ልዩነት፡- የመንፈስ ስጦታዎች (1ኛ ቆሮ. 12፡14-31)

አንድነት ያለ ልዩነት የሚያስገኘው ወጥነትን ነው፤ ወጥነት ደግሞ ሞትን የማምጣት አዝማሚያ አለው። ሕይወት በአንድነት እና በልዩነት መካከል ያለ ሚዛን ነው። የሰው ሰውነት በሚሞትበት ጊዜ፥ «ሥርዓቶቹ» እያዘገሙ ይሄዱና ሁሉም ነገር ወጥ ወደ መሆን ያጋድላል። በእርግጥ ማሳረጊያው፥ ሥጋ ራሱ ወደ አፈር መለወጡ ነው። 

ይህ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት (እንዲሁም ሌሎች ክርስቲያናዊ አገልግሎቶች) ተዳክመው የሞቱበትን ሁኔታ ለማብራራት ይረዳል። ይኸውም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ አንድነት ወደ ወጥነት እንዳይዘቅጥ ለማድረግ በቂ ልዩነት አልነበረም። ዶክተር ቫንስ ሃቭነር እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ «በመጀመሪያ ሰው ነው፥ ከዚያም እንቅስቃሴ፥ ብሎም ማሺን እና በመጨረሻም ሐውልት ነው»። የሞተ ሃይማኖትን» በመቃወም የተወለዱ አገልግሎቶች ራሳቸውም ሙት ሆነዋል፤ ምክንያቱም በዶክትሪን ጤናማ ና ንጹሕ ሆኖ ለመቀጠል ባላቸው ፍላጎት ፈጠራን ና አዳዲስ እሳቦችን በማፈናቸው ነበር። 

ይሁንና ልዩነት በቁጥጥር ሥር ካልዋለ ደግሞ አንድነትን ያጠፋል፤ እና በዚህ ጊዜ ሥርዓት አልበኝነት ይሰፍናል። አንድነትን ና ልዩነትን በሚዛን የሚጠብቀው ብስለት መሆኑን በምዕራፍ 13 እንደርስበታለን። በአካል ውስጥ በእያንዳንዱ ብልት ና በአጠቃላዩ አካል መካከል ያለው ውጥረት የሚፈታው ስብስለት ነው። 

የሰውን አካል እንደ ምሳሌ በመጠቀም፥ ጳውሎስ በክርስቶስ አካል ውስጥ ስላሉ ልዩነቶች ሦስት ጠቃሚ ነጥቦችን ገለጸ። የተለያዩ ብልቶች ያሉት ለምንድን ነው? 

አካል፥ እንዲኖር፥ እንዲያድግ እና እንዲያገለግል ካስፈለገ የተለያዩ ሥራዎች ያስፈልጉታል (12፡14-20)። ማንም ምእመን ከሌላው ከማንም ጋር ራሱን ማወዳደር የለበትም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ልዩ ና ጠቃሚም ነው። በእጆቼ መራመድን መማር እችል እንደነበር እገምታለሁ፤ ነገር ግን እግሮቼን መጠቀምን እመርጣለሁ፣ ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ በእግሮቼ መተየብ ወይም መብላት ባልማርም። ጆሮ አያይም፥ ዓይን እይሰማማ፥ ሆኖም ግን እያንዳንዱ አካል ጠቃሚ አገልግሎት አለው። በጆሮዎችህ ለማሽተት ሞክረህ ታውቃለህን? 

ዛሬ አንዳንድ ሰዎች «ስሜት ቀስቃሽ» ስጦታዎችን ወደ ማጉላቱ አዝማሚያ ላይ ናቸው። አንዳንድ አማኞች ስጦታዎቻቸው ለሕዝብ ዓይን የሚያበቁአቸው ስላይደሉ ጥፋተኝነት ይሰማቸዋል። ጳውሎስ በዚህ አንቀጽ የተቃወመውና ውድቅ ያደረገው እንዲህ ዓይነቱን እመለካከት ነው። ልዩነት የበታችነትን አያመለክትም። እንዲህ ከሆነ ሉዓላዊው ጌታ ስጦታዎችን በሰጠ ጊዜ ስሕተት ሠራ ብለን ልናምን ነውን? 

ብልቶች አንዳቸው በሌላቸው ላይ መደገፋቸውን ሲያውቁት እንድነትን ያጠነክራሉ (12፡21-26)። በአካል ውስጥ የሚታይ ልዩነት የእግዚአብሔር ጥበብ ማስረጃ ነው። እያንዳንዱ ብልት ሌላውን ይፈልጋል፥ የትኛውም ብልት ነፃ መሆን አይችልም። የሰው አካል እንዱ ክፍል ነፃ በሚሆንበት ጊዜ፥ ለበሽታ እና ለሞትም እንኳ የሚዳርግ ከባድ ችግር ይፈጠራል። በጤናማ ሰብአዊ አካል፥ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ ልዩ ልዩ ብልቶች እርስ በርስ ይተባበራሉ፤ ደግሞም አንዱ ሌላውን ይተካል። የአካል የትኛውም ክፍል ለሌላው ክፍል፥ «አታስፈልገኝም!» በሚልበት ጊዜ መዳከም እና መሞት እንዲሁም ለመላው አካል ችግር መፍጠር ይጀመራል። 

እንድ ዝነኛ ሰባኪ በአገልጋዮች ስብሰባ ላይ ይናገር ነበር። ተሳታፊዎቹን ከስብሰባው በፊት ና በኋላ ጊዜ በመውሰድ ሰላምታ ይሰጣቸውና ያነጋግራቸው ነበር። አንዱ ተሳታፊ፥ «ዳግመኛ ከቶ ለማታየው ለዚህ ቡድን ለምን ጊዜ በመውሰድ ትቸገራለህ?» ብሎ ጠየቀው። ይህ ዓለም ያደነቀው ሰባኪ ፈገግታ እያሳየ እንዲህ አለ፥ «ጀግ፥ ባለሁበት ያለሁት እኮ በእነርሱ ምክንያት ነው! በከፍታ ሕይወቴ ባልፈልጋቸው፥ በዝቅታ ሕይወቴ እፈልጋቸው ይሆናል!» የትኛውም ክርስቲያን አገልጋይ ለሌላው አገልጋይ፥ «የእኔ አገልግሎት ያለአንተ ሊከናወን ይችላል!» ብሎ መናገር አይችልም። 

ጳውሎስ ከቁጥር 23-24 ባለው የሚያመለክተው ድብቅ ለሆኑ አካል ክፍሎች ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ከሆነ ደግሞ፥ «ክብር እናለብሳቸዋለን» የሚለው የሚያመለክተው የተዋቡ ልብሶችን ስለ መጠቀም ነው። የበለጠ ውብ የሆኑ የአካል ክፍሎች የተለየ እርዳታ እያስፈልጋቸውም። 

የእግዚአብሔር ፍላጎት በቤተ ክርስቲያን ክፍፍል እንዳይኖር ነው። ብልቶች እርስ በርስ የሚፎካከሩ ከሆነ ልዩነት ወደ መፈራረስ ያመራል። ብልቶች እንዳቸው ለሌላቸው ክብካቤ የሚያደርጉት እንዴት ነው? እያንዳንዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ በመሥራት እና ሌሎች ብልቶች እንዲሠሩ በማገዝ ነው። አንዱ ብልት ቢሠቃይ ሁሉም ብልቶች ይነካሉ። አንዱ ብልት ጤናማ ከሆነ፥ ሌሎች እንዲጠናከሩ ይረዳል። 

የብልቶች ልዩነት እግዚአብሔር በአካሉ ላይ ያለውን ፈቃዱን ከፍጻሜ ያደርሳል (12፡27-31)። ስጦታዎቹንና የአገልግሎት ኃላፊነቶችን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው። እርሱ ለመላው ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን፥ ለእያንዳንዱ አጥቢያ ጉባኤም ፍጹም የሆነ ዕቅድ አለው። በአዲስ ኪዳን ያሉት እያንዳንዱ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ስጦታዎች ይኖሩታል ብለን ለማመን ምክንያት የለንም። በቆሮንቶስ የነበረች ቤተ ክርስቲያን በልዩ ሁኔታ በስጦታዎች የበለጸገች ነበረች (1፡4-7፤ 2ኛ ቆሮ. 8፡7)። ይሁንና፥ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ጉባኤ በሚፈልግበት ወቅት የሚያስፈልጉትን ስጦታዎች ይሰጣል። 

በዚህ አንቀጽ፥ ጳውሎስ እንዳንዶቹን ከሌሎች የበለጠ ተፈላጊ የሚያደርግ «የቅደም ተከተል ዝርዝር» ለስጦታዎቹ መኖሩን ያሳያል። ነገር ግን ይህ እውነት—እያንዳንዱ ስጦታ እና እያንዳንዱ አማኝ አስፈላጊ ነው ተብሎ ቀደም ሲል የተነገረውን አይቃረንም። አለመኖራቸው በመጠኑም ቢሆን ሰንካላ ቢያደርገንም፥ በሰብአዊ አካል አንዳንድ ክፍሎች ጎድለውም በሕይወት መቀጠል ይቻላል። 

ሐዋርያትና ነቢያት፥ በእርግጥ የምሥረታ አገልግሎት (ኤፌ. 2፡20) ስለነበራቸው በመጀመሪያው እይታ ላይ ነበሩ። አስተማሪዎች፥ እማኞችን በእምነት እንዲመሠረቱ ለመርዳት ነበር ያስፈለጉት። ሌሎችም ስጦታዎች እያንዳንዱን እማኝና ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ እንዲረዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተጨመሩ ናቸው። 

ከቁጥር 29-30 ያለው የግሪኩ እገባብ ለእነዚህ ጥያቄዎች ለእያንዳንዳቸው «አይደለም» የሚል ምላሽን የሚፈልግ ነው። ሁሉንም መንፈሳዊ ስጦታዎች የሚያካብት ማንም ግለሰብ አማኝ የለም። እያንዳንዱ አማኝ በጌታ ለእርሱ የተመደበለት/ የተመደቡለት እና ተፈላጊ የሆነ/የሆኑ ስጦታ/ ስጦታዎች ይኖሩታል። 

በቁጥር 31 የሚበልጠውን ተብሎ የተተረጎመው «ከፍተኛውን» ማለት ነው። አንዳንድ የመንፈሳዊ ስጦታዎች ከሌሎች የበለጠ ተፈላጊነት ስላላቸው አማኞች እነዚህን መሻታቸው ተገቢ ነው (14፡1)። ጳውሎስ ለትንቢት ከፍተኛ ዋጋ ሲሰጥ ቆሮንቶላውያን ግን ልሳኖችን አስበልጠው ይመለከቱ ነበር። ጳውሎስ ልሳኖችን ያስቀመጠው በዝርዝሩ መጨረሻ ላይ ነበር። 

እንድነትና ልዩነት ከብስለት ጋር መጣጣም አለባቸው፤ ብዕለት ደግሞ ከፍቅር ጋር አብሮ የሚመጣ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎችንና ከመንፈስ ስጦታዎችን መቀበል ብቻ በቂ አይደለም። ለእርስ በርሳችን ስጦታዎችን በምንጠቀምበት ወቅት የመንፈስ ጸጋዎች ያስፈልጉናል።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: