የትንቢተ ኢዩኤል ዓላማ እና ዐበይት የሥነ መለኮት ትምሕርቶች

የትንቢተ ኢዩኤል ዓላማ

ብዙ ጊዜ የነቢያት ዓላማ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች መተንበይ እንደሆነ እንገምታለን። ምንም እንኳ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለ መጪው ጊዚያት የተነበዩ ቢሆኑም፥ የመልእክታቸው አብዛኛው ክፍል በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች የሚመለከት ነበር። ነቢያት የእግዚአብሔር ሕዝብ በክፋታቸው ተጸጽተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚለምኑ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ነበሩ። ትንቢቶቹ የሚነገሩት ብዙውን ጊዜ የሕዝቡን አደራረግ ውጤቶች ለማመልከት ነበር። የትንቢት ዓላማ ስለ መጪው ጊዜ ብዙ እንድናውቅ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር አሁንና ወደፊት በሚያደርጋቸው ነገሮች ምክንያት አሁን ያለውን ኑሮአችንንና አካሄዳችንን እንድንለውጥ ለማድረግ ነው።

እግዚአብሔር ነቢዩ ኢዩኤልን ወደ ይሁዳ የላከው፥ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሚደርሱባቸውን ነገሮች በመዘርዘር ሊያስጠነቅቃቸው ነበር። የአንበጣው መቅሠፍት እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አለመሰኘቱን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን በመጥቀስ አስጠነቀቃቸው። በንስሐ ካልተመለሱ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ታላቅ መቅሠፍት ለማምጣት፥ በንስሐ ከተመለሱ ግን እንደገና ምድራቸውን ለመባረክ ቃል ገብቶ ነበር።

እንዲሁም ኢዩኤል የአንበጣውን መቅሠፍት ይሁዳን ለመውረር የሚመጣ የሌላ ጦር ኃይል ምልክት አድርጎ ተጠቅሞበታል። ይህ ጦር ስለ ባቢሎን ወይም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመመለሱ ጥቂት ቀደም ብሉ ስለሚመጣ ሌላ ጦር የሚናገር ሊሆን ይችላል። በይሁዳ ላይ የሚመጣው ጦር የአንበጣ መንጋን ያህል እጅግ አጥፊና ብዙ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን በመታደግ፥ እነርሱ የማያውቁአቸውን በረከቶች ያመጣላቸዋል። መንፈስ ቅዱስ በሕዝብ ሁሉ ላይ ይወርዳል። ይህ የመጨረሻ ዘመን እግዚአብሔር ምድርን ከክፋት የሚያጠራበትና በአሕዛብ ሁሉ ላይ የሚፈርድበት ስለሆነ የታላቅ ጥፋት ቀንም ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ንስሐ እንድንገባ እኛንና አገራችንን በሚያስጠነቅቀን ወቅት በሕይወታችንና በአገራችን ላይ የሚመጣውን የማስጠንቀቂያ ጥፋት መገንዘብ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ከርስቲያኖች ከፍተኛ ጥፋት የሚደርስበትንና ታላቅ በረከት የሚያመጣውን የመጨረሻውን ዘመን በንቃት መገንዘባችን ጠቃሚ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? ሐ) ይህ ነገር በአኗኗራችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

በትንቢተ ኢዩኤል ውስጥ የሚገኙ ዐበይት የሥነ-መለኮት ትምህርቶች

1) ክርስቲያን ስለተለያዩ አደጋዎች ያለው ግንዛቤ 

ሰዎች የተለያዩ አደጋዎችን በሚመለከቱበት ጊዜ በአመዛኙ ምላሻቸው ከሚከተሉት ሦስት አሳቦች አንዱ ይሆናል፡-

ሀ) በተለይ በምዕራቡ ዓለም እግዚአብሔር የተለያዩ አደጋዎችን በምንም ዓይነት እንደ ማይቆጣጠራቸው አድርጎ ማሰብ የተለመደ ነው። በሕዝቡ ላይ ያለምንም ዓላማ በድንገት የሚመጡ ነገሮች ስለሆኑ፥ እኛ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር እስኪያልፉ ድረስ መታገሥ ብቻ ነው ይላሉ። 

ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ወይም ሙስሊሞች የተፈጥሮ አደጋዎች በቀጥታ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚመጡ ያምናሉ። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የሚከሠቱት ያለምንም ዓላማ ነው የሚል እምነት አላቸው። እግዚአብሔር እነዚህ ሁኔታዎች እንዲከሠቱ የሚያደርግበትን ምክንያት ሰዎች ሊያውቁ እንደማይችሉ ይናገራሉ። ስለዚህ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር፥ እነዚህን ነገሮች እግዚአብሔር እንደሚያደርጋቸውና እኛም ምንም የምንለውጠው ነገር ስለሌለ አሜን ብሎ መቀበል ነው ይላሉ። 

ሐ) እግዚአብሔር የራሱን ዓላማ ለመፈጸም በሕይወታችንና በአገራችን ላይ የሚደርሱትን ነገሮች ሁሉ እንደሚመራ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ዝናም፥ ፀሐይ፥ ሰብሎች ቁሳዊ ሀብትና የመሳሰሉት መልካም ነገሮች ሁሉ የሚመጡት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ይሁን እንጂ አደጋዎች ወይም ችግሮች የሚመጡት በእርሱ ፈቃድ ነው። የሚመጡትም ያለ ዓላማ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በሚያውቀው ዓላማ ነው። የሁሉ ነገር ኃላፊ እግዚአብሔር ስለሆነ እርሱን ማሰብ ለእኛም ሆነ ለአገራችን እንደሚያስፈልገን ለማሳሰብና ለመርዳት ነው። ስለሚሰጠን በረከቶች እግዚአብሔርን ልናመሰግነውና በችግራችን ጊዜ ልናስበው ይገባናል። ችግሮች እግዚአብሔርን በማወቅና በመንፈሳዊ ባሕርይ እንድናድግ ሊረዱን የሚከሰቱ ናቸው። እግዚአብሔር አደጋ የሚያመጣባቸውን ምክንያቶች ሁሉ ለማወቅ ባንችልም፥ የሚመጡት በእግዚአብሔር ቁጣና ምሕረት የለሽ ፍርድ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት ጭምር እንደሆነ እናውቃለን።

የሚመጣውን በረከትና አደጋ የሚቆጣጠር እግዚአብሔር እንደሆነ ብናውቅም፥ የበረከትን ወይም የአደጋን መኖር እግዚአብሔር በአንድ ሰው ሕይወት ወይም በአንዲት አገር ላይ ፍቅሩ ወይም ፍርዱ እንዲገለጽ የሚጠቀምበት መሣሪያ እንደሆነ ለመወሰን እንዳንጠቀምበት ልንጠነቀቅ ይገባል። እጅግ ሀብታሞች የሆኑ ክፉና ኃጢአተኞች ሰዎች ወይም አገሮች ብዙ ናቸው። በመከራና በችግር ውስጥ የሚያልፉ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች አሉ። በአንድ ሰው ወይም በአንድ አገር ሕዝብ ክፋት ወይም በጎነት ምክንያት መቅሠፍት ወይም በረከት ይደርሳል ብሎ መወሰኑ የእኛ ድርሻ አይደለም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእነዚህ ሦስት መንገዶች መቅሠፍት የደረሰባቸው ሰዎች ምን እንዳደረጉ የሚገልጽ ታሪክ በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) በሕይወትህ ለገጠሙህ የተለያዩ ችግሮች ምላሽ የሰጠህባቸውን የተለያዩ መንገዶች ጥቀስ። ከእነዚህ ምላሾችህ መካከል ዕድገት ያስገኙልህ የትኞቹ ናቸው? ምንም ዕድገት ያላስገኙትስ?

2. የጌታ ቀን 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢዩኤል 1፡15፤ 2፡1-2፤ 3፡18 አንብብ። ሀ) የጌታን ቀን የተለያዩ ባሕርያት ግለጽ። ለ) ይህንን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ በመመልከት የጌታ ቀን ምን እንደሆነ የሚገልጽ አጠር ያለ አንቀጽ ጻፍ።

የብሉይ ኪዳን ነቢያት በሰፊው ከተጠቀሙባቸው ሐረጎች አንቱ «የጌታ ቀን» የሚለው ነው። አይሁድ አንዳንድ ዐበይት ድርጊቶች የተፈጸሙባቸውን ጊዜያት «ቀን» በማለት ይጠሩአቸው ነበር። ነቢያት «የጌታ ቀን» ብለው የጠሯቸው ቀናት እግዚአብሔር በሰዎች ታሪክ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ታላቅና ኃይለኛ ተግባር የፈጸመባቸው ማንኛዎቹም ቀናት ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የፈረደባቸው ቀናት «የጌታ ቀን» ተብለዋል (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2፡22)። በሌሉች ጊዜያት ደግሞ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ወደፊት የሚፈርድባቸው ጊዜያት «የጌታ ቀን» ተብለዋል (ኢዩኤል 2፡1-11)። እንደዚሁም ይህንን ሐረግ በዓለም ታሪክ መጨረሻ ገደማ የሚፈጸሙትን ታላላቅ ድርጊቶች ለመግለጥ ተጠቅመውባቸዋል። ነቢያት እግዚአብሔር ከዚህ ቀደም አድርጎት የማያውቀውን ነገር የሚያደርግበት ጊዜ እንደሚመጣ ነቢያት አመልክተዋል። አንዳንዴ ይህ ጊዜ የሚያመለክተው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለመሞት የመጣበትን ወቅት ነው። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግሥበትን ዳግም ምጽአቱን ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሁለት የክርስቶስ ምጽአቶች በግልጽ ሳይለዩ በአንድነት ተጠቅሰዋል። አንዳንድ ጊዜ ነቢያቱ የእስራኤል ሕዝብ ይለማመዱት የነበረውን ታሪካዊ ድርጊት በማየት፥ በመጨረሻው ዘመን የሚመጣውን ታላቁን የጌታ ቀን እንደሚያመለክት አድርገው ይጠቀሙበታል (ኢሳይያስ 13፡5-10)። ከጌታ ቀን ባሕርያት ውስጥ ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡-

ሀ. የጌታ ቀን በጨለማ፥ ደብዘዝ ባለ ብርሃንና በፍርድ ባሕርዩ ይታወቃል። (ኢሳይያስ 13፡9-10፤ ማቴዎስ 24፡29)። 

ለ. የጌታ ቀን እንደ መሬት መንቀጥቀጥና ረሀብ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ይሞላል። 

ሐ. የጌታ ቀን የጦርነት ጊዜ ይሆናል፥ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ በተለይም በእስራኤል ሕዝብ ላይ በመነሣቱ ይታወቃል፡፡ 

መ. የጌታ ቀን እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ የሚፈርድበት ቀን ይሆናል (ኢዩኤል 3፡19)። 

ሠ. የጌታ ቀን የእስራኤል ሕዝብ በብዛት ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱበት ቀን ነው። እነዚህ ቅሬታዎች ከእግዚአብሔር ከፍተኛ በረከትን ያገኛሉ (ኢዩኤል 2፡32፤ አሞጽ 9፡11-15)። 

ረ. የጌታ ቀን ከዚህ በፊት በጭራሽ ተደርጎ በማያውቅ አኳኋን የእግዚአብሔር መንፈስ በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ውስጥ የሚሠራበት ጊዜ ይሆናል፤ (ኢዩኤል 2፡28)። 

ሰ. የጌታ ቀን ምድር በቃል ሊገለጽ የማይችል ታላቅ በረከትና ብልጽግና የምትለማመድበት ጊዜ ይሆናል (ኢዩኤል 3፡18)። 

ሸ. የጌታ ቀን ምድር በእሳት ፍርድ የምትጠራበት ጊዜ ይሆናል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡10-13)። 

ቀ. የጌታ ቀን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጥበት ጊዜ ይሆናል (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡8)

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ጌታ ቀን የተሰጠው ትምህርት ታላቅ ማስጠንቀቂያና ክርስቲያኖች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠብቁት ጊዜ የሚሆነው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢዩኤል 1-3 አንብብ። ሀ) ኢዩኤል በእስራኤል ሕዝብ ላይ ፈጥኖ እንደሚደርስ የተናገረው ትንቢት ምን ነበር? ለ) ኢዩኤል ንስሐ እንዲገባ የሚያስጠነቅቀው ማንን ነበር? ሐ) ሕዝቡ ንስሐ ከገቡ በኋላ ተስፋ የተሰጣቸው በረከቶች ምን ነበሩ? መ) ለአይሁድ ስለ መጨረሻው ዘመን የተሰጡ የበረከት ተስፋዎች ምንድን ናቸው?

1. ኢዩኤል የጌታን ቀን በአንበጣ መቅሠፍት ተመለከተ (ኢዩኤል )

ትንቢተ ኢዩኤል፥ የእስራኤልን ምድር ሰብል ሙሉ በሙሉ ስላጠፋውና የይሁዳን ሕዝብ ሁሉ ችግር ላይ ስለጣለው የአንበጣ መቅሠፍት በማስረዳት ይጀምራል። ኢዩኤል ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ መሆኑን በመገንዘብ፥ ሕዝቡ ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ ይጋብዛል። 

2. ኢዩኤል ስለሚመጣው የጌታ ቀን ተነበየ (ኢዩኤል 2፡3)

የትንቢተ ኢዩኤል የመጨረሻ ግማሽ ክፍል ወደፊት ከረጅም ጊዜ በኋላ ስለሚሆነው ስለ ሌላ የጌታ ቀን ወደ መናገር ይመለሳል። በዚህ የትንቢተ ኢዩኤል ክፍል «ጣምራ ትንቢት»ን የሚያመለከቱ በርካታ መግለጫዎችን እናያለን። ይህም ሲባል እግዚአብሔር አንድን ትንቢት በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸሙ የተለያዩ ድርጊቶችን ለማመልከት ተጠቅሞበታል ማለት ነው።

ሀ. የይሁዳ ምድር መወረርና መጥፋት (ኢዩኤል 2፡1-11)፡፡ ይህም የሚያመለክተው የአሦርና የባቢሎን ወደ ይሁዳ መምጣትን ሳይሆን አይቀርም። በተጨማሪ ጌታ ኢየሱስ ዳግም ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሌሎች ሕዝቦች እስራኤልን ወርረው እንደሚያጠፏትም ያመለክታል። እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል ላይ የሚሰጠውን ይህን ፍርድ የሚያስቀረው የሕዝቡ በንስሐ መመለስ ብቻ ነበር።

ለ. የእስራኤል መመለስና የአይሁድ ተሐድሶ (ኢዩኤል 2፡18-32)፡- የመጨረሻው ዘመን በረከት የሚገኝበት ጊዜም ነው። እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ይመልሳል፤ ይህም የይሁዳን ሕዝብ የሚመለከቱትን የተላያዩ ጊዜያት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሕዝቡ በንስሐ በተመለሱ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር በሥጋዊ ብልጽግና ይጎበኛቸው ነበር። ዳሩ ግን ይህ ክፍል በአብዛኛው የሚያመለክተው አይሁድ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ተመልሰው በረከት የሚያገኙበትን የመጨረሻ ተሐድሶ ነው። 

ከኢዩኤል ትንቢቶች ሁሉ የላቀውና በሰፊው የሚታወቀው በኢዩኤል 2፡28-32 የሚገኘው ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ በበዓለ ኃምሳ ዕለት ባቀረበው ስብከት ይህን ክፍል ጠቅሷል (የሐዋርያት ሥራ 2፡16-21)። እንደ አብዛኞቹ ትንቢቶች፥ ይህም ክፍል ጣምራ ትርጉም ያለው ነው። መንፈስ ቅዱስ በአዲሲቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በወረደ ጊዜ ሐዋርያት የመጨረሻው ዘመን ደርሶአል ብለው አሰቡ። አዲስ ኪዳን የኢየሱስ መሞትና የመንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሁሉ ላይ መውረድ የመጨረሻውን ዘመን መድረስ ያሳያል ብሎ ያስተምራል። ይሁን እንጂ አማኞች የመጨረሻውን ዘመን መንፈሳዊ ሕይወት በከፊል ቢለማመዱትም፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለመግዛት እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ እንደማይፈጸም አዲስ ኪዳን በተጨማሪ ያስተምራል። ስለዚህ የመጨረሻው ፍጻሜ የሚሆነው ገና ወደፊት ነው።

ይህም በዚህኛው የኢዩኤል ትንቢት በግልጽ ይታያል። ክርስቲያኖች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ቢኖራቸውም፥ ሰዎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ አላቸው ማለት አይደለም። ሁላችንም መንፈስ ቅዱስ የሌላቸውን የማያምኑ ሰዎች እናውቃለን። ነገር ግን አንድ ቀን በምድር የሚኖሩት የተቀደሱ ሕዝቦች ብቻ ስለሚሆኑ ሰዎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ይኖራቸዋል። በኢዩኤል የተነገረው ትንቢት ሰማያት ስለሚለወጡበት ጊዜም ይናገራል። ይህ ደግሞ በበዓለ ኃምሳ እንዳልተፈጸመ ግልጽ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመለስ ይፈጸማል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡10-13)።

ሐ. በአሕዛብ ላይ የሚመጡ ፍርዶችና የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያገኟቸው በረከቶች (ኢዩኤል 3፡1-2)፡- የመጨረሻው የጌታ ቀን በአሕዛብ ላይ በሚሰጡ ፍርዶችም የታወቀ ነው። እጅግ በርካታ ሕዝቦች በጌታ ፊት በመሰብሰብ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነትና በምድር ላይ በፈጸሟቸው ተግባራት ምክንያት ይፈረድባቸዋል። የእግዚአብሔር ሕዝብ በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን ብልጽግናንና በረከት ያገኛል።

የውይይት ጥያቄ፥ ከትንቢተ ኢዩኤል የተማርሃቸውንና ለቤተ ክርስቲያንህ የሚያስፈልጓትን ትምህርቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: