የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ እና ዓላማ

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ

የውይይት ጥያቄ፥ ) ስለሚልክያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ለ) በዚህ ስፍራ ስለ ሚልክያስ የተጠቀሱትን ዐበይት እውነቶችን ዘርዝር።

ሚልክያስ የተጻፈው እጅግ ልዩ በሆነ መንገድ ነበር። በመጀመሪያ አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል የተጻፈው ሚልክያስ እግዚአብሔርን ወክሎ እንደሚናገር ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ራሱ ለእስራኤላውያን በቀጥታ እንደሚናገር ሆኖ ነው። በመጽሐፉ አብዛኛ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሚናገረው «እኔ» የሚለውን ተውላጠ ስም በመጠቀም ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ሚልክያስ በጽሑፉ የተጠቀመው ልዩ የሆነ የአጻጻፍ ሥልትን ነው። አብዛኛዎቹ መልእክቶቹ የሚከተለውን አደረጃጀት የተከተሉ ናቸው፡-

ሀ. እግዚአብሔር ስለ ራሱ ወይም ስለ እስራኤላውያን መንፈሳዊ እውነትን ይናገራል።

ለ. ቀጥሉ እስራኤላውያን በዚህ የእግዚአብሔር ንግግር ላይ ተመሥርተው የሚያነሡት ጥያቄ በመላ ምት ይቀርባል። 

ሐ. እግዚአብሔር፥ ጥያቄአቸው ትክክል አለመሆኑን በሚያስረዳ መንገድ ለእስራኤላውያን ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

መ. እግዚአብሔር ለተናገረው ቃል ማረጋገጫ ያቀርባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሚልክያስ 1፡2-5 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ እነዚህ አራት ደረጃዎች የሚታዩት እንዴት ነው?

ትንቢተ ሚልክያስ መልእክቱን የመሠረተባቸውን ስድስት ስብከቶች ይዟል። እነዚህ ስድስት መልእክቶች መልሶችን የያዙ ጥያቄዎች ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ። 

እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያቀረበው ክስ

1ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡1-5)።

መልስ፡- ሀ) እግዚአብሔርን እስራኤልን የራሱ አድርጎ መርጧታል፤ ለ) እግዚአብሔር እስራኤልን ይጠብቃታል። 

2ኛ ጥያቄ፡- እኛ ካህናት የእግዚአብሔርን ስም የናቅነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡6-2፡9)።

መልስ፡- ሀ) ካህናቱ እግዚአብሔርን አያከብሩም፤ ለ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሐ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ስም ክብር አይሰጡም፤ መ) ካህናቱ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ አያስተምሩም። 

3ኛ ጥያቄ፡- እኛ እስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ታማኞች ያልሆንነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡10-16)። 

መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ ሌሎች አማልክትን ከሚያመልኩ አሕዛብ መካከል ሚስቶችን አግብተዋል፤ ለ) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በቃል ኪዳን ያገቧቸውን ሚስቶቻቸውን ፈትተዋል። 

እግዚአብሔር በፍርድና በመቤዥት ወደ ሕዝቡ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል 

4ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔርን ያሰለቸነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡17-3፡6)።

መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ እግዚአብሔር ጻድቅ አይደለህም ብለው ይከሱት ነበር፤ ለ) እግዚአብሔር በቃላቸውና በተግባራቸው ታማኝ ባልሆኑት ሕዝቡ ላይ ፍርድን ያመጣና ይቀጣቸዋል፤ ያነጻቸዋልም። 

5ኛ ጥያቄ፡- ወደ እግዚአብሔር መመለስ የምንችለው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡7-12)።

መልስ፡- ሀ) ከእግዚአብሔር መስረቅን በማቆምና ለእግዚአብሔር መክፈል የሚገባውን አሥራትና መባ በመስጠት። ለ) ለእግዚአብሔር በሚሰጡበት ጊዜ እርሱ በረከቱን ያፈስላቸዋል። 

6ኛ ጥያቄ፡- በእግዚአብሔር ላይ በድፍረት የተናገርነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡13-4፡3)።

መልስ፡– ሀ) እግዚአብሔርን ማገልገል ምንም ጥቅም የለውም ብላችኋል፤ ለ) የሚያከብሩኝንና የሚታዘዙኝን አስባቸዋለሁ፤ ደግሞም እሸልማቸዋለሁ፤ ሐ) እኔን ባለመታዘዝ የማያከብሩኝን እቀጣቸዋለሁ፤ መ) «የጽድቅ ፀሐይ» በምትወጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በረከትና ፍርድን ያመጣል። 

7. ለሕዝቡ የተሰጠ የመጨረሻ ግሣጹ (ሚልክያስ 4፡4-6)

ሀ) የእግዚአብሔርን ሕግጋት መጠበቅን አስታውሱ፤ ለ) ሕዝቡን ለመሢሑ ለማዘጋጀት ከመሢሑ በፊት የሚመጣውን ኤልያስን ጠብቁ። 

የትንቢተ ሚልክያስ ዓላማ

የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች እምብርት ቃል ኪዳንን የሚመለከት አሳብ ያዘለ ነው። እግዚአብሔር በጸጋውና በፍቅሩ የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንዲሆኑ እስራኤላውያንን መረጣቸው። ይህም የተጀመረው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ነበር። ይህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ለአይሁድ በሲና ተራራ ቃል ኪዳን በሰጣቸው ጊዜ ሊስፋፋ ችሏል። ይህም ከካህናት፥ በኋላም ከዳዊት ጋር የተደረገውን ቃል ኪዳን ይጨምር ነበር። ቃል ኪዳኖቹ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ጸጋ የሚያስረዱ ናቸው። የቃል ኪዳኑ ጀማሪ እርሱ ሲሆን፥ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ነገር ባላደረጉ ጊዜ እንኳ ሊለውጠው አልፈለገም። ይሁን እንጂ ብሉይ ኪዳን የሚያስተምረን በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተጠቀሱትን በረከቶች ለመቀበል ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ መሆናቸው አስፈላጊ እንደ ነበር ነው። ይህ መታዘዝ በውጫዊ ሥርዓት ብቻ የሚሆን ሳይሆን፥ ከሕዝቡ ልብ የሚመነጭ መሆን ነበረበት።

እግዚአብሔር ሚልክያስን በጠራው ጊዜ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታዘዙትን አብዛኛዎቹን ሥርዓቶች እየተከተሉ ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔርን ከልባቸው አያመልኩትም ነበር። መሥዋዕቶችንም ያቀርቡ ነበር፤ ነገር ግን ለእነርሱ የማይጠቅሙትን ሽባ ወይም ዕውር እንስሳት በመስጠት እግዚአብሔርን ያቃልሉት ነበር። እንደ ቀደምት አባቶቻቸው ጣዖትን አያመልኩም ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ የመሆናቸውን እውነታ ለመቀበልና ልባቸውን ለመለወጥ አይፈቅዱም ነበር።

ስለዚህ እግዚአብሔር ነቢዩን ሚልክያስን ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው የመጨረሻ መልእክተኛ አድርጎ ላከው። ሚልክያስ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ ያተኵር ነበር። ይህ ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ፍቅር ማረጋገጫ ነበር። ካህናቱ በእግዚአብሔር ፊት አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙበት መሠረት ነበር። ሚልክያስ የቃል ኪዳኑ ውጤት በእስራኤላውያን ሕይወት ምን መሆን እንዳለበት ተመለከተ። የቃል ኪዳኑ እምብርት ወደ እግዚአብሔር የሚመለከት ትክክለኛ ዝንባሌ ነበር። ቃል ኪዳኑ እግዚአብሔርን እንደ ቅዱስነቱ በክበርና በሙሉ ሕይወታቸው እርሱን ለማክበር ባላቸው ፍላጎት ላይ መመሥረት ነበረበት። ያ አክብሮት ለእግዚአብሔር ወደሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ሊመራቸውና ለእግዚአብሔር የማይረባውን ሳይሆን ከሁሉም የተሻለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። መሪዎችና ሕዝቡ እርስ በርስ በመከባበር እንዲነጋገሩና በተለይም ለሚስቶቻቸው የገቡትን ቃል ኪዳን በመጠበቅ ከመፋታት እንዲታቀቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። በእግዚአብሔር የማያምኑትን እንዳያገቡ እምነታቸውን በንጽሕና የመጠበቅ ፍላጎት ሊያሳድርባቸው ይገባ ነበር። ይህንንም እግዚአብሔር ከሰጣቸው ነገር አሥራታቸውን በታማኝነት በመስጠት ማረጋገጥ ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ቃል ኪዳን ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ በመሆናችን ምክንያት በሕይወታችን ሊለወጡ የሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ እንደሆኑ የሚናገሩባቸው፥ ዳሩ ግን ለዚህ ቃል ኪዳን ባለመታዘዝ እግዚአብሔርን የማያስከብሩባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ነቢዩ ሚልክያስ በእግዚአብሔር የተጠራው አይሁድ ለቃል ኪዳኑ ታዛዦች ይሆኑ ዘንድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነበር። እግዚአብሔር በሚልክያስ በኩል አይሁድን ስለ ኃጢአታቸው ሊወቅሳቸውና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ሊጠራቸው ፈልጎ ነበር። ሚልክያስ ሕዝቡን፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎችን መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው እንደሚፈርድባቸውና ለእግዚአብሔር ታማኞች የሆኑትን ደግሞ እንደሚሸልማቸው ያስታውሳቸዋል።

ልዑል አባት፥ የፍጥረታት ሁሉ ጌታና የቃል ኪዳኑ መሥራች የሆነው እግዚአብሔር ሊከበር፥ ከእርሱ ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ በቃል ኪዳኑ ውስጥ በተመለከተው መንገድ በተገቢ ሁኔታ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል (ዘጸአት 20፡12፤ ዘዳግም 31፡1-10)። እግዚአብሔር ሕዝቡ ንስሐ እንዲገባና ከእርሱ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲያድሱ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ መሠረት፡-

ሀ) የተበላሽውን የክህነት አገልግሎት ማንጻት ነበረባቸው፤ 

ለ) ሥርዓታዊውን አምልኮ ሐሤትና ደስታ ወደሞላበት አምልኮ መለወጥ ነበረባቸው፤ 

ሐ) አሥራት በመክፈልና መሥዋዕት በማቅረብ በኩል የሚታዩትን ድክመቶች ማስተካከል ነበረባቸው፤ 

መ) ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ተገቢ የሆነ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባቸው ነበር፤ 

ሠ) ከጎረቤቶቻቸው ጋር በማኅበራዊ ፍትሕ መኖር ነበረባቸው።

የትንቢተ ሚልክያስ መልእክት ውጤት ምን እንደነበር አልተነገረንም። በቅድሚያ ሕዝቡ መጠነኛ የሆነ ምላሽ ሳይሰጡና ንስሐ ሳይገቡ አልቀሩም። ዳሩ ግን አይሁድ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ቀድምው ዝንባሌያቸው ተመለሱ። ኢየሱስ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ ሕዝቡ በተለይም ፈሪሳውያን የዚህ ዓይነት ዝንባሌ ነበራቸው። የልባቸው ዝንባሌ ትክክል ባይሆንም እንኳ ይከተሉት የነበረው ሥርዓታዊ አምልኮ እግዚአብሔርን ደስ እንደሚያሰኝ አስበው ነበር። ኢየሱስ ስለነበራቸው ዝንባሌ በግልጽ እየወቀሳቸው፥ በልባቸው ተለውጠው እግዚአብሔርን በተገቢው ሁኔታ እንዲያመልኩ በነገራቸው ጊዜ ተቃወሙት፤ በመጨረሻም ሰቅለው ገደሉት። ይህ ብዙ ጊዜ በግልጽ የሚታይ እውነታ ነው። ለትምህርቶቻቸውና ለሥርዓተቸው ጥብቅና ለመቆም የሚፈልጉ የሃይማኖት መሪዎች ሁልጊዜ እውነትን ይቃወማሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ካህናትና በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ያደርጉት እንደነበረው በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ዝንባሌ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚወቀሱበትን ማንኛውንም ስሕተት ላለመቀበል የሚቃወሙትና ከዚህ ቀደም የለመዷቸውን ሥርዓቶች ለመጠበቅ የሚጥሩት ለምን ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: