አሞጽ 1-9

የውይይት ጥያቄ፥ አሞጽ 1-9 አንብብ። ሀ) አሞጽ ትንቢት የተናገረባቸውን ሕዝቦች ዘርዝር። ኃጢአታቸው ምን ነበር? ለ) አሞጽ እስራኤልን የከሰሰባቸውን የተለያዩ ወንጀሎች ዘርዝር። ሐ) አሞጽ እስራኤል በኃጢአትዋ ምክንያት ምን ይደርስባታል አለ? መ) አሞጽ ስለ እስራኤል የወደፊት ሁኔታ የተናገራቸው የተስፋ ቃሎች ምን ነበሩ?

1. አሞጽ በአሕዛብ ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (አሞጽ 1፡1-2፡16) 

አሞጽ ማንኛውም ጥሩ ሰባኪ እንደሚያደርገው እግዚአብሔር ያገለግለው ዘንድ ከላከው ሕዝብ በአንድ ጊዜ ራሱን ማግለል አልፈለገም። ስለዚህ መልእክቱን በአሕዛብ ላይ ስለሚመጡ ፍርዶች በመናገር ጀመረ። በዚህ መልእክት በእስራኤል ዙሪያ የሚገኙ ሕዝቦች በሙሉ ተጠቅሰዋል። ይኼኛው የትንቢተ አሞጽ ክፍል ሦስት ዐበይት ክፍሎች አሉት። በቅድሚያ አሞጽ ከአሕዛብ ይጀምራል። ይህ መልእክት አሕዛብን ይጠሉ በነበሩት በእስራኤላውያን ዘንድ በታላቅ ደስታ ተቀባይነት ማግኘቱ አይጠረጠርም። አሞጽ የአሕዛብን ኃጢአት ለማስተዋወቅ የሚጠቀምበት ልዩ አባባል ነበረው «ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት… ኃጢአት» የሚለው። የዚህ አባባል ትርጉም፥ ሕዝቡ የፈጸሟአቸው በርካታ ኃጢአቶች ቢኖሩም፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የሚፈርደው ግን በተለይ ስለ ሠሩትና ሊጠቀሱ ስለሚችሉት ሦስት ወይም አራት ኃጢአቶች ነው ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ የተጠቀሱት ስድስት የአሕዛብ አገሮች ደማስቆ (ሶርያ)፥ ጋዛ (ፍልስጥኤም)፥ ጢሮስ፥ ኤዶም፥ አሞንና ሞዓብ ነበሩ።

በሁለተኛ ደረጃ፥ አሞጽ በደቡብ የይሁዳ መንግሥት ላይ ትንቢት ተናገረ። እስራኤላውያን ይህንንም ቢሆን የተቀበሉት በታላቅ ደስታ ሳይሆን አይቀርም። እስራኤልና ይሁዳ የቆዩ ጠላቶች ነበሩ። ምናልባትም እስራኤላውያን በሚያመልኩት ሐሰተኛ የጣዖት አምልኮ ምክንያት የይሁዳ ሰዎች የበታች አድርገው ይመለከቷቸው ስለነበር ይጠሏቸው ነበር።

በሦስተኛ ደረጃ፥ አሞጽ በእስራኤል ላይ ትንቢት መናገር ጀመረ። ጻድቃንንና ድሆችን በመሸጣቸው ለተጨቆኑትም ፍትሕን በመከልከላቸው ሕዝቡን ይወቅሳቸዋል። እግዚአብሔር በቅርቡ እንደሚፈርድባቸው ይነግራቸዋል። አሞጽ በቀረው የመጽሐፉ ክፍል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በተናገረው ቃል ላይ ያተኩራል። 

2. አሞጽ በእስራኤል ላይ የተናገረው የፍርድ ትንቢት (አሞጽ 3-6)

እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ነበሩ፤ ከማንኛውም ሕዝብ የበለጠ እግዚአብሔር ሞገስ ሰጥቶአቸው ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ነበራቸው፤ የእግዚአብሔር ሕግጋት ነበራቸው፤ እግዚአብሔር ያስጠነቅቋቸው ዘንድ ነቢያትን ልኮላቸው ነበር። እነዚህን ንቀው እግዚአብሔርን ተዉ። ኅበራዊ ፍትሕ-አልበኝነታቸው ለእግዚአብሔር ሕግጋት የነበራቸውን ዝቅተኛ አመለካከት የሚያሳይ ነበር። ዳሩ ግን ብዙ በረከትና ልዩ መብት ሁልጊዜ ተጨማሪ ኃላፊነትን ይዞ የሚመጣ ነው። እስራኤል በነበራት እውቀት መሠረት ስላልኖረች እግዚአብሔር ታላቅ ፍርድ እንደሚያመጣባት ተናገረ።

እግዚአብሔር ማንኛውም ጥፋት የሚመጣው በአጋጣሚ እንዳልሆነ፥ ነገር ግን የፍርድና የማስጠንቀቂያ ምልክት ሆኖ ከእርሱ ዘንድ እንደሚመጣ ያስታውሳቸዋል። ከዚህ ቀደም የገጠማቸው ድርቅ፥ መቅሠፍትና ወረርሽኝ ሁሉ እስራኤላውያን እንዲደነግጡና በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው እንዲድኑ የሚያነሣሣ የእግዚአብሔር ምሕረት ምልክት ነበር። ዳሩ ግን ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። ስለዚህ ዖሶች በመንጠቆ እንደሚጠመዱ፥ እስራኤሳውያንም እየተማረኩ ይሄዱ ነበር። እነርሱ በረከት ይዞ ይመጣል ብለው የሚያስቡት «የጌታ ቀን» የቅጣትና የጥፋት ቀን ሆነባቸው። ወደ እግዚአብሔር በንስሐ ከተመለሱ ግን እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው ተናግሮ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ታላቅ በረከት ከፍ ያለ ኃላፊነትን ይዞ የመምጣቱ መወመሪያ ዛሬም ለእኛ ተመሳሳይ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? ለ) የእግዚአብሔርን ቃል የማወቅና የደኅንነትን እንዲሁም የሥጋዊ ሀብትን በረከት በቀላሉ ማየት እንደሌለብን ይህ ነገር ማስጠንቀቂያ ሊሆነን የሚገባው እንዴት ነው? 

3. አሞጽ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣ ፍርድ አምስት ራእዮችን አየ (አሞጽ 7-9) 

አሞጽ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ጥፋት የተናገረው በቀጥተኛ ትንቢት ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም፥ እግዚአብሔር የሚመጣውን ጥፋት የሚያሳዩ አምስት ራእዮችን ሰጥቶታል።

ሀ. የምድሪቱን ሰብል የሚያጠፉ አንበጦች ራእይ፤ እዚህ አንበጦች በምድሪቱ ውስጥ የሚገኙትን ሰብሎች በሙሉ ያጠፉ ነበር። ነገር ግን በአሞጽ ጸሎት ምክንያት በእስራኤል ላይ ሊመጣ የነበረው ይህ ፍርድ ታገደ። 

ለ. ምድርን የበላ እሳት ራእይ፡- ይህ እሳት ምድርን ሁሉ የሚያጠፋ ነበር፡- እንደገና አሞጽ ጸለየና እግዚአብሔር ይህንን ፍርድ እንደማይልክ ተናገረ። 

ሐ. በቱንቢ የተሠራ ቅጽር ራእይ፡- ቱንቢ የሕንጻ ሥራ በሚሠራበት ጊዜ የግንቡ ማዕዘን በትክክል መጠበቁን ለማረጋገጥ የሚያገለግል መሣሪያ ነው። ይህ ቱንቢ እስራኤልን እንደ ቅጥር በመቁጠር ትክክለኛ መሆኗን ወይም አለመሆኗን ለማረጋገጥ በእግዚአብሔር መመዘኛ መሠረት እስራኤል በመንፈሳዊ በማኅበራዊና በሥነ-ምግባራዊ ይዘቷ ትክክለኛ ስላልነበረች እግዚአብሔር እስራኤልን በማጥፋት ሊቀጣት ወስኖ ነበር። ዳሩ ግን በዚህ ጊዜ ፍርዱ አልተገለጠም። 

አሞጽ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ሲናገር፥ አሜስያስ የተባለው ካህን ስለዚህ ጉዳይ ለንጉሡ ገለጸ። እንዲሁም አሞጽን ተቃወመና በእስራኤል ወይም የጣዖት አምልኮ ማዕከል በነበረችው በቤቴል ላይ ትንቢት እንዳይናገር አዘዘው። አሞጽ ግን ትንቢት ከመናገር በቀር ሌላ ምርጫ እንደሌለው በመግለጽ መልስ ሰጠው። ነቢይ መሆንን አልመረጠም ነበር። ተራ ገበሬ ነበር። እግዚአብሔር ግን ለነቢይት እንደመረጠውና እንደላከው፥ በመሆኑም በእግዚአብሔር ስም መናገር እንዳለበት ገለጠ። አሞጽ አሜስያስን የእስራኤል ሁሉ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም፥ ስለሚመጣው ጦርነትና የእስራኤል መማረክ ግልጽ የሆነ ትንቢት ተናገረ።

መ. የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ራእይ፡- አሞጽ የተለቀመ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበትን ዕንቅብ ተመለከተ። ልክ እንደዚሁ እስራኤል በአሦራውያን ተማርከው ሊሄዱ ተዘጋጅተው ነበር። የፍርድ ጊዜ ደርሶ ነበር። በምርኮአቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል የማወቅ ራብ በምድሪቱ ሁሉ ይስፋፋል፤ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ለማግኘት ወደየስፍራው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም። 

ሠ. ጌታ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ የታየበት ራእይ፡- እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ፍርድን እንደሚያመጣ ሆኖ ተገልጾአል። ሕዝቡ እግዚአብሔር ሰላምና በረከት እንደሚሰጣቸው በሚያስቡበት በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔር የአምልኮ ስፍራዎችንና የእስራኤልን ከተሞች እንደሚያጠፋ ተናገረ። 

4. አሞጽ ስለ ወደፊቱ የእስራኤል ተሐድሶ ተነበየ (አሞጽ 9፡11-15)

ትንቢተ አሞጽ የሚጠቃለለው በመጽናናትና በተስፋ ቃል ነው። እግዚአብሔር የእስራኤልን ቅሬታ ወደ ምድሪቱ በመመለስ እንደሚመሠርታቸው ተናግሯል። ከዳዊት ዘር በሆነው (የወደቀችው የዳዊት ድንኳን ተብሎ በተጠራው) ንጉሥ በመሢሑ በኢየሱስ ይገዛሉ። የጠላታቸውን ምድር እንደገና በመውረስ፥ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ውስጥ የተሰጡትን በረከተች ያጭዳሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በትንቢተ አሞጽ ውስጥ የተመለከትሃቸውና የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች ሊያውቁአቸው የሚገቡ አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? ለ) ይህንን መጽሐፍና እነዚህን ትምህርቶች ለቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዐቅድ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

2 thoughts on “አሞጽ 1-9”

Leave a Reply

%d bloggers like this: