ሆሴዕ 4-10

ኃጢአት እንደ ተስቦ ነው። የእግዚአብሔርን ሕዝብ በሙሉ እስኪያዳርስ ድረስ በፍጥነት ይስፋፋል። ብዙ ጊዜ ኃጢአት የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት እየቀዘቀዙ በሚሄዱና ኃጢአት ወደ ሕይወታቸው እያደባ እንዲገባ በሚፈቅዱ መሪዎች አማካይነት ሲሆን፥ እነርሱ ደግሞ ሌሉችን ወደ ኃጢአት ይመራሉ። ኃጢአት የሰዎችን የግል ሕይወት መጒዳት ብቻ ሳይሆን፥ ምስክርነታቸውን በማበላሸት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን እውነተኛ አምልኮ ያደናቅፋል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአት በአብያተ ክርስቲያናትና በመንግሥታት ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ ያሳድራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የኃጢአት ውጤት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሲስፋፋ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የኃጢአትን አካሄድ በመጀመር ጕዞውን ባለመግታት መሪዎች ምን ድርሻ ነበራቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሆሴዕ 4-10 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን የተከሰሱባቸውን የኃጢአት ዓይነቶች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ተስፋዎች ምን ነበሩ? ሐ) ከዚህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር ምን መማር እንችላለን? 

1. እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ያቀረበው ክስ (ሆሴዕ 4)

የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን በኃጢአት ወድቀው ነበር። በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት አጕድለው ነበር። እግዚአብሔርን አላወቁትም፥ አላከበሩትምም ነበር (ሆሴዕ 4፡1)። የእውቀት ማነስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያጠፋል (ሆሴዕ 1፡6)። የዚያ ኃጢአት ተጽዕኖ በሕዝቡ መካከል ተስፋፍቶ፥ የሕይወትን የተለያዩ ክፍሎችን ይነካል። ውሸት፥ ነፍሰ ገዳይነት፥ ስርቆትና ማመንዘር በብዙ ተራ ሰዎች ዘንድ የተለመደ ነበር። በመሪዎች፥ በካህናትና በነቢያት ዘንድ ግልጽ የሆነ ኃጢአት ነበር። ምድሪቱን በጣዖት አምልኮ ሞልተዋት ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ምድሪቱ ፍሬ እንዳትሰጥ በማድረግ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ፈረደ።

ማስታወሻ፡- በትንቢተ ሆሴዕና በበርካታ ታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት ውስጥ እስራኤል፥ ኤፍሬምና ሰማርያ የሚሉ ስሞች ተፈራርቀው ይገኛሉ። ኤፍሬም የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ትልቁ ነገድ ነበር። ስለዚህ የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት አንዳንድ ጊዜ ኤፍሬም እየተባለ ይጠራ ነበር። ሰማርያ ደግሞ የሰሜኑ መንግሥት ዋና ከተማ ነበረች። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ሰማርያ የሰሜኑን የእስራኤል መንግሥት ታመለክት ነበር። 

2. እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የሚያመጣው ፍርድ (ሆሴዕ 5)

ከእስራኤል ንጉሥ ጀምሮ እስከ ተራው ሰው ድረስ ኃጢአት ሕዝቡን የሚያጠፋ በሽታ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር እንደሚፈርድባቸው ተናገረ። ያ ፍርድ የጀመረው እግዚአብሔር እነርሱን በተወና ቢጸልዩ እንኳ እንደማይሰማቸው በገለጸ ጊዜ ነበር (ሆሴዕ 5፡6)። ሶርያን በመውጋት እንዲረዳት እስራኤል የጠየቀችው የአሦር መንግሥት መልሶ እስራኤልን ያጠፋል። እንደ እስራኤል ሕዝብ ክፉና ኃጢአተኛ የሆነችው ይሁዳም ይፈረድባታል። 

3. ከኃጢአቷ ትመለስ ዘንድ እግዚአብሔር እስራኤልን ለመናት (ሆሴዕ 6-7) 

እግዚአብሔር በሆሴዕ አፍ እስራኤል እንዳትጠፋ ንስሐ እንድትገባና ወደ እርሱ እንድትመለስ ለምኗት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው በሚቀርብለት የመሥዋዕት ብዛት ሳይሆን፥ ለሕዝቡ ምሕረትን በማድረግ ነበር። ሕዝቡ በመታዘዝ ራሳቸውን እንዲሰጡትና እንዲያከብሩት ይፈልግ ነበር። እስራኤል ግን አሻፈረኝ በማለት ኃጢአትን መረጠች። እግዚአብሔርን በመጥራት ፋንታ ለእርዳታ ሌሎች አሕዛብን ፈለገች። ስለዚህ እግዚአብሔር ቀጣት። 

4. እግዚአብሔር እስራኤልን ለመቅጣት የደነገገው ድንጋጌ ሆሴዕ 8-10) 

እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ወይም ኅብረት ውስጥ ልዩ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ሁላችንም ነፃ ምርጫ እንዲኖረን መፍቀዱ ነው። ምንም ነገር እንድናደርግ አያስገድደንም። ልንታዘዘው ወይም ላንታዘዘው የምንችልበትን ምርጫ ይሰጠናል። ለመምረጥ ነፃ ብንሆንም፥ በምርጫችን የምናደርጋቸው ነገሮች የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች ለመወሰን ነጻ አይደለንም። ያንን የሚወስነው እግዚአብሔር ነው። ምርጫችን መታዘዝ ከሆነ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሸልመን ይወስናል። ምርጫችን አለመታዘዝ ከሆነ ደግሞ እንዴት እንደሚቀጣንና ኃጢአት እንዴት እንደሚጐዳን የሚወስን እግዚአብሔር ነው። እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር አለመታዘዝን መረጡ። ለፍተው ዘርተው ለነፋስ አስረከቡ። የምርጫቸው ውጤት በእግዚአብሔር እጅ ነበረ። ስለዚህ ዓውሎ ነፋስ ላከባቸው (ሆሴዕ 8፡7፤ 10፡12-15)። ከተሞቻቸው ተደመሰሱና ወደ አሦር በምርኮ ተወሰዱ። የአምልኮ ስፍራቸውም ተደመሰሰ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከሆሴዕ 1-10 የተማርካቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን መንፈሳዊ ትምህርቶች የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች ሊያውቋቸውና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዷቸው ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ከሆሴዕ 1-10 ልታገኛቸው የምትችል የመልእክት ርእሶችን ምረጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: