ጳውሎስ በእምነታቸው ጠንካራ የነበሩ በልምድ የዳበሩ ክርስቲያኖች፥ ፈተናን ድል በማድረግ ችሎታቸውን ከሚገባው በላይ እንዳይተማመኑ ያሳስባቸዋል። «ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ» (ቁ. 12)። ጳውሎስ በሳል አማኞች ልምዳቸውን ከጥንቃቄ ጋር እንዲያጣጥሙ ሊያስጠነቅቅ የእስራኤልን ሕዝብ እንደ ምሳሌ ተጠቀመ። ለዚህም ሦስት ማስጠንቀቂያዎችን ሰጥቶአል።
በመጀመሪያ፥ ልዩ መብት ወይም ጥቅሞች ለስኬት ዋስትና እንዳልሆኑ አስጠነቀቀ (10፡1-4)። ልክ እስራኤል በእግዚአብሔር ኃይል ከግብጽ አርነት እንደወጣች ሁሉ ክርስቲያን አማኝም ከኃጢአት አርነት ይወጣል። (በ5፡7-8፥ ጳውሎስ ቀደም ሲል ደኅንነትን ከፋሲካ ጋር አያይዞታል።) እስራኤል በቀይ ባሕሩ «ጥምቀት» ከሙሴ ጋር አንድ እንደሆነች ሁሉ፥ ቆሮንቶሳውያንም በክርስቲያናዊ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድ ይሆናሉ። እስራኤላውያን ከሰማይ የመጣ መና እንደበሉ እና እግዚአብሔር የሰጠውን ውኃ እንደ ጠጡ ሁሉ፥ ክርስቲያኖችም እግዚአብሔር የሚሰጠውን መንፈሳዊ ማዕድ ራሳቸውን ይመግባሉ (ዮሐ 6፡63፥68፤ 7፡37-39)። ሆኖም እነዚህ ልዩ መብቶች እና ጥቅሞች አይሁድን በኃጢአት ከመውደቅ አልከለከሉአቸውም።
ለብስለትም ሆነ ላለመብሰል አደጋዎች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ከሚገባው በላይ በራስ መተማመን ነው። ብርቱ የሆንን ሲመስለን ደካማ መሆናችንን እንደርስበታለን። በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚበላው ብርቱ አማኝ ከዓቅሙ እጅግ ከላቀ ጠላት ጋር ሲታገል ራሱን ያገኘዋል።
ምንም እንኳ አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት አለቆች ቢያስተምሩትም፥ አይሁድ በምድረበዳ ጉዞአቸው እውነተኛ ድንጋይ ይዘው እንደዞሩ ጳውሎስ በቁጥር 4 ላይ አይጠቁምም። ያኔ ያስፈለጋቸውን ነገር ያቀረበላቸው መንፈሳዊው ድንጋይ፥ እርሱም ክርስቶስ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከድንጋይ (ዘጸ. 17፡1-7፤ ዘኁ. 20፡7-11) በሌሎች ጊዜያት ከጉድጓድ (ዘኁ. 21፡16-18) ውኃ ይወጣ ነበር። ውኃውን የሰጠው እግዚአብሔር ነው።
ጳውሎስ ሁለተኛውን ማስጠንቀቂያ ሰጠ። መልካም ጅማሬዎች ለመልካም ፍጻሜ ዋስትና አይሰጡም (10፡5-12)። አይሁድ የእግዚአብሔርን ተአምራት የተለማመዱ ቢሆኑም፥ በምድረበዳ በተፈተኑበት ጊዜ ግን ተሸነፉ። ልምዱ ሁልጊዜ ከጥንቃቄ ጋር መጣጣም አለበት፥ ምክንያቱም በክርስቲያናዊ አካሄዳችን ከፈተና እና ከውድቀት አዴጋ ነፃ ወደሚኮንበት ደረጃ ከቶውንም ልንደርስበት አንችልም። ኢያሱ እና ካሌብ ሲቀሩ 20 ዓመት እና ከዚያም በላይ የሆኑ ሁሉ፥ የሞቱት በመቅበዝበዝ ዘመናቸው በምድረበዳ ውስጥ ነው (ዘኁ. 14፡26)።
አንዳንድ የቆሮንቶስ ሰዎች «ያ ታዲያ ከእኛ ጋር ምን ግንኙነት አለው ሲሉ ልንሰማ እንችላለን። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አይሁዶች ከፈጸሙት ጋር አንድ ዓይነት ኃጢአቶችን የመፈጸም ተጠያቂነት እንዳለባት ጳውሎስ እመለከተ። ለክፉ ነገሮች ከነበራቸው ምኞት የተነሣ፥ ቆሮንቶሳውያን በዝሙት (ምዕ. 6)፥ በጣዖት አምልኮ (ምዕ. 8፤10) እና እግዚአብሔር ላይ በማንጎራጎር (2ኛ ቆሮ. 12፡20-21) ተጠያቂ ነበሩ። ልክ እንደ እስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ይፈታተኑትና እንዲሠራ «ያደፋፍሩት» ነበር።
ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ያለ ጥርጥር ያውቅ ነበር፥ አንባቢያኑም ደግሞ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ያውቁ ነበር። «መጎምጀት» በዘኁል. 11፡4፥ ጣዖትን ማምለክ በዘጸ. 32፥ እና ዝሙት በዘኁል. 25 ይገኛሉ። እስራኤላውያን ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን ይፈታተኑት ነበር፥ ምናልባት ጳውሎስ በአእምሮው የያዘው ማጣቀሻ ዘኁል. 21፡4-6 ሊሆን ይቻላል። ለማጉረምረማቸው ዘኁል 14 እና 16ን ተመልከት።
ይህ ዓይነቱ ኃጢአት ከባድ ስለሆነ የእግዚአብሔር ፍርድ የተገባው ነው። ከእነዚህ ዓመፀኞች አንዳንዶቹ ወዲያውኑ የሞቱ (1ኛ ቆሮ. 11፡29-31ን ተመልከት ብቻ ሳይሆን፥ የተረፉትም የተስፋይቱን ምድር ለመውረስ አልተፈቀደላቸውም። ከግብጽ የዳኑ ቢሆንም፥ ነገር ግን የበለጸገ ውርሳቸውን ለመቀዳጀት አልቻሉም። ጳውሎስ የሚታገለው አንባቢያኑ ደኅንነታቸውን እንዳያጡ ሳይሆን፥ ነገር ግን አንዳንዶቻቸው «የተጣሉ» (9፡27)፥ እግዚአብሔር የተዋቸው እና ምንም ዋጋ የማያገኙ እንዳይሆኑ ነው።
«የቅዱሳን ኃጢአት» በሚል ተከታታይ ስብከት ስለሰጠ አንድ መጋቢ ሰምቼ ነበር። ወቀሳው የተመለከታት ይመስላል፥ አንዲት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል «ምንም ቢሆን እኮ በክርስቲያን ሕይወት የሚከሰት ኃጢአት ባልዳነ ሰው ሕይወት ከሚከሰተው የተለየ ነው» በማለት መጋቢውን፥ ትምህርትህ ውድቅ ነው አለችው።
መጋቢውም በመመለስ፥ «አዎን የተለየ ነው፥ በክርስቲያን ሕይወት የሚከሰት ኃጢአት የባሰ ነው!» አላት።
አይሁድ በሕግ ቀንበር ሥር ስለነበሩ የእነርሱ ኃጢአት ከእኛ የተለየ በመሆኑ ከበድ ባለ ሁኔታ ይስተናገዳል ብለን ማሰብ የለብንም። በዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ኃጢአት እጅግ የከፋ ነው፤ ምክንያቱም ትምህርት የሚሆነን የእስራኤል ምሳሌ በፊታችን ስላለን እና «በዘመን ፍጻሜ» ስለምንኖር ነው። በሕግ ላይ ኃጢአት መሥራት አንድ ነገር ነው፤ በጸጋ ላይ ኃጢአት መሥራት ግን በጣም የተለየ ነው።
የጳውሎስ ሦስተኛ ማስጠንቀቂያ ቃሉን አጥብቀን ከፈለግን እግዚአብሔር ፈተናን እንድናሸንፍ ያስችለናል የሚል ነበር (10፡13-22)። እግዚአብሔር እንድንፈተን የሚፈቅደው ዓቅማችንን ስለሚያውቅም ነው፤ ደግሞም እርሱን የምንተማመን ከሆነና ፈተናውን በበጎ አመለካከት የምንቀበል ከሆነ ሁልጊዜም መውጫውን ያዘጋጅልናል። በራሱ ሊቆም እንደሚችል የሚያስብ አማኝ ይወድቃል፤ ከሚፈትን ነገር የሚርቅ አማኝ ግን መቆም ይችላል።
ጳውሎስ አንባቢያኑን ቀደም ሲል «ከዝሙት ሽሹ» ብሎ ነግሮአቸው ነበር (6፡18)፤ የአሁኑ ማስጠንቀቂያው፥ «ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ» (10፡14) የሚል ነው። ጣዖት በራሱ ምንም እንዳይደለ፥ ነገር ግን የሰይጣን መሣሪያ በመሆን ለምን ወደ ኃጢአት ሊመራህ እንደሚችል ምክንያቱን አብራራ። አምልኮተ ጣዖት አጋንንታዊ (ዘጸ 32፡17፤ መዝ. (106)፡37) ነው። በጣዖት ማዕድ መቀመጥ ከአጋንንት ጋር ኅብረት (አንድነት፥ ተካፋይነትን) ማድረግ ሊመስል ይችላል። ጳውሎስ ከኃጢአት የመለየትን ጠቃሚ ዶክትሪን እንደገና ያጸና ነበር (2ኛ ቆሮ 6፡14-7፡1)
የጌታን እራት እንደ ምሳሌ ተጠቅሞአል። በጌታ እራት ጊዜ አማኙ ከጽዋውና ከኅብስቱ በሚጋራበት ጊዜ፥ በመንፈሳዊ መንገድ፥ ከክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር ኅብረት ማድረጉ ነው። የክርስቶስን ሞት በማስታወስ፥ አማኙ ከተነሣው ጌታ ጋር አንድነት ውስጥ ይገባል። በቁጥር 18፥ የቤተ መቅደስ መሠዊያንና መሥዋዕትን የዚህ እውነት ሌላኛው ምሳሌ አድርጎ ያቀርበዋል። ተዛምዶው ግልጽ ነው፡- አንድ አማኝ ራሱን ለአደጋ ሳያጋልጥና ጌታን ሳያስቆጣ የጌታን ማዕድ (የብሉይ ኪዳኑ መሥዋዕት፥ የአዲስ ኪዳኑ እራት) ተካፋይ ሊሆን አይችልም።
«እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን?» (ቁ 22) የሚለው ሐረግ የተነጣጠረው ምንም ጉዳት ሳያገኘው በጣዖት አምላኪዎች ቤተ መቅደስ አርነቱን ሊደሰትበት እንደሚችል እርግጠኛ በሆነው ብርቱ ክርስቲያን ላይ ነው። «ከደካማው ወንድምህ የበረታህ ትሆን ይሆናል»፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የበረታህ አይደለህም!» በማለት ጳውሎስ እንደ ምሥጢር አድርጎ ተናገረ። በኃጢአት መጫወት እና እግዚአብሔርን መፈታተን አደገኛ ነው።
ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው