መቅድም
በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ ክርስቲያኖች በነበሩአቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች እና እውቀት ይታበዩ ነበር። እንዲህም ሆኖ በግል ሕይወታቸው ውስጥ እና በጉባኤያቸው መካከል ጉልህ ስሕተት ነበረባቸው።
ጳውሎስ የሚያስፈልጋቸው እውነተኛ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን ደርሶበታል። ይህም የዓለም ጥበብ ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ብቻ የሚፈልቅ ጥበብ ነው።
እኛም ዛሬ የሚያስፈልገን ይኸው ጥበብ ሲሆን የሚገኝበትን እንድናውቅ ይህ መልእክት ጥሩ መነሻ ይሆነናል። ሃይማኖታዊ መሪነታችን «ለቀዳሽ አወዳሾች» ወጥመድ እንዳያደርገን፥ ጳውሎስ ስለ ወንጌል መልእክት እና አገልግሎት እንዴት ልባም መሆን እንደሚገባን ይናገረናል። በአምልኮአችን ምን ዓይነት ሥርዓት ልንይዝ እንደሚገባና መንፈሳዊ ስጦታዎቻችንን እንዴት እንደምናውቃቸውና እንደምናዳብራቸው ይነግረናል። እግዚአብሔርን ለማክበርና ከዓለም እድፈት ለማምለጥ ይቻለን ዘንድ እንዴት ራሳችንን በንጽሕና መጠበቅ እንዳለብንም ይነግረናል።
በዚህ አጭር የገለጣ ጥናት፥ አንደኛ ቆሮንቶስን በመሰለ ሰፊ መልእክት ውስጥ ያሉትን ዝርዝር ጠጣር አሳቦች ሁሉ ማጠናቀቅ አንችልም። የእኔ ዓላማ የመልእክቱን አንኳር ትምህርቶች ማብራራት እና ለሕይወታችንና ለቤተ ክርስቲያኖቻችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የእርሱን መንፈሳዊ ጥበብ እንድንቀበል እና በግል ሕይወታችንም ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል ጌታ ይርዳን።
ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ
በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን መሠረተ አቋም
ጳውሎስ በ 50 ዓ.ም መኸር ወቅት አካባቢ ወደ ቆሮንቶስ መጥቶ 18 ወራት በዚያው በመቆየት (የሐዋ. ሥራ 18፡1-17) ቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ። ከዚያም ቀጥሎ ወደ ኤፌሶን ተጓዘ (ቁ 18– 19)።
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ችግሮች አሉ በሚል የደረሰው ዜና ዛሬ በእጃችን ያልገባውን መልእክት እንዲጽፍ አነሣሣው (1ኛ ቆሮ. 5፡9)። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መካከል የከፉ ችግሮች ስለመኖራቸው ከቀሎዔ ቤተሰቦች የመጣው ተጨማሪ መልእክት (1ኛ ቆሮ. 1፡1ህ የሚያመለክተው፥ ይህ «የጠፋ ደብዳቤ» የጳውሎስን ፍላጎት እንዳልፈጸመለት ነበር። ከዚያ በኋላ ቤተክርስቲያኒቱ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን ልምምድ እና ዶክትሪን ጥያቄዎችን ያዘለ ደብዳቤ አስይዛ አንድ ልዑክ ወደ ጳውሎስ ላከች (1ኛ ቆሮ. 7፡1፤ 16፡17–18)።
በዚህ ደብዳቤ ስለደረሰው የከፋ ዜና ምላሽ፥ ጳውሎስ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ሲባል የምናውቀውን ደብዳቤ ጻፈ። የጻፈውም በ57 ዓ.ም. አካባቢ በኤፌሶን ሆኖ ነበር።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጳውሎስን ሐዋሪያዊ ሥልጣን የማይቀበል ቡድን ተነሥቶ ነበር። በመሆኑም ሐዋርያው ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ «ኦስቸኳይ ጉብኝት» አደረገ፥ ይሁን እንጂ ውጤቶቹ አርኪ አልነበሩም (2ኛ ቆሮ. 2፡1፤ 12፡14፤ 13፡1)። ከዚያ በኋላ «የሰላ ደብዳቤ» (2ኛ ቆሮ. 7፡8-12) ጽፎ በቲቶ አማካኝነት ላከባቸው።
ጳውሎስ ቲቶን በጢሮአዳ አግኝቶ (2ኛ ቆሮ. 2፡12-13፤ 7፡6-16) ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን ትእዛዝ ስለ መቀበሏና የተቃዋሚዎቹን መሪም እንደቀጣች መልካም ዜና ሰማ። ከዚያ በኋላ ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን ጻፈ።
የ 1ኛ ቆሮንቶስ አስተዋጽኦ
1. ሰላምታ- 1፡1-3
2. ግሣጼ፡- በቤተ ክርስቲያን ስለነበረው ኃጢአት ዘገባ- 1፡4-6፡20
ሀ. መከፋፍል በቤተ ክርስቲያን – 1፡4-4፡21
ለ. ፍርድ በቤተክርስቲያን ውስጥ – 5፡1-13
ሐ. በችሎት ፊት መፋረድ (መካሰስ) – 6፡1-8
መ. በዓለም ውስጥ መርከስ – 6፡9-20
3. መመሪያ፡- ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ – 7፡1-16፡12
ሀ. ጋብቻ 7፡1-40
ለ. ለጣዖት ስለተሠዋ ምግብ– 8፡1-10።3
ሐ. የቤተ ክርስቲያን ሥልጣናዊ አመራር- 11፡1-34
መ. መንፈሳዊ ስጦታዎች– 12፡1-14፡40
ሠ. ትንሣኤ-15፡1-58
ረ የገንዘብ መዋጮ – 16፡1-12
4. መደምደሚያ – 16፡13-24
ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው