ሕዝቅኤል 33-39

የውይይት ጥያቄ፣ እግዚአብሔር ያለፈውንና አሁን ያለውን እንደሚያውቅ ሁሉ፥ የወደፊቱንም ነገር እንደሚያውቅና እንደሚቆጣጠር መረዳት አበራታች የሚሆነው ለምንድን ነው?

እንደ እኛ በጊዜ ለማይወሰነው እግዚአብሔር፥ የወደፊቱ ሁኔታ የአሁኑን ያህል ግልጽ ነው። እግዚአብሔር ቀድም የሆነውንና አሁን በመፈጸም ላይ ያለውን ብቻ ሳይሆን፥ ወደ ፊት ምን እንደሚሆንም በትክክል ያውቃል።

በሕዝቅኤል 33-48 ስለ ወደፊት የተነገሩ በርካታ ትንቢቶችን እናገኛለን። አንዳንዶቹ ለእስራኤል ሕዝብ እንደማስጠንቀቂያ ነበር የተሰጡት። ሌሎች ደግሞ በምርኮ የነበሩትን አይሁድ ለማበረታታት ነበር። እዚህ ምዕራፎች በቀጥታ እኛን የሚመለከቱ ትንቢቶችን የያዙ ባይሆኑም እንኳ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንዲሁም ወደ ፊት የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን ሳይቀር እንደሚቆጣጠር በማወቅ እንድንበረታታ የተሰጡ ናቸው። እግዚአብሔር የማይቆጣጠረው አንዳችም ነገር አይደርስብንም። ዓላማውን ለመፈጸም ነገሮችን ሁሉ ይጠቀምባቸዋል።

እነዚህ ምዕራፎች ስለ መጨረሻዎቹ የሚናገሩ በርካታ ትንቢቶችን ስለያዙ፥ ምሁራን ትርጕማቸውን በሚመለከት ብዙ ጊዜ ይወዛገባሉ። አንድ ሰው በትንቢተ ሕዝቅኤል መጨረሻ የሚገኙትን ትንቢቶች የሚረዳው እግዚአብሔር ስለመጨረሻው ዘመን ያለውን ዓላማና በእርሱም ውስጥ እስራኤል ያላትን ስፍራ መረዳት በሚችልበት መንገድ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 33-39 አንብብ። ሀ) ሕዝቅኤል በጠባቂነቱ በነበረበት ኃላፊነት እግዚአብሔር ምን ማስጠንቀቂያ ሰጠው? ለ) ሕዝቅኤል በምርኮ የነበሩትን አይሁድን ለማበረታታት የፈለገባቸውን መንገዶች ዝርዝር። ሐ) እነዚህ ጥቅሶችስ ለኢየሩሳሌም ውድቀት የሚሰጧቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? መ) ሕዝቅኤል ያየው ራእይና ትርጕም ምንድን ነው? ሠ) የጎግና ማጎግ ሕዝቦች ምን ያደርጋሉ?

1. ሕዝቅኤል፥ የእስራኤል ጉበኛ ወይም ጠባቂ (ሕዝቅኤል 33፡1-20)

ሕዝቅኤል የነቢይነት ሥራውን በጀመረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በባቢሎናውያን አማካይነት ሊመጣ ስላለው አደጋና ስለ እነርሱ ንስሐ የመግባት አስፈላጊነት በመንገር፥ የሚያስጠነቅቅቅ ጉበኛ ወይም ጠባቂ መሆን እንደሚገባው አስጠንቅቆት ነበር። በሕዝቅኤል 33 በጉበኛነቱ ያለበትን ኃላፊነት በመንገር እንደገና ያስጠነቅቀዋል። ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡ ማስገደድ የሕዝቅኤል ኃላፊነት አልነበረም። ሕዝቅኤል ቢያስጠነቅቃቸውና እነርሱ ከክፋታቸው አንመለስም ቢሉ፥ ጥፋቱ መስማት እንቢ ያሉት የሕዝቡ እንጂ የሕዝቅኤል አልነበረም። ሕዝቅኤል ግን ዝም ቢልና ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ሳያስጠነቅቅ እንዲሁም ንስሐ እንዲገቡ ባያበረታታ፥ እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን በኃላፊነት ይጠይቀዋል። የእግዚአብሔር ፍላጎት ኃጢአተኛው እንዲሞት ሳይሆን፥ ንስሐ እንዲገባና እንዲድን ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል በጉበኛነት የነበረበት ኃላፊነት ዛሪም እኛ ላላመኑ ሰዎች ወንጌልን ለማድረስ ካለን ኃላፊነት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? 

2. የኢየሩሳሌምን ውድቀት የሚመለከት ገለጻ (ሕዝቅኤል 33፡21-33)

ከተማይቱ በወደቀች ጊዜ ከሞት ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ሕዝቅኤል መጣና ኢየሩሳሌም እንደወደቀች ነገረው። በዚያን ጊዜ ሕዝቅኤል መልእክቱን በግልጽ ለሕዝብ መናገር ይጀምር ዘንድ እግዚአብሔር ፈቀደለት። ሕዝቅኤል የተናገራቸው ትንቢቶች በሙሉ ስለተፈጸሙ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ መሆኑ ታወቀ። ከዚህ በኋላ የሕዝቅኤል መልእክት ከፍርድ ወደ ማጽናናት ተቀየረ።

በኢየሩሳሌም የነበሩ ሰዎች ከውድቀት በኋላ ንስሐ ያልገቡ ይመስላሉ። አንድ ብቸኛ ሰው የነበረው አብርሃም ታላቅ ሕዝብ ከሆነ፥ ከአንድ በላይ የሆንን እኛ ሕዝቡንና መንግሥታችንን እንደገና ለመመሥረት እንችላለን ብለው ነበር። እግዚአብሔር ይባርካቸው ዘንድ ከኃጢአታቸው ንስሐ መግባት እንደነበረባቸው አሁንም አልተገነዘቡም ነበር። እንዲሁም ሕዝቅኤል መልእክቱን መስማት ይፈልጉ የነበሩትንና ልባቸውን ያልለወጡትን ምርኮኞች ገሥጾአል። በአፋቸው እግዚአብሔርን እንከተላለን ቢሉም፥ በልባቸው ግን ኃጢአት ነበር፤ ቃላቸውም በተግባር አይተረጉምም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን የሰዎች ቃልና ተግባር በአንድ ላይ አብሮ አይሄዱም፤ እንዲህ ዓይነቱ ተመሳሳይ ችግር የሚከሠተው እንዴት ነው? መግለፃዎችን ስጥ። 

3. የእረኛውና የበጎች ምሳሌ (ሕዝቅኤል 34)

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችንና የሕዝቡን ግንኙነት ለመግለጽ ካገለገሉ ማነጻጸሪያዎች እጅግ የተለመደው የእረኛና የበጎች ምሳሌ ነው። ይህ ምዕራፍ መሪዎቹ ኃላፊነታቸውን ካልተገነዘቡና መልካም እረኛ ካልሆኑ የሚመጣባቸውን ፍርድ የሚገልጽ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጥንቃቄ ሊያነብቡት የሚገባ እጅግ ጠቃሚ ክፍል ነው።

የእስራኤል መሪዎች የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑት የእስራኤላውያን እረኞች ነበሩ። እነዚህ መሪዎች ግን ለመንጋው እንክብካቤ ከማድረግ ይልቅ የራሳቸውን የስግብግብነት ዓላማ ያራምዱ ነበር። ለራሳቸው ሕይወት ቁሳዊ ጥቅማ ጥቅሞችን በማሳደድ፥ ለሕዝቡ ተገቢውን እንክብካቤ አያደርጉም ነበር። ስለዚህ የመንጋው ጠላቶች መንጋውን እንዲያጠፉ በር ከፍተው ነበር። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ፈረደባቸውና በባቢሎን ምርኮ የአመራር ስፍራቸውን አሳጣቸው።

ዳሩ ግን እግዚአብሔር አንድ ቀን ለመንጋው ሰላምና ደኅንነት በሚያመጣ መንገድ፥ የእግዚአብሔርን መንጋ የሚመራ፥ እንደ ዳዊት ያለ አንድ መሪ እንደሚያስነሣ ተስፋ ሰጥቶ ነበር፤ ያም እረኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ዮሐንስ 10 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በጥንቷ እስራኤል የነበረው የእረኞች ችግር ዛሬ በመጥፎ መሪዎቻቸው ምክንያት ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) መልካም እረኛ የሆነውን ኢየሱስን ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር አወዳድር። የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያን አባሎች በመምራት ረገድ ያላቸው ተመሳሳይነት እንዴት ነው? 

4. በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 35)

ኤዶም የእስራኤልንና የይሁዳን ምድር ለመውሰድ በመፈለግ እስራኤልን በማጥፋት ድርጊት ስለተባበረች እግዚአብሔር እንደሚያጠፋት ለሁለተኛ ጊዜ ተናገረ። 

5. ስለ እስራኤል ተራሮች የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 36)

የእስራኤል ተራሮች እግዚአብሔር ለአይሁድ ሊሰጣቸው ቃል የገባላቸውን የተስፋይቱን ምድር የሚወክሉ ናቸው። ሌሎች መንግሥታትና ሕዝቦች በኢየሩሳሌም ውድቀትና ጥፋት ተደስተው ነበር። አብዛኛው ሕዝብ በምርኮ ተወስዶ ስለነበር በእስራኤል አብዛኛዎቹ አይሁድ ይኖሩባቸው የነበሩት ተራራማ ስፍራዎች ሰው የማይኖርባቸው ሆነው ነበር። እግዚአብሔር ግን አንድ ቀን አይሁድ ከምርኮ እንደሚመለሱና እነዚህ ተራራማ ስፍራዎች በሰዎች የተሞሉ ፍሬያማ እንደሚሆኑ ተናገረ። እንዲያውም ምድሪቱ ከፊት ይልቅ እጅግ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደምትሆን ተስፋ ሰጠ።

አይሁድ በኃጢአት ድርጊታቸው በራሳቸው ላይ ባመጡት ጥፋት የእግዚአብሔርን ስም ያሰደቡ ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር አንድ ቀን ቅዱስ መሆኑን በመግለጽ ራሱን ለእስራኤል እንደሚያሳይ ተስፋ ሰጠ። ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ እንደገና እንደሚሰበስባቸው ተናገረ። ከኃጢአታቸውና ከክፉ መንገዳቸው ሁሉ እንደሚያነጻቸውና ሕጉን በልባቸው ላይ በመጻፍ ለእርሱ በፍጹምነት እንዲታዘዙ እንደሚያደርግ ቃል ገባላቸው።

እነዚህ የተስፋ ቃሎች አይሁድ በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት በተመለሱ ጊዜ በከፊል የተፈጸሙ ቢሆኑም፥ ሙሉ በሙሉ የሚፈጸሙት ግን አይሁድ በሙሉ ወደ ተስፋይቱ ምድር ተመልሰው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነትና በበረከቱ በሚጥለቀለቁበት በመጨረሻው ዘመን ይመስላል።

የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) ከእነዚህ የተስፋ ቃሉች አንዳንዶቹ ዛሬ በክርስቲያኖች ወይም በመንግሥተ ሰማያት የሚፈጸሙት እንዴት ነው?) ከእነዚህ የተስፋ ቃሎች አብዛኛዎቹ ለክርስቲያኖች ቃል በቃል ሳይሆን ለአይሁድ ብቻ መፈጸም ያለባቸው የሚመስሉት እንዴት ነው? 

6. የደረቁ አጥንቶች የሞሉበት ሸለቆ ራእይ (ሕዝቅኤል 37)

በትንቢተ ሕዝቅኤል ውስጥ በሚገባ ከታወቁት ክፍሎች አንዱ የደረቁ አጥንቶች ስለሞሉበት ሸለቆ የተሰጠው ራእይ የሚገኝበት ክፍል ነው። አጥንቶቹ ሕያዋን ፍጥረታት ሆነው ሊቆሙ በሚችሉበት አኳኋን እግዚአብሔር ሠራ። እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ከእስራኤልና ከይሁዳ የሆኑትን አይሁድ የሚወክሉ ነበሩ (ሕዝቅኤል 37፡11)። በምርኮ ላይ ለነበሩ አይሁድ ምንም ተስፋ የሌለና የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝቦችም የሞተ ያህል በመሰሉበት ጊዜ፥ አንድ ቀን እግዚአብሔር የሕይወትን እስትንፋስ እንደሚዘራባቸውና ወደ ከነዓን እንደሚመልሳቸው ቃል ገባላቸው።

እንዲሁም እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን፡- አንዱ እስራኤል ሌላው ይሁዳ ተብሎ የሚጠራ ሁለት በትር እንዲወስድና አንድ ላይ እንዲያስራቸው ነገረው። ይህም አንድ ቀን የተከፋፈሉት የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት አንድ እንደሚሆኑ የሚያመለክት ነበር። በዚያን ጊዜ በእስራኤል ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር አገልጋይ ተብሎ የሚጠራው መሢሑ-ዳዊት ይነግሣል። እግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል ኪዳንን ከእነርሱ ጋር በመመሥረት በመካከላቸው ለዘላለም ይኖራል።

እነዚህ ትንቢቶች ደግሞ የተፈጸሙት በከፊል ነበር። ከሰባ ዓመታት ምርኮ በኋላ ከአይሁድ አንዳንዶቹ ወደ ምድራቸው የተመለሱ ቢሆንም ድሮ የነበራቸውን ክብር ግን አላገኙም። በ70 ዓ.ም. ደግሞ አይሁድ እንደገና ተበተኑ። ከዚያ በኋላ ወደገዛ ምድራቸው መመለስ የጀመሩት በ1948 ዓ.ም. ነበር። አብዛኛዎቹ አይሁድ ግን እስካሁን ድረስ በአሕዛብ መካከል ተበትነው ይኖራሉ። ስለዚህ መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ቀን አንድ ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ አይሁድን በመሰብሰብ በላያቸው ይነግሣል። እነዚህ የተስፋ ቃሎች ሙሉ በሙሉ የሚፈጸሙት ያኔ ብቻ ነው።

7. በጎግ ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 38-39)

ሕዝቅኤል ስለ መጪው ጊዜ ከተናገራቸው ትንቢቶች መካከል አስደሳች ያልሆኑም ነበሩባቸው። ነቢዩ ከእስራኤል በስተሰሜን እጅግ ርቆ ስለሚገኘው ስለ ጎግ ምድር በተናገረው ትንቢት ውስጥ ወደገዛ ምድራቸው እንደገና በተሰበሰቡ አይሁድ ላይ ጎግ ጦርነት እንደሚከፍት ይገልጣል። ይህ ሕዝብ ሌሎችን ብዙ የአሕዛብ መንግሥታት በማስተባበር ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ ይሻል። ዳሩ ግን እግዚአብሔር በመሬት መንቀጥቀጥና ጦሩ እርስ በርሱ እንዲዋጋ በማድረግ ታላቁን ሠራዊት ይገለብጠዋል፤ ሕዝቡን ግን ይጠብቃል። በዚህ ዓይነት አሕዛብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቅድስናና ታላቅነት ያያሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ከእነዚህ ምዕራፎች የተማርሃቸውን የተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: