Site icon

ሕዝቅኤል 25-32

የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙር (115)፡ 1-3 (135)፡5-6 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር በነገሮች ሁሉ ላይ የበላይ ተቁጣጣሪ ስለ መሆን እነዚህ ቍጥሮች ምን ያስተምሩናል? ለ) እነዚህን ትምህርቶች ማስታወሱ ለምን አስፈለገ?

አብዛኛው ትንቢተ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለሆኑት አይሁድ ኃጢአትና በእነርሱ ላይ ስለሚመጣው ፍርድ የሚናገር ቢሆንም እንደ አብዛኛዎቹ የትንቢት መጻሕፍት፥ እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ስለሚያመጣው ፍርድም ይናገራል። ይህ ከመንፈሳዊ መመሪያ ጋር የሚስማማ ነው። የእግዚአብሔር ፍርድ ወይም ቅጣት የሚጀምረው የእግዚአብሔር ቤተሰብ ከሆኑት ከልጆቹ ነው (1ኛ ጴጥሮስ 4፡17)። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ በሚያምኑ ሁሉ ላይም ይደርሳል። እግዚአብሔር አይሁድን ለመቅጣት አሕዛብን ቢጠቀምም እንኳ እነርሱም የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ እንዳለባቸው በማሳሰብ ያስጠነቅቃቸዋል።

በምድር ላይ የምንኖረው ኑሮ እግዚአብሔርን ከማያውቁ ሰዎች ጋርና በእነርሱም ቍጥጥር ሥር ቢሆንም፥ የምናመልከው አምላክ ግን በክፉ ሰዎች ወይም በክፉ መንግሥታት ዕቅድ ቍጥጥር ሥር አለመሆኑን ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነው። ይልቁንም የእኛ አምላክ እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ስለሚቁጣጠር ወደዱም ጠሉም ፈቃዱን ይፈጽማሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 25-32 አንብብ። ሀ) ሕዝቅኤል ትንቢት የተናገረባቸውን የተለያዩ ሕዝቦች ስም ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ሕዝቦች ላይ የተነገሩትን ዐበይት ትንቢቶች ዘርዝር። ሐ) እነዚህ ሕዝቦች የት እንደሚገኙ ለማወቅ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ የሚገኝ “ካርታ ተመልከት። 

1. በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 25፡1-7)

በአሁኑ ጊዜ የዮርዳኖስ ክፍል አካል የሆነችው የጥንቷ አሞን የእስራኤል የቀድሞ ጠላት ነበረች። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉ ጊዜ፥ አሞናውያን ሁኔታውን በደስታ ከመመልከት ሌላ፥ ኢየሩሳሌምን በማጥፋት ረገድም ተባባሪ ሆነዋል። ስለዚህ እግዚአብሔር አሞናውያንን እንደሚያጠፋ ተናገረ። በአሁኑ ጊዜ አሞናውያን የሚባል ሕዝብ የለም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር የተናገረው ትንቢት በመፈጸሙ አካባቢው ዛሬ የዐረብ ከብት አርቢዎች የቀንድ ከብቶቻቸውን፥ በጎቻቸውንና ግመሎቻቸውን የሚያሰመሩበት ስፍራ ሆኗል። 

2. በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 25፡8-11)

ሴይር በመባል የምትታወቀው ሞዓብ ከአሞን በስተደቡብ የምትገኝ ነበረች። እግዚአብሔር ዓብን ስለ ኃጢአቷ እንደሚቀጣት ተናገረ። 

3. በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 25፡12-14) 

ኤዶም በደቡብ ሞዓብ የምትገኝ አገር ስትሆን፥ የይሁዳ የረጅም ጊዜ ጠላት ነበረች። እስራኤላውያን ወደ ኤዶም እንደሚመጡና እንደሚያሸንፏቸው እግዚአብሔር ተስፋ ሰጠ። 

4. በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 25፡15-17)

በእስራኤልና በይሁዳ በስተምዕራብ ይገኙ የነበሩት ፍልስጥኤማውያን ለረጅም ዘመናት የአይሁድ ጠላቶች ነበሩ። የፍልስጥኤም ጦር ብዙ ጊዜ ይሁዳን ለመውጋትና ለመውረር ከሚዘምት ጦር ጋር ይተባበር ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንን እንደሚቀጣቸው አስቀድሞ ተናገረ።

እነዚህ ሦስት መንግሥታት ወዲያውኑ በባቢሎናውያን ተደመሰሱ። ቆይቶ ደግሞ ኤዶምና ፍልስጥኤም በእስራኤል ቍጥጥር ሥር ዋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ በእዚህ ሕዝቦች ላይ የተነገረውን ትንቢቶ የእያንዳንዱ ትንቢት የመጨረሻ ክፍል ተመልከት። አሕዛብ ከእግዚአብሔር ዘንድ በመጣባቸው ቅጣት ምክንያት ምን ይገነዘባሉ?

5. በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 26-28፡19)

ከማንኛውም የትንቢት መጽሐፍ ይልቅ በጢሮስ ላይ የተነገረውን ትንቢት የያዘው ትንቢተ ሕዝቅኤል ነው። የአሁኒቷ ሊባኖስ ጢሮስ አንዳንድ ጊዜ የይሁዳ ጠላቶች ተባባሪ ስትሆን፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ ራሷን የቻለች ጠላት ነበረች። ኢየሩሳሌም ስትደመሰስ የመካከለኛው ምሥራቅ ንግድ ብቸኛ የበላይ ተቆጣጣሪ እንደምትሆን በማሰብ ደስ ተሰኘች። ይህ ሕዝብ በሜዲተራኒያን ባሕር ላይ በመርከብ በሚካሄድ ንግድ ገናና ስምን፥ ሥልጣንንና ኃይልን ያተረፈ ነበረ። ጢሮስ ለጠላት ወረራ አመቺ እንዳትሆን የዋና ከተማዋ ምሽግ በባሕር ዳርቻ ባለ ደሴት ላይ የተሠራ ነበር። ስለዚህ ሕዝቡ ማንም ሊያጠፋው እንደማይችል በመገመት ታበየ፤ ተኲራራም።

እግዚአብሔር ጢሮስን ሙሉ በሙሉ እንደሚያጠፋ ተናገረ። ይህም በሁለት ደረጃዎች ተፈጸመ። በመጀመሪያ፥ ናቡከደነፆር በየብስ በእርሱ ምድር ላይ ወደምትገኘው ወደ ዋናዋ ከተማ በመምጣት አጠፋት። በደሴት ላይ ተመሥርታ የነበረችውን ከተማ ለመውጋት ግን አልቻለም ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ በ331 ዓ.ዓ. ታላቁ እስክንድር የጥንቷን የጢሮስ ከተማ ፍርስራሽ ወደ ባሕሩ በመጣል፥ ከርእሰ ምድሩ አንሥቶ በደሴት ላይ እስከምትገኘዋ ከተማ የሚደርስ መንገድ ሠራ። እግዚአብሔር እንደተናገረው፥ በደሴት ላይ የነበረችዋን ከተማ ለማጥፋት ቻለ። በርእሰ ምድሩ ላይ የነበረችው የጥንቷ ዋና ከተማም ሆነች፤ በደሴት ላይ የምትገኘዋ ከተማ እንደገና ሊሠሩ አልቻሉም። የአሁኒቱ የጢሮስ ከተማ ከቀድሞዋ ጢሮስ የምትመሳሰል ብትሆንም፥ የጥንቷ ከተማ ግን አይደለችም።

የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ብዙ መቶ ዓመታት የወሰደ ቢሆንም እንኳ አንድም ሳይቀር ተፈጸሞአል።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ስለ እግዚአብሔር ቃል ትክክለኛነት ይህ ምን ያስተምረናል? ለ) ያልተፈጸሙ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች እንደሚፈጸሙ ይህ ምን ዋስትና ይሰጠናል? ሐ ካልተፈጸሙ ትንቢት (የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች) አንዳንዶቹን ዘርዝር።

ሕዝቅኤል 28 በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ትንቢት ነው። ሕዝቅኤል 28፡12-17 በምሁራን መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሣ ክፍል ነው። አንዳንዶች እነዚህ ቊጥሮች የሚናገሩት በትዕቢቱ ምክንያት በራሱ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ስላመጣው ስለ ጢሮስ ንጉሥ ብቻ ነው ይላሉ። ሌሎች ግን እነዚህ ጥቅሶች የሚናገሩት በተለይ የእግዚአብሔር ጠላት ስለሆነው ስለ ሰይጣን ነው ብለው ያምናሉ። ሕዝቅኤል የጢሮስን ንጉሥ ትዕቢት በሥዕላዊ መግለጫነት በመጠቀም የሰይጣንን ውድቀት መግለጡ ነው ብለው ያስተምራሉ። እርግጠኞች ለመሆን ባንችልም እንኳ እነዚህ ቊጥሮች የሚገልጡት ከሥጋ ለባሹ የጢሮስ ንጉሥ የሚልቅ ፍጡርን ይመስላል። ይህ ፍጡር ከጢሮስ ንጉሥ ኃይልና ዝንባሌ በስተኋላ የነበረውና ከጢሮስ ንጉሥ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ሰይጣን ነበር። ይህ ትንቢት ስለ ሰይጣን የተነገረ ከሆነ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

ሀ. ሰይጣን እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ታላላቅ ፍጥረታት አንዱና ከሁሉም ይልቅ የተዋበ ፍጡር ነበር። በዚያን ዘመን ከነበሩት እጅግ የከበሩ ድንጋዮች ሁሉ ጋር ተወዳድሯል። ሕዝቅኤል በራእዮቹ እንዳያቸው አራት እንስሳት፥ የእግዚአብሔርን ዙፋን እንደሚጋርዱ መላእክት ዓይነት እርሱም እንደ እርሱ ኪሩቤል ነበር (ሕዝቅኤል 13)፤ በእግዚአብሔርም ፊት ይኖር ነበር። 

ለ. የሰይጣን ውድቀት የትዕቢቱ ውጤት ነበር። ትዕቢት ሰይጣንን ከመንግሥተ ሰማያት ተባርሮ እንዲወጣና ለመጨረሻም ጥፋት ዳረገው።

** ማስታወሻ፡- ስለ ሰይጣን ውድቀት በኢሳይያስ 14፡12-15 የተነጋገርንበትን ማብራሪያ ተመልከት።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ትዕቢትን ስለ መጥላቱ እዚህ ጥቅሶች የሚያስተምሩት ምንድን ነው?

6. በሲዶና ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 28፡20-26)

ሲዶና ከጢሮስ በስተሰሜን 40 ኪሎ ማትር ያህል ርቃ የምትገኝ የወደብ ከተማ ስትሆን፥ ብዙ ጊዜ ከጢሮስ ጋር ትተባበር ነበር። በጢሮስ ኃጢአት ስለተባበረች እግዚአብሔር በሲዶና ላይ ሊፈርድ ቃል ገብቶ ነበር። አይሁድ ደግሞ ወደ ከነዓን እንደሚመለሱና በዚያ በሰላም እንደሚኖሩ ተስፋ ሰጥቷል። 

7. በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 29-32)

ግብፅ ከይሁዳ በስተደቡብ የምትገኝ ታላቅ አገር ነበረች። ንጉሥ ኢዮስያስን የገደለችና ልጁን በምርኮ የወሰደችው ግብፅ እንደነበረች የሚታወስ ነው። በውጊያው እንደምትረዳ ቃል በመግባት፥ ይሁዳ በባቢሎን ላይ እንድታምፅ ያበረታታች ግብፅ ነበረች። ዳሩ ግን ግብፅ ጦርነቱ በተጀመረ ጊዜ ይሁዳን ለመርዳት ሳትፈቅድ ቀረች። ይህም ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ጥፋት ምክንያት ነበር። ስለዚህ ናቡከደነፆር ግብፅን እንደሚያሸንፍ እግዚአብሔር ተናገረ። ግብፅ የቀድሞ ክብሯንና ኃይሏን አጣች። እንደ አይሁድ ሁሉ ግብፃውያንም በአሕዛብ መካከል ተበተኑ። በዘመናቸው ታላቅ እንደነበሩትና እንደወደቁት አምራውያን ታላቁ የግብፅ መንግሥትም ይወድቃል። የሕዝቡ ምልክት ወይም ተወካይ የሆነው ፈርዖንም ሊሸነፍና ከእርሱ በፊት የተሸነፉት ሌሎች ነገሥታትና አሕዛብ በሙሉ ወደ አሉበት ሙታን መንደር ሊሄድ ግድ ነበር።

** ማስታወሻ፡- ስለ ግብፅ የተነገሩት እነዚህ ትንቢቶች ከ587-571 ዓ.ዓ. ባለው በ15 ዓመታት ጊዜ የተሰጡ ነበሩ። የመጨረሻ የሕዝቅኤል ትንቢት ስለ ግብፅ የሚናገር ነበር። ስለ ግብፅ የተነገረው ትንቢት የሚገኘው በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አይደለም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች ልንማራቸው የምንችል ትምህርቶችን ዘርዝር። ለ) ስለ እግዚአብሔርና ከሕዝቦች ጋር ስላለው ግንኙነት ምን ልንማር እንችላለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/V5h1jB7VwUauSx3W6
Exit mobile version