የትንቢተ ዮናስ ዓላማ

ትንቢተ ዮናስ ትንቢትን የያዘ ባይሆንም እንኳ አመዳደቡ ከትንቢት መጻሕፍት ውስጥ ነው። አይሁዶች ይህንን ያደረጉት ለምድን ነው? የዮናስ ታሪክ የተጻፈው ለአሦራውያን ጥቅም ሳይሆን፥ ለአይሁድ ነበር። እግዚአብሔር ለእነርሱ ስላለው ዓላማና ፍላጎት በርካታ የሆኑ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንዲማሩ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነበር። ዮናስ ራሱ መማር የነበረበትን ትምህርት የእስራኤል ሕዝብ መማር ነበረባቸው፡፡ 

1. እግዚአብሔር አይሁድን ሲጠራ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ በስግብግብነት በመኖር በእግዚአብሔር በረከት ብቻቸውን ደስ እንዲሰኙ ሳይሆን ለአሕዛብም በማዳረስ የእግዚአብሔር መሣሪያዎች እንዲሆኑ ነበር። «የካህናት መንግሥት» ነበሩ (ዘጸአት 19፡6)። ለአሕዛብ ብርሃን መሆን ይጠበቅባቸው ነበር (ኢሳያያስ 42፡6፤ 49፡6)። አሕዛብ የሚባረኩት በእነርሱ በኩል ነበር (ዘፍጥረት 12፡3)። እስራኤላውያን ግን ይህንን በመዘንጋት እግዚአብሔር መባረክ ያለበት እነርሱን ብቻ እንደሆነና አሕዛብ መረገምና መደምሰስ እንዳለባቸው አሰቡ። እግዚአብሔር የዮናስን ሕይወት እስራኤላውያን የተመረጡበትን ዓላማ ለማስታወስ ተጠቀመበት። በዮናስና በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን ተመሳሳይ ነገሮች ተመልከት፡-

– ለአሕዛብ ወንጌል ይሰብኩ ዘንድ እግዚአብሔር ዮናስንና እስራኤልን ጠራቸው። 

– ዮናስና እስራኤል ግን ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመታዘዝ ሳይፈቅዱ ቀሩ። 

– ዮናስ በባሕር ውስጥ በመጣል፥ እስራኤል ደግሞ በአሕዛብ መካከል በመበትን ተቀጡ። (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሕር ብዙ ጊዜ የአሕዛብ ምሳሌ ነው።) 

– እግዚአብሔር ዮናስን በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ እንደጠበቀው፥ የእስራኤልንም ሕዝብ ይጠብቃል። 

– ዮናስ ንስሐ ገብቶ ተመለሰ። አንድ ቀን እስራኤልም ንስሐ ገብታ ትመለሳለች። ዮናስ በመጨረሻ ለእግዚአብሔር እንደታዘዘ፥ እስራኤልም አንድ ቀን ለእግዚአብሔር በመታዘዝ የዓለም ብርሃን ትሆናለች።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእስራኤልና የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው? ለ) ዮናስ ለነነዌ የነበረው አመለካከት ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን በሌሎች ነገዶች ደኅንነት ላይ ካላቸው አመለካከት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) የአንተ ቤተ ክርስቲያን እንደ እስራኤልና ዮናስ የመሆን አደጋ ይገጥማታል ብለህ ታስባለህ? መልስህን አብራራ።

2. በአንዳንድ ምሁራን አስተሳሰብ የመጽሐፉ ዓላማ፥ እግዚአብሔር – አሕዛብ ለነበሩት ለነነዌ ሰዎች እንደራራ፥ እስራኤልም በዙሪያዋ ላሉት አሕዛብ በመራራት ይቅር እንድትል ማስተማር ነው (ማቴዎስ 5፡44 ተመልከት)።

3. ሌሎች ምሁራን ደግሞ የዚህ መጽሐፍ ትኩረት በእግዚአብሔርና በባሕርዩ እንዲሁም ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ነው ይላሉ። የመጽሐፉ ትኩረትና ዐቢይ ትምህርት እግዚአብሔር ለመረጠው ሕዝብ ቸር ለመሆን ያለውን ችሎታና መብት ማሳየት በመግለጽ፥ እግዚአብሔር በማን ላይ መፍረድና ማንን ይቅር ማለት እንዳለበት መወሰን የሰዎች መብት አይደለም። እግዚአብሔር ሰዎችን ይቅር ለማለትና ሁለተኛ ዕድል ለመስጠት ያለውን ፍላጎት የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዮናስና ነነዌ ተመሳሳይ ነበሩ። ሁለቱም ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ይኖሩ ነበር። ይህ አለመታዘዛቸው ወደ እግዚአብሔር ፍርድ መራቸው። ሁለቱም ከነበሩበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ በራሳቸው ኃይል ለመውጣት አልቻሉም ነበር። በመጨረሻ ሁለቱም የነበሩበትን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ አስተዋሉና በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። እግዚአብሔር ሁለቱንም ያዳናቸውና የታደጋቸው በጸጋው ነው። ሰዎች ኃጢአት ከበዛበት መንገዳቸው ወደርሱ ሲመለሱ፥ እግዚአብሔር ጸጋውን ለማሳየት ይወዳል። ለሰዎች ሁለተኛ ዕድል መስጠት ይወዳል።

ነነዌ ከእግዚአብሔር ፍርድ ራስዋን ማዳን አትችልም ነበር። ለሕዝቦቿ ብቸኛው ዕድላቸው ወደ እግዚአብሔር በንስሐ መመለስ ነበር። ይህም በመሆኑ፥ እግዚአብሔር በትክክለኛ አቅጣጫ የጀመሩትን ርምጃ በማክበር በእነርሱ ላይ ሊያመጣ የነበረውን ፍርድ ለጊዜው አስተላለፈው። የነነዌ ሰዎች ብዙ ሳይቆዩ ወደ ቀድሞው ኃጢአታቸው ስለተመለሱ ንስሐቸው በጣም የላላ ነበርና እግዚአብሔርን በእውነት አምነው ነበር ለማለት አይቻልም። በጥቂት ዓመታት ውስጥ እስራኤልን ይወጋሉ፤ ፈጽመውም ያጠፏታል፤ ሕዝቡንም ይማርካሉ። ቆይተን በትንቢተ ናሆም ውስጥ እንደምናየው እግዚአብሔር በነነዌ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ሊለወጥ የማይችል ነበር።

ነነዌና ዮናስ ለእስራኤል ሕዝብ ትምህርት ሰጪዎች ነበሩ። ስለዚህ ትንቢተ ዮናስ ለእስራኤል ሕዝብ ማስጠንቀቂያ ነበር። ዮናስ መጻሕፍት ካዘጋጁት ከመጀመሪያዎቹ ነቢያት አንዱ ነበር። ከእርሱ በኋላ የተነሡ ነቢያት ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እንደሚጠፉ አመልክተዋል። በትንቢተ ዮናስ ግን እስራኤላውያን እንደ ነነዌ ሕዝብ እንደነበሩ በመጥቀስ ያስጠነቅቃቸዋል። በኃጢአታቸው ምክንያት ሊፈረድባቸውና ሊጠፉ ይገባቸው ነበር። እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ጥበቃ የመጠየቅ መብት እንደሌላቸው አለመታዘዛቸውን ያመለክት ነበር። እግዚአብሔር ግን ጸጋውን ሊያሳያቸው ፈለገ። ስለዚህ ንስሐ ሲገቡና ከክፋታቸው ቢመለሱ እግዚአብሔር የፍርድ እጁን ከእነርሱ ላይ ሊያነሣ ደስታው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ መጽሐፍ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምን እንማራለን? ለ) ስለ ንስሐና ደኅንነት ምን እንማራለን? ሐ) ከዚህ ውስጥ ስለ እውነተኛ ንስሐና ስለ ሐሰተኛ ንስሐ ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d