1. የእግዚአብሔር ባሕርይ፡- በትንቢተ ሆሴዕ ውስጥ ሦስት ዋና ዋና የእግዚአብሔር ባሕርያትን እንመለከታለን። የመጀመሪያው፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ያለውን ኃጢአት የሚቀጣ ወይም በበደላቸው ላይ የሚፈርድ መሆኑ ነው። ይህም ሕዝቡን በሕይወታቸው ካለው ኃጢአት ለማጥራት ነው። ሁለተኛው፥ የእግዚአብሔር ምሕረት ነው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ነገር ግን ለብዙ ዓመታት ሕዝቡን በተደጋጋሚ በማስጠንቀቅ በትዕግሥት ጠበቃቸው። በፍርድ ጊዜ እንኳ አልጣላቸውም። ሦስተኛ፥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር ጥልቅና ዘላለማዊ ነው። እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ሕዝቡን የሚወድ፥ በሌላ በኩል ኃጢአት ሲሠሩ የሚጠላቸው አይደለም። እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት ሕዝቡን ይቀጣል። ዳሩ ግን ያ ቅጣት ለእነርሱ ያለውን ታላቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው። እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ ወይም ኅብረት ከፈጠረ ለዘላለም ይወዳቸዋል። ኃጢአት ሲያደርጉ እንኳ አይተዋቸውም (ሮሜ 8፡38-39)።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች እነዚህን ሦስት የእግዚአብሔር ባሕርያት ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር እነዚህን ባሕርያት በሕይወትህ ሲገልጥ ያየኸው እንዴት ነው?
2. ምንዝርና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ከባድና ክፉ ስለ መሆኑ፡- ኃጢአት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ቢሆንም፥ ከሌሎች ይልቅ አስከፊ ውጤት የሚያስከትሉ አንዳንድ ኃጢአቶች አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ከተጠቀሱ ኃጢአቶች ዋነኛው የምንዝርና ኃጢአት ሳይሆን አይቀርም።
ወንድና ሴት በሚጋቡበት ጊዜ አንዳቸው ለሌላቸው ታማኝ ለመሆን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ይገባሉ። እርስ በርስ ይሰጣጣሉ፤ በወሲብ ግንኙነት አንዳቸው ለሌላቸው ታማኞች እንደሚሆኑ ቃል ይገባሉ። በስሜትና በአካል አንድ ይሆናሉ። እግዚአብሔር ጋብቻን የሠራው በዚህ ዓይነት ነው። ወንዱ ወይም ሴቷ ያንን ቃል ኪዳን በሚያፈርሱበትና ምንዝርና በሚፈጽሙበት ጊዜ አንዳቸው ሌላቸውን መዋሸታቸው ብቻ ሳይሆን በጋብቻው ውስጥ የነበረውን ቃል ኪዳንና አንድነት ያፈርሳሉ፤ ወይም ደግሞ አንድ ጊዜ በጋብቻ ውስጥ የነበረውን አንድነት ያፋልሳሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመልካም ግንኙነት መቀጠል አስቸጋሪ ይሆናል። አንዱ ሌላውን ማመን ይከብደዋል፤ ልጆቻቸው ይሠቃያሉ፤ ጋብቻቸውም ሊፈርስ ይችላል። ቤተ ክርስቲያንንና መንግሥትን ብርቱ የሚያደርገው ጠንካራ ቤተሰብ ይፈርሳል። መልካም ጋብቻ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የሚመሠረቱበት ጥሩ መሠረት ነው። ብዙ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ባሎች ቢያመነዝሩ ምንም እንዳይደለ፥ ሚስቶች ግን ይህን ማድረግ እንደሌለባቸው የሚያቀርቡትን አሳብ መጽሐፍ ቅዱስ አይቀበልም። በእግዚአብሔር ፊት ሁለቱም ታማኞች መሆን አለባቸው።
መንፈሳዊ ምንዝርናም በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር ነው። ሁላችንም ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛችን አድርገን በተቀበልን ጊዜ እግዚአብሔርን ብቻ ለማምለክ ቃል ኪዳን ገብተናል ማለት ነው። ከእግዚአብሔርና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ሆነናል። የዚህ ዓለም ነገሮች ለምሳሌ፡- ቍሳዊ ሀብት ወይም ሐሰተኛ አምልኮ ዝንባሌያችንን ከኢየሱስ እንዲያርቀን በምንፈቅድበት ጊዜ መንፈሳዊ ምንዝርና እየፈጸምን ነው ማለት ነው። በእኛና በእግዚአብሐር መካከል ያለው ግልጽ ግንኙነት ይበላሻል። ምስክርነታችን ይበላሻል። የእግዚአብሔርን ስም እናሰድባለን። በቤተሰባችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይደርስባቸዋል።
የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች በምንዝርና የሚወድቁት ለምንድን ነው? ለ) ይህስ ጋብቻቸውን የሚጐዳው እንዴት ነው? ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ አመንዝራነትን አጥብቆ የሚቃወመው ለምን ይመስልሃል? መ) ሥጋዊና መንፈሳዊ ምንዝርና የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? )
ክርስቲያኖች ከሁለቱም ዓይነት ምንዝርና ራሳቸውን እንዴት ሊጠብቁ ይችላሉ?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡