Site icon

የእግዚአብሔር ራእይና የሕዝቅኤል ጥሪ (ሕዝቅኤል 1-3)

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡1-13 አንብብ። ሀ) ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ስላልተመለሰ ምን ብለው ያስባሉ? ለ) እስካሁን ያልተመለሰው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር ምን እየጠበቀ ነው? ሐ) አንድ ቀን ምድርና ሰማይ ምን ይሆናሉ? መ) ክርስቲያኖች ያንን ታሪካዊ ድርጊት በሚመለከት መኖር ያለባቸው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር የምሕረትና የፍቅር አምላክ ነው። የደኅንነት ተስፋ ያገኙት በዚህ እውነት ምክንያት ብቻ መሆኑን ስለሚያውቁ ይህ እውነት ለክርስቲያኖች ታላቅ ማበረታቻ ነው። እግዚአብሔር የምሕረትና የፍቅር አምላክ ስለሆነ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና እንዳይጠፉ ብዙ ጊዜ ፍርዱን ያዘገያል። የሚያሳዝነው ግን ሰዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር ያለ አግባብ በመተርጐም ባደረጉት ኃጢአት ምክንያት ወዲያውኑ ስለማይፈርድባቸው እግዚአብሔር ጨርሶ የማይፈርድ መሆኑን ማሰብ መጀመራቸው ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት ሰዎችን ወደ ንስሐ ከመምራት ይልቅ ፍርድን ባለመፍራት በኃጢአት እንዲኖሩ አድርጎአቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህንን ዓይነት ተመሳሳይ ዝንባሌ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ያየኸው እንዴት ነው?) ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የፍቅርና የምሕረት አምላክ ብቻ ሳይሆን፥ የቁጣ፥ የጽድቅና የፍርድ አምላክ ጭምር መሆኑን ማስታወሳቸው የሚጠቅመው ለምንድን ነው?

በሕዝቅኤል ዘመን በነበሩ አይሁድ ሕይወት የተፈጸመው ነገር ይህ ነበር። አይሁድ በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚፈረድባቸው ለብዙ ዘመናት በእግዚአብሔር ነቢያት በኩል ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው ኖረዋል። እግዚአብሔር መሐሪ ስለሆነ ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡና እንዳይፈረድባቸው ሲል በሕዝቡ ላይ ወዲያውኑ አልፈረደም። ይህ ግን ከሕዝቡ በኩል ከፍተኛ ድፍረትን አስከተለ። በኃጢአታቸው ምክንያት ከቶ እንደማይፈረድባቸው ይመስላቸው ነበር። ከዚህ የተነሣ ኃጢአታቸው እጅግ እየተባባሰ ሄደ። ከኃጢአታቸው ንስሐ ለመግባት የነበራቸው ፈቃደኝነትም እየቀነሰ መጣ።

ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ጠራና ራእይን ሰጠው። በዚህም ራእይ እግዚአብሔር ደካማ አምላክ ሳይሆን ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ሊቀጣ የተዘጋጀ ቅዱስ አምላክ እንደሆን ለሕዝቅኤል አሳይቷል። የእግዚአብሔር የምሕረት ዘመን አልቆ የፍርድ ዘመን ከመጀመሩ በፊት ከነበሩ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች አንዱ ሕዝቅኤል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 1-3 አንብብ። ሀ) ሕዝቅኤል ያየውን የእግዚአብሔር ራእይ ግለጽ። ለ. በዚህ ራእይ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ምልክቶች ትርጕም ምን ይመስልሃል?

እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ሁሉ፥ የሕዝቅኤል የነቢይነት ጥሪ የተጀመረው በእግዚአብሔር ራእይ ነበር። ኢሳይያስ ያየው ራእይ ያተኮረው በእግዚአብሔር ታላቅነትና ክብር ላይ ሲሆን፥ የሕዝቅኤል ራእይ ደግሞ በእግዚአብሔር ዙሪያ ባሉ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነበር። ሕዝቅኤል በራእዩ አራት ዐበይት ነገሮችን አይቶአል።

ሀ. አራቱ እንስሶች (ሕዝቅኤል 1፡4-9)፡- እነዚህ አራት እንስሶች ኪሩቤል ተብለው የሚጠሩ የእግዚአብሔር መላእክት ነበሩ (ሕዝቅኤል 10፡1)። የተሰጣቸው ኃላፊነት እግዚአብሔርንና ዙፋኑን ማጀብና ክብሩን መጠበቅ ነው። ስለ እነዚህ አራት ፍጥረታት የተሰጠው ገለጣ እጅግ ሰፊና ዝርዝር አሳብ የያዘ ነበር። (ቍጥር አራት የፍጹምነትና የምሉእነት መግለጫ ነው)። እነዚህ አራት ፍጥረታት እያንዳንዳቸው አራት ራሶችና አራት ክንፎች ነበሯቸው። የእያንዳንዳቸው አራት ራሶች የእግዚአብሔርን ፍጥረት ይወክሉ ነበር። አንዱ ራስ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ የሆነውን ሰውን፥ ሌላው ከዱር እንስሳት ሁሉ ኃይለኛና ብርቱ የሆነውን አንበሳን፥ ሌላው ከአዕዋፋት ሁሉ ጠንካራና ኃይለኛ የሆነውን ንስርን ሲመስል የመጨረሻው ደግሞ ከቤት እንስሳት ሁሉ ኃይለኛ የሆነውን በሬን ይመስል ነበር። (ለተመሳሳይ ገለጻ ራእይ 4፡7 ተመልከት።)

ለ. የሠረገላው አራት መንኰራኲሮች፡- እነዚህን መንኲራኲሮች ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር አቅጣጫቸውን ሳይለውጡ በፈለጉት አቅጣጫ ለመዞር እንዲችሉ በመንኰራኵር ውስጥ ሌላ መንኰራኵር መኖሩ ነው። እነዚህ መንኲራኲሮች ዓይኖች ሞልተውባቸው ነበር። እነዚህ ሁለት እውነቶች በምሳሌ የሚገልጹት የእግዚአብሔር ዙፋንና ሕልውና በአንድ ጊዜ በሁሉ ቦታ መሆኑንና ሁሉንም ነገር ለማየት እንደሚችል ነበር። 

ሐ. ከመንኰራኵሮቹ በላይ ያለው ሰፊ ስፍራ 

መ. «የሰውን ልጅ የሚመስል» ወይም እግዚአብሔር ራሱ የተቀመጠበት ዙፋን፡- ሕዝቅኤል እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል ላለመግለጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል። መልኩንና የከበበውን የክብር ነጸብራቅን ብቻ በአጭሩ ይገልጻል። ሕዝቅኤል ላየው ለዚህ ታላቅ ራእይ የሰጠው ምላሽ በአምልኮና እግዚአብሔርን በመፍራት በግንባሩ መውደቅ ብቻ ነበር።

ሕዝቅኤል እግዚአብሔርን ካየ በኋላ ከእግዚአብሔር ጥሪ ተቀበለ። እግዚአብሔርም እርሱን መስማትና ንስሐ መግባት አሻፈረኝ ወዳለ ዓመፀኛ ሕዝብ እንደሚልከው ለሕዝቅኤል ይነግረዋል። እነርሱን እንዳይመስልና እንዳይፈራቸውም ያስጠነቅቀዋል። ከዚያም ይበላው ዘንድ የመጽሐፍ ጥቅልል ሰጠው። የመጽሐፉ ጥቅልል የእግዚአብሔር ቃል ስለነበረ እንደ ማር ይጣፍጥ ነበር። የመጽሐፉ ጥቅልል ሕዝቅኤል ለሕዝቡ መናገር ያለበትን የትንቢት ቃላት የያዘ ነበር። ሕዝቅኤል በጥቅልሉ ላይ በነበረው ጽሑፍና ስለ ሕዝቡ ኃጢአተኛነት ባገኘው አዲስ ግንዛቤ በመንፈሱ ተቈጣ፤ ተማረረም። ከመጠን በላይ ከመመሰጡ የተነሣ ለማንም ሰው ሳይናገር ሰባት ቀን ተቀመጠ።

የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔርን ቃል በተገቢው መንገድ መረዳት በሕይወታችን ውስጥ ይህን የመሰለ ምላሽ መፍጠር ያለበት በምን መንገድ ነው?

ከሰባት ቀናት በኋላ እግዚአብሔር እንደገና ለሕዝቅኤል ተናገረ፤ የሕዝቡ «ጠባቂ»ም አደረገው። ጠባቂ በአንዲት ከተማ ከፍተኛ ስፍራ ላይ በመቀመጥ የጠላትን መምጣት በከተማ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚናገር ነበር። ጠባቂ እንደ መሆኑ መጠን የሕዝቅኤል ኃላፊነት ከፍተኛ እንደሆነ እግዚአብሔር አስጠነቀቀው። የእግዚአብሔርን የተግሣጽና የፍርድ መልእክት ለክፉው ሰውና ከመንገዱ ለመመለስ ለሚያመነታው ወይም የመኮብለል አሳብ ለሚፈታተነው ጻድቅ ሰው ንስሐ እንዲገባ የሚያበረታታ ቃል መናገር ነበረበት። ሕዝቅኤል ይህን መልእክት ለማስተላለፍ ባይፈቅድ፥ ክፉው ወይም ከእግዚአብሔር ፊቱን የመለሰው ጻድቅ ሰው ስለ ራሱ ኃጢአት በጥፋተኛነት የሚጠየቅ ቢሆንና ሕዝቅኤልም ይህን ሰው ባለማስጠንቀቁ ተጠያቂ ይሆን ነበር። ሕዝቅኤል የማስጠንቀቂያ መልእክቱን መናገር የነበረበት በክፋት ለሚመላለሰው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፥ እያንዳንዱ ሰው በግል ለሚፈጽመው ማንኛውም ተግባር ተጠያቂ መሆኑን ጭምር ነበር።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ይህ ትምህርት በአሁኑ ጊዜ ወንጌል ላለን ለእኛ ብርቱ ማስጠንቀቂያ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ዛሬ ይህን ትምህርት በቤተ ክርስቲያንህ የሚገኙ ሰዎች የጥበቃ ኃላፊነት እንዳለባቸው ለማስተማር ልትጠቀምበት የምትችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?

ኢየሩሳሌም ከስድስት ዓመት በኋላ በባቢሎን እጅ እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ፥ ሕዝቅኤል ለሕዝቡ የሚሆን ግልጽ ከእግዚአብሔር መልእክት ካልተቀበለ በቀር ለመናገር አልቻለም ነበር (ሕዝቅኤል 24፡27፤ 33፡22)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/D9kwWxbtE9VRRvfKA
Exit mobile version