የትንቢተ አሞጽ ዓላማ እና ዐበይት የሥነ መለኮት ትምሕርቶች

የትንቢተ አሞጽ ዓላማ 

ሰላምና ብልጽግና ሁልጊዜ በአንድ ሕዝብም ሆነ ግለሰብ ላይ የሚወርዱ የእግዚአብሔር በረከት ምልክቶች አይደሉም። አሞጽ በእስራኤል ላይ ትንቢት እንዲናገር በተጠራ ጊዜ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች የፖለቲካ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ብልጽግና ያገኙበት ወቅት ነበር። በመካከላቸው ታላቅ ኃጢአት ስለነበር፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ነበር። ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔር አሞጽን ከይሁዳ ወደ እስራኤል በመላክ የፍርድ ጊዜ መድረሱን እንዲነግራቸው አደረገ። ምድሪቱ በጣዖት አምልኮና በማኅበራዊ ኃጢአቶች ተሞልታ ነበር። መሪዎች ፍትሕ በጎደለው መንገድ ይገዙና ኃይላቸውን ለግል ጥቅም ማግኛ ይገለገሉበት ነበር። ነጋዴዎች እየጨመረ የሚሄድ ሀብታቸውን ድሆችን ያላግባባ ለመበዝበዝ፣ ባሪያ ለማድረግና ያላቸውን ጥቂት ሀብትና ንብረት ለመንጠቅ ይጠቀሙበት ነበር። እስራኤላውያን ለምን እንደሚፈረድባቸውና ወደ ምርኮ እንደሚወሰዱ እግዚአብሔር በአሞጽ በኩል የተናገረው በዚህ ወቅት ነበር። ንስሐ እንዲገቡ ለመናቸው ጠየቃቸው። እነርሱ ግን አሞጽን ወደ ይሁዳ አባርረው የኃጢአት መንገዶቻቸውን ስለቀጠሉ፥ የተሰጣቸውን ዕድል አልተጠቀሙም። በጥቂት ዓመታት ውስጥ አሦር ሰላምና ብልጽግናን ከእስራኤል ላይ ቀማች። በ722 ዓ.ዓ. ብሔረ እስራኤል ተደመሰሰ፤ ሕዝቡም በምርኮ ተጋዘ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሰላምና ብልጽግና የሞላበት ሕይወት መኖር ማለት እግዚአብሔር በእነርሱ ተደስቶአል ማለት እንደሆነ የሚመስላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ሁልጊዜ እውነት ነውን? መልስህን አብራራ። ሐ) ሰላምና ብልጽግና በክርስትና ሕይወት መንፈሳዊ ዕድገት ውስጥ ብዙ ጊዜ ወሳኝ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

በትንቢተ አሞጽ ውስጥ የሚገኙ ዐበይት የሥነ-መለኮት ትምህርቶች

1. እግዚአብሔር በድሆች ላይ የሚፈጸመውን ፍትሕ-አልበኝነትን ይጠላል።

የውይይት ጥያቄ፥ አሞጽ 2፡6-7፤ 3፡10፤4፡1፤5፡7፥11-12፤ 6፡14፤8፡46 አንብብ። ሀ) አሞጽ እስራኤልን የሚከስባቸውን ማኅበረሰባዊ ኃጢአቶች ዘርዝር። ለ) ፍትሕን ያለ አግባብ በማዛባታቸው የተከሰሱትን ሰዎች ዘርዝር።

አብዛኛዎቹ ነቢያት ያወገዙት የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንፈሳዊ ኃጢአት ቢሆንም፥ የአሞጽ መልእክት የሚያተኩረው በእስራኤላውያን ማኅበራዊና ሥነ-ምግባራዊ ኃጢአት ላይ ነበር። አሞጽ «ለማኅበራዊ ፍትሕ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ» ተብሉ ይጠራል።

ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት፥ እስራኤላውያንም ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን አምልኮ ከዕለታዊ ተግባራቸው ይለዩት ነበር። ውጫዊ የሆነውን ሥርዓት እስከፈጸሙ ድረስ፥ እግዚአብሔር እንደሚቀበላቸውና ደስ እንደሚሰኝባቸው ያስቡ ነበር። ስለዚህ በሃይማኖታዊ በዓላት ይገኙ፥ መሥዋዕቶችን ያቀርቡ፥ ይጾሙና ይጸልዩ ነበር። ሥርዓተ አምልኮ በማያካሂዱበት ጊዜ ግን እግዚአብሔርን ደስ በማያሰኝ ሁኔታ ይኖሩ ነበር። እግዚአብሔር አድልዎ የሌለበት መልካም ኅብረተሰብ ለመመሥረት ይረዳቸው ዘንድ ሕግን ቢሰጣቸውም፥ የእስራኤል ምድር ግን ፍትሕ ጐድሏት ነበር። ሀብታም የነበሩ አይሁዳውያን ድሆችንና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ይጨቁኑ ነበር። ይህን የሚያደርጉትም በሀብታቸው ላይ ሌላ ሀብት ለመጨመር ያገኙትን ይህን ተገቢ ያልሆነ ዕድል ለመጠቀም ነበር። ድሆችን ባሪያዎች አድርገው ይሸጡ ነበር። የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ለሀብታሞቹ የቆሙ በመሆናቸው፥ አድልዎ የሞላበት ፍርድ ይፈርዱ ነበር፤ ድሆች ደግሞ ከፍተኛ ቀረጥ እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር። የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ድሆችን በመርዳት ፈንታ፥ እነርሱን የሚጐዳ ነገር ያደርጉ ነበር። ኑሮአቸውን ለማሻሻል ዕድሉ ለሌላቸው፥ ለድሆች፥ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶችና ለሙት ልጆች ርኅራኄ የሚያሳይ ማንም አልነበረም። ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በትንቢተ ሆሴዕ እንደምንመለከተው ስለ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ስለ ማኅበራዊ ኃጢአታቸውም እንደሚቀጣቸውና ወደ ምርኮ እንደሚወሰዱ ተናገረ።

መጽሐፍ ቅዱስ፥ የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን፥ እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን መውደድ እንዳለብን ይነግረናል (ማርቆስ 12:30-31 ተመልከት)። እግዚአብሔር በየእሑዱ ከምናደርገው ውጫዊ የአምልኮ ሥርዓታችን ይልቅ ከእርሱ ጋር ስላለን ውስጣዊ ግንኙነት ይገደዋል። ይህ ውስጣዊ ግንኙነት እውነተኛ እንዲሆን በዙሪያችን ከሚገኙ ሰዎች ጋር ትክክለኛ የሆነ ግንኙነት ሊኖረን ያስፈልጋል። ይህ ትክክለኛ ግንኙነት ከሰዎች ሁሉ ጋር በፍትሕ መኖርን፥ በተለይ ደግሞ በዙሪያችን የሚገኙትን ድሆችና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች መርዳትን ይጨምራል። ድሆችን የማንረዳ ከሆነ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ትክክል ይሆናል ማለት ያጠራጥራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሉቃስ 10፡25-37 አንብብ። ሀ) እዚህ ጥቅሶች ሌሎችን ለመርዳት ስላለብን ኃላፊነት የሚያስተምሩን ምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህና ባለህበት ኅብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ድሆችና ኑሮ ያልተሳካላቸውን ሰዎች ዘርዝር። ሐ) አሞጽ ዛሬ በምድር ላይ የሚኖር ቢሆን ኖሮ፥ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በአገሪቱ መሪዎች ላይ ምን ዓይነት መልእክት የሚያቀርብ ይመስልሃል? መ) በዚህ ዘመን የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች በአሞጽ ዘመን የነበሩትን አይሁድ የሚመስሉባቸውን መንገዶች ጥቀስ። ሠ) ባለህበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለፍትሕ-አልበኝነት የተጋለጡትን ሰዎች ለመርዳት ቤተ ክርስቲያንህ ምን ማድረግ ያለባት ይመስልሃል? ረ) እግዚአብሔር ማኅበራዊ ፍትሕ-አልበኝነትን አጥብቆ የሚቃወመው ለምን ይመስልሃል?

የሰዎች ሁሉ ፈጣሪ ለሆነው እግዚአብሔር፥ ሰዎች ሁሉ እኩል የመዳኘታቸው ጉዳይ አጥብቆ ይገደዋል። ክፋትንና ፍትሕ-አልበኝነትን ይጠላል። የእርሱ ፍላጎት «ጽድቅ እንደማይደርቅ ፈሳሽ» እንዲፈስ ነው (አሞጽ 5፡24)። ምንም እንኳ የምንኖረው አብዛኛው ሰው ጽድቅን በማይለማመድበትና ሰዎች ለድሆች በማያስቡበት ዓለም ቢሆንም፥ እኛ ግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ከዚህ የተለየን መሆን አለብን። እግዚአብሔር የመበለቶች፥ የሙት ልጆችና የድሆች አምላክ ነው። እግዚአብሔር ለእነርሱ የተለየ አትኩሮት አለው (መዝሙር (146)፡7-9)። እኛም የእርሱ ልጆች ከሆንን ይህ ዝንባሌ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በአካባቢያችን ስለሚኖሩ ሰዎች ችግር ግድየለሾች ከሆንን፥ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው አምልኮ ተቀባይነት ማግኘቱ ያጠራጥራል። 

2. እግዚአብሔር የአሕዛብ ሁሉ አምላክ ነው።

በትንቢተ አሞጽ ውስጥ እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይሆን፥ የአሕዛብ ሁሉ አምላክ እንደሆነ በተደጋጋሚ እንመለከታለን። የፈጠራቸው እርሱ ነው (አሞጽ 9፡7)፤ ስለሚያደርጉት ነገር በኃላፊነት የሚጠይቀው እነርሱን ነው (አሞጽ 1፡3-2፡3)። ብሔራዊ ኃጢአት በሚኖርበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ሕዝብ ላይ ፍርድን ያመጣል። እግዚአብሐር በሕዝቦች ላይ የሚፈርደው በሚፈጽሙት ኢ-ፍትሐዊ ወይም ፍትሕ-አልባ ድርጊትና በሕዝቦች ላይ በሚያደርሱት ግፍና በደል መሠረት ነው። እግዚአብሔርን የሚያከብሩና እርሱ በዝርዝር የደነገጋቸውን የጽድቅ ሕግጋት የሚጠብቁ ሕዝቦችን፥ እግዚአብሔር ያከብራቸዋል ይሸልማቸዋልም። ዳሩ ግን እግዚአብሔርን የማያከብሩ፥ በጭካኔና በፍትሕ-አልበኝነት የሚገዙ ይቀጣቸዋል።

ትንቢተ አሞጽ የሚያስተምረን፥ እግዚአብሔር ለምንኖርበት አገር ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፥ ለሕዝቦች ሁሉ እኩል እንደሚገደው ነው። እግዚአብሔር ሶማሌን፥ ኬንያን፥ ሱዳንን፥ አሜሪካንን፥ እንግሊዝንና የቀሩትን አገሮች ሕዝቦች ሁሉ እኩል ይወዳቸዋል። ይህ እውነት እኛ ክርስቲያኖች ሌሎች ሕዝቦችን በአንዳንድ ቅድመ-ሁኔታዎች ላይ ተመሥርተን ፍትሕ በጐደለው ሁኔታ ወይም በጥላቻ ስሜት እንዳንመለከታቸው ሊረዳን ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር የእኛን ሕዝብና አገር ብቻ ሳይሆን ሕቦችንና አገሮችን ሁሉ እኩል እንደሚወድ የምንረዳው በምን መንገዶች ነው? ለ) ፍትሕ በሌለበት አገር የሚኖር ክርስቲያን ፍትሕን ለማራመድ ያለው ኃላፊነት ምንድን ነው? ) በትንቢተ አሞጽ ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች ዛሬ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሊያውቁና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዱ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: