የብሉይ ኪዳን ጥናት ክለሳ

የብሉይ ኪዳንን የተለያዩ መጻሕፍት ስናጠና ቆይተናል። የእያንዳንዱ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን እንደሆነ፥ የመጽሐፉን ታሪካዊ ሥረ-መሠረት፥ ዓላማና ዐበይት ትምህርቶች ተመልክተናል። እያንዳንዱን መጽሐፍ ያጠናነው በግል ስለሆነ በመጨረሻ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ በአንድነት እንዴት እንደተዋሀዱ ለመረዳት ጠቃሚ የሆነውን የመጻሕፍቱን ክለሳ መመልከት አስፈላጊ ነው።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በብሉይ ኪዳን የሚገኙ መጻሕፍት ስንት ናቸው? ለ) የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ዋና ዋና ክፍሎች ጥቀስና በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ዘርዝር።

1. ፔንታቱክ (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት)

ብሉይ ኪዳን በአራት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። የመጀመሪያው ዋና ክፍል ፔንታቱክ ወይም አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት የሚባለው ሲሆን፥ የብሉይ ኪዳንን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት የያዘ ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረጋቸውን ቃል ኪዳኖች ስለሚገልጹ በብዙ አንጻር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ ቃል ኪዳኖች ብሉይና አዲስ ኪዳን የተመሠረቱባቸው መሠረች ናቸው።

ከፔንታቱክ መጻሕፍት ግማሽ ያህሉ ታሪካዊ መጻሕፍትን የያዘ ነው፡- (ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘኁልቁ)። ቀሪው ግማሽ ያህል ደግሞ ይኖሩበት ዘንድ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሰጣቸውን ቃል ኪዳንና ሕግጋት የያዘ ነው (ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን፥ ዘዳግም)። ታሪክ የሚጀምረው ስለ ፍጥረታት አጀማመር የሚናገሩ ታሪኮችን በያዘው በኦሪት ዘፍጥረት ነው። ይህ መጽሐፍ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአንድ ሰው፥ ማለትም ከአብርሃም በመጀመር፥ በግብፅ ታላቅ ሕዝብ እስኪሆኑ ድረስ እንዴት እንደበዙ ያሳየናል።

የኦሪት ዘጸአት የመጀመሪያ ግማሽ ክፍል፥ እግዚአብሔር ሕዝቡ በግብፅ የነበሩበትን ቀንበር ለመስበርና ነፃ ለማውጣት በኃይልና በሥልጣን እንዴት እንደሠራ ያሳየናል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ወዳደረገበት ወደ ሲና ተራራ መራቸው። የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይህን ቃል ኪዳን በዝርዝር ያሳየናል። ቃል ኪዳኑ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ስለነበር ለሕጉ በመታዘዝ ሲኖሩ እግዚአብሔር እንደሚባርካቸው፥ ካልታዘዙት ደግሞ እንደሚቀጣቸው ተናግሮ ነበር። የቃል ኪዳኑ ማዕከል በመካከላቸው የእግዚአብሔርን ዙፋን መገኘት የሚያመለክተው የቃል ኪዳኑ ታቦት የነበረበት የመገናኛው ድንኳን ነበር። እስራኤላውያን የሲናን ተራራ ከመልቀቃቸው በፊት ዕቅዱ በእግዚአብሔር የተነደፈውን የመገናኛ ድንኳን ሠሩ።

ኦሪት ዘሌዋውያን፥ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጡ ቅዱስ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ ሕግጋትን ይዟል። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ሊያቀርቧቸው ስለሚገቡ የተለያዩ መሥዋዕቶች ይገልጻል። ሕዝቡ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ነገሮች የሚያስታውሱባቸው የተለያዩ የሃይማኖት በዓላትን ይደነግጋል። ካህናት ደግሞ ሕዝቡን በተቀደሰ አምልኮ መምራት ይችሉ ዘንድ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ይዘረዝራል። አይሁድ ሁሉ በየዕለቱ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ እንዴት እንደሚኖሩና የእግዚአብሔርን በረከቶች ለማግኘት እንዴት እርግጠኛች መሆን እንደሚችሉ ግልጽ መመሪያዎችን ይሰጣል።

ኦሪት ዘኍልቍ የሚያተኩረው የእግዚአብሔር ሕዝብ በተስፋዪቱ ምድር ያሉ ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍ በእግዚአብሔር መታመን ስላቃታቸው በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት መንከራተታቸውን በሚናገረው አሳዛኝ ታሪክ ላይ ነው፡፡ አንድ ትውልድ ባለመታዘዙ ምክንያት ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን የሚናገር ታሪክ ነው። ኦሪት ዘኁልቁ የሚጠናቀቀው አይሁድ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን ምድር ወርረው በማሸነፍ እግዚአብሔር ወደሰጣቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እንደተዘጋጁ በመናገር ነው።

በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ሙሴ በሲና ተራራ የተሰጡትን ሕግጋት ለአዲሱ ትውልድ በድጋሚ ሲናገር እንመለከታለን። ሙሴ የተስፋይቱን ምድር ከሩቅ አሻግሮ ቢመለከትም እንኳ ወደ ከነዓን ሳይገባ ሞተ።

የፔንታቱክ ታሪክ የሚጀምረው እግዚአብሔር ምድርን ከፈጠረበት ካልታወቀ ጊዜ ሲሆን፥ የሚደመደመው ደግሞ በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ ነው። 

2. የታሪክ መጻሕፍት

ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ አስቴር ድረስ ያሉት የሚቀጥሉት አሥራ ሁለት መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸመውን የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚናገሩ ናቸው። ይህም ከነዓን ድል ከሆነችበት ከ1400 ዓ.ዓ. ጀምሮ፥ ከምርኮ መልስ የኢየሩሳሌም ቅጥር እስከተሠራበት እስከ 400 ዓ.ዓ. ድረስ የነበረውን ታሪክ ያጠቃልላል። 

ኢያሱ ስለ ከነዓን ድል መሆን ይናገራል። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ በነበራቸው እምነት ምክንያት አብዛኞቹን የከነዓንን ምድር ከተሞች ለማሸነፍና በዚያ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማንበርከክ ችለው ነበር።

መጽሐፈ መሳፍንት የሚናገረው ግን እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዝዘው ከነዓናውያንን ባለማጥፋታቸው ምን እንደ ተፈጸመ ነው። አይሁድ ከከነዓናውያን ጋር ጎን ለጎን በመኖራቸው፥ ወዲያውኑ በባዕድ አምልኮ ኃጢአት ወደቁ። እግዚአብሔር በባርነት ይገዟቸው ዘንድ ለተለያዩ ከነዓናውያን መንግሥታት አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። እስራኤላውያን ንስሐ በሚገቡበትና ወደ እግዚአብሔር በሚጮሁበት ጊዜ ከጠላቶቻቸው የሚታደጉአቸው የተለያዩ ተዋጊዎችን (መሳፍንትን) ያስነሣላቸው ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ቀድሞው የኃጢአት መንገዳቸው ይመለሱና እግዚአብሔር ይቀጣቸው ነበር። በዘመነ መሳፍንት ለእግዚአብሔር በታማኝነት የቆሙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ለዚህ ምሳሌ ከሚሆኑት መካከል ሩትና ቦዔዝ ይገኛሉ። ለእግዚአብሔር ተስፋ ታማኞች ሆነው በመቆየታቸው በእስራኤል ላይ ከነገሡ ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነው የንጉሥ ዳዊት አያቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቀደ።

1ኛ ሳሙኤል የሚያስተዋውቀን ከመሳፍንት ወደ ነገሥታት ዘመን የተደረገውን የሽግግር ወቅት ነው። የመጨረሻዎቹ ሁለት መሳፍንት ዔሊና ሳሙኤል ነበሩ። ይህ ማለት የግል ነፃነትን ማጣትና ከፍተኛ ግብር መገበር ማለት ቢሆንም እንኳ ሕዝቡ እንደቀሩት አሕዛብ ንጉሥ እንዲኖራቸው ፈለጉ። ሳኦል የእስራኤል ሕዝብ የመጀመሪያ ንጉሥ ነበር። ሳኦል አጀማመሩ መልካም ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ባለመጠበቁ፥ መንግሥቱ ከእርሱ ተወስዳ ለዳዊት ተሰጠች። የ1ኛ ሳሙኤል አብዛኛው ታሪክ የያዘው ሳኦል፥ ዳዊት ንጉሥ እንዳይሆን ባደረበት ቅንዓት እርሱን ለመግደል ያደረጋቸውን የተለያዩ ሙከራዎች ነው።

2ኛ ሳሙኤል በእስራኤል ላይ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነውን የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ ይናገራል። ዳዊት እግዚአብሔርን ይወድ ነበር። ምንም እንኳ በኃጢአት ቢወድቅም፥ ዝርያዎቹ የእስራኤልን ዙፋን እንደሚቆጣጠሩ የተስፋ ቃል በመስጠት እግዚአብሔር አከበረው። ይህም የዳዊት ልጅ በሆነው በመሢሑ በኢየሱስ ሙሉ ለሙሉ ይፈጸማል።

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት የነገሥታትን ታሪክ መናገሩን ይቀጥላል። የሚጀምረው በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የላቀ ጥበበኛ በነበረው በዳዊት ልጅ በሰሎሞን ነው። ዳሩ ግን ሰሎሞን ለሴቶች የነበረው ፍቅር ወደ ጣዖት አምልኮ መርቶት፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲቀበል አደረገው። ከሰሎሞን ሞት በኋላ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት የሰሜኑን ክፍል የእስራኤል መንግሥትና የደቡቡን የይሁዳ መንግሥት ተብሎ እንዲከፈል አደረገ፡፡ የቀረው 1ኛ እና 2ኛ መጽሐፈ ነገሥት እግዚአብሔር ሰሜኑ የእስራኤልን መንግሥት ወደ አሦር፣ ደቡቡ የይሁዳን መንግሥት ወደ ባቢሎን በምርኮ እንዲወሰድ ከማድረጉ በፊት የነበሩትን ነገሥታት ታሪክ በአጭሩ ያብራራል።

1ኛ- 2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ከዳዊት እስከ ምርኮ ድረስ ያለውን የደቡቡ የዳዊትን ዝርያ የሆኑ ነገሥታት ታሪክ በድጋሚ ይተርካል። እነዚህን ጊዜያት ከታሪክ አቅጣጫ ከመመልከት ይልቅ አንድ ንጉሥ እግዚአብሔርን በሚያከብርበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚባረክ። ንጉሡ ለእግዚአብሔርና ለሕግጋቱ በማይታዘዝበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚፈረድበት እነዚህ መጻሕፍት ይናገራሉ።

መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር የይሁዳ ሕዝብ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ስለተፈጸሙ ድርጊቶች የሚናገሩ ናቸው። መጽሐፈ ዕዝራ የሚገልጸው ከባቢሎን ወደ ምድራቸው ስለተመለሱት ሁለት የመጀመሪያ የአይሁድ ቡድኖች ጉዳይና ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራት ነው። ነህምያ ደግሞ ወደ ምድሪቱ ስለተመለሰ ሌላ ቡድን ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መሠራት ይናገራል። መጽሐፈ አስቴር በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን እግዚአብሔር አይሁድን በአሕዛብ ፈጽመው ከመደምሰስ እንዴት እንደጠበቃቸው ይናገራል።

ከእዚህ አሥራ ሁለት መጻሕፍት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ትረካ ያበቃል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለመኖር እስከመጣበት ጊዜ ድረስ 400 የጸጥታ ዘመናት ነበሩ። የእነዚህን የጸጥታ ዘመናት ታሪክ ሌሎች መጻሕፍት የዘገቡት ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ እርሱ ምንም አይናገርም። 

3. የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ መጻሕፍት መካከል አምስቱ የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት ይገኛሉ። እነርሱም መጽሐፈ ኢዮብ መዝሙረ ዳዊት መጽሐፈ ምሳሌ፥ መጽሐፈ መክብብና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው። መዝሙረ ዳዊት የአይሁድ የአምልኮ መዝሙራት መጽሐፍ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ መዝሙራት የተጻፉት ለእግዚአብሔር ምስጋናን በሚገልጡና እግዚአብሔር ክፉዎችን በመቅጣት ጻድቃንን እንደሚባርክ በሚያስረዱ መንገዶች ነው። ሌሎቹ መጻሕፍት የጥበብ መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ፤ ምክንያቱም አይሁድ እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ እግዚአብሔር ስለሰጣቸው ጥበብና በጊዜው ይቸገሩባቸው ስለነበሩ አንዳንድ የፍልስፍና ጥያቄዎች የሰጣቸውን መልስ ስለሚያስረዱ ነው። መጽሐፈ ኢዮብ የሚያስተምረን ጻድቅ ሰው ከቶ ባልታወቀ ምክንያት መከራን ቢቀበል እንኳ በእግዚአብሔር ታምኖ መከራውን በትዕግሥት ሊቀበለው እንደሚገባ ነው። መጽሐፈ ምሳሌ ደግሞ ማንኛውም የሕይወት ሁኔታ ውስጥ በጥበብ መኖር እንዴት እንደሚቻል የሚያሳዩ ቀለል ያሉ መመሪያዎችን የያዙ አጫጭር አባባሎችን አካትቷል። መጽሐፈ መክብብ ሕይወትን ከዓለም አመለካከት አንጻር ያያታል። ሰሎሞን ሰዎች ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው ብለው ያመኑባቸውን ነገሮች ሁሉ ተመልክቶ ሁሉም ከንቱ መሆናቸውን መሰከረ። ሕይወትን እውነተኛ ትርጉም ያለው የሚያደርግ እግዚአብሔርን ማወቅና ማምለክ ብቻ ነው። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን የፍቅር ታሪክ ሲሆን በወንድና በሴት መካከል ያለ ፍቅር የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ያስተምራል። 

4. የትንቢት መጻሕፍት

የእስራኤል ታሪክ ከምርኮ በፊት በነበሩት ዓመታት (ከ850-400 ዓ.ዓ.) ሊደመደም ገደማ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ወደገባው ቃል ኪዳን ይመለሱ ዘንድ አለበለዚያ ግን እንደሚፈረድባቸው ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቁ ያስነሣቸው ነቢያት የተባሉ ቃል አቀባዮች ነበሩት። ነቢያት ስለሚመጣው ፍርድ ካሳወቁበት ከማስጠንቀቂያ መልእክታቸው ጋር ጽድቅና ቅንነት ያለበትን መንግሥት ስለሚያመጣው መሢሕ የሚያመለክቱ የተስፋ መልእክቶችም ነበሩ። ከእነዚህ ነቢያት አብዛኛዎቹ ያገለገሉት ታሪካቸው በ1ኛና 2ኛ ነገሥት እንዲሁም በ1ኛና 2ኛ መዋዕል ዜና ካልዕ በሚገኝ ነገሥታት ዘመን ነበር፡፡

ነቢያት በሁለት የተከፈሉ ናቸው፤ የመጀመሪያዎቹ፥ ታላላቅ ነቢያት የምንላቸው፡- ኢሳያያስ፥ ኤርምያስ (ከሰቆቃወ ኤርምያስ ጋር)፥ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው። እነዚህ ታላላቅ የተባሉበት ምክንያት መልእክታቸው ረጅምና ታላቅ ስለሆነ ነው። ሁለተኛዎቹ አሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት ሲሆኑ፥ እነርሱም፡- ሆሴዕ፥ አሞጽ፥ ሚክያስ፥ ኢዩኤል፥ አብድዩ፥ ዮናስ፥ ናሆም፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስ፥ ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው።

ሀ. ታላላቅ ነቢያት

ኢሳይያስ፡- የእስራኤል መንግሥት ከመውደቁ በፊት ጽፎ እስራኤል በአሦር፥ ይሁዳ ደግሞ በባቢሎን እንደሚማረኩ ያመለከተ ነቢይ ነው። ኢሳይያስ ከየትኛውም ነቢይ በላቀ ሁኔታ ስለ መሢሑ መምጣትና እርሱ ስለሚያመጣው ሰላም ተናገሯል።

ኤርምያስ፡- በእግዚአብሔር የተጠራው ይሁዳ ከመማረክዋ ጥቂት ቀደም ብሎ ነበር። ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ቢያስጠነቅቅም እንኳ ንስሐ ለመግባት አልፈለጉም ነበር። ኤርምያስ ሕዝቡ በባቢሎን ሲማረክ አይቶ ነበርና የተሰማውን ኃዘን በሰቆቃወ ኤርምያስ ጽፏል። ኤርምያስ ስለ ሰባው ዓመት ምርኮና ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን መምጣት አስቀድሞ ተናገረ።

ሕዝቅኤል፡- በምርኮ ምድር በባቢሎን ካገለገሉት ሁለት ነቢያት አንዱ ነበር። ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም በመጨረሻ ከመውደቋ በፊት የይሁዳን ውድቀትና ምርኮ አስቅድሞ አመለከተ። አይሁድ ከምርኮ መቼ እንደሚመለሱና አንድ ሕዝብ ሆነው እንደሚዋሐዱም ተናግሯል። እግዚአብሔር በመካከላቸው እንደሚኖር፥ መሢሑ በእነርሱ ላይ እንደሚነግሥና ቤተ መቅደሱ እንደገና እንደሚሠራ ተናገረ።

ዳንኤል፡- በባቢሎን ያገለገለ ሁለተኛው ነቢይ ሲሆን አንዳንዶች «የትንቢት ቁልፍ» በማለት ይጠሩት ነበር። ለእግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት የሚገልጥ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፥ ከባቢሎን ጀምሮ እስከ ሮም ድረስ ያለውን የመንግሥታትን ታሪክና ክርስቶስ በመጨረሻው ዘመን እንደሚነግሥ የሚናገሩ ታሪኮችን ይዟል።

ለ. አሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት

አሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት በተለያዩ መንገዶች ሊመደቡ ይችሉ፡፡ አንደኛው መንገድ ከምርኮ በፊት ያገለገሉትን ዘጠኙንና ከምርኮ መልስ ያገለገሉትን ሦስቱን ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ) መዘርዘር ነው። ሌላው መንገድ መልእክቱ በቅድሚያ እንዲደርሳቸው በታቀደላቸው ሕዝቦች መሠረት መመደብ ነው፡-

1. እስራኤልን ያገለገሉ ነቢያት – ሆሴዕና አሞጽ 

2. ይሁዳን ያገለገሉ ነቢያት – ዕንባቆም፥ ኢዩኤል፥ ሚክያስና ሶፎንያስ 

3. አሕዛብን ያገለገሉ ነቢያት – ዮናስ፥ ናሆምና አብድዩ 

4. ከምርኮ በኋላ ያገለገሉ ነቢያት – ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው 

እነዚህ መጻሕፍት እያንዳንዳቸው ማስጠንቀቂያና የሚማጣውን የበረከት ጊዜ የሚመለከቱ ትንቢቶችን የያዙ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሠላሳ ዘጠኙን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስም ዘርዝር። ለ) እያንዳንዱ መጽሐፍ የሚናገረው ስለምን እንደሆነ ባጭሩ ጻፍ። ሐ) ለእያንዳንዱ መጽሐፍ አንድ ዓላማ ጻፍ። ም) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አንድ መንፈሳዊ ትምህርት ጻፍ።

ብሉይ ኪዳን በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን የያዘ ቢሆንም፥ ከሁሉም በላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ነው። እግዚአብሔር ስለ ራሱ፥ ስለ መንገዶቹና ፈቃዱ፥ ለአይሁድ ዛሬም ለእኛ ለማስተማር የሰጠን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስሕተት የገባ አንድም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ የለም። ሁሉም መጻሕፍት አስፈላጊዎች ናቸው። ስለ ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይህን የጥናት መምሪያ ስንጽፍ፣ እያንዳንዱን መጽሐፍ እንድትወደው፥ ስለ ታላቁ እግዚአብሔርና እርሱ ለእኛ ስላለው ፈቃዱ የበለጠ ለማወቅ በእያንዳንዱ መጽሐፍ መጠቀምን እንድትማር በማሰብ ነው። አንተ ደግሞ በተራህ እነዚህን መጻሕፍትና በውስጣቸው ያሉትን እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ አባላት ታስተምር ዘንድ ጸሎታችን ነው።

ኢየሱስ በሉቃስ 24፡44 ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፡- «በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል።» ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ድረስ ብሉይ ኪዳን ወደ መሢሑ ወደ ኢየሱስ ያመለክታሉ። በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ጌታችንና አዳኛችን ስለ ሆነው ስለ ኢየሱስና ስለ እግዚአብሔር አብ የበለጠ ለመማር እነዚህን መጻሕፍት ማጥናታችንን መቀጠል አለብን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: