የትንቢተ ዳንኤል ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

ዳንኤል በተወለደበት ወቅት የነበሩት ሁኔታዎች ለይሁዳ ሕዝብ እጅግ መልካም የሚመስሉ ነበሩ። እግዚአብሔርን የሚፈራው ንጉሥ ኢዮስያስ በዙፋን ላይ ነበር። ቤተ መቅደሱ ነጽቶ ነበር። ቢያንስ ቢያንስ ለይስሙላ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደሚያከብሩና እንደሚያመልኩ ይናገሩ ነበር፤ ነገር ግን አይሁድ የለወጡት ባሕርያቸውን እንጂ ልባቸውን አልነበረም። በይሁዳ ሰላም የነበረ ቢመስልም እንኳ በሰሜን ምዕራብ ራቅ ብሎ ጦርነት ይካሄድ ነበር። በአሦራውያን ቊጥጥር ሥር የነበረው የባቢሎን ሕዝብ ዓምጾ ነበር። በ626 ዓ.ዓ. ናቦፓላሳር የተባለው የባቢሎን ንጉሥ አሦራውያንን አሸንፎ ለባቢሎን ነፃነትን አወጀ። ከዚያም ከሜዶን ጋር በመተባበር አሦርን መውጋት ጀመረ። በ612 ዓ.ዓ. የአሦር ዋና ከተማ ነነዌን ተቈጣጠረ። በ609 ዓ.ዓ. ግብፃውያንና አምራውያን ከባቢሎናውያን ጋር የተዋጉበት አንድ የመጨረሻ ጦርነት ነበር፤ ነገር ግን ተሸነፉ። ንጉሥ ኢዮስያስ የተገደለው ግብፃውያን ከባቢሎን ጋር ለመዋጋት በሚሄዱበት ጊዜ በይሁዳ እንዳያልፉ ለመከልከል ባደረገው ሙከራ ከዚህ የመዉረሻ ጦርነት ጥቂት ቀደም ብሎ ነበር። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቦፓላሳር የአሦራውያን የነበረውን ምድር ለመቆጣጠር ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም።

በዚህ መሃል የንጉሥ ኢዮስያስ መሞት የይሁዳን ሕዝብ ሁከት ውስጥ ከተታቸው። የኢዮስያስ ትልቁ ልጅ ዮአኪን በምርኮ ወደ ግብፅ ተወሰደ። የኢዮስያስ ሌላው ልጅ ኢዮአቄም በመጀመሪያ የግብፅ፥ ከዚያም የባቢሎን መንግሥት አሻንጉሊት ንጉሥ ሆነ። እጅግ ክፉና ኃጢአተኛ ሰው ስለነበር ሕዝቡን እውነተኛውን አምላክ ከማምለክ ይልቅ፥ ብዙ ሐሰተኞች አማልክትን ወደ ማምለክ መራቸው። እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያቱ በኩል ለብዙ ዓመታት እንደተናገረው ፍርዱ በይሁዳ ላይ ወረደ። በ605 ዓ.ዓ. ንጉሥ ኢዮአቄም በባቢሎን ላይ ዓመፀ። የባቢሎን ጦር መሪ የነበረው ናቡከደነፆር በይሁዳ ላይ በፍጥነት ወረደና አሸንፋት። ይህ በእንዲህ እንዳለ አባቱ ናቦፖላሳር ሞተና ናቡከደነፆር የባቢሎን መንግሥት ንጉሠ ነገሥት ሆነ። የጥንቱ ዓለም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ባላየው ሁኔታ የባቢሎንን መንግሥት በማስፋት ታላቁ የባቢሎን መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ነበር።

ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን፣ እንዲሁም የተማሩና እጅግ ባለጠጎች የነበሩ የአንዳንድ አይሁዳውያንን ልጆች ወደ ባቢሎን ወሰደ፡፡ ይህ የመጀመሪያው ምርኮ የተፈጸመው በ605 ዓ.ዓ. ነው። ዳንኤል በድንገት ወደ ባቢሎን ከተማረኩት ከእነዚህ ከተማሩ ወጣቶች አንዱ ነበር።

ናቡከደነፆር ከ605-562 ዓ.ዓ. ድረስ የባቢሎን ንጉሥ ነበር። ዳንኤል በእርሱ አገዛዝ ሥር ሥልጣንን በመያዝ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ውስጥ ሠርቷል። በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት ይሁዳ ከዚህ ሌላ ሁለት ጊዜ ዓምፃለች፡፡ በ597 ዓ.ዓ. የናቡከደነፆር ጦር ይሁዳን ለሁለተኛ ጊዜ በጦርነት ድል አደረጋትና አብዛኞቹ የተማሩና ሀብታሞች የነበሩ ሰዎች በምርኮ ተወሰዱ። ሕዝቅኤል በምርኮ የተወሰደው በዚህ ጊዜ ነበር። በ586 ዓ.ዓ. ደግሞ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሲያምፅ ናቡከደነፆር ትዕግሥቱ አለቀበትና የኢየሩሳሌምን ከተማ በመደምሰስ ከይሁዳ ሕዝብ አብዛኛዎቹን በምርኮ ወሰዳቸው። የእግዚአብሔር ቃል ተፈጸመ። ሕዝቡ ተፈረደባቸው። እግዚአብሔርን ለመከተል ቃል የገቡት ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢሆንም ልባቸው አልተለወጠም ነበር። የተለያዩ ጣዖታትን ማምለካቸውን አላቋረጡም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሰዎችን ተግባር ከመለወጥ ይልቅ ልባቸውን መለወጥ የሚከብደው ለምንድን ነው? ለ) ዛሬም ልባቸው ከእግዚአብሔር ሩቅ የሆነ ብዙ ክርስቲያኖች ድርጊታቸውን የሚለውጡት እንዴት ነው? መግለጫዎችን ስጥ። ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕዝቡ ድርጊታቸውን ብቻ ሳይሆን፥ ልባቸውንም እንዲለውጡ ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላሉ?

ናቡከደነፆር በሞተ ጊዜ የባቢሎን መንግሥት ኃይል እየተዳከመ ሄደ፡፡ ከእርሱ ቀጥሎ የነገሡት ነገሥታት የእርሱን ያህል ብርታትና ብቃት ያላቸው አልነበሩም። ከናቡከደነፆር ቀጥሎ የነገሠው ሰው ከ562-560 ዓ.ዓ. ብቻ በሥልጣን ላይ የቆየው ኢቭል-ሜሮዳሽ ነበር። ይህ ሰው ሲገደል ኔሪግሊሣር በቦታው ተተክቶ ከ560-556 ዓ.ዓ. ነገሠ። ቀጣዩ ንጉሥ ላባሺ ማርዱክ የገዛው ለሁለት ወራት (በ556 ዓ.ዓ.) ብቻ ነበር። የመጨረሻ ንጉሥ ከ556-539 ዓ.ዓ. የቆየው ናቦኒዳስ ነበር። ይሁን እንጂ መግዛት ስላልወደደ አብዛኛውን ኃላፊነቱ አብሮት ለነገሠው ለልጁ ሰጠው። ይህ ንጉሥ ብልጣሶር የተባለው ሲሆን ከአባቱ ጋር ከ553-539 ዓ.ዓ. ነግሦአል። በዚህ ጊዜ የባቢሎን ነገሥታት ምግባረ ብልሹዎችና ደካሞች ስለነበሩ ሕዝቡ ሌላ መሪ እየፈለገ ነበር። ዳንኤል ስላልነገረን፥ ከናቡከደነፆር ሞት በኋላ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ስለነበረው ሚና ብዙ የምናውቀው ነገር የለም። ዳንኤል በብልጣሶር ዘመነ መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ የታወቀ ቢሆንም፥ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ውስጥ ግን የክብር ስፍራ አልነበረውም።

በባቢሎን መንግሥት ላይ የተካሄደው ዓመፅ የተጀመረው በፋርስ ምድር ነበር። የዓመፁ መሪ ታላቁ ንጉሥ ቂሮስ ነበር። ከሜዶን ጋር በመተባበር ከዚህ በፊት በባቢሎን ተይዞ የነበረውን ምድር በሙሉ በጦርነት እያሸነፈ ያዘ። የባቢሎንን ምድር ለማጥቃት በመጣ ጊዜ ሕዝቡ የከተማይቱን በር በመክፈት እንደ ወራሪና አጥቂ ሳይሆን፥ እንደ ነጻ አውጪ አድርጎ ተቀበለው። ቂሮስ የተለያዩ መንግሥታት ሕዝቦችን በምርኮ በመውሰድ ከመግዛት ይልቅ በምርኮ ለያዘው ሕዝብ ቸርና ርኅሩኅ  ነበር። አሦራውያንና ባቢሎናውያን ከዚህ ቀደም በምርኮ ይዘው ያመጧቸውን ሕዝቦች በሙሉ ወደ ገዛ ምድራቸው እንዲመለሱ  ፈቀደላቸው። እግዚአብሔርም ይህንን ሁኔታ ከሰባ ዓመታት በኋላ አይሁድ ወደ ምድራቸው እንደሚመለሱ የተናገረውን ቃል ለመፈጸም ተጠቀመበት። የአይሁድ ሕዝብ መሪዎች በሆኑት በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት ሦስት ቡድኖች ወደ ጳለስጢና ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ዳንኤል ከ80 ዓመት በላይ የሆነው ሽማግሌ ስለነበር ወደ አገሩ ጳለስጢና ለመመለስ ባይችልም የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ሲፈጸሙና ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመለስ በዓይኑ በመመልከት ምስክር ሆኗል። እርሱም በንጉሥ ቂሮስ ክብር ከማግኘቱም በላይ በፋርስ መንግሥት ከነበሩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ ነበር። ንጉሥ ቂሮስ ከ539-530 ዓ.ዓ. በሜዶንና ፋርስ መንግሥት ላይ ነግሦአል።

የፋርስ መንግሥት ከባቢሎን መንግሥትም እንኳ የበለጠ ሆነ። ድንበሩ ከቱርክ ጀምሮ እስከ ሕንድ፥ ወረድ ብሎም እስከ ግብፅ ድረስ ይዘልቅ ነበር። በ331 ዓ.ዓ. ግሪኮች እስካሸነፉት ድረስ ለዘመናት ቆይቷል። የብሉይ ኪዳን ታሪክ የተደመደመው የፋርስ መንግሥት በሥልጣን ላይ ሳለ ነው። በትንቢተ ዳንኤል እንደምንመለከተው ግን ነቢዩ ዳንኤል የግሪክና የሮም መንግሥታትን መምጣት ሳይቀር ተመልክቶ ነበር።

ዳንኤል ከሕይወቱ አብዛኛውን ክፍል የኖረው በገዛ አገሩ ሳይሆን በምርኮ ምድር ነበር። ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለነበርና በአሕዛብ ምድር ሳይቀር እርሱን ስለተከተለ እግዚአብሔር አከበረውና በአሕዛብ መንግሥት ውስጥ በከፍተኛ የሥልጣን ስፍራ አስቀመጠው። ዳንኤል የአሕዛብን ባህልና ሃይማኖት ሳይቀበል ከ80 ዓመታት በላይ ጸንቶ ቆየ። የእርሱ ሕይወት ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነን ብንኖር እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያከብረን የሚያሳይ ምሳሌ ነው።

በትንቢተ ዳንኤል የመጀመሪያ ክፍል የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ የሆነውን ዳንኤልንና ሦስቱን አይሁዳዊያን ጓደኞቹን እንመለከታለን። እነዚህ አራት ሰዎች በአሕዛብ ምድር በመኖራቸው ስለ ገጠማቸው ፈተና በቅድሚያ እንመለከታለን። «የእግዚአብሔርን ሕግጋት» በመተው፥ የአሕዛብን የአኗኗር ስልትና አምልኮ ተለማምደው ይሆን? በምርኮ ላይ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር ታማኞች ነበሩን? በባዕድ አገር በነበሩበት ጊዜ እግዚአብሔር መታዘዛቸውን በማክበር ሕይወታቸውን ተቀጣጥሮ ይሆን? በዚህ ምዕራፍ እግዚአብሔር ለእርሱ ታማኝ የሆኑትን በማክበር ሥልጣንን ይሰጣቸው ዘንድ ድርጊቶችን በመቆጣጠር ረገድ ያለውን ሉዓላዊነት እንመለከታለን።

ከዳንኤል 2-7 የሚገኘው ሁለተኛው ክፍል የተጻፈው በአራማይክ ሲሆን፥ ታሪኮችንና ሕልሞችን የያዘ ነው። እነዚህ ታሪኮች ንጹሕ የሆነው የአይሁዳውያን አምልኮ እንዴት እንደተፈተነና አይሁድ ለእግዚአብሔር እንዴት ታማኞች ሆነው እንደቆዩ የሚያስረዳ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር እምነታቸውን አከበረ፤ ከጉዳትም ጠበቃቸው። ሕልሞቹ ደግሞ እግዚአብሔር የአሕዛብን ታሪክ በሚቈጣጠርበት ሁኔታ ሉዓላዊ እንደሆነና ዘላለማዊ መንግሥቱ በምትመጣበት አቅጣጫ ታሪከን እንደሚያዝዝ ያስረዳሉ።

ሦስተኛው ክፍል ከምዕራፍ 8-12 የሚገኘው ሲሆን፥ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈና በይበልጥ ሕልሞችንና ራእዮችን የሚያካትት ነው። ወደፊት በአይሁድ ላይ ምን እንደሚሆን በመናገር ላይ የሚያተኩር ነው። እግዚአብሔር ከዳንኤል ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ዘመን ድረስ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያለውን የበላይ ተቆጣጣሪነት ያሳያል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከፍተኛ ስደት ቢደርስባቸውም እንኳ አይጠፉም። ይልቁንም እግዚአብሔር የሚሠራው የአይሁድን መንግሥትና ሕዝብ እንደገና ለማቋቋም ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: