የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች

የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ

እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታቸውና ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው በመናገር ይሁዳን እንዲያስጠነቅቅ ሚክያስን ላከው። ሕዝቡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በመተዋቸው በይሁዳ ላይ ስለሚመጣው ቅጣት ተናገረ፡፡ ምንም እንኳ ውጫዊ በሆነው ሥርዓት እግዚአብሔርን ሊያመልኩ ቢችሉም ሕይወታቸው ግን እግዚአብሔርን በመፍራት የሚመራ አልነበረም። ይህም በተለይ ግልጽ ሆኖ የታየው እርስ በርስ በነበራቸው ግንኙነት ውስጥ ነበር። ሀብታሞች ድሆችን ይጨቁኑ ነበር፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ በሀብታሞችና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ይከሰታል። የእግዚአብሔር ፍርድ ታማኝ ባልሆነችው ይሁዳ ላይ የሚመጣ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን ሙሉ በሉ አያጠፉም። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽል። አንድ ቀን እግዚአብሐር እርሱ በሚፈልገው መንገድ በጽድቅ የሚገዛ ሰው ከዳዊት ዘር ያስነሣል። ይህ ንጉሥ በእግዚአብሔር ሕዝብ ልብ ውስጥ አንዳችም ክፋት የማይኖርበትንና ሕዘቡ ከእውነት ጨርሶ የማይርቁበትን አዲስ ዘመን ያመጣል። ጦርነት ተሽሮ ሰዎች ሁሉ በእውነተኛ ሰላም ይኖራሉ። እስከ ዛሬ ድረስ በፍትሕ መጉደል የሚሠቃዩ ሰዎች በእነዚህ ጥቅሶች ከፍተኛ መጽናናትን ያገኛሉ። አንድ ቀን እግዚአብሐር በዘላለም መንግሥቱ ያስተናግዳቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፣ በችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ ጽድቅና ቅን ፍርድ የሞላበት አስተዳደር የመምጣቱ ተስፋ የሚያበረታታህ በምን መንገድ ነው?

የትንቢተ ሚክያስ ዋና ዋና ትምሕርቶች

የውይይት ጥያቄ፣ ሚክያስ 6፡6-8 አንብብ። ሀ) ሚክያስ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ የማይፈልገው ምንድር ነው አለ? ለ) ሚክያስ እዚአብሔር ከሰው የሚፈልገው ነገር ምንድር ነው አለ፤ ሐ) እነዚህን ጥሶች ከሕይወትህ ጋር የምታዛምድባቸውን መንገዶች ዘርዝር። መ) ሚክያስ 6፡8 በቃልህ አጥና። 

1. ጌታ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ትንቢተ ሚክያስ በኃጢአት ላይ የሚመጣውን ፍርድ ወደፊት ከሚገለጡ ታላላቅ ዘመናት ጋር በማቀናጀት የሚናገር ነው። በተለይ የሚያተኩረው ድሆችን በሚጨቁኑ ሀብታሞች ኃጢአት ላይ ነው (ሚክያስ 2፡1-2፤ 3፡1-3፥ 9-11)። ሚክያስ የይሁዳን ኃጢአት በሚገልጽበት ክፍል መሀል እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሁለት ጥያቄዎችን ይጠይቃል፤ በመጀመሪያ፥ “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? (ሚክያስ 6፡6) የሚል ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው?» (ሚክያስ 6፡8) የሚል ነው። በዘመናችን ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት በሚክያስ ዘመንም ሕዝቡ እግዚአብሔር ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርገው በአምልኮ ሥርዓቶች ላይ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ሕዝቡ ወደ ቤተ-መቅደስ ከመጡ፥ መዝሙራትን ከዘመሩና በሙሴ ሕግጋት መሠረት መሥዋዕቶችን ካቀረቡ እግዚአብሔር የሚፈልግባቸውን ነገሮች ሁሉ ያሟሉ ይመስላቸው ነበር። የአምልኮ ሥርዓቶችን በመፈጸም፥ በክፉ ሥራዎቻቸው ምክንያት ከተቆጣው ቁጣ እግዚአብሔርን የሚመልሱት ይመስላቸው ነበር። እግዚአብሔር አምልኮ በሚፈጽሙበት ጊዜ ስለሚያደርጉት ነገር ብቻ እንጂ በቀሩት የሳምንቱ ቀናት ስለሚያደርጉት ነገር ግድ የሌለው ይመስላቸው ነበር። 

ነገር ግን ሚክያስ የልብና የአኗኗር ለውጥ እስከሌለ ድረስ፥ እግዚአብሔር ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ግድ እንደሌለው አይቷል። ምንም ያህል ሰዎች ቢዘምሩ፥ ቢጸልዩ፥ ቢጾሙና ለሌሎች ሰዎች ቢመሰክሩ ወይም ሌሎች ሰዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው የሚሏቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓተች ቢፈጽሙ፥ በትክክል እግዚአብሔርን የመታዘዝ ሕይወት እስካልኖሩ ድረስ፥ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም። እውነተኛ አምልኮ ሁለንተናችንን የሚጠይቅ ነው። እግዚአብሔር ስንዘምር፥ ስንጸልይ፥ ስንጾምና ለሌሎች ስንመሰክር ደስ የሚለው መላ ሕይወታችንን የሰጠነው እንደሆነ ነው።

ሚክያስ እግዚአብሔር በእርግጥ የሚፈልገው ከልብ መታዘዝን እንደሆነ በማስጠንቀቅ ሕዝቡን የሚያስታውሳቸው ለዚህ ነው (1ኛ ሳሙኤል 15፡22 ተመልከት)። ይህ መታዘዝ ሕይወታቸውን በሙሉ ማጠቃለል አለበት። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ የሚያጠቃልል መሆን አለበት («ከእግዚአብሔር ጋር በትሕትና ኑሩ»)፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚጨምር መሆንም አለበት። («በጽድቅ ሥሩ ምሕረትንም ውደዱ»)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕይወትህን መርምር። ሀ) ለእግዚአብሔር አምልኮ እንዲሆኑ የምታደርጋቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ነገሮች ሊፈጸሙ የሚችሉትና በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ተቀባይነት የማያገኙት እንዴት ነው? ሐ) በዚህ ሳምንት ያደረግሃቸውን ጽድቅና ምሕረት የሚያመለክቱ ነገሮችን ዘርዝር። መ) ሁለንተናህ ለእግዚአብሔር መታዘዙን ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው? ሠ) እነዚህን እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ ለማስተማር የምትችለው እንዴት ነው?

2. የሚመጣው ንጉሥና የእግዚአብሔር መንግሥት፡- የትንቢተ ሚክያስ አብዛኛው ክፍል በኃጢአት ላይ ስለሚፈጸም ፍርድና ስለሚመጣው ፍርድ የተነገረ ትንቢት ቢሆንም፥ ሚክያስ የፍርድ ትንቢቶችን ከተስፋ ትንቢቶች ጋር አቀናጅቶ ያቀርባል። ትንቢተ ሚክያስ የመጨረሻውን ዘመን ማለት የሁሉ መደምደሚያ የሆነው እረኛ ንጉሥና መሢሕ በዘመኑ ፍጻሜ ላይ በእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገዛ የሚያሳይ ታላቅ ሥዕላዊ ትዕይንት ያቀርባል። በዚያ መንግሥት ጦርነት አይኖርም፤ ሁሉ ነገር ሰላም ይሆናል። እግዚአብሔር ራሱ ሕዝቡን ስለሚያስተምር ምንም ዓይነት የውሸት አምልኮ አይኖርም። የተበተኑት የእስራኤል ቅሬታዎች ወደ እግዚአብሔር በመመለስ፥ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ያመልካሉ። እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ይቅር ይላል። የሚመጣው ንጉሥ፥ መሢሑ የዳዊት ከተማ በሆነችው ቤተልሔም ይወለዳል። አመጣጡ ከዳዊት ዘር ነው፤ ነገር ግን ደካሞችና ኃጢአተኞች ከሆኑት ከዳዊት በኩል ከተነሡት ነገሥታት የተለየ ይሆናል። አመጣጡ ከጥንት ዘመን ስለሆነ አምላክ ነው። ምድርን ሁሉ በጽድቅ መግዛት ብቻ ሳይሆን ደግና ርኅሩኅ እረኛ ይሆናል።

ማስታወሻ፡- ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የመጀመሪያና ዳግም ምጽአት የተነገሩ ትንቢቶች በታሪክ በተፈጸሙበት አኳኋን ተነጣጥለው ሳይሆን እንዴት ተጣምረው እንደቀረቡ አስተውል። ነቢያት የወደፊቱን ሁኔታ አርቀው በመመልከት ስለ ክርስቶስ መምጣት ሲናገሩ፥ መሚሑ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው:- መጀመሪያ በቤተልሔም ተወልዶ በመስቀል ላይ ለመሞት፥ ቀጥሎ ደግሞ እንደ ድል ነሺ ንጉሥ እንደሚሆን አላስተዋሉም ነበር። እና ይህን ልዩነት ልንረዳ የቻልነው የምንኖረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደትና ሞት በኋላ ስለሆነ ብቻ ነው። ይህ አይሁዶች በተለይ ደግሞ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰና በሞተ ጊዜ የተፈጠረባቸውን ግራ የመጋባት ሁኔታ ለመገንዘብ ይረዳናል። ድል በመንሣት ይገዛል ብለው ይጠብቁት የነበረውን መሢሕ ሁኔታ አላሟላላቸውም ነበር።

ከእነዚህ ትንቢቶች አብዛኛዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ የሚገዛበትን የመጨረሻውን ዘመን የሚመለከቱ ናቸው። በእርሱ ዘመነ መንግሥት ጽድቅና ቅን ፍርድ በምድር ላይ ይንሰራፋል። ኃጢአት ይደመሰስና ሰው ሁሉ በተለወጠ ልብ እግዚአብሔርን ያመልካል።

የውይይት ጥያቄ ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ከምድር ላይ ፍትሕና ጽድቅ በሚጠፉበት ጊዜ ማበረታቻ የሚሆኑን እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች ይህንን እውነት በልባቸው መያዝ ያለባቸው ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር በአምልኮአቸው ደስ ይሰኝ ዘንድ እርሱን በሚያስደስተው መንገድ እንዲኖሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/NuHmWCM9EsPFQkUX9

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading