ለቤተ ክርስቲያን የነበረው ሥጋት (2ኛ ቆሮ. 11፡ 16-33)

የዚህ ረዥም ክፍል ቁልፍ አሳብ ቁጥር 28 ሲሆን፥ አሳቡን እንደሚከተለው ለመግለጽ ይቻላል፡- «አዎን፥ በብዙ መከራዎች ውስጥ አልፌአለሁ፤ ይሁንና ከሁሉም የሚበልጠው መከራ፥ ከሁሉም የሚከብደው ሸክም፥ ለአብያተ ክርስቲያናት ያለኝ አሳብ ነው!» አሳብ ተብሎ የተተረጎመው ቃል፡ «ውጥረት፥ ጭንቀት፥ ሥጋት» ማለት ነው። ሌሉች መከራዎች ውጫዊና ወቅታዊ ሲሆኑ፥ ዳሩ ግን የአብያተ ክርስቲያናት ሸክም ውስጣዊና ዘለቄታነት ያለው ነበር። 

ሄንሪ ዎርድ ቢቸር፥ «ራሳችን ወላጆች እስክንሆን ድረስ የወላጆችን ፍቅር በፍጹም አንረዳም» ብለው ነበር፤ ትክክል ናቸው። ታላቁ ልጃችን ሕፃን በነበረ ጊዜ፥ አንድ አሻንጉሊት ከኤሌክትሪክ ሶኬት ውስጥ አስገባለሁ ሲል ኮረንቲ ይዞ እንዳስደነገጠው አስታውሳለሁ። እርሱም በተራው ልጅ ወለደና፥ ይህን ልጁን አንድ ቀን ከሶኬት ጋር ሲጫወት ያየዋል፥ እናም ገና ዓመት ባልሞላው በዚያ ሕፃን ላይ በመጮህ ያስደነግጠዋል። ወዲያውኑም ወደ እኔ ስልክ በመደወል፥ «ሕፃን ሳለሁ አንተና እማማ ስለ እኔ እንዴት ትጨነቁ እንደ ነበረ የተረዳሁት አሁን ነው» በማለት አጫወተኝ። «ወላጅ መሆን የራሱ የሆነ ደስታና ፍርሃት አለው አለ።» 

ጳውሎስ ያለፈባቸውን የተለያዩ የመከራ ዓይነቶች ከመዘርዘሩ በፊት፥ በዚህ ዓይነት ለምን «እንደሚመካ» ለመግለጽ ጥንቃቄ አድርጓል። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ለመመካትና ስለ መከራዎቹ ለመናገር ምንም ችግር አልነበረውም፤ ዳሩ ግን ሁልጊዜም የእግዚአብሔር ባሪያ እንደ መሆኑ ስለሚጋፈጣቸው ከባባድ መከራዎች ለመናገር ያመነታ ነበር። ጳውሎስና መጥምቁ ዮሐንስ፥ «እርሱ [ክርስቶስ] ሊልቅ፥ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል» በሚለው አሳብ ይስማማሉ (ዮሐ. 3፡30)። «የሚመካ ግን በጌታ ይመካ» (2ኛ ቆሮ. 10፡17)። 

ጳውሎስ ስለ ራሱ እንዲጽፍ በእነዚህ ባለፈባቸው የመከራ ልምምዶች እንዲመካ (እንዲኮራ) ያስገደደ፥ ጥሬና መንፈሳዊነት የጎደለውና የቆሮንቶስ ሰዎች አመለካከት ነበር። በመሆኑም ይህንን ክፍል (11፡1) የጀመረው ስለ መመካቱ በቅድሚያ ይቅርታ በመጠየቅ ሆኖ በቁጥር 16 ላይም ይህንኑ ዓረፍተ-ነገር ይደግማል። በቁጥር 17 ላይ፥ ጳውሎስ የቃላቱን የመንፈስ ቅዱስ ምሪት አይክድም፤ ዳሩ ግን በመመካቱ፥ ከጌታ ባሕርይ ጋር የማይዛመድ ነገር ላለማድረጉ ይገልጻል (10፡1 ተመልከት)። ይሁንና ለቆሮንቶስ ሰዎች የነበረውን ፍቅር ለመግለጽና በዚህም ዓይነት ወደ ጥፋት ከሚመሩዋቸው ሐሰተኞች ለመጠበቅ ይህንኑ ተግባር መፈጸም ነበረበት። 

ቀድሞ ነገር፥ የሐሰት አስተማሪዎቹ ለመመካት አላፈሩም ነበር፤ የቆሮንቶስ ሰዎችም መመካታቸውን ለመቀበል ፍርሃት አላደረባቸውም ነበር። ጳውሎስ፥ «በኅብረታችሁ ውስጥ ዋና ነገር መመካት ስለ ሆነ፥ እኔም እመካለሁ» የሚል ይመስላል። ጳውሎስ የምሳሌ 26:5ን መመሪያ በአእምሮው የያዘ ይመስላል፡- «ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው፥ ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት።» 

በተጨማሪም፥ ጳውሎስ የተመካው ቤተ ክርስቲያንን ለመርዳት ሲሆን፥ የሐሰት መምህራን ግን ከቤተ ክርስቲያን ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም አስተማማኝ ለማድረግና «ራሳቸውን ለመርዳት» ይመኩ ነበር። የጳውሎስ ዓላማ ንጹሕ ሲሆን፥ የእነርሱ ግን በራስ-ወዳድነት የተበከለና የረከሰ ነበር። ቁጥር 20 የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ቤተ ክርስቲያንን የበዘበዙባቸውን የተለያዩ መንገዶች ይዘረዝራል። 

ባሪያዎች አደረጉአቸው፡- ከጸጋው ወንጌል ጋር የሚቃረን የሕግ ትምህርት ያስተምሩ ነበር። 

በሉአቸው፡- በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያገኙ የሚችሉትን ነገር ሁሉ «በማጋበስ በልተዋል»። መዋዕለ ንዋይ የማግኘት መብታቸውን በመጠቀም በዘበዙአቸው። 

ቀሙአቸው፡- «ቀሙዋቸው፥ » አሞኙአቸው። ምስሉ የሚያመለክተው በወጥመድ የተያዘችውን ወፍ ወይም በማጥመጃ የተጠመደውን የዓሣ ሁኔታ ነው። «በወጥመዳቸው ላይ የሚጥም ነገር አኑረው አጠመዱአችሁ!» 

ኮሩባቸው፡- ራሳቸውን እንጂ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ከፍ ከፍ አላደረጉም ነበር፤ ሰዎች እንዲያከብሯቸውና እንደ ታላላቅ መሪዎች እንዲቆጥሩአቸው ወደዱ። 

መቱአቸው፡- ይህ ከሥጋዊ ጥቃት ይልቅ፥ የቃላት ተቃውሞን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም፤ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች የቆሮንቶስን ሰዎች «ፊት በጥፊ ለመምታት» እና በሕዝብ ፊት ለማሳፈር አልቦዘኑም ነበር። 

ጳውሎስ እነዚህን መንፈሳዊነት የጎደላቸውን የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች አመለካከቶችና ተግባራት ገለጻ የደመደመው፥ አንዳንድ «የመንፈስ ምሪት ያለባቸውን ቅኔዎች» በማከል ነበር። «ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ» (ቁ 2)። የቆሮንቶስ ሰዎች የጳውሎስ የዋህነት ብርታት ሆኖ ሳለ፥ ድክመት ነው ብለው አሰቡ። የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ትዕቢት ደግሞ ኃይል መሰላቸው። ቅዱሳን አንዳንድ ጊዜ አላዋቂ ሆነው ሲገኙ የቱን ያህል ያስደንቅ! 

የአይሁዳዊነት ዝርያን በተመለከተ፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎቹ ከጳውሎስ ጋር እኩል ነበሩ፤ ዳሩ ግን የክርስቶስን አገልግሎት በተመለከተ፥ «ቁንጮው ወይም ምጡቁ-ሐዋርያ» ጳውሎስ እንጂ፥ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች አልነበሩም። እስቲ ጳውሎስ ለክርስቶስና ለአብያተ ክርስቲያናት ብሎ የታገሣቸውን መከራዎች እናስታውስ። 

ለክርስቶስ የተቀበላቸው መከራዎች (2ኛ ቆሮ. 11፡23-25)። ጳውሎስ ሐዋርያ ባይሆን ኖሮ፥ እነዚህን መከራዎች ባልተቀበለ ነበር። ከአሕዛብም ሆነ ከአይሁድ «ከልክ ያለፈ ግርፋት» ተቀብሏል። አሕዛብ ሦስት ጊዜ በበትር መቱት፤ አይሁድ ሦስት ጊዜ 39 ጅራፍ ገረፉት። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ እንደ ደበደቡት (16፡22) እና አንድ ጊዜ በድንጋይ እንደ ወገሩት(14፡19) ብቻ ነው። 

ጳውሎስ ገና ከአገልግሉቱ ጅማሬ ላይ ስለ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበል ያወቀው ከመሆኑም (የሐዋ. 9፡15-16)፡ አገልግሎቱን ቀጥሉ ሳለም እግዚአብሔር ይህንኑ በድጋሚ አረጋግጦለታል (የሐዋ. 20፡23)። ሌሉች ስለ እምነታቸው መከራ እንዲቀበሉ ምክንያት የሆነው ሰው፥ ራሱ ስለ እምነቱ መከራ መቀበል ነበረበት። 

ተፈጥሮአዊ ችግሮች (ቁ 25-27)። በዚያን ጊዜ ማንኛውም ተጓዥ ለማለት ይቻላል፤ ከእነዚህ ችግሮች አንዳንዶቹ ሊያጋጥሙት ይችሉ ነበር፤ ጳውሎስ የተጋፈጣቸውን ዓይነት ችግሮች ግን የጌታን ሥራ ለማደናቀፍ ጠላት የተጠቀመባቸው ናቸው ከማለት በስተቀር ሌላ የምንሰጠው አጥጋቢ ምክንያት አናገኝም። የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 27 ከሦስት የመርከብ ስብራት አደጋዎች አንዱን ይዘግባል። ስለ ተቀሩት ሁለቱ ግን የምናውቀው ነገር የለም። ጳውሎስ በዚህ ጉዞ ምን ያህል የግል ንብረቶቹን እንዳጣ ማሰባችን የማይቀር ነው። 

ጳውሎስ ባለማቋረጥ ይጓዝ ስለ ነበር፥ ለጉዞ አደጋዎች የተጋለጠ ሰው ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ሰላም ወደሰፈረባቸው ስፍራዎች ይሄድ ነበር። ዳሩ ግን ጳውሎስ ተራ ተጓዥ ሳይሆን፥ ተለይቶ የታወቀ ሰው ነበር። ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ ጠላቶች ነበሩት፤ አንዳንዶችም ሞቱን ይመኙ ነበር። 

ሁለተኛ ቆሮንቶስ 11፡27 የዚህን አስቸጋሪ ጉዞ ውጤቶች ይገልጻል። እኔ እንኳን ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወርሁ በማከናውነው ውስን አገልግሎቴ፥ አመቺ በሆኑ መኪኖችና አውሮፓላኖች እጓዛለሁ፤ ይሁን እንጂ ከቦታ ቦታ መጓዝ ምን ያህል እንደሚያዝለኝና እንደሚያሰለቸኝ መናዘዝ ይኖርብኛል። ታዲያ ለጳውሎስ የቱን ያህል ከዚህ የበለጠ አሰልቺና አስቸጋሪ ሆኖበት ይሆን! በድካምና በሕመም የተጎሳቆለና የተሰቃየ መሆኑ የሚያስደንቅ አይሆንም። ብዙውን ጊዜ ምግብ፥ መጠጥና እንቅልፍ ያጣ ነበር፤ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ለሰውነቱ በቂ ሙቀት የሚለግስ ልብስ እንኳ አያገኝም ነበር። 

ምንም እንኳ እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች ማንኛውም ሌላ ተጓዥ ሊገጥሙት ቢችሉም፥ ጳውሎስ ግን ለክርስቶስና ለቤተ ክርስቲያን ከነበረው ፍቅር የተነሣ ይህን ሁሉ ችግር ያለ አንዳች ማማረር በጽናት ተቋቋመ። ከሁሉም የሚልቀው ሸክሙ፥ በዙርያው ከሚመለከተው ነገር የተፈጠረ ሳይሆን፥ ከውስጡ የሚመነጨው ስሜት ነበር – የእነዚያ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ደኅንነት ነበር ጭንቀቱ! ግን ለምን ይህን ያህል ተጨነቀ? ምክንያቱም ራሱን ከአማኞች ጋር በይፋ አንድ በማድረጉ ነው (ቁ 29)። በመንፈሳዊ «ልጆቹ» ላይ የሚደርሰው ነገር ሁሉ ልቡን ይነካው ስለ ነበር፥ ጥሎአቸው ሊሔድ አልቻለም ነበር። 

ጳውሎስ ይህን በችግር የመፈተን ትረካውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሰው፥ እርሱን የመሰለ ታላቅ ሐዋርያ፥ በቅርጫት ውስጥ ተጨምሮ በቅጥር ላይ በማለፍ፥ ከደማስቆ ከተማ የወጣበትን የውርደት ልምምድበመግለጽነው(ቁ. 32-33)። ከአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች መካከል እንዲህ ዓይነቱን ታሪክ ለመናገር የሚደፍር ይኖር ይሆን? በፍጹም አይኖርም! ጳውሎስ ስለ መከራዎቹ በሚተርክበት ጊዜ እንኳ፥ ክብሩን የሚቀበለው ክርስቶስ እንጂ ራሱ እንዳይሆን ይጠነቀቅ ነበር። 

እነዚህን ቁጥሮች በምናነብበት ጊዜ፥ የሐዋርያውን ብርታትና መሰጠት ሳናደንቅ አናልፍም። እያንዳንዱ መከራ በሕይወቱ ውስጥ ምልክት እየጣለ ቢያልፍም፥ እርሱ ግን ጌታን እያገለገለ ወደ ፊት ይራመድ ነበር። «ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ» (የሐዋ.20፡24)። 

ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን የነበረውን ፍቅር በርግጥ አረጋግጧል፤ አሁን ቤተ ክርስቲያን ለጳውሎስ የነበራትን ፍቅር ማረጋገጥ ነበረባት። 

ዛሬ በወንጌሉ በረከቶች እንደሰት ዘንድ፥ ሌሎች አስቀድመው የካፈሉዋቸውን መሥዋዕቶች እንደ ዋዛ-ፈዛዛ እንዳንመለከት እግዚአብሔር ይርዳን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: