠላት ነበረች። በኤልያስ ጊዜ ከእስራኤል ጋር እንዴት እንደተዋጉና አንድ ጊዜ ደግሞ በንጉሥ አካዝ አማካይነት ከእስራኤል ጋር በመተባበር ይሁዳን እንደወጉ የሚታወስ ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚቀጣና የደማስቆ ከተማ እንደምትደመሰስ ተናገረ። ይህ በታሪክ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተፈጽሟል።

ሰ. ዐረቢያ (ኤር. 49፡28-33)

ኤርምያስ በዚህ ስፍራ የጠቀሰው ዛሬ ሳውዲ ዐረቢያ ተብላ በምትጠራው አገር ይኖሩ የነበሩትን ሁለት ሕዝቦች ነው። እነርሱም ቄዳርና አሶር ነበሩ። ስለ እነዚህ ሁለት ሕዝቦች የምናውቀው ብዙ ነገር ባይኖርም፥ ብዙ ጊዜ ይሁዳን ይወጉ የነበሩ በርካታ ትንንሽ ሕዝቦች በዐረቢያ ይኖሩ እንደነበር እናውቃለን። እነርሱም ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ አልቻሉም። እግዚአብሔር እነርሱን ለመቅጣት ናቡከደነፆርን ተጠቅሞበታል።

ሸ. ኤላም (ኤር. 49፡34-39) [የአሁኗ ኢራን ናት]

የኤላም ሕዝብ ከይሁዳ እጅግ ርቆ የሚገኝ ሕዝብ ነበር። ከኤፍራጥስ ወንዝ ሰሜናዊ ምሥራቅ፥ ከባቢሎን በስተምሥራቅ የምትገኝ ምድር ነበረች። የኤላም አገር በኋላ የታላቁ የሜዶንና ፋርስ መንግሥት አካል ሆና ነበር። የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ባቢሎንን በመደምሰስ ዓለምን ለብዙ መቶ ዓመታት ገዝቷል። የኤላም ሕዝቦች ከባቢሎን ጋር በመተባበር ይሁዳን ሳይወጉ አልቀሩም። ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱም ላይ ጥፋትን እንደሚያመጣ ተናገረ። 

ቀ. ባቢሎን (ኤር. 51፡1-51፡64) [የአሁኗ ኢራቅ ናት]

ኤርምያስ ከባድ የፍርድ ቃሉቹን እስከመጨረሻው ድረስ አዘግይቶ ነበር። በአሕዛብ ላይ ስለሚመጡ ፍርዶች በተናገራቸው እጅግ ረጃጅም በሆኑ ትንቢቶቹ ኤርምያስ ስለ ባቢሎን መደምሰስ ተናግሮ ነበር። ይህ ትንቢት በሚነገርበት ጊዜ ባቢሎን በኋያልነቷ ከመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰችና የማትጠፋ ትመስል ነበር። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ታላቅ በመሆኑ ስለ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ መውደም አስቀድሞ ተናገረ። የባቢሎን መንግሥት ከ70 ዓመታት ብዙም አልዘለለም። ከዚያም የሜዶንና ፋርስ መንግሥት አሸንፎ አጠፋት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ቃል ስላለው ኃይል ከእነዚህ ምዕራፎች ምን እንማራለን? ለ) እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ የሚቆጣጠር ስለ መሆኑ ምን እንማራለን? ሐ) እነዚህ ምዕራፎች ዛሬስ የሚያበረታቱን እንዴት ነው?

2. ስለ ኢየሩሳሌም ውድቀት የተሰጠ መግለጫ (ኤር. 52)

የትንቢተ ኤርምያስ የመጨረሻ ምዕራፍ የኢየሩሳሌም ከተማ የነበረችበትን የመጨረሻ ጥቂት ቀናት ሁኔታ የሚገልጽ ታሪካዊ ክፍል ነው። ኢየሩሳሌምን ለመያዝ ስለተደረገው ከበባ፥ ስለ ኢየሩሳሌም ውድቀት፥ ስለ ከተማይቱ መበዝበዝ፥ ስለ አብዛኞቹ የኢየሩሳሌም መሪዎች መሞት፥ እንዲሁም ስለ ይሁዳ ሕዝብ መማረክ ይገልጻል። ይሁን እንጂ መጽሐፉ ስለ ተስፋ በሚናገር አንድ ማስታወሻ ይጠቃለላል። ከብዙ ዓመታት በፊት ተማርኮ ወደ ባቢሎን ተወስዶ የነበረው ንጉሥ ዮአኪን ከወኅኒ ቤት ተለቀቀ። በምርኮ ምድር እንኳ እግዚአብሔር እየሠራና ሕዝቡን እየባረከ ነበር።

ይህ የመጨረሻ ምዕራፍ የሚያሳየው ከ40 ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ኤርምያስ ሲናገራቸው የነበሩ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ነው። ኤርምያስ እውነተኛው የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነና የቀሩት ሐሰተኞች ነቢያት በሙሉ የተሳሳቱ መሆናቸው በግልጽ ታወቀ። እግዚአብሔር፥ ኤርምያስ ብቸኛ ሆኖ መልእክቱን በማስተላለፍ ያገለገለባቸውን ዓመታት እውነተኛነት በማስረጃ አረጋገጠ። በወቅቱ የእግዚአብሔር መልእክት በሕዝቡ ዘንድ የተወደደ ባይሆንም፥ ኤርምያስ ግን በታማኝነት አስተላለፈው። እግዚአብሔርም የኤርምያስን ትንቢት መፈጸም ለአይሁድ ተስፋን ለማምጣት ተጠቀመበት። አይሁድ ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም ውድቀት የተነበየው ትንቢት አንዳችም ስሕተት የሌለበት ፍጹም እውነት እንደነበረ ስላዩ ከ70 ዓመታት የምርኮ ቆይታ በኋላ ወደገዛ ምድራቸው እንደሚመለሱ የተነበየው ትንቢት በትክክል እንደሚፈጸም ያውቁ ነበር። ዳንኤል ትንቢተ ኤርምያስን በሚያነብበት ጊዜ በዚህ ክፍል የተጻፈውን ተስፋ በመቀበል በሕይወት ዘመኑ መጨረሻ ገደማ አይሁድ የሚመለሱበት ጊዜ መቃረቡን አወቀ (ዳንኤል 9)።

የእግዚአብሔር ቃል ዘወትር እውነት ነው። የተነገረው ነገር ሁሉ ይፈጸማል። ሰዎች ላይቀበሉት፥ ሊያፌዙበት ወይም ላያምኑት ይችላሉ። አንድ ቀን ግን እውነትነቱ በግልጽ ይታወቃል። ገና ሊፈጸሙ ያሉ በርካታ ትንቢቶች አሉ። እግዚአብሔር ከዚህ ቀደም የተናገራቸውን ቃላት ያለ አንዳች ስሕተት መፈጸሙ፥ ገና ያልተፈጸሙ ትንቢቶችም እንደሚፈጸሙ ያረጋግጥልናል። እግዚአብሔር በቃሉ በሰጠን ተስፋ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ይመለሳል። ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወስደናል። ሰይጣንና ሞትን ጨምሮ ጠላቶቹን ሁሉ ይደመስሳል። ቃሉ የሚፈጸም ስለሆነ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንደሚቈጣጠር በፍጹም አትጠራጠር።

ገና ባልተፈጸሙት የእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት መሠረት በታማኝነት ጸንተህ ለመኖር እግዚአብሔር ይርዳህ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ኤርምያስ ልንማር የምንችላቸውን ዋና ዋና ትምህርቶች ዘርዝር።ለ) የቤተ ክርስቲያንህ ሰዎች የትንቢተ ኤርምያስ የሚያስተምረውን ትምህርት ተረድተው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ እንዴት ለማስተማር እንደምትችል ዕቅድ አውጣ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading