ሕዝቅኤል 18-24

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 18፡2 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን ይጠቅሱት የነበሩት ምሳሌያዊ አነጋገር ምንድን ነው? ለ) የዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ትርጉም ምን ይመስልሃል? ሐ) ይህ ምሳሌ በከፊል እውነት የሚሆነው መቼ ነው? መ) ይህ ምሳሌ ውሸት የሚሆነው መቼ ነው?

ኤርምያስና ሕዝቅኤል በነበሩበት ዘመን ምሳሌያዊ አነጋገሮች በእስራኤል አገር የተለመዱ ነበሩ። ከምሳሌያዊ አነጋገሮች አንዱ፡«አባቶች ጮርቃ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ» የሚል ነበር። የዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ትርጕም፥ ልጆች የወላጆቻቸውን ክፉ ድርጊት ውጤት ያጭዳሉ ማለት ነው። ይህ አነጋገር ብዙ ጊዜ እውነት ነው (ዘጸአት 20፡5 ተመልከት)። ለምሳሌ አንዲት ሴት በሴሰኝነቷ ምክንያት የኤድስ በሽታ ቢይዛትና ብታረግዝ፥ የኃጢአትዋ ውጤት የሆነውን የኤድስ በሽታ ምንም ወደማያውቀው ሕፃን ልጇ ታስተላልፋለች። ወይም ሱስ የሚያሲዙ ዕፆችን የሚወዱ ወላጆች ልጆቻቸው አካለ ስንኩላን ሆነው እንዲወለዱ ምክንያት ይሆናሉ። ከእዚህ ሁለት ምሳሌዎች እንደተረዳነው፥ የወላጆች ኃጢአት ምንም በማያውቁና በኃጢአታቸው ባልተባበሩ ልጆቻቸው ላይ ክፉ ውጤቶችን ያመጣል።

አይሁድ ግን ምሳሌያዊ አነጋገሩን የተጠቀሙበት በዚህ መንገድ አልነበረም። በእግዚአብሔር ፊት ንጹሐን ብንሆንም እንኳ አሁን የተለያዩ መከራዎችን የምንቀበለውና በባቢሎናውያን ወረራና ብዝበዛ እንድንቀጣ የተፈረደብን ወላጆቻችን በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ነው የሚል ነበር። ዕጣ-ፈንታቸውም የራሳቸው ምርጫና ድርጊት ውጤት ሳይሆን፥ የወላጆቻቸው ምርጫ እንደነበር በመናገር ራሳቸውን ነፃ የማውጣት ሙከራ ያደርጉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም ቢሆን የተለያዩ ሰዎች የዚህ ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት የሚያደርጉትና ክርስቲያን ወላጆች ያሏቸው ልጆች ሳይቀሩ እንኳ እንዲህ የሚያስቡት እንዴት ነው? ላ) ይህ አስተሳሰብ ስሕተት የሆነው ለምንድን ነው?

ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ያላቸውን ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለመከላከል፥ እግዚአብሔር የሦስት ትውልድ ሕዝቦች ምን እንደደረሰባቸው በምዕራፍ 18 ለሕዝቅኤል ይገልጥለታል። በመጀመሪያው ትውልድ፥ ሰውዩው እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፥ በእግዚአብሔር ያምን ነበር፤ እግዚአብሔርን ያመልክና ይታዘዝ ነበር። ይህ የሚያረጋግጠው ሰውዬው በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት እውነተኛ መሆኑንና ሰውየውም ጻድቅ ስለነበር እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠው ነው። በሁለተኛው ትውልድ፥ የጻድቁ ሰውዩ ልጅ ግን እንደ አባቱ አልነበረም። ይልቁንም ክፉና ኃጢአተኛ ነበር። በግሉ እግዚአብሔርን አላመነም ነበር። ለእግዚአብሔር የሚታዘዝ ሕይወትም አልነበረውም። ስለዚህ ምንም እንኳ አባቱ ጻድቅ ቢሆንም፥ ክፉው ልጅ በራሱ ምርጫዎች ባደረጋቸው ነገሮች ምክንያት ጻድቅ አልነበረም። እግዚአብሔርም በመንፈሳዊ ሞት ይቀጣዋል። «ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።» በሦስተኛው ትውልድ፥ የክፉው ሰውዩ ልጅ አባቱ የሚያደርገውን ክፋት አየ። ነገር ግን የአባቱን ፈለግ አልተከተለም። ይልቁንም አያቱ እንዳደረገው በእግዚአብሔር አመነ። ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ሕይወት መኖሩን ቀጠለ። ስለዚህ እግዚአብሔር በአባቱ ኃጢአት ምክንያት አይቀጣውም፤ ስለ እምነቱና ስለ ታዛዥነቱ የዘላለምን ሕይወት ይሰጠዋል።

ክፉ የሆንና ከኃጢአቱ ንስሐ የገባው ሰውስ ምን ይሆናል? እግዚአብሔር ኃጢአተኛ በኃጢአቱ እንዲሞት ይፈቅዳልን? አይፈቅድም! የእግዚአብሔር ፍላጎት ሰው ሁሉ በሕይወት እንዲኖር ነው። ስለዚህ አንድ ክፉ ሰው ስለ እግዚአብሔር የነበረውን አስተሳሰብ ቢለውጥና ቢያምን፥ በመታዘዝም የእምነቱን እውነተኛነት ቢያረጋግጥ እግዚአብሔር ያንን ሰው ይቅር ይለዋል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይሰጠዋል።

እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሊያስጠነቅቅ የፈለገው፡- ችግር የደረሰባቸው በወላጆቻቸው ኃጢአት ሳይሆን በራሳቸው ኃጢአት ምክንያት መሆኑን ነው። ስለዚህ ንስሐ መግባት ነበረባቸው። ንስሐ ቢገቡ እግዚአብሔር ይፈውሳቸው፥ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይሰጣቸው ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምን ይነግረናል? ለ) ከሁሉ የላቀ ኃጢአተኛ የሆነውን ሰው እንኳ እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለው በመተማመን እንድንመሰክር ይህ እንዴት ያበረታታናል? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 18-24 አንብብ። ሀ) የሕዝቅኤል 18 ዐቢይ ትምህርት ምንድን ነው? ለ) በምዕራፍ 20 እንደተገለጠው፥ የእስራኤልን ሕዝብ የዓመፃ ታሪክ በተከታታይ አሳይ። ሐ) ስለ እስራኤል የወደፊት ሁኔታ የተሰጠው ተስፋ ምንድን ነው? መ) ሁለቱ አመንዝራ እኅትማማች እነማን ናቸው? የሚያመለክቱትስ ምንድን ነው? ሠ) እግዚአብሔር ስለ ሚስቱ ለሕዝቅኤል የሰጠው ትእዛዝ ምን ነበር?

ይህ የትንቢተ ሕዝቅኤል ክፍል ሕዝቅኤል በምርኮ ለነበሩ አይሁድ የተነበያቸውን በርካታ ትንቢቶች ይዟል። 

1. እግዚአብሔር ጥፋት የሌለባቸውን ሰዎች አይቀጣም፤ ነገር ግን ጻድቃንን ይባርካቸዋል፤ ክፉዎችንም ይቀጣል (ሕዝቅኤል 18)። 

2. ስለ እስራኤል መሪዎች የቀረበ ሙሾ (ሕዝቅኤል 19)

ሕዝቅኤል የአንበሳዪቱንና የደቦልዋን ሥዕላዊ መግለጫ በመጠቀም የእስራኤልን መሪዎች ውድቀት ያብራራል። አንበሳም የነገሥታት እናት የሆነችው የይሁዳ ወይም የኢየሩሳሌም ምሳሌያዊ ምልክት ሳይሆን አይቀርም። የመጀመሪያው ደቦል ወደ ግብፅ በምርኮ የተወሰደው ኢዮአካዝ ነው። ሁለተኛው ደቦል ደግሞ ከሕዝቅኤል ጋር ወደ ባቢሎን በምርኮ የተወሰደው ኢዮአኪን ወይም ኢየሩሳሌም በተደመሰሰች ጊዜ ወደ ባቢሎን የተወሰደው ሴዴቅያስ ነው። 

3. የዓመፀኛይቱ እስራኤል ታሪክ (ሕዝቅኤል 20)

በምርኮ ይኖሩ የነበሩ የአይሁድ መሪዎች የሆኑ ሽማግሌዎች እግዚአብሔር ለእነርሱ መልእክት ይኖረው እንደሆነ ለመጠየቅ ወደ ሕዝቅኤል በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ክፋት የሚገልጽ የታሪክ ትምህርት ሰጣቸው። እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከግብፅ ነፃ ካወጣቸው ቀን ጀምሮ እስከ ሕዝቅኤል ዘመን ድረስ በተደጋጋሚ ቢያምፁበትም የፍርድ እጆቹን ከመዘርጋት ለረጅም ጊዜ ተቆጥቦ ቆይቷል። ይህንን ያደረገው ስሙ ወይም ክብሩ በአሕዛብ ዘንድ እንዳይጐድፍ ነበር (ሕዝቅኤል 20፡9፡ 14፥ 22)። አሁን ግን የእግዚአብሔር ቍጣና ፍርድ የሚገለጥበት፥ ኢየሩሳሌም የምትደመሰሰበትና ሕዝቡ የሚበተኑበት ጊዜ እንደደረሰ ተረጋገጦ ነበር። ይሁን እንጂ ፍርድ የሚያገለግለው አይሁድን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ሳይሆን፥ አንድ ቀን የእስራኤል ሕዝብ ዓመፅ እንዲያበቃና እስራኤላውያን ከየተበተኑባቸው አገሮች ተሰብስበው እግዚአብሔርን በኢየሩሳሌም እንዲያገለግሉት ለማጥራት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር «… ስለ ስሜ ስል በሠራሁላችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ» ሲል ምን ማለቱ ነው? ለ) እግዚአብሔር ዛሬ «ስለ ስሙ» ብሎ የሚያደርገው ነገር ምን አለ?

4. ባቢሎን የእግዚአብሔር የፍርድ ሰይፍ ነበረች (ሕዝቅኤል 21)

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 22፡30 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ከይሁዳ ያጣውና በዚህም ምክንያት ፍርድ ያመጣበት ነገር ምን ነበር? ለ) ይህ እውነት ዛሬም ለቤተ ክርስቲያን ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው?

5. የኢየሩሳሌም ኃጢአቶች ባጭሩ (ሕዝቅኤል 22) 

6. የሁለቱ አመንዝራ እኅትማማች ምሳሌ (ሕዝቅኤል 23)

እግዚአብሔር የእስራኤልን ኃጢአት ግልጽ በሆነ መንገድ ለማወዳደር እስራኤልንና ይሁዳን በሁለት አመንዝራ እኅትማማች ምሳሌነት ያወዳድራል። እነዚህ ሁለት እኅትማማች ከልዩ ልዩ አሕዛብ ጋር በመተባበራቸውና ሐሰተኞች አማልክትን በማምለካቸው አመንዝራዎች ነበሩ። ይህ ምዕራፍ በምንዝርና ላይ ያተኮረው እስራኤል ከልዩ ልዩ አሕዛብ ጋር በነበራት ስምምነት ምክንያት ነው።

የመጀመሪያዪቱ አመንዝራ እኅት ኦሖላ ስትባል ትርጒሙም «ድንኳኔ» ማለት ነው። ይህ የሚወክለው ሰማርያን ወይም እስራኤል ተብለው የሚጠሩት አሥሩን የሰሜን ነገዶች ነው። ሁለተኛዋ ደግሞ እሖሊባ ስትባል ትርጒሙ «ድንኳኔ በእርሷ ዘንድ ነው» የሚል ነው። ይህም ኢየሩሳሌምን ወይም የደቡቡን የይሁዳ መንግሥት ይወክላል። ሰማርያ በእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ ከአሦር ጋር ስምምነት በማድረጓ ተገቢ ያልሆነ ነገር በእርሷ ላይ በመፈጸም ወደ ምርኮ ይወስዷት ዘንድ እግዚአብሔር ለአሦራውያን አሳልፎ ሰጣት። ኢየሩሳሌም በሰማርያ ላይ ከደረሰው ነገር መማር ሲገባት ከእርስዋ የበለጠ ክፉና ኃጢአተኛ ሆነች። ከባቢሎናውያን ወይም ከከለዳውያን ጋር ስምምነት አደረገች፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንደሚከዷት፥ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደሚፈጽሙባትና ወደ ምርኮ እንደሚወስዷት ተናገረ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሕዝቡ ከአሕዛብ መንግሥታት ጋር ስምምነት እንዲያደርጉ የማይፈልገው ለምን ይመስልሃል? ለ) ሥጋዊ ምንዝርና ከመንፈሳዊ ምንዝርና ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) ዛሬ ክርስቲያን መንፈሳዊ ምንዝርናን ሊፈጽም የሚችለው እንዴት ነው?

7. የማብሰያ ድስት ምሳሌ (ሕዝቅኤል 24፡1-14)

በዚህ ምሳሌ፥ በእሳት ላይ የተጣደው ድስት የኢየሩሳሌም ምሳሌ ሲሆን፥ ሥጋው ወደ ባቢሎን ምርኮ ገና ያልተወሰዱት አይሁድ ናቸው። እሳቱ ደግሞ ባቢሎንን ይወክላል። ሕዝቅኤል ይህንን መልእክት የጻፈው ኢየሩሳሌም በመጨረሻ የምትወረርበት ጊዜ ሊጀምር በተቃረበበት በ588 ዓ.ዓ. ነበር። 

8. የሕዝቅኤል ሚስት መሞት ምልክት (ሕዝቅኤል 24፡15-27)

እግዚአብሔር የሕዝቅኤልን ሚስት ሞት ሳይቀር ሊመጣ ስላለው ኃዘንና ስለ ኢየሩሳሌም ሕዝብ ሞት ለምርኮኞቹ እንደ ምልክት ተጠቅሞበታል። ሚስቱ እንደምትሞት በመንገር ሕዝቅኤልን አስጠነቀቀው። እርሷም በሚቀጥለው ቀን ሞተች። ሕዝቅኤል ማንኛውም ሰው የሚወደው ሰው በሚሞትበት ጊዜ የሚያሳየውን ኃዘን እንዲያዝን አልፈቀደለትም ነበር። ጮኾ እንዲያለቅስ፥ መጐናጸፊያውን እንዲያወልቅ፥ በራሱ ላይ አመድና ትቢያ እንዲነሰንስ፥ ወይም ለሞተ ሰው የሚያዝኑና የሚያለቅሱ ሰዎች የሚበሉትን የእዝን እንጀራ እንኳ እንዲበላ አልፈቀደለትም ነበር። ይህ ሁሉ ኢየሩሳሌም እንደምትደመሰስ፥ አይሁድም ሞት ወይም ምርኮ እንደሚገጥማቸው ለማመልከት ነበር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፥ ተማርከው የሚሄዱት አይሁድ ስለ ከተማቸው ሞት እንዳያዝኑና እንዳያለቅሱ ተከልክለው ነበር። ምክንያቱም በምርኮ ላይ ስለነበሩ ይህን ማድረግ በባቢሎን ላይ እንደማመፅ ይቆጠርባቸው ነበር። የሕዝቅኤል ሚስት የሞተችው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በባቢሎናውያን በተቃጠለበት ዕለት ነበር።

ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም መደምሰስ ከመጀመሪያዎቹ ምርኮኞች በሰማ ጊዜ ለሕዝቡ እንዲናገር ተፈቀደለት። በዝምታ እንዲቆይ ከእግዚአብሔር ተጥሎበት የነበረው ግዳጅ በመጨረሻ ተነሣለት (ሕዝቅኤል 3፡26)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኃጢአት ከእዚህ ምዕራፎች ምን ልንማር እንችላለን? ለ) ለቤተ ክርስቲያንህ አባላት ለማስተማር በጣም ጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ትምህርቶች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: