Site icon

የትንቢተ አሞጽ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ያዕቆብ 1፡27 አንብብ። ሀ) ሐዋርያው ያዕቆብ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕና ነውርም የሌለበት አምልኮ ምንድን ነው ይላል? ለ) ይህን ያለው ለምን ይመስልሃል? ይህን ጥቅስ በግል በምትወስደው ክርስቲያናዊ እርምጃህ ከሕይወትህ ጋር ለማዛመድ የፈለግኸው እንዴት ነው? መ) ቤተ ክርስቲያንህ ይህን ጥቅስ ለመፈጸም የምትጥረው እንዴት ነው?

ትንቢተ አሞጽ ስለ እውነተኛ፥ ንጹሕና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ስላለው ሃይማኖት ይናገራል። ብዙዎቻችን እግዚአብሔር ጉዳይ ያለው ከልባችን ጋር ብቻ የሆነ ይመስለናል። በእግዚአብሔር ላይ ትክክለኛና ተገቢ የሆነ እምነት ካለን፥ ከኃጢአት ንጹሐን ሆነን ለመኖር ከጣርን፥ ለማያምኑ ሰዎች ከመሰከርን ብቻ እግዚአብሔር በእኛ ደስ የሚለው ይመስለናል። እነዚህ ሁሉ አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም፥ በእግዚአብሔር ፊት ግን እነዚህ ብቻ በቂ አይደሉም። መዘመር፥ መጸለይ፥ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ወይም መመስከር የመሳሰሉትን ተገቢ የሆኑ ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን ብንፈጽምም እንኳ ድሆችን፣ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና የሙት ልጆችን ለመሳሰሉ እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማድረግ ካልጣርን እውነተኛውን ሃይማኖት እየተከተልን አለመሆናችንን እንደ ያዕቆብ መልእክት ሁሉ ትንቢተ አሞጽም ያስተምረናል። በእግዚአብሔር አመላካከት እውነተኛ ሃይማኖት የሚጀምረው ከልብ በሚደረግ እምነትና አምልኮ ቢሆንም፥ ዳሩ ግን ይህን መሰሉ ልብ በችግር ውስጥ ስለሚገኙ ሰዎች ሁልጊዜ ግድ የሚለውና እነርሱንም ለመርዳት ፈጥኖ የሚደርስ መሆን አለበት። ብዙዎቻችን ግን እነዚህን ጥቅሶች በተግባር ላይ አናውላቸውም።

በአሞጽ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ይህን አላደረጉም ነበር። ስለዚህ አሞጽ ራሳቸውን እንደ ጻድቃን የሚጥሩና ድሆችን በመናቅ ይጨቁኑ የነበሩትን መሪዎች ይከሳል። እግዚአብሔር ይበልጥ ደስ የሚሰኘው በሃይማኖታዊ አምልኮ (ለምሳሌ መሥዋዕቶችን በማቅረብ) ሳይሆን በፍርድ፥ በጽድቅ፥ በፍቅርና ለድሆች በሚደረግ ምሕረት ነው (አሞጽ 5፡21-24 ተመልከት)። 

የትንቢተ አሞጽ ጸሐፊ 

የትንቢተ አሞጽ ጸሐፊ አሞጽ የተባለው ሰው ነው። አመጣጡ ከደቡብ የይሁዳ መንግሥት ሲሆን፥ የተወለደባት ከተማ በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተ ልሔም 9 ኪ.ሜ. ያህል ርቃ በስተደቡብ የምትገኝ ቴቁሔ የምትባል ስፍራ ነበረች። በዘመኑ የነበሩት አብዛኛዎቹ ነቢያት የነቢይነትን አገልግሎት ያከናውኑ የነበረው ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ሲሆን፥ አሞጽ ግን እንደዚያ አልነበረም። ይህንን ስንል አሞጽ የነቢይነት አገልግሎት ሙያው አልነበረም ወይም ቤተሰቡ ከነቢያት ወገን አልነበረም ማለታችን ነው (አሞጽ 7፡14-15)። ይልቁንም አሞጽ ገበሬ ነበር። ላም ጠባቂና የሾላ ፍሪ ለቃሚ ሲሆን፥ አመጣጡ ከይሁዳ ድሀ ቤተሰብ ነበር።

ይህ ሐቅ እግዚአብሔር ዕቅዱን ለመፈጸም የሚጠቀመው በተማሩት ሰዎች ብቻ እንዳይደለ ሊያስታውሰን ይገባል። ብዙዎቻችን እግዚአብሔር የሚጠቀመው በተማሩ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በሠለጠኑ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክብር ስፍራ ባላቸው ሰዎች ብቻ የሆነ ይመስለናል። ነገር ግን ይህ የሰይጣን ሽንገላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እግዚአብሔር ሞኞችን፥ ያልተማሩትንና የተጣሉትን ሰዎች ከፍተኛ ተግባር እንዲፈጽሙለት እንደሚመርጣቸው ነው። በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ጥበበኞችና ሀብታሞች የሆኑትን ሰዎች በማስገረም፥ በሥራው ውስጥ የሚታየውን ክብር ሁሉ ለራሱ ይወስዳል።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡17-31 አንብብ። ሀ) አሞጽ እነዚህን ጥቅሶች የሚገልጠው እንዴት ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የእነዚህ ጥቅሶች እውነትነት ሲረጋገጥ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) በርካታ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አገልጋዮችን ለመምረጥ በትምህርት፥ በሀብትና፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሥልጠና ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

እግዚአብሔር አሞጽን ጠርቶ ወደ ሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ላከው። አሞጽ ያገለገለው የእስራኤል የሃይማኖት ማዕከል በነበረችው በቤቴል ይመስላል። አሞጽ በእስራኤልና በይሁዳ ውስጥ የነበረውን ሥነ-ምግባራዊ ውድቀትና ማኅበረሰባዊ ብልሹነት እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በቅርቡ ከሚያመጣው ፍርድ ጋር በግልጽና በታማኝነት ያወጀው በዚህ ስፍራ ነበር። የአሞጽ መልእክት በሚገባ ተቀባይነት አላገኘም። ወደ ቤቱ እንዲሄድ በማስፈራራት ከነገረው ከአሜስያስ ጋር ተጋፍጧል (አሞጽ 7-12)። ለዳግማዊ ኢዮርብዓም ስለ አሞጽ ተነግሮት ነበር። በአሞጽ ላይ ምን እንደደረሰበት አናውቅም። ወደ ይሁዳ ተባርሮ ወይም ኢዮርብዓም አስሮት እንደሆነ አናውቅም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው አንዳችም ነገር የለም። ዳሩ ግን አሞጽ ለእስራኤላውያን ያስተላለፈውን መልእክት የያዘው መጽሐፍ በእጃችን አለ። የአሞጽ መልእክት አጭርና ቀጥተኛ ነው። አሞጽ በሕዝቡ ላይ ካቀረባቸው ወቀሳዎች አብዛኛዎቹ ዛሬም በእኛ ላይ ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው።

ከትንቢተ አሞጽ መግቢያ (አሞጽ 1፡1) በመነሣት፥ ከ750-748 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ማለት ዳግማዊ ኢዮርብዓም እንደሞተ የአሞጽ አጭር አገልግሎት እንደተከናወነ መገመት እንችላለን። አሞጽ ይህንን ትንቢት የጻፈው በእስራኤል ያካሄደውን የስብከት አገልግሎት ጨርሶ እንደተመለሰ ሳይሆን አይቀርም። ትንቢቱ የተጻፈው ጳለስጢንን ከፍተኛ የመሬት መናውጥ ከመታት በኋላ ነበር። አሞጽ ይህን የመሬት መንቀጥቀጥ የትንቢቱ ፍጻሜና የእግዚአብሔርን ፍርድ ጅማሬ ከሚያሳዩ ምልክቶች አንዱ አድርጎ ቈጥሮት ነበር (አሞጽ 2፡13፤ 9፡1)። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ እጅግ ታላቅ ስለነበር ለብዙ ምእተ ዓመት ይወሳ ነበር (ዘካርያስ 14፡5)። 

በዚህ ጊዜ በእስራኤልና በይሁዳ ይሠራ የነበረ ነቢይ አሞጽ ብቻ አልነበረም፡፡ ዮናስና ሆሴዕ በእስራኤል፥ በይሁዳ ደግሞ ሚክያስና ኢሳይያስ ያገለግሉ ነበር። አሞጽ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ሕዝቡን የሚያግባባ ከእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ውስጥ አንዱ ነበር። ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣባቸውን ፍርድ በመናገር ሕዝቡን ያስጠነቅቅ ነበር።

የትንቢተ አሞጽ ታሪካዊ ሥረ መሠረት

አሞጽ ትንቢቱን የጻፈበትን ዘመን የሚቆጥረው ከዳዊትና ከሰሎሞን አገዛዝ በኋላ ከተነሡት ሁለት ታላላቅ የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት ዘመነ መንግሥት ጋር በማያያዝ ነው። ነገሥታቱ የይሁዳው ዖዝያንና የእስራኤሉ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነበሩ። ሁለቱም ነገሥታት በሥልጣን ላይ የቆዩት ከ40 ዓመታት በላይ ነበር። ሁለቱም ይገዙ የነበረው ታላላቅ የአሕዛብ መንግሥታት ባልነበሩበት ዘመን ነበር። ስለዚህ ዖዝያንም ሆነ ዳግማዊ ኢዮርብዓም የአገራቸውን ድንበር በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን ተይዞ እስከነበረው ዳርቻ ድረስ ለማስፋት ችለው ነበር። በተጨማሪም ለሕዝባቸው የፖለቲካ መረጋጋትን፥ የጦር ኃይል ገናናነትንና የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማምጣት ችለው ነበር። ምናልባት ይህ በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ የሕዝቦች መደብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። የኢኮኖሚ ሁኔታው እጅግ መልካም ስለነበር ነጋዴዎች በሀብታቸው በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ በመሄድ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለመታውቅ በቁ። ደግሞም በባለጠጎችና ብዙውን ጊዜ ገበሬዎች በነበሩት ድሆች መካከል የነበረው የኢኮኖሚ ልዩነት እየሰፋ ሄደ። ነጋዴዎች መሪዎችን እንደፈለጉ በመጠምዘዝ ድሆችን እያጎሳቆሉ መሬታቸውንና ቤቶቻቸውን ቀሙ። በመሆኑም፥ እነዚህ ሀብታም መሪዎች ድሆችን መጨቆን ጀመሩ።

ስለዚህ በእስራኤል ምድር የፖለቲካና የኢኮኖሚ መረጋጋት ቢኖርም እንኳ ሕዝቡ በመንፈሳዊ፥ በማኅበራዊና በሥነ-ምግባር ክፋት ተሞልተው ነበር። ከጠላቶቻቸው ደጋፊዎቻቸው ዋስትና እንዳላቸው ተሰማቸው። በመሆኑም የእግዚአብሔርን ጸጋና ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጠላቶቻቸው እንዴት እንዳዳናቸው ዘነጉ። የእስራኤል ብልጽግና ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ብልሹነተን አባባሰው። እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ እንደሚፈርድ የተናገረውን ቃል ዘነጋች። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት የሚያበቃበት ጊዜ ደረሰ። ከድሀው መደብና በሀብታሞች ይጨቆኑ ከነበሩት መካከል አንዱ የነበረው አሞጽ እነዚህን ክፉ ቀናት በመቃወም እንዲናገር በእግዚአብሔር ተመረጠ። ሁለቱም ብሔሮች ማለት እስራኤልና ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች እንደነበሩ፥ የፍርድ ጊዜም እንደደረሰ ተናገረ (አሞጽ 8፡1-2፤ 3፡9-15)። ከዚህም በኋላ፥ እስራኤል ተደምስሳ ሕዝቡ በምርኮ ወደ አሦር በመወሰዳቸው የአሞጽ ትንቢት በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በከፊል ተፈጸመ።

የውይይት ጥያቄ፥ የዳግማዊ ኢዮርብዓምን ዘመን ከዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋር አወዳድር። ሀ) የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ለ) የሚለያዩትስ፣ ሐ) ከዚህ የእስራኤል ታሪክ፣ ሰላምና ብልጽግና ሊኖር የሕዝቡ ሥን ምግባራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ብዙውን ጊዜ ምን እንደሚደርስበት ልንማር እንችላለን? 

የውይይት ጥያቄ፣ ስለ አሞጽ የተሰጠውን መረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በዚያ ስፍራ የተጠቀሱትን ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር። 

የትንቢተ አሞጽ አስተዋጽኦ 

1. አሞጽ በአሕዛብ ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (አሞጽ 1-2)፥

ሀ. በደማስቆና በሶርያ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡3-5)፥ 

ለ. በጋዛና በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡6-8)፥ 

ሐ. በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡9-10)፥ 

መ. በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡11-12)፥ 

ሠ. በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 1፡13-15)፥ 

ረ. በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 2፡1-3)። 

ሰ. በይሁዳ ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 2፡4-5)፥ 

ሸ. በእስራኤል ላይ የተነገረ ትንቢት (አሞጽ 2፡6-16) ናቸው። 

2. በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው ፍርድ አሞጽ የተናገራቸው ትንቢቶች (አሞጽ 3-6)

ሀ. አሞጽ ለምን ፍርድ እንደሚገባቸው ይናገራል (አሞጽ 3)። 

ለ. አሞጽ እስራኤላውያን ከዚህ ቀደም ከደረሰባቸው የእግዚአብሔር ቅጣት እንዳልተማሩ ለማሳየት የቀድሞ ታሪካቸውን ያነሣል (አሞጽ 4)። 

ሐ. አሞጽ ሕዝቡ ንስሐ ይገቡ ዘንድ ጥሪ ያደርጋል (አሞጽ 5)።

መ. አሞጽ የእስራኤልን ክፋት ይዘረዝራል (አሞጽ 6)። 

3. አሞጽ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣ ፍርድ ያያቸው አምስት ራእዮች (አሞጽ 7-9) 

ሀ. የምድሪቱን ሰብል የሚያጠፋ የአንበጣ መንጋ ራእይ (አሞጽ 7፡1-3)፡ 

ለ. ምድርን የምትበላ እሳት ራእይ (አሞጽ 7፡4-6)፥ 

ሐ. የቱንቢ ቅጽር ራእይ (አሞጽ 7፡7-17) 

መ. የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት እንቅብ ራእይ (አሞጽ 8፡1-14)

ሠ. በመሠዊያው አጠገብ የቆመው የጌታ ራእይ (አሞጽ 9፡1-10) ናቸው። 

4. አሞጽ ወደፊት ስለሚሆነው የእስራኤል መመለስ ያያቸው ራእዮች አሞጽ (9፡11-15)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/3R6VJYEMMx89RRBf9
Exit mobile version