የውይይት ጥያቄ) እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በተለያዩ ስጦታዎች፥ ሥልጠናዎችና ሥረ መሠረቶች የተጠቀመባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር በዚህ መንገድ የሚሠራው ለምንድን ነው ብለህ ታስባለህ?
የእግዚአብሔርን አሠራር ልዩ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የተለያዩ ባህሎች፥ ስጦታዎች፡ ሥልጠናዎችና ሥረ መሠረቶች ያሏቸውን ሰዎች ወደ አንድ አካል ማምጣቱ ነው። የክርስቶስ አካል የሆነው ያ ቡድንም የእግዚአብሐርን ዓላማዎች ለመፈጸም ጠንካራና ብርቱ ኃይል ይሆናል። በሌላም በኩል ሰዎች ሌሎች ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ሰዎች፥ የተለያዩ ባህሎችና ሥረ መሠረቶች ወይም የተለያዩ ስጦታዎችና ችሎታዎች ካሏቸው ሰዎች፥ ጋር ከመሆን ይልቅ፥ ተመሳሳይ ሥረ-መሠረቶችና ባህሎች፥ እንዲሁም ተመሳሳይ ስጦታዎች ካሏቸው ሰዎች ጋር መሥራትን ይመርጣሉ። ይህ ምርጫ አንድነትን በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን የሚያጠናክር ቢመስለንም፥ በመሠረቱ የዚህ ውጤት ደካማ ቤተ ክርስቲያንን መመሥረት ነው።
በብሉይ ኪዳን ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ሆነው ያገለገሉትን ነቢያት ሕይወት ስንመረምር እጅግ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች እንደነበሩ እንመለከታለን። እንደ ኤልያስና ኤልሳዕ ያሉት የነቢያት ጉባኤ አባላት ሲሆኑ፥ የነቢይነት ሥራቸውን የሚያከናውኑት ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ነበር። እንደ አሞጽ ያሉት ሌሎች ደግሞ ግብርናን በመሰለ ሌላ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበሩና የነቢይነት ሥራን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚሠሩ ነበሩ። እንደ ዳንኤልና ኢሳይያስ ያሉት ደግሞ ከንጉሣዊ ቤተሰብ የመጡ የኅብረተሰቡ ከፍተኛ መደብ አባሎች ነበሩ። እንደ ሚክያስ ያሉት ከድሀ ወይም ከዝቅተኛ መደብ የመጡ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ነቢያት ብቻ ሳይሆን፥ ካህናትም ነበሩ (ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል)። እነዚህ ሁሉ እጅግ የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር ሁሉንም የራሱ ቃል አቀባዮች ሆነው እንዲያገለግሉ አድርጎ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፣ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስጦታዎች ባሏቸው የተለያዩ ሰዎች የተገነባች መሆኗን ማስታወስ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) እያንዳንዱ ክርስቲያን የተሰጠውን ስጦታ በማወቅ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግል ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ከእኛ የተለዩ ስጦታዎች ወይም ባህሎች ያሏቸውን ሰዎች በአክብሮት ላለማስተናገድ ይህ እውነት ምን ሊያስተምረን ይገባል? መ) እያንዳንዱ አባል የተሰጠውን ስጦታ እንዲያውቅና እንዲጠቀምበት ለመርዳት ቤተ ክርስቲያህ ማድረግ የምትችላቸውን ነገሮች ዘርዝር።
የትንቢተ ሚክያስ ጸሐፊ
ትንቢተ ሚክያስ የተጻፈው ሚክያስ በተባለ ሰው ነው። ስለ ነቢዩ ሚክያስ የምናውቀው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ሚክያስ የመጣው አንዳንድ ጊዜ ሞሬሼት ተብላ ትጠራ ከነበረችው ከሞሬሽትጌት ከተማ ነው (ሚክያስ 1፡1፥14)። ይህች ከተማ የምትገኘው ከኢየሩሳሌም ደቡብ ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በሜድትራንያን ባሕርና በኢየሩሳሌም ከተ መመካከል ነበር። በኋላ ቀርነታቸው እጅግ ከሚታወቁት የይሁዳ ክፍሎች አንዱ በመሆንዋ ትታወቅ ነበር፡፡ በዚህች ከተማ ብዙ ድሀ ገበሬዎች ይኖሩ ነበር። ሚክያስ የይሁዳ ሕዝብ በድሆች ላይ ስለፈጽሟቸው ማህበራዊ ኃጢአቶች የፍርድ ቃል በተናገረበት በመጽሐፉ ውስጥ ስለ እነዚህ ድሆች የነበረውን አትኩሮት ልንመለከት እንትላለን፡፡
ሚክያስ በይሁዳ ሕዝብ መካከል የነቢይነት አገልግሎት የሰጠው ከ750-686 ዓ.ዓ. ነበር። ይህም በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት መሆኑ ነው (ሚክያስ 1፡1)። ምናልባት ከትንቢቶቹ አብዛኛው ክፍል የተነገረው በንጉሥ ሕዝቅያስ መሪነት ተካሄዶ ከነበረው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተሐድሶ በፊት ሳይሆን አይቀርም። በዚያን ዘመን ያገለግል የነበረ ነቢይ ሚክያስ ብቻ አልነበረም። ሆሴዕና አሞጽ በእስራኤል ላይ ትንቢት ሲናገሩ፥ በይሁዳ ደግሞ ከሚክያስ ጋር ኢሳይያስም ያገለግል ነበር። በኢሳይያስና በሚክያስ መልእክቶች መካከል ካለው ግልጽ ተመሳሳይነት የተነሣ (ሚክያስ 4፡1-3 ና ኢሳይያስ 2፡1-4)፥ ብዙ ምሁራን ሚክያስ ኢሳያይስን እንደሚያውቅና ምናልባትም የእርሱ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ይናገራሉ። የኢሳይያስ አገልግሉት በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ሲሆን፥ የሚክያስ አገልግሎት ደግሞ ምናልባት ደግሞ በገጠር የነበረ ሊሆን ይችላል።
ሚክያስ በነቢይነቱ በሕዝቡ መካከል የነበረው ምስክርነት መልካም ነበር፤ እንዲሁም ከብዙ ዓመታት በኋላ በኤርምያስ ዘመን፥ ኤርምያስ በኢየሩላሉም ላይ በተናገረው ትንቢት ምክንያት ሕዝቡ ከመገደል የተረፈው የሚክያስን ትንቢት በመመልከታቸው ነበር (ኤር. 26፡15-19 ተመልከት)።
እግዚአብሔር በይሁዳ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር፥ እንደ ኢሳያይስ ካሉ ነቢያትና ፈሪሀ እግዚአብሔር ካደረበት ንጉሥ ሕዝቅያስ ጐን ሚክያስንም ተጠቅሞበታል። የእግዚአብሔር ፍርድ ለብዙ ዓመታት ተፈጻሚ ሳይሆን የቆየው በእርሱ ምክንያት ነበር።
የትንቢተ ሚክያስ ታሪካዊ ሥረ መሠረት
ሚክያስ የተወለደው ንጉሥ ዖዝያን በይሁዳ ዙፋን ላይ እያለ ነበር። ዖዝያን እግዚአብሔርን የሚፈራ ታላቅ መሪ ነበር። በእርሱ አመራር ወቅት በእስራኤል ፍጹም ሰላምና ብልጽግና ነበረ። ሰዎች የጣዖት አምልኮአቸውን እየተዉ በቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ መነቃቃት የታየበት ጊዜ ነበር። ዳሩ ግን ሀብትና ንግድ ዕድገት እያሳየ በመሄዱ ምክንያት አዲስ ዓይነት ሰዎች በይሁዳ ተነሡ። እነዚህ ነጋዴዎች እጅግ ሀብታሞች ስለሆኑ በይሁዳ እጅግ ይከበሩ ጀመር። የሚያሳዝነው ግን ለሀብት የነበራቸው ስግብግብነት ገበሬዎችንና ድሆችን እንዲጨቁኑና ከታዋቂ ሰዎችና ከመሪዎች ጋር በመሆን በተራው ሕዝብ ላይ የፍትሕ መዛባት እንዲያደርሱ አደረጋቸው። ንጉሥ ዖዝያን በሞተ ጊዜ ነገሮች ቀስ በቀስ መለወጥ ጀመሩ። ልጁ ንጉሥ ኢዮአታም በአባቱ ዘመን የነበረውን ሀብትና ሰላም ለማስጠበቅ ወይም ለማቆየት ችሎ ነበር። ሚክያስ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆኖ በይሁዳ ማገልገል የጀመረው በእነዚህ ጊዜያት ነበር።
የኢዮአታም ልጅ አካዝ በነገሠ ጊዜ ነገሮች ሁሉ ፈጥነው ተቀየሩ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ስለነበር ሕዝቡን ፈጥኖ ወደ ጣዖት አምልኮ መለሳቸው። በመሆኑም፥ በይሁዳ የነበረው መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ እጅግ ተበላሸ። የሰው ልጆች መሥዋዕት ተደርገው የሚቀርቡበት የጣዖት አምልኮ ተስፋፋ። የሃይማኖት መሪዎች የነበሩት ካህናትና ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል ስለመናገርና ማስተማር የማይገባቸው ሆኑ። በዚህ ፋንታ ለገንዘብ መሯሯጥ ጀመሩ። የፖለቲካ መሪዎች፥ ነገሥታትና መሳፍንት ለራሳቸው ደኅንነትና ዋስትና ብቻ በመጨነቅ፥ የድሆችን፥ የመበለቶችንና የሙት ልጆችን ጥሪት የሚነጥቁ ሆኑ። ቤተሰብ መፈራረስ ጀመረ፤ በምድሪቱም ሁሉ አለመተማመን ነገሠ (ሚክያስ 7፡5-6)።
የዖዝያንና የኢዮአታም የሰላም ጊዜያት አከተሙ። የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔና የሶርያ ንጉሥ ረኦሶን ይሁዳን ይወጉ ጀመር። በዚህ ምክንያት ንጉሥ አካዝ የአሦርን እርዳታ ለመነ። አሦርም ሶርያን በ732 ዓ.ዓ.፥ እስራኤልን ደግሞ በ722 ዓ.ዓ. አሸነፈች። ሚክያስ የሰማርያን ውድቀት አመለከተ (ሚክያስ 1፡6)። አንድ ቀን ይሁዳ በተመሳሳይ መንገድ በምርኮ እንደምትወሰድ በማወቅ ይህንን ከፍተኛ ኃዘን ይጠባበቅ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። የሚክያስ አብዛኛው መልእክት ሥነ-ምግባራዊና መንፈሳዊ ክፋት የነበረበትን ይህን ጊዜ ያመለክታል።
ንጉሥ ሕዝቅያስ ወደ ሥልጣን በመጣና ሁኔታዎች መለዋወጥ በጀመሩ ጊዜ ሚክያስ እጅግ ሳይደሰት አልቀረም። ሕዝቅያስ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የጣረ መልካም ንጉሥ ነበር። በዚህ ተሐድሶ ሚክያስ እንደ ተካፈለ ጥርጥር የለውም። ሕዝቅያስ ይሁዳ ራሷን ከጠላቶችዋ የምትጠብቅበትን መከላከያ አጠንክሮ ነበር። ነገር ግን ምንም አልረዳውም። በ701 ዓ.ዓ. አሦር ይሁዳን በማጥቃት አብዛኛውን የይሁዳ ምድር ያዘች። ኢየሩሳሌም የዳነችው በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ብቻ ነበር (2ኛ ነገሥት 18-19)። ሚክያስ ይህ ጥፋት ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት አንድ የሚመጣባቸው ምልክት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፣ ስለ ሚክያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ትንቢተ ሚክያስ የተጠቀሱትን ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር።
የትንቢተ ሚክያስ አስተዋጽኦ
1. ሚክያስ በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 1)፥
2. ሚክያስ በይሁዳ መሪዎች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 2-3)፡
3. ሚክያስ ስለ ጽዮን ተሐድሶ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 4-5)
ሀ. የሚመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት (ሚክያስ 4)
ለ. ንጉሥና እረኛ ሆኖ የሚመጣው የመንግሥቱ ገዥ (ሚክያስ 5)፡
4. ሚክያስ ስለ ይሁዳ ክፋትና ስለሚመጣበት ፍርድ የተናገረው ትንቢት (ክያስ 6፥7፡6)።
5. ሚክያስ፥ የእስራኤል ቅሬታዎች በወደፊቱ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚቀበሉት ይቅርታ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 7፡7-20)።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡