ዘካርያስ 1-14

ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ትንቢትን የሰጠው ወደፊት ምን እንደሚሆን እንድናውቅ ነው ብለው ያስባሉ። ስለዚህ የትንቢትን መጻሕፍት የሚያጠኑት በከፍተኛ ጉጉት ነው። ወደፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ምን እንደሚሆን ለማወቅ፥ ወይም ሩስያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሳ እንደሆነ ወይም በመጨረሻዎቹ ቀናት ከእስራኤል ጋር የሚዋጉት አገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ በመጓጓት ያጠናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ትንቢትን በተመለከተ የዚህ ዓይነት አመለካከት ሲጠቀሙ ያየኸው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር የትንቢት መጻሕፍትን መልእክት የሰጠን ወደፊት ምን እንደሚሆን የማወቅ ፍላጎታችንን ለማርካት አይደለም። ትንቢት የተሰጠው የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በተለይም ደግሞ በስደት ውስጥ የሚኖሩትን እግዚአብሔር የበላይ ተቆጣጣሪ መሆኑን በማስተማር ለማበረታታት ነው። እግዚአብሔር ስለመጪው ጊዜ ዕቅድ አለው። ይህ ዕቅድ ጦርነቶችንና ፍርድን የሚጨምር ነው። ይህም ቢሆን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር የሚፈጸም ነው። ይህ ዕቅድ በሚጠቃለልበት ጊዜ እግዚአብሔር ፍጹም በሆነው ምድር ይነግሣል። ኃጢአትና ሞት ይደመሰሳሉ። ክርስቲያኖች በእምነታችን ምክንያት በምንሰደድበት ጊዜ ወይም ብዙ ችግሮች ሲያጋጥሙን ፍጻሜያችን መልካም መሆኑን በማስታወስ ልብ ገዝተን ልንኖርና በእምነታችን ልንጸና እንችላለን። ወደፊት እግዚአብሔር ምን ሊያደርግ እንዳለው በእምነት መመልከት እንችላለን።

በትንቢተ ዘካርያስ ውስጥ ዘካርያስ ተስፋ የቆረጡትን አይሁድ የሚያበረታታበት ዋና መንገድ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መምጣትና እርሱም የሚያመጣውን በረከት በማሳየት እግዚአብሔር የሁሉ ነገር የበላይ ተቆጣጣሪ መሆንን በማረጋገጥ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘካርያስ 1-14 አንብብ። ሀ) ዘካርያስ ያያቸውን የተለያዩ ራእዮች ዘርዝር። የእነዚህ ራእዮች ትርጉም ምን ይመስልሃል? ለ) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች የተጠቀሱትን የተለያዩ ትንቢቶች ዘርዝር። ሐ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠቀሱትን የተለያዩ ትንቢቶች ዘርዝር።

ክፍል 1፥ አይሁድ ቤተ መቅደሱን በመሥራት ላይ ሳሉ የመጡላቸው መልእክቶች (ዘካርያስ 1-8)

1. ዘካርያስ ንስሐ እንዲገቡ ለሕዝቡ ጥሪ አደረገ (ዘካርያስ 1፡1-6)

አይሁድ ለእግዚአብሔር ታዝዘው ቤተ መቅደሱን እየሠሩ ቢሆኑም እንኳ በሕይወታቸው አሁንም ኃጢአት ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ዘካርያስ የሚጀምረው አይሁድን ስለ ኃጢአታቸው በመውቀስና ንስሐ እንዲገቡ ጥሪ በማድረግ ነው። ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ከምናደርግለት ይልቅ ብንቀደስለት ይመረጣል። እግዚአብሔር የምናደርግለትን ነገር የሚቀበለው ከኃጢአታችን ንስሐ ስንገባ ብቻ ነው። አይሁድ የዘካርያስን መልእክት ከሰሙ በኋላ ንስሐ ገቡ። እግዚአብሔርም ይባርካቸው ዘንድ ከሚችልበት ሁኔታ ላይ ደረሱ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚህ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች ቅዱሳን ከመሆን ይልቅ የእግዚአብሔርን ነገር ማከናወን የሚቀላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ነገር ሲፈጸም እንዴት እንደተመለከትህ የሚያስረዱ ሥዕላዊ መግለጫዎችን ዘርዝር። ሐ) እግዚአብሔር ለእርሱ ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት እንቀደስ ዘንድ በእጅጉ አበክሮ የሚናገረው ለምን ይመስልሃል? 

2. ዘካርያስ በሌሊት ያያቸው ስምንት ራእዮች (ዘካርያስ 1፡7-6፡8)

ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው ካደረገው መልእክቱ ቀጥሎ፥ ዘካርያስ በአንድ ሌሊት ያያቸውን ስምንት ራእዮች ያቀርባል። እነዚህ ራእዮች በአሕዛብ እንደተጨቆኑ በመቁጠር ኃዘን የተሰማቸውንና ለእግዚአብሔር በሚሠሩት ሥራ ተስፋ ቆርጠው የነበሩትን አይሁዶች የሚያበረታቱ ነበሩ፤ እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጠውን ግልጽ የሆነ ልዩ የማበረታቻ መልእክት የያዙ ነበሩ።

ሀ. የመጀመሪያው ራእይ – በዛፎች መካከል ቆሞ የነበረው ፈረሰኛ (ዘካርያስ 1፡7-17) 

አይሁድ ወደ አገራቸው ቢመለሱም፥ ገና በአሕዛብ ቁጥጥር ሥር ነበሩ። አሕዛብ በምቾት ሲዝናኑ እነርሱ ግን በመከራ ውስጥ ነበሩ። ነገር ግን እግዚአብሔር ነገሮችን ተቀጣጥሮ ነበር። ፈረሰኛው በዓለም ሁሉ ተዘዋውሮ ሰላምን እንዳገኘ ሁሉ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደሱ እንደሚሠራና የእስራኤል ሕዝብ በሰላም እንደሚኖር ለአይሁድ ተስፋ ሰጠ። ሰላም እየመጣ ነበር፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ምትክ ሆኖ እስኪሠራና የይሁዳን ምድር እስኪያድስ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው።

ለ. ሁለተኛው ራእይ – አራት ቀንዶችና አራት ጠራቢዎች (ዘካርያስ 1፡18-21) 

ለአይሁድ ቀንድ የብርታትና የኃይል ምልክት ነበር። እነዚህ ቀንዶች እስራኤልን የበተኑትን መንግሥታት ወይም በአሕዛብ ላይ የነገሡትን ነገሥታት ሊያመለክቱ ይችላሉ። ቀንዶቹ እስራኤልን የበተኑና አይሁድን ወደ ምርኮ የወሰዱትን መንግሥታት የሚወክሉ ነበሩ። በዚህ ስፍራ የቀንዶቹ አራት መሆን አራት የተለያዩ መንግሥታትን የሚወክል ይሆናል የሚለው አሳብ ምሁራንን ያከራክራቸዋል። አንዳንዶች እነዚህ አራት መንግሥታት ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ፥ ግሪክና ሮም ናቸው ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ አሦር፥ ግብፅ፥ ባቢሎንና እንዲሁም ሜዶንና ፋርስ ናቸው ይላሉ።

አራቱ ጠራቢዎች የሚወክሉት ደግሞ ለአይሁድ መበተን ምክንያት የሆኑት የአሕዛብ መንግሥታት የሚቀጡባቸውን የእግዚአብሔርን የፍርድ መሣሪያዎች ነው። እስራኤልን የወጉ ሁሉ በተራቸው ይደመሰሳሉ። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ አራት ጠራቢዎች ባቢሎንን የደመሰሰው ሜዶንና ፋርስ፥ ሜዶንና ፋርስን የደመሰሰው ግሪክ፣ ግሪክን የደመሰሰው ሮም፥ በመጨረሻ ላይ የሮምን መንግሥት የሚደመስሰው መሢሑ ነው ብለው ያምናሉ።

ዋናው ትምህርት የእስራኤልን ጠላቶች እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ይደመስሳቸዋል የሚለው ነው። እግዚአብሔር ጠላቶቹን የሚደመስስባቸው የተለያዩ ዓይነት ጠራቢዎች አሉት።

ሐ. ሦስተኛው ራእይ – የመለኪያ ገመድ የያዘው ሰው (ዘካርያስ 2)

በዘካርያስ ዘመን የኢየሩሳሌም ቅጥሮችና የከተማው አብዛኛው ክፍል ተደምስሶ ነበር። ነህምያ ከአይሁድ ጋር ቅጥሩን ለመሥራት የሚመጣው ገና ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር። በጥንት ጊዜያት አንድ ከተማ ቅጥር ከሌለው፥ የማይረባና ጥቃት መፈጸም ለሚፈልግ ጠላት ሁሉ የተጋለጠ ነበር።

በዚህ ራእይ ዘካርያስ የኢየሩሳሌምን ከተማ ለመለካት የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው ይመለከታል። ዳሩ ግን በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖረው ሕዝብ እጅግ ብዙ ስለነበር ለመለካት ጨርሶ የማይቻል ነበር። እግዚአብሔር አንድ ቀን የኢየሩሳሌም ከተማ ቅጥር ሊኖራት እስከማይችል ድረስ እጅግ ታላቅ ትሆናለች የሚል ተስፋ ሰጠ። እግዚአብሔር ራሱ በከተማዋ ውስጥ ስለሚኖርና የእሳት ቅጥር ስለሚሆናት ለጥበቃ የሚሆን ምንም ዓይነት ቅጥር የማያስፈልግበት ጊዜ ይመጣል።

ከአይሁድ መካከል ከምርኮ የተመለሱት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ብዙዎቹ በባቢሎንና በሌሎች አሕዛብ መካከል በምቾት መኖርን መረጡ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ጥሪ አደረገላቸው። አንድ ቀን አይሁድን ሁሉ ከዓለም ዙሪያ በመሰብሰብ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚያመጣቸው ተናገረ። በዚያም ከእነርሱ ጋር ከሚተባበሩ ሌሎች ሕዝቦች ጋር እግዚአብሔር አብሮአቸው ይሆንና ይባርካቸዋል።

መ. አራተኛ ራእይ – ለታላቁ ካህን ለኢያሱ የተሰጡ ንጹሕ አልባሳት (ዘካርያስ 3) 

ኢያሱ የእስራኤል ሊቀ ካህን ነበር። ይሁን እንጂ የሚሠራበት ቤተ መቅደስና ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩ ካህናት ይለብሱአቸው የነበሩት ዓይነት ንጹሕና ጌጠኛ አልባሳት አልነበሩትም። ታዲያ እርሱ በእርግጥ የሕዝቡ መንፈሳዊ መሪ ነበርን? እግዚአብሔር አገልግሎቱን ተቀብሏልን? ኢያሱ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሣሪያ መሆኑን ለሕዝቡ ለማሳየት እግዚአብሔር ለዘካርያስ ራእይ ሰጠው። በዚያ ራእይ ሰይጣን ንጹሕ አይደለም በማለት ኢያሱን በእግዚአብሔር ፊት ሲከሰው እንመለከታለን። (እድፋም ልብስ የመንፈሳዊ ንጽሕና ጉድለት ምልክት ነበር።) እግዚአብሔር ግን ኢያሱን የመረጠው እርሱ እንደሆነና በፊቱ ንጹሕ እንደሆነ ለሰይጣን ያረጋግጥለታል። (ጥሩ ልብስና ንጹሕ ጥምጥም ተደረገለት።) ሊቀ ካህን መሆን እንደሚገባው ለማረጋገጥ እግዚአብሔር ለኢያሱ የሊቀ ካህን ልብስ ሰጠው።

ካህን እንዲሆን የተጠራው ኢያሱ የእስራኤል ሕዝብ ተምሳሌትም ነበር (ዘጸአት 19፡5-6)። ሰይጣን ኢያሱን እንደከሰሰ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ የሆኑትን እስራኤልንም ንጹሕ አይደላችሁም በማለት ከሰሳቸው። ዳሩ ግን እግዚአብሔር አንጽቶ እንደገና የእርሱ ካህናት ይሆኑ ዘንድ ጠራቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰይጣን ኃጢአተኛ ነህ በማለት ለሚከሰው ክርስቲያን እግዚአብሔር ስለሚሰጠው መልስ ይህ ራእይ ጥሩ መግለጫ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ኃጢአታችን የተሸፈነው በምንድን ነው?

በዚህ ራእይ ስለ ኢየሱስ የሚናገር አሳብ እናገኛለን፤ እርሱም ቅርንጫፍ ተብሏል። ይህም በኢሳይያስ 4፡2 እና በሌሎችም የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ከዳዊት ሥር የሚመጣውን መሢሕ ለማመልከት የተጠቀሰ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው። ይህ ትንቢት ሙሉ በሙሉ የሚፈጸመው በእርሱ ብቻ ነው። የሰዎችን ኃጢአት ለመሸፈንና አይሁድን ለማዳን በመስቀል ላይ በተፈጸመው የክርስቶስ የሞቱ ሥራ አንድ ቀን ኃጢአት ከምድሪቱ ፍጹም ይወገዳል፤ ሰላምም ይኖራል።

ሠ. አምስተኛ ራእይ – የወርቅ መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች (ዘካርያስ 4) 

የቤተ መቅደሱ ሥራ መጓተት ብዙዎቹን አይሁድ ተስፋ አስቆርጦ ነበር። የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ያህል ትልቅ እንዳልነበር አወቁ። ስለሆነም ምናልባት በዘሩባቤልና በኢያሱ ላይ ማጉረምረም ሳይጀምሩ አልቀሩም።

እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ የፖለቲካ መሪ የነበረውን ዘሩባቤልንና መንፈሳዊ መሪ የነበረውን ኢያሱን በመንፈሱ እንዳበረታቸው ለሕዝቡ የሚያስረዳ አምስተኛ ራእይ ለዘካርያስ ሰጠው። በዚህ ራእይ ዘካርያስ ሰባት መብራቶች የነበሩበትን አንድ የወርቅ መቅረዝ አየ። በወርቅ መቅረዙ ላይ የዘይት ማሰሮ ነበር። በወርቅ መቅረዙ አጠገብ በማሰሮው ግራና ቀኝ አይሁድ ለመቅረዙ ብርሃን ዘይት የሚያወጡባቸው ሁለት የወይራ ዛፎች ነበሩ። ከማሰሮው ወደ ሰባቱ መብራቶች ያለማቋረጥ ዘይት የሚያስተላልፉ ሰባት ቧንቧዎች ነበሩ። ዘሩባቤልና ኢያሱ ሁለቱ የወይራ ዛፎች ነበሩ። እግዚአብሔር እነዚህን ሁለት ሰዎች ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መርጦአቸው ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ምልቷቸው ነበር። እነዚህ መሪዎች የጌታን ሥራ የሚያከናውኑትና ቤተ መቅደሱን የሚሠሩት በኃይል ወይም በራሳቸው ብርታት እንዳልሆነ ማስታወስ አስፈላጊያቸው ነበር። ነገር ግን ኃይልን በሚያስታጥቃቸው፥ በእነርሱ በኩል በሚሠራውና ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ይሠሩ ዘንድ በሚያበረታቸው በእግዚአብሔር መንፈስ ላይ መደገፍ ነበረባቸው። የወርቅ መቅረዙና መብራቶቹ ደግሞ የሚያመለክቱት፥ እግዚአብሔር እስራኤልን ለአሕዛብ ብርሃን እንድትሆን እንደመረጣት ሳይሆን አይቀርም (ኢሳይያስ 42፡6፤ 49፡6)። ቤተ መቅደሱን በመሥራት እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ችሎታ እግዚአብሔር ከሚሰጣቸው ከመንፈስ ቅዱስ ማግኘት አስፈላጊያቸው ነበር። እስራኤላውያንም ልክ እንደ ዘሩባቤል መታመን ያለባቸው በራሳቸው ችሎታ ብቻ ሳይሆን፥ የሁሉ ነገር ምንጭ የሆነውን እግዚአብሔርን በመፈለግ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚህ ዘመን ያሉ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔርን ሥራ በራሳቸው ብርታት ለመሥራት የሚሞክሩባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ለዘሩባቤልና ለኢያሱ የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች ዛሬ ለእኛ ከሰጠን ጋር ተመሳሳይ የሚሆኑት እንዴት ነው?

ረ. ስድስተኛው ራእይ – በራሪው የመጽሐፍ ጥቅልል (ዘካርያስ 5፡1-4) 

ዘካርያስ በስድስተኛው ራእይ 9 ሜትር ርዝመትና 4.5 ሜትር ወርድ የነበረውን አንድ የመጽሐፍ ጥቅልል ተመለከተ። በመጽሐፉ ሁለት ጐን እርግማን ተጽፎ ነበር። የመጽሐፉ ጥቅልል በአየር ላይ ይበርር ነበር።

ይህ ራእይ እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ሳይቀጣ እንደማይተው የሚያሳስብ ነበር። ንስሐ ገብተው ካልተመለሱና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወትን ካልኖሩ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉትን እርግማኖች በሙሉ ሊያመጣባቸው ወስኖ ነበር (ዘዳግም 28፡5-68)። ይህ ክፍል የሚያተኩረው ግለሰቦች በሚሠሩት ኃጢአት ላይ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡ በማኅበር ደረጃ እንዲቀደሱ ይፈልግ ነበር። ነገር ግን እያንዳንዱ ግለሰብም በግሉ ደግሞ እንዲቀደስ ይፈልግ ነበር። የሚሰርቁ ወይም የሚዋሹ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ይደርስባቸው ነበር።

ሰ. ሰባተኛው ራእይ – በኢፍ መስፈሪያ ውስጥ ተቀምጣ የነበረችው ክፉ ሴት (ዘካርያስ 5፡5-11)

ስድስተኛው ራእይ በተለይ የሚናገረው ስለ ግለሰቦች ክፋትና ኃጢአት ሲሆን፥ ሰባተኛው ደግሞ እስራኤላውያን በሕዝብነታቸው የሠሩትን ኃጢአት ይገልጣል። ዘካርያስ በእርሳስ መክሊት የተከደነ አንድ የኢፍ መስፈሪያ አየ። በውስጡ አንዲት ሴት ነበረች። ሌሎች ሴቶች የኢፍ መስፈሪያውን አንሥተው በመብረር ወደ ሰናዖር ወሰዱት። (ሰናዖር የባቢሎን ሌላው ስም ነው።)

ይህ ራእይ እግዚአብሔር ክፋትን መታገሥ እንደማይችል ያሳያል። በክፋታቸው የሚቀጥሉ ሰዎች ከምድሪቱ መወገድ ነበረባቸው። ይህ ነገር በተለይ አንድ ቀን እግዚአብሔር ክፋትን ሁሉ ከሕዝቡ እንደሚያስወግድ የሚያመለክት ነበር። የክፋት ስፍራ ተምሳሌት ወደሆነችው ወደ ባቢሎን ይወሰዳል። በዚያ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንደገና ጨርሶ ሊያውክ በማይችልበት ሁኔታ ይጠበቃል።

የእስራኤልን ሕዝብና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ፥ ዋናው ችግር ስደት አልነበረም። ይልቁንም ቀስ በቀስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርጎ የሚገባው ክፋትና ኃጢአት ነው። ይህ ክፋትና ኃጢአት ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር እርስ በርስና ከዓለም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ ያበላሻል። ዛሬም ቢሆን ቅድስናችንን ለመጠበቅ መታገል አለብን። አለበለዚያ ከእግዚአብሔር የበረከት ስፍራ እንወገዳለን። ለሁላችንም ማበረታቻ የሚሆነን ተስፋ ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ክፋትን ሁሉ ከምድር የሚያስወግድ መሆኑ ነው። ያኔ በእውነት እንቀደሳለን። 

ሸ. ስምንተኛው ራእይ – አራቱ ሰረገሎች (ዘካርያስ 6፡1-8)

ዘካርያስ በመጨረሻው ሌሊት በተሰጠው ራእይ አራት ሰረገሎችን አየ። አራቱ ሰረገሎች በቡድን በተጣመሩ ፈረሶች የሚጎተቱ ነበሩ። የመጀመሪያው ሰረገላ በመጋላ፥ ሁለተኛው በዱሪ፥ ሦስተኛው በአምባላይ አራተኛው ደግሞ በቅጠልማ ፈረሶች የሚመሩ ነበሩ። እነዚህ አራት ሰረገሎች እንደ መጀመሪያው ራእይ እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ እንደሆነ ያሳዩ ነበር። እርሱ የታሪክና የሕዝቦች ሁሉ የበላይ ተቆጣጣሪ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑትን እስራኤልን በሚወጉ ሁሉ ላይ ይፈርዳል። እነዚህ ሰረገሎች ታሪክን በመቆጣጠር ሂደት ውስጥ የእግዚአብሔርን መላእክት ሥራ የሚያሳዩ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የስምንቱን ራእዮች ዐበይት ትምህርቶች በአጭሩ አቅርብ። ለ) እነዚህን ትምህርቶች ከሕይወታችን ጋር የምናዛምደው እንዴት ነው?

3. የሊቀ ካህኑ የኢያሱ ተምሳሌታዊ አክሊል መጫን (ዘካርያስ 6፡9-15) 

እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል መካከል ባዋቀረው መዋቅር ውስጥ ሦስት የተለያዩ ዓይነት መሪዎች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው፥ የፖለቲካ አመራሩን የሚይዘው ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የፖለቲካ መሪነት ሥልጣን እንዲይዝ ያደረገው ከይሁዳ ነገድ የዳዊትን ዘር ነበር። ሁለተኛው፥ የሃይማኖት መሪዎች የሆኑት ካህናት ነበሩ። ይኸኛው ደግሞ ከሌዊ ነገድ ለአሮን ዘር የተሰጠ ኃላፊነት ነበር። ሦስተኛው፥ እግዚአብሔር ከየትኛውም ነገድ የሚመርጣቸውና የእርሱን መልእክት ወደ ሕዝቡ የሚያመጡ ነቢያት ነበሩ። እነዚህ ሦስት ዓይነት መሪዎች ብዙ ጊዜ ለብቻ ተለይተው ያሉ ነበሩ። እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው የመሪነትን ሚዛናዊነት ለመጠበቅ ነበር።

ዳሩ ግን ኣንድ ቀን እግዚአብሔር ለዘካርያስ አክሊል ሠርቶ በሊቀ ካህኑ በኢያሱ ላይ እንዲጭን ነገረው። እግዚአብሔር በዚህ ተምሳሌት የተናገረው አንድ ቀን የካህንና የንጉሥ ሥልጣን እንደሚዋሐዱ ነበር። ኢያሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌት ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌዊ ነገድ ሳይሆን ከመልከ ጼዴቅ ወገን የነበረ ካህን ነው። ደግሞም ከዳዊት ነገድ የሆነ ንጉሥ ነው። በዚህ ስፍራ ይህንን የሚያመለክት ነገር ባይኖርም እንኳ ኢየሱስ ነቢይ እንደ ነበረ እናውቃለን። ስለዚህ ሦስቱንም ዓይነት አመራር በአንድ ላይ የያዘ ነበር።

ዘካርያስ አንድ ቀን «ቁጥቋጦ» እንደሚመጣ ተነበየ። ይህም የመሢሑ ሌላው ስሙ ነው። በንጉሣዊ ማዕረግ ልብሱን ለብሶ ዙፋን ላይ ይቀመጣል። ቤተ መቅደሱንም ደግሞ ይሠራል። ሁለቱን የንጉሥና የካህንን ሥልጣን ያጣምራል።

4. ጾምን ስለሚመለከት ችግርና ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች የተነገሩ ታላላቅ ተስፋዎች (ዘካርያስ 7-8) 

ሰዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ይጾማሉ። አንዳንዶች በቋሚነት የሚጾሙት የቤተ ክርስቲያናቸው ልማድ ስለሆነ ነው። ጾም በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለው ስፍራ እጅግ አነስተኛ ነው። ሌሎች ደግሞ የሚጾሙት ሊጸልዩበት የሚፈልጉት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ሲኖራቸው ነው። ሁሉን ነገር መብላትንም ቢሆን እንኳ ትተው ከልባቸው በመጸለይ በእግዚአብሔር ፊት ይቆያሉ። በብሉይ ኪዳን ሕግጋት እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሚጾሙባቸውን የተለዩ ቀናት ደንግጎላቸው ነበር። ራሳቸውን የሚመረምሩበትና ከኃጢአታቸው የሚነጹበት ጊዜ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አይሁድ እግዚአብሔር በሰጣቸው የጾም ቀናት ላይ ሌሎች ቀናትን ጨመሩ። ከምርኮ በኋላ አይሁድ ኢየሩሳሌም በተደመሰሰችበት ጊዜ፥ ቤተ መቅደሱ በፈራረሰበትና ጎቶልያ በተገደለችበት ቀን ይጾሙ ነበር። የምርኮው ዘመን አብቅቶ አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በተመለሱ ጊዜ እነዚህን ሦስት የጾም ቀናት ማክበር እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ማወቅ ፈለጉ።

እግዚአብሔር በዘካርያስ በኩል ለዚህ ጥያቄአቸው መልስ ሰጣቸው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡ በተለይም የሃይማኖት መሪዎች በሚጾሙበት ወይም የሃይማኖት በዓላትን በሚያከብሩበት ጊዜ ትክክለኛ ዝንባሌ የሌላቸው መሆኑን በመጥቀስ ወቀሳቸው። ጾምና በዓል እውነተኛ የሆነውን የመጀመሪያ ትርጉማቸውን እየሳቱ ሥርዓት ብቻ ሆነው ይፈጸማሉ። የሃይማኖት ሥርዓቶች ተገቢውን ትርጉም ይዘው ትክክለኛ በሆነ ግንዛቤ እንዲሁም ትክክለኛ በሆነ ልብ ካልተፈጸሙ ዋጋ የሌላቸው ተግባራት መሆናቸውን እግዚአብሔር ለአይሁዶች ኣስተማራቸው።

በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር፥ እርሱን ደስ የሚያሰኙ የሚያደርጓቸውን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የሕይወት ቁም-ነገሮችን ለአይሁዶች ያስታውሳቸዋል። እግዚአብሔርን ማክበር ከፈለጉ፥ በእርስ በርስ ግንኙነታቸው ትክክለኛ ፍርድን በማድረግ በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በመርዳትና አንዳቸው ለሌላቸው መልካምን እንጂ ክፉን ባለማሰብ መኖር ነበረባቸው። እግዚአብሔር አባቶቻቸውን በምርኮ የቀጣው ሃይማኖታቸውን በተግባር ባለሙግለጻቸውና ፍቅርን ለሰዎች ሁሉ ባለማሳየታቸው ነበር።

በሦስተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ወደ ፊት ለሕዝቡ ለእስራኤልና ለኢየሩሳሌም የሚሰጣቸውን በረከቶች አመለከተ። ኢየሩሳሌም ትባረካለች፤ እግዚአብሔር በውስጧ ያድራል፥ እርስዋም በእውነት ትሞላለች። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ ተመልሰው እርሱን በጽድቅ እንዲያመልኩት ጥሪ ያቀርብላቸዋል። አሕዛብም የጌታን በረከት ለመቀበል ከእስራኤላውያን ጋር ይተባበራሉ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዚህ መንገድ ከባረከ የመታሰቢያ ጾማቸው ወደ ደስታ ይለወጣል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ የምንፈጽማቸውን የሃይማኖት ሥርዓቶች ከልብ እንጂ ከልማዳዊ ሥርዓት አንጻር ብቻ እንዳናደርጋቸው ይህ ክፍል የሚያስታውሰን እንዴት ነው? ለ) ከልብ ካልሆኑና በትክክለኛ ዝንባሌ ካልተደረጉ በስተቀር መልካም ቢሆኑም እንኳ ዋጋ የሌላቸውን አንዳንድ ተግባራት ጥቀስ።

ክፍል 2፥ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ለአይሁድ የተነገሩ ሁለት መልእክቶች (ዘካርያስ 9-12)

የትንቢተ ዘካርያስ የመጨረሻ ክፍል በተለይ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች የተነገሩ ትንቢቶችን የያዘ ነው። የሚከተሉትን ትንቢቶች ልብ ብለህ ተመልከት፡-

1. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በከበቡት አሕዛብ ሁሉ ላይ ይፈርዳል (ዘካርያስ 9፡1-8) 

2. የእስራኤል ንጉሥ መሢሑ በውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣል። በጥንት ዘመን የነበሩ ነገሥታት የሚመጡት ለሰላም እንጂ ለጦርነት አለመሆኑን ለመግለጽ በአህያ ላይ ይቀመጡ ነበር (መሳፍንት 10፡4፤ 2ኛ ሳሙኤል 16፡2 ተመልከት)። መሢሑ የሰላም ንጉሥ በመሆኑ፥ የጦር መሣሪያዎችን ሁሉ በመደምሰስ ለሕዝቡ ደኅንነትን ያመጣል፤ የታሰሩትን ነፃ ያወጣል። እግዚአብሔር ሕዝቡን በሚያድንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ጸጋ ጽዋዎች ይሆናሉ (ዘካርያስ 9፡9-17)። 

3. እግዚአብሔር ይሁዳን ይንከባከባል። ምድሪቱን ይባርካል። እስራኤልን ያስኮበለሉትን እረኞች (ክፉ መሪዎች) ይቀጣል። እግዚአብሔር የተበተኑትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ እስራኤል መልሶ ይሰበስባቸዋል (ዘካርያስ 10)።

4. እግዚአብሔር በዘካርያስ ሕይወት አማካይነት መልካምና ክፉ እረኞችን በማነጻጸር አቅርቦአል። በዚህ ረገድ ዘካርያስ የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ ታይቷል (ዮሐንስ 10)። አንዳንድ ምሁራን፥ ዘካርያስ የሚያመለክተው መሢሑን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመቀበላቸው በአይሁድ ላይ የሚመጣውን ፍርድ ነው ይላሉ። ኢየሱስ በአብዛኛው ያገለገለው ተጨቁነው የነበሩትን ሰዎች እንደሆነ ሁሉ፥ ዘካርያስም በሌሉች የተጨቆኑ የበጎች መንጋ እረኛ ሆነ። የዘካርያስ ሁለት በትሮች፡- ውበት (ሞገስ) እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጣትን ውበት (ሞገስ) ሲያመለክት፥ ማሰሪያ ደግሞ ከሮብዓም ዘመን ጀምሮ ተከፋፍለው የነበሩት አይሁዳውያንና እስራኤላውያን አንድ እንደሚሆኑ የሚያመለክት ነበር (ዘካ. 11፡7)። ዘካርያስ በእስራኤል ክፉ እረኞችን ወይም የእስራኤልን ገዥዎች ለማጥፋት ጥረት አድርጎ ነበር። ነገር ግን በጎቹ (እስራኤላውያን) እንኳ ዘካርያስን ወይም መሢሑን አልሰሙም። ዘካርያስ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የነበረው ውበት (ሞገስ) መቋረጡን ለማሳየት ሁለቱን በትሮች ሰበራቸው። እንደ አንድ ባሪያ ለሥራው የተከፈለው ዋጋ ሠላሳ ብር ብቻ ሲሆን፥ ገንዘቡን በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ አኖረው። ይህም ይሁዳ ኢየሱስን እንዴት በሠላሳ ብር እንደ ሸጠውና የተቀበለውንም ገንዘብ እንዳልተጠቀመበት የሚያሳይ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። በዚህ ዘመን ያሉ አይሁዶች በዓለም ዙሪያ ተበትነው በግዞት እንዳሉ ሁሉ በጎቹ ወይም አይሁዶች በእግዚአብሔር ፍርድ ይበተናሉ። እረኛቸው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላልተቀበሉ በላያቸው ክፉ እረኞች ይሠለጥኑባቸዋል።

በኋላም ዘካርያስ እረኛው ሲመታ በጎቹ እንዴት እንደሚበተኑ በመናገር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ይተነብያል (ዘካርያስ 11፤ 13፡7-9)። 

5. እግዚአብሔር እስራኤልን ከጠላቶችዋ ይጠብቃታል። የኢየሩሳለምንም ጠላተት ይደመስሳል ዘካርያስ (12፡1-9)።

6. አይሁድ፥ በመስቀል ላይ የወጉትን ሚሑን ያዩታል። በዘመናት ሁሉ ስለፈጸሙት ድርጊትና ስለ አለማመናቸው በማዘን ንስሓ ይገባሉ። መሢሑ ምድሪቱን ፍጹም ያድሳታል፥ ያነጻታልም። የሐሰት አምልኮና ሐሰተኞች ነቢያት ይደመሰሳሉ (ዘካርያስ 12፡10-13፡6)። 

7. ጌታ ኢየሱስ ዳግም ሲመለስ ሁሉም ነገር ይለወጣል። መንግሥታት ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ ቢፈልጉም እንኳ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስለሚዋጋ ይደመስሳቸዋል። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዘላለማዊ ብርሃን ይሆናል። በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን መንፈሳዊ በረከትን የሚያስገኝ የሕይወት ውኃ ምንጭ ይፈልቃል። በሕይወት የሚቀሩ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመፍራት በኢየሩሳሌም ያመልኩታል። በምድር ላይ አንዳችም ክፋትና ኃጢአት አይኖርም። ነገር ግን ሁሉም ነገር “ለእግዚአብሔር የተቀደሰ” ይሆናል (ዘካርያስ 14)። 

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ከትንቢተ ዘካርያስ የተማርካቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) የቤተ ክርስቲያን አባሎች እነዚህን ትምህርቶች ሊማሯቸው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: