ለምስጋና የቀረበ ልመና (2ኛ ቆሮ. 6፡ 1-10)

እነዚህ ሁለት ምዕራፎች ጳውሎስ ስለ አገልግሉቱ ለሚሰጠው ማብራሪያ እውነተኛ ማጠቃለያ ያቀርባሉ። ባለፍንባቸው ምዕራፎች ውስጥ ለአንባቢዎቹ፥ ከመከራዎቹ ባሻገር አገልግሎቱ ድል-ነሺ (ምዕ. 1-2) እና የከሰረ (ምዕ. 3) መሆኑን በመግለጽ፥ ከመታከት የተነሣ ከዓላማው ከቶውንም ዝንፍ እንደማይል ተናግሯል። ባላንጣዎቹ አገልግሎቱን ለግል ጥቅም ማግኛ እንዳዋለ አድርገው የከሰሱት ቢሆንም፥ ዳሩ ግን አገልግሎቱ እውነተኛ (ምዕ. 4) እና በእግዚአብሔር ላይ በተጣለ እምነት የተመሠረተ (ምዕ. 5) መሆኑን አረጋግጧል። አሁን የቀረው ነገር ቢኖር የቆሮንቶስን ሰዎች ልብ ማነሣሣትና እንደሚያፈቅራቸው ማረጋገጥ ብቻ ነበር። ይህንንም ለማሳካት ሲል የሚከተሉትን ሦስት የፍቅር ልመናዎችን ያቀርባል። 

ለምስጋና የቀረበ ልመና (2ኛ ቆሮ. 6፡ 1-10) 

የሥነ-ልቦና መመሪያዎች በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የዊልያም ጄምስ መጽሐፍ፥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውና በመስኩም ቀደምትነት ያለው ሥራ ነበር። ዳሩ ግን ደራሲው ከመጽሐፉ ውስጥ አንድ «ትልቅ ነገር እንደ ጎደለ» አምኖ ነበር። «የሰብዓዊ ባሕርይ እጅግ የጠለቀ መሻት ምስጋናን ማትረፍ» እንደ ሆነ ይገልጹና ዳሩ ግን በመጽሐፋቸው ውስጥ ይህንን ጉዳይ እንዳላነሡት ይናገራሉ። 

የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት በምናነብበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በጳውሎስ ራሱም ሆነ በመካከላቸው በሠራቸው ሥራዎች ጭምር ተደስታ ምስጋና እንዳላቀረበች ያለ ጥርጥር እንረዳለን። እነርሱ ለጳውሎስ ሊሟገቱለት እንጂ፥ እርሱ ለራሱ እንዲሟገት ሊያስገድዱት ባልተገባቸውም ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱን ስለወረሩ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች በመኩራራት ቢናገሩም፥ እነዚህ ሰዎች ግን ምንም አልፈየዱላቸውም ነበር። ስለ ሆነም እግዚአብሔር በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ስለ ሰጠው አገልግሎት ጳውሎስ ያስታውሳቸዋል። 

ወንጌላዊው ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ. 6፡1-2)። የወንጌሉን የምሥራች ይዞ ወደ ቆሮንቶስ የሄደው ጳውሎስ ነበር፤ በዚህም አገልግሎት ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች። በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡18-21 የተገለጸውን «የአምባሳደርነቱን» ተልዕኮ በሚገባ ተወጥቶት ነበር። እነርሱንም ወደ ክርስቶስ የመለሳቸው ጳውሎስ እንጂ፥ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች አልነበሩም። 

ይህም ሆኖ ግን ጳውሎስ፦ «ድኛለሁ» በማለት በቤተ ክርስቲያኗ የታቀፉትን ሁሉ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች ስለ መሆናቸው እርግጠኛ አልነበረም (13፡5 ተመልከት)። የእግዚአብሔርን ጸጋ ይቀበሉ ዘንድ፥ ኢሳይያስ 49፡8ን እንደ ልመና አድርጎ ጠቅሶላቸዋል። በመስቀል ላይ ከተፈጸመው የክርስቶስ የዕርቅ ሥራ የተነሣ (2ኛ ቆሮ. 5፡18-19)፥ በርግጥም «የመዳን ቀን» ዛሬ ነው በማለትም አሳስቧቸዋል። ለማንኛውም ኃጢአተኛ ነገ የመዳን ዕድል ሊኖረው እንደሚችል የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ዋስትና የለም። «እግዚአብሔር ቀርቦ ሳለ ጥሩት» (ኢሳ 55፡6)። 

አንድ መጋቢ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል ገና ብዙ ጊዜ እንዳላት በመግለጽ ከምትሟገት ወጣት ሴት ጋር ይነጋገር ነበር። መጋቢውም ቁራጭ ወረቀት ሰጣትና፥ «ደኅንነትን በአንድ ዓመት ለማዘግየት ፈቃደኛ መሆንሽን በመግለጽ ጽፈሽ ትፈርሚሰታለሽ ወይ?» አላት። «አይ፥ ፈቃደኛ አልሆንም» አለች። ለስድስት ወራትስ? አሁንም አይሆንም። ለአንድ ወር? አመነታችና «አይሆንም» አለች። ከዛሬ በስተቀር ሌላ ቀን ዕድል እንደሚኖራት የሚያረጋግጥ ዋስትና ስላላገኘች፥ የሙግቷን እርባና-ቢስነት ተመለከተችና ክርስቶስን ያኔውኑ ተቀበለች። 

ምሳሌ የሆነው ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ. 6፡3-10)። ለወንጌል መስፋፋት እንቅፋት ከሚሆኑ ነገሮች አንዱ ክርስቲያኖች ነን የሚሉት ሰዎች እኩይ ምሳሌነት ነው። ደኅንነትን ያላገኙ ሰዎች የቅዱሳንን – በተለይም የሰባኪዎችን – የቃልና የተግባር መለያየት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ላለመቀበል ማመካኛ ለማድረግ ይሻሉ። ጳውሎስ በኃጢአተኞች ወይም በቅዱሳን ጎዳና ላይ መሰናክል የሚፈጥር ማንኛውንም ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቅ ነበር (ሮሜ 14 ተመልከት)። ከግል ሕይወቱ ግድፈት የተነሣ አገልግሎቱ በማንኛውም መንገድ ዋጋ እንዳያጣ(«እንዳይነቀፍ») ይጠነቀቅ ነበር። 

ጳውሎስ ለአንባቢዎቹ ለእነርሱ ብሉ የተቀበላቸውን መከራዎች ያስታውሳቸዋል (2ኛ ቆሮ.6፡4-5)። ጳውሎስ የጽናት («የትዕግሥት») ሰው ስለ ነበር፥ ነገሮች አቀበት ሲሆኑበት ጥሎ አልፈረጠጠም። ከራዎች ስንል፥ በአካባቢ ተፅዕኖዎች የተነሣ በሕይወታችን ላይ የሚደርሱ ጫናዎትና ፈተናዎች ሊሆኑ ይችላሉ። መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማጣት የሚመጡ ችግሮች ዕለታዊ የሕይወት ጉብታዎች ሲሆኑ፥ ጭንቀት ማምለጫ የሌለበት ወደሚመስለን ጥግ የሚገፋንን ልምምድ ያመለክታል። የግሪኩ ቃል «በጠባብ ማነቆ» ይመስለዋል። 

ምንም እንኳን እነዚህ መከራዎች የማያምኑም ሰዎች የሚያልፉባቸው ልምምዶች ቢሆኑም፥ ጳውሎስ ግን ከሕዝቡ ተቃውሞ የተነሣ አንዳንድ የጸናባቸውን መከራዎች ብቻ ዘርዝሮአል – መገረፍ፥ ወኅኒ ሙግባት፥ ሁከት እነዚህን ችግሮች በሕይወቱ ውስጥ ማሳልፉ ጌታን በታማኝነት ያገለግል ስለ ነበር ነው። ከዚያም ለአገልግሎቱ ብሉ በፈቃደኛነት የከፈላቸውን አንዳንድ መሥዋዕቶች ዘርዝሮአል – ድካም ( ከመንገድና ከሥራ ብዛት)፥ እንቅልፍ ማጣት፥ ጾም (በፈቃደኛነት አለመመገብን መምረጥ)። በርግጥ ጳውሎስ እነዚህን ነገሮች በይፋ እያወጀ አልነበረም። በዚህ ደብዳቤ ውስጥ የጠቀሰበት ብቸኛው ምክንያት ለቆሮንቶስ ሰዎች ያለውን ፍቅር ለማረጋገጥ ነበር። 

በተጨማሪም በአገልግሎቱ ስለ ተገለገለባቸው መሣሪያዎች ያስታውሳቸዋል (6፡6-7)። ንጽሕና የሚለው «ከትዳር ውጭ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት አለመፈጸምን» የሚያመለክት ነው (11፡2 ተመልከት)። ጳውሎስ የራሱን ግብረ-ገባዊ ሕይወት በንጽሕና ጠብቋል። ትዕግሥት አስቸጋሪ ሰዎችን መታገሥ ሲሆን፥ መጽናት (6፡4) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መጽናናትን ያመለከታል። ጳውሎስ እንደ ቸርነትና እውነተኛ ፍቅር ያሉትን የመንፈስ ፍሬዎች ለማፍራት የተደገፈው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ ነበር። መንፈሳዊ እውቀትን ለማስተላለፍ የእግዚአብሔርን ቃል ይጠቀማል፤ ከሰይጣናዊ ጥቃቶች ለመከለልም የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ይለብሳል (ኤፌ 6 ቁ 10 ጀምሮ)። 

በመጨረሻም፥ የሕይወት ምስክርነቱን ያስታውሳቸዋል (2ኛ ቆሮ. 6፡8-10)። ጳውሎስ ሁሉም ሰዎች እርሱንና አገልግሉቱን በትክክል እንዳልተረዱ በማወቁ፥ የተቃራኒ ነገሮችን ዝርዝር ያቀርባል። የጳውሎስ ባላንጣዎች ስሙን ለማጥፋት እንደለየለት አጭበርባሪ አድርገው ዘገባ አቅርበውበት ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ጳውሎስ ክብር የሚገባውና እውነተኛ መሆኑን የሚያመለክት መልካም ዘገባ አቀረበለት። ጳውሎስ በአንድ በኩል በሚገባ የታወቀ ሲሆን፥ በዚያው መጠን ደግሞ በሌላ በኩል ያልታወቀ ሰው ነበር። 

ጳውሎስ በአገልግሉቱ ታማኝ ለመሆን የከፈለው ዋጋ ምንኛ ውድ ነበረ! ይሁንና የቆሮንቶስስ ሰዎች ላደረገላቸው መልካም ነገር ሁሉ የሰጡት ምስጋና ምንኛ አናሳ ነው! ልቡን በኃዘን አደሙበት፤ ይሁንና እርሱ «ሁልጊዜም» በኢየሱስ ክርስቶስ «ይደሰት» ነበር። እነርሱ ሀብታም እንዲሆኑ፥ እርሱ ድሀ ሆነ (1ኛ ቆሮ. 1፡5፤ 2ኛ ቆሮ. 8፡9 ተመልከት)። ድሀ ተብሎ የተተረጎመው ቃል «ፍጹም የሆነ የለማኝነት 

ደረጃ» ማለት ነው። 

ጳውሎስስ እንዲያመሰግኑት በመፈለጉ ጥፋተኛ ይሆን ይሆን? አይመስለኝም። እርግጥ እጅግ በርካታ ክርስቲያኖች የመጋቢዎችን፥ የሚሲዮናውያንንና፥ ታማኝ የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞችን አገልግሎት የዋዛ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ አላቸው። ደግሞም እኮ ጳውሎስም ቢሆን እንዲያመሰግኑት እየለመናቸው አልነበረም፤ ዳሩ ግን በቆሮንቶስ ለነበሩት ወዳጆቹ ያበረከተላቸው አገልግሎት ውድ ዋጋ እንዳስከፈለው ሊያስታውሳቸው ብቻ ነበር የፈለገው። 

በርግጥ በዚህ ሁሉ የግል ምስክርነቱ፥ ጳውሎስ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ያስነሡበትን የሐሰት ክሶች እያፈራረሰባቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች በቆሮንቶስ ለነበሩ ወገኖች ምን ያህል መከራ ተቀብለዋል? ለአገልግሎታቸው ምን ያህል ዋጋ ከፍለዋል? ዛሬ እንደምናያቸው በርካታ «ኑፋቄዎች» ሁሉ፥ እነዚያም የሐሰት አስተማሪዎች በሌላው ሰው ምስክርነት የዳኑትን ሰዎች ሰረቁ እንጂ፥ ራሳቸው ወደ ጠፉት በጎች ተጉዘው ነፍሳትን አልማረኩም ነበር። 

«ምስጋናን ብትሻ የምታገኘው ከመዝገበ-ቃላት ውስጥ ብቻ ነው» የሚለው አባባል እውነትነት ያለው ነው። እኛስ አገልግሎት ላበረከቱልን ሰዎች ምስጋናችንን ከልብ እየገለጽንላቸው ይሆን?

Leave a Reply

%d bloggers like this: