የትንቢተ ሆሴዕ አስተዋጽኦ እና ዋና ዋና አላማዎች

I. የትንቢተ ሆሴዕ አስተዋጽኦ 

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ሆሴዕ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የምታገኘውን በማንበብ እርሱን በሚመለከት የተጠቀሱትን ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝር።

ትንቢተ ሆሴዕ በማያሻማ መንገድ በሁለት ክፍሎች ተከፍሏል።

ክፍል 1፡- ሆሴዕ 1-3 ስለ ሆሴዕ ቤተሰብ ታሪክ የቀረበ ትረካ ነው። ሆሴዕ ከሚስቱ ከጎሜር ጋር የነበረው ግንኙነት እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረው ግንኙነት ምሳሌ ነበር። የሆሴዕ ልጆች በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ፍርድ አስቀድመው የሚናገሩ ምልክቶች ሆነው ቀርበዋል።

ክፍል 2:- ሆሴዕ 4-14 ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጡትን ትንቢቶች የሚያካትት ሲሆን፥ እነዚህም ስለ መጥፋታቸው በመጨረሻም ስለ መመለሳቸው የሚናገሩ ናቸው። የሚከተለውን የትንቢተ ሆሴዕ አስተዋጽኦ መርምር፡-

1. በሆሴዕ ቤተሰብ ታሪክ አማካይነት የተሰጡ ትንቢቶች (ሆሴዕ 1-3)፡

ሀ. በሆሴዕ ልጆች ምክንያት የተሰጠ ትንቢት (ሆሴዕ 1፡1-2፡1)፥ 

ለ. ሆሴዕ ከአመንዝራይቱ ሚስቱ ከጎሜር ጋር በነበረው ግንኙነት ተምሳሌት የተሰጠ ትንቢት (ሆሴዕ 2፡2-3፡5)። 

2. ስለ እስራኤል የተሰጡ ትንቢቶች (ሆሴዕ 4-14)፡-

ሀ. የእስራኤልን አለመታመን የሚመለከት (ሆሴዕ 4-6፡3)። 

ለ. አሦር በእስራኤል ላይ ስለምትፈጽመው ጥፋት የተነገረ ትንቢት (ሆሴዕ 6፡4-10፡15)፣ 

ሐ. እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለው ታማኝነትና ፍቅር የእስራኤል መመለስ ማለት ነው (ሆሴዕ 11-14)። 

II. የትንቢተ ሆሴዕ ዓላማ

እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ቃል ኪዳን አድርጎ ነበር። በዚያ ቃል ኪዳን ከተጠቀሱት ነገሮች አንዱ እግዚአብሔር ሕዝቡ በእርሱ ላይ ባላቸው መታመን እንደሚባርካቸው ነበር። ዳሩ ግን በእርሱ ላይ ካመፁና ሐሰተኞች አማልክትን ካመለኩ ደግሞ እንደሚቀጣቸው ተናግሮ ነበር። ይህ ቃል ኪዳን ባልና ሚስት በመጀመሪያ በሚጋቡበት ጊዜ ከሚገቡት ቃል ኪዳን ጋር የሚመሳሰል ነበር። የሁለቱንም ግን ታማኝነት የሚጠይቅ ቃል ኪዳን መሆን ነበረበት። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን በምሳሌነት የእስራኤል ባል ሆኖ የምናየው በዚህ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውን ፍቅር ከሕዝቡ አባቶች ጋር በገባው ቃል ኪዳን በኩል አሳይቷል (ሆሴዕ 12፡2-6)። የእስራኤልን ሕዝብ ገና ከለጋነታቸው ጊዜ ጀምሮ ጠበቃቸው (ሆሴዕ 11፡1-4፤ 12፡9፤ 13፡4)።

ከሰሎሞን ሞት በኋላ የእስራኤል መንግሥት ከተከፈለበት ከ931 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከ ሆሴዕ ዘመን 750 ዓ.ዓ. ድረስ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይታገሥ ነበር። ለእርሱ ታማኝ እንዳልሆኑ ይገልጡላቸውና ያስጠነቅቁአቸው ዘንድ በርካታ ነቢያትን በተደጋጋሚ ይልክ ነበር። የእስራኤላውያንን ልብ ለመመለስ ኤልያስን፥ ኤልሳዕን፥ አሞጾንና ሌሎች ነቢያትን ላከላቸው። እነርሱ ግን በንስሐ ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። ይልቁንም በከፊል እግዚአብሔርን፥ በከፊል ደግሞ ሌሎች ጣዖታትን ለማምለክ ፈለጉ። እስራኤል አግብታ በትዳር ላይ እያለች ለባሏ ታማኝ ባለመሆን ከሌሎች ወንዶች እንደምትፈልግ ሴት ነበረች።

በመጨረሻ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት አለቀ። የፍርድ ጊዜ መጣ። እግዚአብሔር እስራኤላውያን በንስሐ ይመለሱ ዘንድ የመጨረሻ ዕድል ለመስጠት ሆሴዕን ላከላቸው። አለበለዚያ ወደ ምርኮ በመውሰድ እንደሚቀጣቸው ተናገረ።

ትንቢተ ሆሴዕ ታማኝ ላልሆነችው እስራኤል እግዚአብሔር የሰጠው መልእክት ነው። እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ምርኮን በማምጣት ከመቅጣቱ በፊት ያስተላለፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነበር። የማይታዘዙ ከሆነ በምርኮ እንደሚወሰዱ በሲና ተራራ በተደረገው ቃል ኪዳን ላይ እንደ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ተሰጥቶ እንደነበር የሚታወስ ነው (ዘዳግም 28፡64)።

የእስራኤልን አለመታመንና ክፋት በሚታይ መንገድ ለመግለጥ፥ እግዚአብሔር የሆሴዕን ቤተሰብ በምሳሌ ተጠቀመበት። የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሚስት እንደሆነችውና ከአሕዛብ ጋር በነበራት ግንኙነት ሌሎች አማልክትን በማምለክ ምንዝርና እንደፈጸመችው እስራኤል እንዲሁም የሆሴዕ ሚስት የነበረችው ጎሜርም ለሆሴዕ ታማኝ አልነበረችም። ሁለቱም አመንዝራዎች ነበሩ። ከዚህ የተነሣ ለተወሰነ ጊዜ ግንኙነቱን ለማቋረጥ ወሰነ። የሆሴዕ የመጀመሪያ ክፍል የተጻፈው እግዚአብሔር ፍቺን እንደሚደግፍ በሚመስል መልኩ ነው። ሆሴዕ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የነበረውን ግንኙነት ማቋረጡን ለማሳየት በአይሁድ ባህላዊ የፍቺ ዘዴ ተጠቀመ (ሆሴዕ 2፡2)። ይህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ክስ እንደመሠረተ ተደርጎ የቀረበ ዓይነት ነው (ሆሴዕ 4፡1፥ 4፥ 15፤ 5፡1፥ 7)። የሆሴዕና የጎሜር ልጆች እግዚአብሔር ከዚያ በኋላ ለእስራኤል ምሕረት እንደማያደርግ፥ ከእንግዲህ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች እንዳይደሉና በኢይዝራኤል እንደሚቀጡ የሚያሳዩ ምሳሌያዊ ስሞች ነበሯቸው።

ዳሩ ግን እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የሚፈርደው ፍርድ ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም እንኳ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የሚኖረው መለያየት ዘላቂ አልነበረም። ሆሴዕ ለጎሜር የነበረውን ዘላቂ ፍቅር ከባርነት በመዋጀትና እንደገና በማግባት እንዳሳየ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንደገና የቃል ኪዳን ግንኙነት ያደርጋል። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረው ፍቅር ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ ከቶ አይችልም። እግዚአብሔር አንድ ቀን ወደ እስራኤል ይመልሳቸውና ይፈውሳቸዋል፤ እንዲሁ ይወዳቸዋል (ሆሴዕ 14፡4)። ባለፈው የእስራኤል ታሪክ የታየው የማይለወጠው የእግዚአብሔር ፍቅር ወደፊት ለእነርሱ ላለው ፍቅር ዋስትና ነበር።

ሆሴዕ እስራኤል በእግዚአብሔር ላይ የፈጸመችውን ምንዝርና በምሳሌ መልክ ማሳየት ብቻ ሳይሆን፥ ሕዝቡንና መሪዎቹን ስለ መንፈሳዊ አመንዝራነታቸው በቀጥታ ይገሥጻቸዋል። በእግዚአብሔር ላይ ለማመፅ ከአሕዛብ ጋር ቃል ኪዳን አድርገው ነበር። በአልን የመሳሰሉ ባዕድ አማልክትንም ያመልኩ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ አሦር በማስማረክ እነርሱን የሚቀጣበት ጊዜ ደርሶ ነበር (ሆሴዕ 5፡8-9)።

5ኛ ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች ዛሬ መንፈሳዊ ምንዝርና መፈጸም የሚችሉት እንዴት ነው? ለ) ይህ ነገር ሲፈጸም ያየህባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ። ሐ) የቤተ ክርስቲያን አባላት ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው እንዲቆዩ ለማድረግ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምን ሚና መጫወት አለበት? መ) የመንፈሳዊ ምንዝርናን አደገኛነት ለማስተማር ትንቢተ ሆሴዕን እንዴት ልትጠቀምበት የምትችል ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d