የሰቆቃወ ኤርምያስ ዓላማ እና ዓበይት እውነቶች

በእውነት ላይ ተመሥርቶ በትረካ መልክ የሚቀርብ ጽሑፍ የሚናገረው ለአእምሮ ሲሆን፥ ግጥም ግን ለልብ ይናገራል የሚል ፈሊጥ አለ። 2ኛ ነገሥት፥ 2ኛ ዘናና የትንቢተ ኤርምያስ በእውነት ላይ ተመሥርተው የኢየሩሳሌምን ውድቀት ገልጸዋል። ነገር ግን ይህ በወቅቱ በአይሁድ ላይ የነበረውን ጥልቅ የኃዘን ስሜት አይገልጽም። የደረሰባቸውን ጉዳት በሚገባ ለመግለጽ ሰቆቃወ ኤርምያስ በግጥም መልክ ተጻፈ።

የሰቆቃወ ኤርምያስ የተጻፈባቸው ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ፡-

1. የሰቆቃው ኤርምያስ የተጻፈው የዳዊት ከተማና ቤተ መቅደሱ የነበረበት የጽዮን ተራራ በመደምሰሱ፥ የተመረጡት የእግዚአብሔር ሕዝብም ተሸንፈው በመማረካቸው ምክንያት የነበረውን ጥልቅ ኃዘን ለመግለጥ ነበር። ይህ መጽሐፍ ብዙ ሕዝብ መሞታቸውን፥ ወላጅ እናቶች እንኳ ልጆቻቸውን እስኪበሉ ድረስ ራብ መጽናቱን፥ የሕዝቡን ወደ ምርኮ መወሰድና የቤተ መቅደስ አምልኮ መቅረቱን ይገልጣል። ይህ መጽሐፍ ከዚህ ቀደም ስለሆነው ነገር ለአይሁድ የሚያስታውስ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ለእርሱ በማይታዘዙበት ጊዜ ምን እንደሚደርስባቸው ያለማቋረጥ የሚያስታውሰን መጽሐፍ ነው።

(ማስታወሻ፡. ጽዮን የሚለው ቃል የተገኘው ቤተ መቅደሱ ከተሠራበት ተራራ ነው። ቆይቶ ይህ ቃል የኢየሩሳሌም ሌላው ስሟ ሆኗል)። 

2. ሰቆቃወ ኤርምያስ የተጻፈበት ሌላው ምክንያት በዘዳግም 28 በሙሴ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች በሙሉ በኢየሩሳሌም ውድቀት መፈጸማቸውን ለማሳየት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሰቆቃወ ኤርምያስ ከተጻፈባቸው ከእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ምን መንፈሳዊ ትምህርቶችን መማር እንችላለን?

በሰቆቃወ ኤርምያስ ውስጥ የሚታዩ ዐበይት እውነቶች

ሰቆቃወ ኤርምያስ በኃዘንና በታላቅ ሥቃይ የተሞላ ጠንከር ያለ መጽሐፍ ነው። ነገር ግን ክርስቲያኖች ሊረዱት የሚገባ ጠቃሚ መጽሐፍ ነው። ከዚህ ቀጥሎ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን ዐበይት እውነቶችን እንመለከታለን፡-

1. ኃጢአት የሚያስከትላቸው ውጤቶች አሉት። ኃጢአት የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጣብናል። ፍርዱ በፍጥነት ላይፈጸም ይችላል። እግዚአብሔር አይሁድ ንስሐ ይገቡ ዘንድ ለብዙ መቶ ዓመታት በትዕግሥት ጠብቆአል። በመጨረሻ ግን እጅግ አስከፊ የሆነውን የኃጢአታቸውን ቅጣት አመጣባቸው (ሰቆ. ኤር. 1፡5፥ 8-9፤ 4፡13)። ባቢሎናውያን የእግዚአብሔር ፍርድ መሣሪያዎች ነበሩ (ሰቆ. ኤር. 1፡12-15፤ 2፡1-8)። ኃጢአት ወደ ሕይወታችን በሚያመጣው ኃዘን ማልቀስ የሚገባን ቢሆንም፥ ዋናው ነገር ንስሐ መግባታችንና ይቀበለን ዘንድ ሁልጊዜ ዝግጁ ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር መመለሳችን ነው (ሰቆ. ኤር. 1፡1-2፤ 3፡40-42፤ 5፡21-22)። 

2. በመቀጣት ላይ ያለን ብንሆንም እንኳ የእግዚአብሔር ፍቅርና ርኅራኄ አያልቅም። ቅጣት እግዚአብሔር የራሱ የሆነውን ሕዝብ ወደራሱ ለመመለስ ያለውን ፍቅርና ፍላጎት የሚያመለክት እንጂ እግዚአብሔር እንደተወን የሚያሳይ ምልክት አይደለም (ሰቆ. ኤር. 3፡21-25)። 

3. እግዚአብሔር ሁልጊዜ ቃሉን ይፈጽማል። ለ200 ዓመታት እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት ስለሚመጣው ጥፋት አስጠንቅቆ ነበር። በዚያን ጊዜ ይህ ቃሉ የሚፈጸም አይመስልም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን እግዚአብሔር እንደተናገረው የኢየሩሳሌም ከተማ ወደቀች፤ ሕዝቡም ተማረከ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሰቆቃወ ኤርምያስ 1-5 አንብብ። ሀ) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከምናያቸው የጸሐፊው ስሜቶች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ። እነዚህ ስሜቶች እንዴት ተሰምተውሃል? ለ) ኢየሩሳሌም በወደቀች ጊዜ ከተፈጸሙት ክፉ ድርጊቶች አንዳንዶቹን ግለጽ። ሐ) ይህ መጽሐፍ ስለ ኃጢአት የሚያስተምረው ምንድን ነው? መ) ይህ መጽሐፍ ስለ እግዚአብሔር ምን ያስተምረናል? ሀ) ንስሐ ገብተን በምንመለስበት ጊዜ ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ይቅርታ ይህ መጽሐፍ ምን ያስተምረናል? ረ) ይህን መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ሰዎችን ለማስተማር የምትችልበትን መንገድ አቅድ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: