የውይይት ጥያቄ፥ ሆሴዕ 1-3 አንብብ። ሀ) በሆሴዕ 1፡2 እግዚአብሔር ሆሴዕን እንዲያደርግ ያዘዘው ምን ነበር? ለ) የሆሴዕን ልጆች ስሞች ከነትርጕማቸው ግለጥ። ሐ) እግዚአብሔር እስራኤልን የሚቀጣባቸው መንገዶች ምን ነበሩ? መ) ለእስራኤል የተሰጡ የወደፊት ተስፋዎች ምን ምን ነበሩ? ሠ) እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረው ግንኙነት ሆሴዕ ከጎሜር ጋር ከነበረው ግንኙነት የተነጻጸረው እንዴት ነው?
1. የሆሴዕ ጋብቻና ልጆቹ (ሆሴዕ 1)
ሆሴዕ መጽሐፉን የሚጀምረው እርሱ በነበረበት ዘመን የነገሡትን የይሁዳ ነገሥታት ስም በመዘርዘር ነው። ሆሴዕ እዚህን ነገሥታት የዘረዘረው እንደ ዓመፀኞቹ የእስራኤል ነገሥታት ሳይሆን በእስራኤል ሁሉ ላይ ሊነግሡ የሚገባቸው ሕጋውያን ነገሥታት ናቸው ብሎ ያምን ስለነበር ሳይሆን አይቀርም።
እግዚአብሔር ሆሴዕን «ጋለሞታ ሴት» እንዲያገባ አዘዘው። ሚስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ግልሙትና የምትወክል ነበረች። ሆሴዕ ተማርን በማግባት ከእርሷ ሦስት ልጆችን ወለደ።
ሀ. ኢይዝራኤል፡- በእስራኤል ይገኙ ከነበሩ ዋና ዋና ከተሞች አንዱ ኢይዝራኤል ነበር። ይህ ስም ለእስራኤላውያን ልዩ ትርጒም ነበረው። ምክንያቱም ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የኢዮርብዓምን ሥርወ መንግሥት የመሠረተው ኢዩ ኤልዛቤልን የገደለው በኢይዝራኤል ነበር (2ኛ ነገሥት 9-10)። ይህ ስም የሚያመለክተው የኢዩ ቤት እንደ አክዓብ ቤት እንዴት እንደሚቀጣና የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ እንደሚደመሰስ ነበር። ሆሴዕ ይህን መልእክት በሚናገርበት ጊዜ የዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት በመገባደድ ላይ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ ተገደለና የኢዩ ንጉሣዊ ቤተሰብ ዘር ተደመሰሰ። የሆሴዕ ትንቢትም በዚህ ዓይነት ተፈጸመ።
ለ. ሎሩሃማ፡- ሎሩሃማ ማለት ያልተወደደ ወይም ምሕረትና ርኅራኄ ያልተደረገለት ማለት ነው። ይህ ሰም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለውን ርኅራኄና ፍቅር እንደሚያቆምና (ዘጸአት 33፡19) እንደሚቀጣቸው የሚያመለክት ትንቢት ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔር እስራኤልን የሚተወው እስከ መጨረሻ አልነበረም፤ ምክንያቱም አንድ ቀን እርሱ ለእስራኤል ያለውን ፍቅር ለመመለስ ዝግጁ ነበርና (ሆሴዕ 2፡23)።
ሐ. ሉዓሚ፡- ሉዓሚ ማለት ሕዝቤ አይደላችሁምን ማለት ነው። ይህ ስም የሚያመለክተው እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረውን ግንኙነት ማቋረጡን ነበር (ዘጸአት 6፡7፤ ኤርምያስ 7፡23)። የጥበቃና የበረከት ቃል ኪዳን ፈርሶ ነበር። እስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆኗ ወይም እርሱ የእርስዋ ጠባቂ መሆኑ ቀርቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መለያየት ቋሚ አልነበረም። አንድ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን «ሕዝቤ» ብሎ የሚጠራት ቀን ይመጣል (ሆሴዕ 1፡10፤ 2፡1፥ 23)።
2. ስለ እስራኤል የተነገረ ትንቢት (ሆሴዕ 2)
እግዚአብሔር ሙሽራው የሆነችውን እስራኤል ስለ ግልሙትናዋ እንደሚቀጣት ተናግሮ ነበር። በግልሙትናዋ ምክንያት እርሷና ልጆችዋ ሊቀጡ የግድ ነበር። ወዳጆችዋ አብረዋት የጋራ ስምምነት ያደረጉ አሕዛብና መሥዋዕት ያቀረበችላቸው አማልክት ነበሩ። እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የነበረውን የበረከት እጅ አነሣ የጣዖት አምልኮዋንም ደመሰሰ።
ነገር ግን አንድ ቀን እስራኤል ትነጻለች። እንደ ታማኝ ሚስት ሆና ራስዋን ለእግዚአብሔር ትሰጣለች። እግዚአብሔርም ለዘላለም ይወዳታል። ተስፋ የገባላትን በረከትም ይመልስላታል። የፍርድ እጁንም ያነሣላታል።
3. ሆሴዕ ከሚስቱ ጋር ታረቀ (ሆሴዕ 3)
ተሜር ሆሴዕንና ልጆችዋን ትታ ወደ ግልሙትና ተሰማራች። በአመንዝራነቷም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወደቀች። ምን እንደደረሰባት አናውቅም። ምናልባት የሌላ ሰው ባርያ ወይም ዕቁባት ሆና ይሆናል። ወይም በታላቅ ሐፍረት ወደ አባቷ ተመልሳ ይሆናል። ሆሴዕ እንደገና የሙሽርነት ጥሉሽ ከፍሎ ሊወስዳት አስፈልጎት ይሆናል። ወይም በዕዳ ተይዛ ለባርነት በመዳረጓ በገበያ ልትሸጥ የቀረበች ይመስላል። እግዚአብሔር ግን ወደ ገበያ በመሄድ ገንዘቡን እንዲከፍልና እንደገና ለራሱ ሚስት አድርጎ እንዲወስዳት ሆሴዕን አዘዘው።
ይህም እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውን ታላቅ ፍቅርና የቅጣት ዓመታት ካለፉ በኋላ እንደገና የራሱ እንደሚያደርጋት የሚያሳይ መግለጥ ነበር። ሆሴዕ 3፡5 የሚያመለክተው እስራኤላውያን ጌታንና ንጉሣቸውን ዳዊትን እንደገና እንደሚፈልጉ ነው። ንጉሣቸው ዳዊት የሚያመለክተው መሢሐዊውን ንጉሥና እግዚአብሔር እንዲያገኙት የሚፈልገውን በረከት የሚያገኙበትን ጊዜ ነው።
ይህም በብዙ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዳችን ያደረገውን ነገር የሚገልጽ ነው። እኛ በኃጢአት ባርነት የጠፋን ነበርን። እግዚአብሔር እንዲያድነን የሚያደርግ አንዳችም በጎ ነገር በእኛ ውስጥ አልነበረም። በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ባልተመሠረተው የክርስቶስ ፍቅር ምክንያት ግን ኢየሱስ ለእኛ ሲል በመሞት የኃጢአታችንን ዕዳ ከፍሎ የእግዚአብሔር ልጆችና የራሱ ሙሽራዎች አደረገን።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ ታሪክ ስለ ሆሴዕ ባሕርይ ምን እንማራለን? ለ) ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምን እንማራለን? ሐ) ስለ ኃጢአት ምን እንማራለን? መ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንማራለን?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡