የትንቢተ አብድዩ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርት

የትንቢተ አብድዩ ዓላማ

ነቢያት በኤዶም ላይ ከተናገሯቸው በርካታ ትንቢቶች መካከል ትንቢተ አብድዩ አንደኛው ነው (ኢሳይያስ 21፡11-12፤ 34፡5-17፤ ኤርምያስ 49፡7-22፤ ሕዝቅኤል 25፡12-14፤ አሞጽ 1፡11-12)። ትንቢተ አብድዩ ሁለት ዐበይት ዓላማዎች አሉት፡-

ሀ. የኤዶማውያንን ኃጢአት ማውገዝ ወይም መኮነን ነው። እነዚህ ኃጢአቶች ኤዶማውያን በጥበባቸውና የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመቋቋም በመቻላቸው ትምክሕት ስላደረባቸው በአይሁድ ላይ መጨከናቸውና ኢየሩሳሌም በወደቀች ጊዜ በአይሁድ ላይ በደል መፈጸማቸው ነበሩ (አብድዩ 2-9)። 

ለ. እግዚአብሔር በጌታ ቀን በክፉ ሕዝቦችና አገሮች ሁሉ ላይ ድል እንደሚነሣ ለአይሁድ ቅሬታዎች ለማስታወስ ነው (አብድዩ 17-21)። 

የትንቢተ አብድዩ ዋና ትምህርት

የውይይት ጥያቄ አብድዩ 15-16 አንብብ። በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ መመሪያ ምንድን ነው?

ትንቢተ አብድዩ እግዚአብሔር ሕዝቦችና መንግሥታት የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ እንደሚመለከትና እንደሚቆጣጠር ለድርጊታቸውም ሁሉ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው የሚያስጠነቅቅ ነው። እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ በሉዓላዊነት ይገዛል። ጽድቅና ቅን ፍርድ የጎደለው ድርጊታቸውን ሁሉ ይመለከታል ያስታውሳቸዋልም። እግዚአብሔር ሰዎችንና መንግሥታትን ሁሉ ስለ ድርጊታቸው እንደሚቀጣቸው ይናገራል። እግዚአብሔር ሰዎችን ሲቀጣ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀምበት መንገድ እነዚያ ሰዎች ሌሎችን ለመቅጣት የተጠቀሙበት መንገድ ከቅን ፍርድና ከጽድቅ የራቀ ነበር፡፡ ጨካኞች ከሆኑ ጭካኔ ይገጥማቸዋል። (አብድዩ 15-16፤ መዝሙር 7፡15-16፤ ምሳሌ 26፡27፥ ገላ. 6፡7-10 ተመልከት)። አሦር እስራኤልን እንደመታች ሁሉ እርስዋም በተራዋ በባቢሎን ተመታች። 

አገሮች ወይም ሕዝቦች ቅን ፍርድን በማዛባት ጽድቅ የጎደለው ተግባር እየፈጸሙ ከፍርድ ያመለጡ ቢመስሉም፥ ክፉና ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቆም የኃጢአታቸውን ዋጋ የሚቀበሉበት የመጨረሻ የፍርድ ቀን ግን አለ። በክርስቶስ ደም እስካልተሸፈነ ድረስ ሳይቀጣ የሚቀር ኃጢአትና ክፉ ተግባር አይኖርም።

በተቃራኒ ትንቢተ አብድዩ በአድልዎ ግፍ ለሚፈጸምባቸው ክርስቲያኖች ማበረታቻ ሊሆን ይገባል። አንድ ቀን እግዚአብሔር ክፉና ኃጢአተኞች ሰዎችን በመቅጣት አማኞችን ስለ ጽድቅ ሥራቸው እንደሚሸልማቸው ሊያስታውሱ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በጽድቅ ይገዛል።

የውይይት ጥያቄ፥ የትንቢተ አብድዩን ዋና ትምህርት መረዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? «በሌሎች ላይ ያደረግኸው በአንተም ላይ ይደረግብሃል። ድርጊትህ በራስህ ላይ ይመለስብሃል» የሚለው መንፈሳዊ መርሕ ሲሠራ ያየኸውና እውነት መሆኑን ያረጋገጥኸው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ትንቢተ አብድዩን አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ኤዶምን እንደሚቀጣ የወሰነባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) በኤዶም ላይ እንደሚፈጸሙ የተነገሩ የፍርድ ትንቢቶች ምን ነበሩ? ሐ) እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባው ተስፋ ምን ነበር? መ) ከዚህ መጽሐፍ የምንማራቸው ጠቃሚ መንፈሳዊ ትምህርተች ምንድን ናቸው?

ኤዶማውያን ማንም ሊቋቋማቸው እንደማይችል በማሰብ የሚኩራሩ ትዕቢተኞች ነበሩ። ዋና ከተማቸው ጴጥራ ለጥቃትና ለሽንፈት ፈጽሞ በማትመችበት ሁኔታ ላይ ነበረች። ከተማይቱ በኮረብታዎች ግርጌ የተሠራች ስለነበረች፥ ጥቂት ሰዎች ሊከላከሉት በሚያመች ሁኔታ ላይ ነበረች። ኤዶማውያን በቁጥር ጥቂት ሕዝብ ቢሆኑም በጥንቱ ዓለም በጥበባቸው እጅግ ታዋቂ ሕዝብ ነበሩ። ይህም ወደ ትዕቢት መራቸው። እግዚአብሔር ትዕቢትን ስለሚጠላ ኤዶማውያንን እንደሚያዋርድ ተናገረ። 

ኤዶማውያን ጨካኞችም ነበሩ። ከባቢሎናውያን ጋር በመተባበር ይሁዳን ከማጥቃታቸውም ሌላ፥ ከይሁዳ የተሰደዱ ሰዎች መጠጊያ ፍለጋ ወደ እነርሱ ሲሸሹ ይጨፈጭፏቸው ዘንድ ከባቢሎናውያን ጋር ተባበሩ። በኢየሩሳሌም መደምሰስ ታላቅ ደስታ ተሰማቸው። ይህ ሁሉ በአንድነት ተዳምሮ የእግዚአብሔርን ፍርድ አመጣባቸው። እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ በፈጸሙት ዓይነት ወንጀል ፍርድ አመጣባቸው። በይሁዳ ላይ የፈጸሙትን በመሰለ ተመሳሳይ ጥፋት እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸው ተናገረ።

በጌታ ቀን፥ ፍርድ በኤዶም ብቻ ሳይሆን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ይሆናል። እግዚአብሔር ግን የጽዮንን ተራራ ኢየሩሳሌምን በመታደግ በምርኮ ለነበሩት እስራኤላውያን በረከትን ያመጣል። በአንድ ወቅት የኤዶም የነበረውን ምድር ሳይቀር ይገዛሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ለቤተ ክርስቲያንህ አባላት ልታስተምራቸው የምትችል መንፈሳዊ እውነቶችን ከትንቢተ አብድዩ ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: