ሕዝቅኤል 4-12

ምክንያታዊ የሚመስሉና በሌሎች ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸውን ነገሮች ማድረግ ቀላል ነው። ዳሩ ግን ሰዎች እንግዳ አድርገው የሚቆጥሩትንና በእኛ ላይ እንዲሳለቁ የሚያደርጋቸውን ነገር ማድረግ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን ሌሉች ሰዎች እንዲያፌዙብንና እንዲስቁብን የሚጋብዝ ነገር ቢሆንም እንኳ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ለመኖር መወሰን አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች ከሚያደርጓቸውና ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እንግዳና አስቂኝ አድርገው ከሚያስቧቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እንዳይስቁባቸውና እንዳያፌዙባቸው በመፍራት ባሕርያቸውን የሚለውጡት ወይም የሚደብቁት ለምንድን ነው?

ከማንኛውም ሌላ ነቢይ ይበልጥ ሕዝቅኤል ትንቢቶቹን ባልተለመዱ መንገዶች አቅርቧል። እነዚህ አቀራረቦች ለእኛ እንግዳ ናቸው። ዳሩ ቀን እግዚአብሔር እነዚህ መልእክቶች እንግዳ በሆነ መንገድ እንዲቀርቡ ያደረገው ሰዎች ለሕዝቅኤልና ለመልእክቱ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ለማበረታታት እንደነበር ጥርጥር የለውም። እነዚህን ነገሮች ማድረ ፈጽሞ ያልተለመዱ ተግባራትን መፈጸም ቢሆንም ሕዝቅኤል እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 4-12 አንብብ። ሀ) ሕዝቅኤል ያደረጋቸውን የተለያዩ ተምሳሌታዊ ተግባራት ዘርዝር። የእያንዳንዱ ተምሳሌ ተግባር ትርጕም ምን ይመስልሃል? ለ) ሕዝቅኤል በዚህ ክፍል የተናገራቸውን ትንቢቶች በአጭሩ አቅርብ።

1. በጡብ አማካይነት የተካሄደው ተምሳሌታዊ ድርጊት (ሕዝቅኤል 4፡1-3)፡- የኢየሩሳሌም ከተማን ሥዕል በጡብ ላይ እንዲስል እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል ነገረው። በዚያ የጡብ ሥዕል ዙሪያ የከተማይቱን መከበብ የሚያሳዩ ትንንሽ ነገሮች እንዲያስቀምጥ ታዝዞ ነበር። ቀጥሉ ሕዝቅኤል የብረት ምጣድ ወስዶ በእርሱና በጡብ በሠራት ከተማ መካከል ምጣዱን ማስቀመጥ ነበረበት። ይህ ሁሉ የኢየሩሳሌም ከተማ በባቢሎን ጦር እንደምትወረርና እንደምትያዝ፣ ልክ የብረት ምጣዱ እንደማይሰበር ሁሉ ወረራውንም ሊሰብር ወይ ሊያሸንፍ የሚችል አንዳችም ነገር እንደሌለ የሚያመለክት ነበር፡፡ ሕዝቅኤል እግዚአብሔርን ወክሉ በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጣው ጦርነት ከጌታ እንደሆነ ለማሳየት ከተማይቱን በዚያ መልኩ መክበብ ነበረበት።

2. በጐድኑ የመተኛቱና በድርቅ ጊዜ ምግብ የመብላቱ ተምሳሌታዊ ድርጊት (ሕዝቅኤል 4፡4-17)፡- ሕዝቅኤል በአንድ ጐድኑ ለ390 ቀናት፥ በሌላው ጐድኑ ደግሞ ለ40 ቀናት ተኛ። ሕዝቅኤል በአንድ ጐድኑ 390 ቀናት በመተኛት የእስራኤልን ሕዝብ ኃጢአትና ዓመፅ ርዝመት በተምሳሌታዊ ድርጊት አሳየ። ለ40 ቀናት በአንድ ጐድኑ በመተኛት ደግሞ የይሁዳን ኃጢአትና ዓመፅ አሳየ። የቍጥሮቹን ተምሳሌታዊ ድርጊቶች በሚመለከት ምሁራን የተለያየ አስተሳሰብ አላቸው። 390 ቀናት የጣዖት አምልኮ በእስራኤል መንግሥት ውስጥ ከተጀመረበት ከሰሎሞን ጊዜ አንሥቶ ኢየሩሳሌም እስከተደመሰሰችበት ጊዜ ድረስ ያለውን የ390 ዓመታት ርዝመት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። 40 ቀናት ደግሞ ክፉና ኃጢአተኛ ንጉሥ የነበረው ምናሴ ንስሐ ከመግባቱ በፊት የነበሩትን 40 የዓመፅ ዓመታት የሚያሳይ ነው ሊባል ይችላል።

ጥቂት ምግብ እንዲበላና ጥቂት ውኃ እንዲጠጣ እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል የነገረው ኢየሩሳሌም በወረራ በምትያዝበት ጊዜ በከተማው ውስጥ ራብ እንደሚኖርና በቂ ምግብና ውኃ እንደማይገኝ ለማሳየት ነበር። እንዲሁም ምግቡን ለማብሰል የሰውን እዳሪ እንደማገዶ እንዲጠቀም እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን አዝዞት ነበር። ይህ ግን ሕዝቅኤልን በሃይማኖታዊ ሥርዓት ርኩስ የሚያደርገው ነገር ስለነበር አጕረመረመ። ስለዚህ የከብት እበት እንዲጠቀም እግዚአብሔር ፈቀደለት። ይህም የሚያሳየው፡- ኢየሩሳሌም በወረራ በምትያዝበት ጊዜ ሁኔታዎች እጅግ የከፉ ከመሆናቸው የተነሣ ለማገዶነት የሚያገለግል እንጨትም ሆነ የማንኛውም እንስሳ እበት እንደማይገኝና ስለዚህም ሰዎች የራሳቸውን እዳሪ ለማገዶነት ለመጠቀም እንደሚገደዱ ነው። 

3. የሕዝቅኤል ጠጕር ተምሳሌታዊ ድርጊት (ሕዝቅኤል 5)፡- በአይሁድ ዘንድ ጠጕርን መላጨት ትልቅ ሐፍረት ነበር። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ረጃጅም ጠጕርና ጢም ነበራቸው። ዳሩ ግን ሰዎች ወደ ምርኮ በሚወሰዱበት ጊዜ በማራኪዎቻቸው አማካይነት ራሳቸው ሙልጭ ተደርጎ ይላጭ ነበር። ስለዚህ ምርኮን በተምሳሌታዊ መግለጫነት ለማስረዳት፥ ጠጕሩንና ጢሙን እንዲላጭ እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን አዘዘው። ጠጕሩንም በትክክል ሦስት ቦታ እንዲከፍል አዘዘው። የጠጕሩን ሢሶ በሠራው የሸክላ ከተማ ቅርጽ ውስጥ እንዲያቃጥል አዘዘው። ይህ የሚያመለክተው:- የኢየሩሳሌም ከተማ በምትያዝበት ጊዜ በሚፈጠረው ራብ፥ ችግርና መቅሠፍት ምክንያት የሕዝቡ ሲሶ በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ እንደሚሞት ነበር። ሕዝቅኤል ሁለተኛውን የጠጕሩን ሲሶ ደግሞ በሰይፍ እንዲቈራርጠው ታዝዞ ነበር። ይህ ደግሞ የሚያመለክተው ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሲሶው ከከተማው ውጭ ከባቢሎናውያን ጋር በሚደረግ ጦርነት እንደሚሞት ነበር። የመጨረሻውን የጠጒሩን ሲሶ በነፋስ ላይ እንዲበትነው ታዝዞ ነበር። ይህም የኢየሩሳሌም ሕዝብ በአሕዛብ መካከል እንደ ጠጕር እንደሚበተኑ የሚያሳይ ነበር። ዳሩ ግን ሕዝቅኤል ከጠጕሩ ጥቂቱን ደግሞ በመጐናጸፊያው ውስጥ ሸሽጎ እንዲያስቀምጥ ታዝዞ ነበር። ይህም እግዚአብሔር በጸጋው ሁልጊዜ እንዳይጠፉ የሚጠብቃቸው ቀሬታዎት እንዳሉት የሚያሳይ ነበር። እነርሱም ከጠቅላላ የአይሁድ ሕዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር በቍጥር ጥቂት ናቸው። 

4. በእስራኤል ተራሮች ላይ የተነገረ ትንቢት ሕዝቅኤል 6)፡- በዚያን ዘመን፥ ብዙውን ጊዜ አይሁድ የሐሰት አማልክትን ወይም ጣዖታትን በኮረብታዎችና በተራራዎች ላይ ያመልኩ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር የጣዖት ማምለኪያ ስፍራዎችና ጣዖት አምላኪዎች እንደሚደመሰሱ ተናገረ። የጣዖታቱ መደምሰስ ብቻ ሳይሆን ሊያመልካቸው የሚችል ማንም አይኖርም። ከንቱና የማይጠቅሙ ሆነው በእግዚአብሔር ይሸነፋሉ።

5. የኢየሩሳሌምና በእርስዋም የሚቀሩ ሰዎች ጥፋት እርግጠኛ ስለ መሆኑ የተሰጠ ትንቢት (ሕዝቅኤል 7)፡- ሕዝቅኤል እንደገና ሕዝቡ የጦርነት ሰለባ በመሆን በችግር፥ በራብና በመቅሠፍት፥ በአሕዛብ መካከል በመበተን፥ በተለያዩ መንገዶች እንደሚቀጡ ተነበየ።

6. በቤተ መቅደስ ውስጥ ስለሚፈጸም የጣዖት አምልኮ የተሰጠ ራእይ (ሕዝቅኤል 8-9)፡- እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን በራእይ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መለሰው። በዚያም በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚፈጸም የተለያየ የጣዖት አምልኮን አሳየው። ይህም በሕዝቡ ላይ የሚመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ እርግጠኛ እንዲሆን ያደረገው ጸያፍ ተግባር ነበር።

ሀ. ቀናተኛነትን ያነሣሣ የነበረው ጣዖት (የተቀረጸ ምስል)፡- ይህ የተቀረጸ ምስል የሚገኘው በቤተ መቅደሱ ውጫዊ ክፍል ነበር። ይህ ጣዖት ኢዮስያስ ከሠላሳ ዓመታት በፊት ያስወገደው ዓይነት፥ የከነዓናውያን የልምላሜ አምላክ የነበረችው የአስታሮት ምስል ሳይሆን አይቀርም (2ኛ ነገሥት 23፡6)። 

ለ. የተንቀሳቃሾችና የርኩሳን አራዊት የሌሎችም አማልክት ምስሎች፡- እዚህ በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ግድግዳ ላይ የተሳሉ ነበሩ። እነዚህ ከግብፃውያን የጣዖት አምልኮ የተቀዱ ሳይሆኑ አይቀሩም። በእነዚህ ጣዖታት ወይም የተቀረጹ ምስሎች ፊት ለፊት ሐሰተኞች አማልክትን በሥውር ያመልኩ የነበሩ ሰባዎቹ ሽማግሌዎች ነበሩ። እነርሱም የይሁዳ የፖለቲካ መሪዎች ነበሩ። 

ሐ. ተሙዝ የተባለው ጣዖት፡- ይህ የባቢሎናውያን የወላድነት አምላክ ነበር። ይህንን ጣዖት በተለይ የሚያመልኩት ሴቶች ነበሩ። እነዚህ ሴቶች በየዓመቱ ዝናብ በሚያቆምበት ጊዜ ዕፀዋት እንደሚደርቁና በዝናም ወራት እንደገና እንደሚለመልሙ፥ ይህ ጣዖትም ሕይወትን የመስጠትና ወላድ የማድረግ ችሎታ አለው ብለው ያምኑ ነበር። ጣዖቱ የሚገኘው በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ነበር።

መ. ፀሐይ አምላኪዎች፡- በጥንት ዘመን ቤተ መቅደሶች የሚመለከቱት ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ነበር። እነዚህ ሰዎች (ምናልባት ካህናት ሳይሆኑ አይቀሩም) በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ነበሩ። እውነተኛውን አምልኮ ለሚገባው አምላክ ጀርባቸውን ሰጥተው ፀሐይን ያመልኩ ነበር። 

እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው አራት ነገሮች በይሁዳ እውነተኛው አምላክ እንዲመለክበት በተሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንኳ የጣዖት አምልኮ ተስፋፍቶ እንደነበር የሚያስነዝቡ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለመፍረድ የወሰነው በዚህ ምክንያት ነበር። እግዚአብሔር በጣዖት አምላኪዎች ላይ እንደሚፈርድ ለማሳየት ከሰሜን የመጡ ስድስት ቀሳፊ መላእክትን ለሕዝቅኤል አሳየው። መላእክቱን የጣዖት አምላኪዎችን እንዲያጠፉ ይመራቸው የነበረ አንድ በፍታ (ሐር) የለበሰ ሰውም ነበር። እነዚህ መላእክት የባቢሎንን ሠራዊት የሚያመለክቱ ነበሩ። እግዚአብሔር እርሱን የተከተሉትንና በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚደረገው የጣዖት አምልኮ የሚያለቅሱትን ሰዎች ለይቶ አወጣ፡፡ በግምባራቸው ላይ «ታው» የሚል የዕብራውያን ምልክት አደረገ። የ «ታው» ቅርጽ ከመስቀል ቅርጽ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ የሚያስገርም ነገር ነው። መላእክቱ በቤተ መቅደስ ውስጥ ጣዖትን ያመልኩ ከነበሩ ሰዎች ጀምረው በከተማው ውስጥ የሚገኙትን ጣዖት አምላኪዎችን በሙሉ ገደሉ። እንደገና እግዚአብሔር በጣዖት አምልኮ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንደነበረውና ኃጢአትን በመጥላት እርሱን በማይከተሉ ሁሉ ላይ እንደሚፈርድ የሚያሳይ ራእይ እንደሆነ ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር የሐሰት አምልኮን ይጠላል ይቀጣልም ከሚለው አባባል ምን ትምህርት እንማራለን? ለ) የእግዚአብሔር ሕዝብ ለሐሰት አምልኮ ሊሰጡት ስለሚገባ ምላሽና በአምልኮአቸው ንጹሐን ሆነው ለመጽናት ስለሚያደርጉት ውሳኔ ምን እንማራለን

7. የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ለቆ መሄዱን የሚመለከት ራእይ (ሕዝቅኤል 10)፡- እግዚአብሔር እጅግ ታጋሽ ቢሆንም እንኳ ከኃጢአት ጋር ለዘላለም ሊኖር አለመቻሉ ግልጽ ነው። በውሸት እናመልክሃለን የሚሉትን ትቶ «በእውነትና በመንፈስ» ወደሚያመልኩት ወደ ሌሎች የሚሄድበት ጊዜ አለ። እግዚአብሔር ከ400 ዓመታት በላይ የተመለከበትን ቤተ መቅደስ ትቶ መሄዱን በማሳየት፥ ሕዝቅኤል ስለ እግዚአብሔር መጀመሪያ ባየው ራእይ ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደሱ እንደተለየ እንዲገነዘብ ተደረገ። በሰሎሞን ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር በቤተ መቅደሱ ላይ ወርዶ ነበር (1ኛ ነገሥት 8)። በዚህ ጊዜ ግን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ግልጽ የሆነ የጣዖት አምልኮ ስለተጀመረ የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ትቶ ሄደ፡፡ የእግዚአብሔር ክብር ለቆ የሄደበትን የተለያዩ ደረጃዎች ተመልከት። በመጀመሪያ፥ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ክብር አየ (ሕዝቅኤል 8፡4)። በሁለተኛ ደረጃ፥ የእግዚአብሔር ክብር በቅድስተ ቅዱሳን ከነበረበት ከኪሩቤል ተነሥቶ የቤተ መቅደሱ መግቢያ ወደሆነው መድረክ ሄደ (ሕዝቅኤል 9፡3)። በሦስተኛ ደረጃ፥ የእግዚአብሔር ክብር ወደ ቤተ መቅደሱ የምሥራቅ በር ሄደ (ሕዝቅኤል 10፡19)። በመጨረሻ፥ የእግዚአብሔር ክብር ከከተማው ወጥቶ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በኩል ባለው የደብረ ዘይት ተራራ ላይ ቆመ (ሕዝቅኤል 11፡23)። እዚአብሔር ሕዝቡ ኃጢአታቸውን ተገንዝበው በንስሐ እንደሚመለሱ ተስፋ አድርጎ በየስፍራው ይቆም የነበረ ይመስላል። ሕዝቡ ግን በንስሐ ሊመለሱ ከቶ ስላልቻሉ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱንና ከተማውን ትቶ ሄደ። አሁን ቤተ መቅደሱ የእግዚአብሔር የቅጣት መሣሪያዎች በሆኑት በባቢሎናውያን የሚጠፋበት መንገድ ተከፈተ ማለት ነው።

ይውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን የሚተውበት ጊዜ መቼ ነው? ለ) ለእግዚአብሔር ያለን አምልኮ ንጹሕና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንድናረጋግጥ ይህ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን የሚገባው እንዴት ነው?

8. በእስራኤል መሪዎች ላይ የተነገረው የፍርድ ትንቢት ሕዝቅኤል 11፡1-5)፡- እነዚህ መሪዎችና ሐሰተኞች ነቢያት ሕዝቡ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም በቅርብ ጊዜ እንደሚመለሱና ከተማይቱን እንደገና እንደሚሠሯት ቢናገሩም፥ ሕዝቅኤል ሕዝቡ በውኃ ድስት ውስጥ የተጣደና ከሥሩም እሳት የሚነድበት ሥጋ ዓይነት እንደሆኑ ተናግሯል። እሳቱ የባቢሎን ሠራዊት ሲሆን ድስቱ ደሞ ኢየሩሳለም ነበረች። መሪዎች ደግሞ በሚገባ ተቀቅለው ለመብል እንደተዘጋጁ የሥጋ ቊራጮች ነበሩ። እግዚአብሔር የጠራቸው ሕዝቡን በጽድቅ መንገድ እንዲመሩ ነበር። እነርሱ ግን በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁ፤ ስለዚህ ይገደላሉ ወይም ይማረካሉ። እነዚህ መሪዎች ለእግዚአብሔር ሕግጋት ከመታዘዝ ይልቅ በዙሪያቸው ያሉ አሕዛብ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ይፈጽሙ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም አባላት ለእግዚአብሔር ሕግጋት ከመታዘዝ ይልቅ በአካባቢያቸው የሚገኙትን ሰዎች ልምድ መከተል የሚቀላቸው እንዴት ነው? ይህ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት እንደሆነ ለማሳየት አንዳንድ መግለጫዎችን ስጥ።

9. ስለ ቅሬታዎች መመለስ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 11፡16-25)፡- አብዛኛው ሕዝብ እግዚአብሔርን የረሳና የተወ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔርን በታማኝነት የሚያመልኩ ቅሬታዎች ነበሩ። ለሐሰተኞች አማልክት አክብሮት አንሰጥም ያሉ ኤርምያስ ሕዝቅኤልና ሌሎችም ነበሩ። እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሕዝቡን ሙሉ በሙሉ እንደማያጠፉ ቃል ገብቶ ነበር። ይልቁንም ለእርሱ ታማኝ የሆኑትን ወደ ምድራቸው ለመመለስ ተስፋ ሰጥቶ ነበር፡፡ አንድ ቀን ጣዖትን ለማምለክ ያላቸውን ፍላጎት ከልባቸው ያስወግዳል። እግዚአብሔር የሥጋን ልብ ወይም ለእርሱ ለመታዘዝ ሙሉ ፍላጎት ያለውን ልብ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባ። አዎ፥ ያ እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን የሥጋ ልብን ለእኛም ይሰጠናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ልብህ እንዴት ነው? ለጥቂት ጊዜ ራስህን መርምር። የልብህን እንደ ድንጋይ ያጠነከረውን የተሠወረ ኃጢአት እንዲገልጥልህ እግዚአብሔርን ጠይቅ። እግዚአብሔር ዛሬ እውነተኛ ልብን እንዲሰጥህ ለምነው።

10. የምርኮ ተምሳሌታዊ መግለፃ (ሕዝቅኤል 12)፡- ምርኮው የማይቀር መሆኑን ለማሳየት ሕዝቅኤል በየቀኑ እክቱን (ጓዙን) እየጠቀለለ በትከሻው ተሸክሞ ይሄድ ነበር። ቀኑ ሲመሽ ግድግዳውን ነድሎ ባበጀው ቀዳዳ በቀስታ ቤቱን ትቶ ይሄድ ነበር። ይህ በምርኮ ለነበሩት አይሁዳውያን የኢየሩሳሌም መደምሰስ የማይቀር እርግጠኛ ነገር መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነበር። ሕዝቅኤል ከቤቱ ለማምለጥ እንደሞከረ ሕዝቡ ከኢየሩሳሌም ለማምለጥ ይሞክራሉ (ለምሳሌ፡- 2ኛ ነገሥት 25፡4-7)። ሆኖም ግን በስደተኝነት ተማርከው ወደ ግዞት ይሄዳሉ። 

ሕዝቅኤል የራብ ጊዜ እንጀራውን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዲበላ ተነግሮት ነበር። ይህም በከተማዋ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ይሁዳ ስትጠፋና የባቢሎን ሠራዊት እየተመመ ሲመጣ የሚደርስባቸውን ታላቅ ፍርሃት ለማሳየት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ከእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ እግዚአብሔርን በመፍራት ስለ መኖር የሚናገሩ አንዳንድ መንፈሳዊ መመሪያዎችን ዘርዝር፡፡ 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: