የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ እና ዐብይ ትምሕርት

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ

ከይሁዳ ውድቀት በፊት እግዚአብሔር የመጨረሻ መልእክተኞች ካደረጋቸው ቃል አቀባዮቹ አንዱ ሶፎንያስ ነበር። ሶፎንያስ በእግዚአብሔር የተላከው በክፋታቸው ምክንያት በቅርብ ጊዜ ስለሚፈጸምባቸው ፍርድ በመናገር የይሁዳን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ ነበር። ሕዝቡ ንስሐ ካልገቡና አኗኗራቸውን ካልለወጡ ሊመጣባቸው ስላለው ፍርድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለማቅረብ እግዚአብሔር ተጠቀመበት። በመሆኑም ሊመጣ ስላለው «የጌታ ቀን» ተናገረ። ይህ ቀን አብዛኛው ሕዝብ እንደሚጠብቀው የደስታና የበረከት ቀን አይሆንም። ይልቁንም ከበረከቱ ጊዜ በፊት በኃጢአተኞች ሁሉ ላይ ከፍተኛ የፍርድ ጊዜ ይኖራል። ፍርዱ የሚጀምረው በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ነው። ነገር ግን ክፉና ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች ሁሉ ላይም ይፈጸማል። ትሑታን የሆኑና ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የሚፈልጉ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲፈልጉ ተጠርተው ነበር። ሶፎንያስ የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ወደ ባቢሎን እንደሚወሰዱ በግልጽ ባያመለክትም፥ በይሁዳ ላይ ስለሚመጣ ትልቅ ጥፋትና ከምርኮ ስለ መመለሷም ተናግሮ ነበር (ሶፎንያስ 3፡20)።

ዛሬ ለሰዎች መስበክ ያለብን ወንጌል ሶፎንያስ ከብዙ ዓመታት በፊት ካስተላለፈው መልእክት ጋር ተመሳሳይ ነው። በአንድ በኩል ንስሐ ለሚገቡና ለእግዚአብሔር ወደ መታዘዝ ዞር ለሚሉ ሰዎች የደስታ፥ የሰላምና የመንፈሳዊ በረከት ተስፋ እንዳላቸው ልንነግራቸው እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን ነገሮች ለሰዎች ማሳየት አስፈላጊ ነው። ወንጌል በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች የዘላለም ሥቃይ እንደሚያገኛቸው የሚናገር መልእክትም አለው። ልክ አይሁዶች ያስቡት እንደነበረው፥ ሰዎች መልካም ሆኑ ክፉ እግዚአብሔር ግድ እንደሌለው አድርገው እንዲያስቡ መፍቀድ የለብንም። ንስሐ ገብተው፥ በኢየሱስ ማመንና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መራመድ እንዳለባቸው። አለበለዚያ ግን የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ልናሳስባቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ በእግዚአብሔር እንደሚፈረድባቸው በመናገር የሚያስጠነቅቁትን ጥቅሶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ጥቅሶች ለማያምኑ ሰዎች ልንነግራቸው የሚገባው የወንጌል ክፍል የሚሆኑት እንዴት ነው? ሐ) ክርስቲያኖችን ሳይቀር ስለሚመጣው ፍርድ በመናገር የሚያስጠነቅቁ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓቢይ ትምህርት

እንደ አብዛኛዎቹ ሌሎች ነቢያት፥ ሶፎንያስም ሊመጣ ባለው «የጌታ ቀን» ላይ በማተኮር ይናገራል። ሶፎንያስ ስለ ጌታ ቀን የሚያስተምራቸው ትምህርቶች በአንድ ክፍለ ጊዜ ውስጥ መድቦ ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ናቸው። ሶፎንያስ ስለ ጌታ ቀን የሚናገረው ሰፋ ያለ አሳብ በሚገልጡ ቃላት ነው። በመሆኑም በዚያኑ ዘመን በይሁዳና በአሕዛብ ሁሉ ላይ በሚመጣው የጌታ ቀንና በመጨረሻው ዘመን በሚመጣው የጌታ ቀን መካከል ብዙ ልዩነት አላደረገም።

በትንቢተ ሶፎንያስ ውስጥ የጌታ ቀን የተገለጸው በታሪክ ውስጥ የሚከሰት አንድ የተወሰነ ቀን ወይም ጊዜ ተደርጎ ሳይሆን፥ የማያቋርጥ የታሪክ ሂደት ሆኖ ነው። እግዚአብሔር በፍርድ ወይም በበረከት ፈቃዱን የፈጸመበት ማንኛውም ቀን የጌታ ቀን ተብሎ ሊጠራ ይችል ነበር። ያ የጌታ ቀን ሰዎችንና ነገሮችን ሁሉ የሚነካ ነው። በጌታ ቀን የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

1. ለይሁዳ፥ የጌታ ቀን ሶፎንያስ ከነበረበት ዘመን ጋር የሚቀራረቡ ውጤቶች ነበሩት። የጌታ ቀን አይሁድ እጅግ ከባድ በሆነ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚቀበሉበት ቀን ነው። ይህ ቀን ተማርኮ ወደ ባቢሎን መሄድንም እንደሚያጠቃልል እናውቃለን። በተጨማሪም ያ የባቢሎን ምርኮ በዘመን መጨረሻ ኢየሱስ ለመግዛት ከመምጣቱ በፊት ይሁዳ የምትጋፈጠውን ከፍተኛ ጥፋት የሚያመለክት ተምሳሌት ነው። ስለዚህ ይህ ቀን በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት አይሁድ ከምርኮ የሚመለሱበትን ጊዜ ስለሚጨምር የበረከት ጊዜም ነበር። እንደዚሁም በዘመናት መጨረሻ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በአካል ወደ ምድራቸው ተመልሰው፥ ከመንጻታቸው የተነሣ በረከቶችን የሚቋደሱበትና አይሁድ ሁሉ እግዚአብሔርን በእውነት የሚያመልኩበትን ታላቁን የጌታ ቀን የሚያመለክት ነበር። 

2. አሕዛብም የጌታን ቀን ምንነት ያውቃሉ። አሦርና ሌሎች አሕዛብ እግዚአብሔር ፍርድን አምጥቶባቸዋልና በታሪክ ያንን የፍርድ ቀን ያውቃሉ። በዚህ ዓይነት አሦር በባቢሎን ተደመሰሰች፤ ፍልስጥኤም፥ ሞዓብ፥ አሞንና ኩሽም ጠፉ። እነዚህ ጥፋቶች አሕዛብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚቀበሉበት የመጨረሻው ታላቁ የጌታ ቀን ምሳሌዎች ነበሩ። 

ያ ቀን ለአይሁድ እንደሆነው ሁሉ ለአሕዛብም የበረከት ቀን ይሆናል። እግዚአብሔርን ለማክበር የሚመለሱ አሕዛብም በረከትን ያገኛሉ። 

3. ፍጥረታት ሁሉ የጌታን ቀን ያውቃሉ። እንስሳት፥ ከዋክብት፥ ፀሐይ ወዘተ. ሁሉም እግዚአብሔር በፍርድ በሚሠራበት ቀን የፍርዱ ተካፋዮች ይሆናሉ። ይህም ምድርን በተለያዩ ጊዜያት በሚመቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በከፊል ታይቷል። ይሁን እንጂ በተለይ የሚታየው በዘመናት ፍጻሜ ነው። የዮሐንስ ራእይ ፍጥረታት በተለያየ ሁኔታ የሚመቱባቸዉን መንገዶች በግልጽ ያሳያል። ያ ቀን የሚያበቃው እግዚአብሔር አሁን ያሉትን ሰማይና ምድርን በእሳት ሲያጠፋና አዲስ ሰማይና ምድር ሲፈጥር ይሆናል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡10፤ ራእይ 21፡1)።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡10-13 አንብብ። ሀ) ስለ ጌታ ቀን የሚኖረን ግልጽ ግንዛቤ፥ ዛሬ የምንኖረውን ኑሮ መለወጥ የሚገባው በምን መንገዶች ነው? ለ) ስለ ጌታ ቀንና በዚህም ምክንያት እንዴት መኖር እንዳለባቸው የቤተ ክርስቲያንህን አባላት ለማስተማር ዐቅድ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሶፎንያስ 1-3 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ይሁዳ ይፈረድባታል ያለው ለምንድን ነው? ለ) በጌታ ቀን የሚፈጸሙ ሁኔታዎች የሚነኳቸውን ነገሮች ዝርዝር። ሐ) በጌታ ቀን እንደሚሆኑ ተስፋ የተሰጡ በረከተች ምንድን ናቸው? 

1. በሁሉም ላይ ስለሚደርስ ፍርድ የተነገረ አጠቃላይ መልእክት (ሶፎንያስ 1፡1-3)

የሶፎንያስ መልእክት ጠንከር ያለና አስደንጋጭ ነበር። ሶፎንያስ በምድር ላይ ስለሚሆነው ታላቅ ጥፋት በመናገሩ፥ ሰዎች ራሳቸውን በመመርመር በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይጥራሉ የሚል እምነት አድሮበት ነበር። በራሳቸው ረክተው በመኖራቸው እንዲደነግጡና ካሉበት ሁኔታ እንዲወጡ ለማድረግ አስቦ ነበር። ሶፎንያስ የዘመን መጨረሻን አሻግሮ በማየት ነገሮች ሁሉ እንዴት በእግዚአብሔር እንደሚዳኙ ሰፋ አድርጎ አሳይቷል። 

2. በጌታ ቀን በይሁዳ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 1፡4-18)

ቀጥሎ ሶፎንያስ ወደ ይሁዳ ዞረ። የእግዚአብሔርን ፍርድ ሊያመጣባቸው ወዳለው ወደ ይሁዳ ኃጢአት አመለከተ። የጣዖት አምልኮ በእጅጉ ተንሰራፍተ ነበር። ሕዝቡ እግዚአብሔርን አልፈለጉም፤ ወይም ከኃጢአታቸው ንስሐ አልገቡም። መሪዎች በኃጢአት ይኖሩ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ፍርድ እንደሚያመጣና የይሁዳ ምድር እንደምትደምሰስ ተናገረ። ይህም ከ40 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በባቢሎናውያን አማካይነት ተፈጸመ። 

3. በጌታ ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 2፡1-3፡8)

እግዚአብሔር ንስሐ እንዲገቡ ዕድል ሳይሰጥ በሰዎች ላይ አይፈርድም። ሶፎንያስ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በዚያን ቀን ከሚገለጠው ቁጣ እንዲያመልጡ ሕዝቡን፥ በተለይም አይሁድን አጥብቆ ጠይቆአቸው ነበር።

ሶፎንያስ በዙሪያው ያሉትን አንዳንድ አሕዛብና መንግሥታት በመመልከት፥ እግዚአብሔር በእነርሱም ላይ እንደሚፈርድ አመለከተ። እነዚህ የአሕዛብ መንግሥታት በይሁዳ ላይ ችግር የፈጠሩ ነበሩ። መደምሰስና መጥፋት ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን የእነዚህን አሕዛብ ምድር አይሁድ ይወርሱታል።

4. በጌታ ቀን የሚመጡ በረከቶች (ሶፎንያስ 3፡9-20)

የነቢያት መልእክት ብዙ ጊዜ የሚጠቃለለው፥ በፍርድ ሳይሆን በማበረታቻ ወይም በማጽናኛ ቃል ነበር። ሶፎንያስ ስለ መጪው የጌታ ቀን በድጋሚ ይናገራል። በዚህ ጊዜ ግን የሰዎች ክፋት አንድ ቀን እንደሚወገድ ይናገራል። ከናፍርት ለአምልኮ ይነጻሉ። ሰዎች ለእግዚአብሔር ይታዘዛሉ። በተበተኑት አይሁድ መካከል ትሑታን የነበሩትና በእግዚአብሔር የሚያምኑት ሰዎች ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ ይለዋል። እነርሱም በሁሉ ይከበራሉ።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በትንቢተ ሶፎንያስ ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር ለ) የቤተ ክርስቲያን አባሎች በሙሉ እነዚህን ትምህርቶች ማወቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: