ሙታን የሚነሡት ለምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 15፡29-34፥ 49-58)

የሰው አካል ትንሣኤ ለግል ሕይወታችን አስገዳጅ ውጤቶችን ያዘለ መጻኢ ሁኔታ ነው። ትንሣኤ እውነት ካልሆነ፥ ስለ ወደፊቱ በመርሳት እንደፈለግን መኖር እንችላለን! ነገር ግን ትንሣኤ እውነት ነው! ኢየሱስ ዳግም ይመጣል! እርሱ ከመምጣቱ በፊት ብንሞትም እንኳ፥ በሚመጣበት ጊዜ ተነሥተን በከበረ አካል በፊቱ እንቆማለን። 

ጳውሎስ ከትንሣኤ እውነታ ጋር የሚነካኩ አራት ክርስቲያናዊ ልምምዶችን ጠቅሶአል። 

የወንጌል ስርጭት (15፡29)። «ለሙታን መጠመቅ» ማለት ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች ይህን «የአማላጅነት ጥምቀት» ነው ይሉታል፥ ይህም ማለት እማኙ በሞተው ዘመዱ ምትክ መጠመቁ ነው፤ ነገር ግን በአዲስ ኪዳን እንዲህ ያለ ነገር የለም። በሁለተኛው ምእተ ዓመት፥ «የውክልና ጥምቀቶች»ን የሚለማመዱ አንዳንድ መናፍቃን ቡድኖች ነበሩ። (ቤተክርስቲያን ግን በአጠቃላይ ይህን ተቀብላ አታውቅም።) በመጀመሪያ፥ ደኅንነት እያንዳንዱ ሰው ለራሱ የሚወስነው ግላዊ ጉዳይ ነው፤ ሁለተኛ፥ ማንም ለመዳን ሲል መጠመቅ አያስፈልገውም። 

አባባሉ ምናልባት «የሞቱትን ተክቶ መጠመቅ» ማለት ሊሆን ይችላል። በሌላ አነጋገር ትንሣኤ ከሌለ፥ ለመመስከርና ሌሎችን ወደ ክርስቶስ ለመመለስ መጨነቅ ለምን ያስፈልጋል? በኋላ እንዲጠመቁ ለምንስ ኃጢአተኞችን እንደርሳቸዋለን? ለምንስ የውክልና ጥምቀት እንወስዳለን? ክርስቲያናዊ ሕይወት መጨረሻው ዝግ የሆነ መንገድ ከሆነ ለቅቀህ ውጣ! 

በዚህች ምድር ኃላፊነት ያለበት ማንኛውም ሰው፥ አንድም በሕይወት ትንሣኤ ተሳታፊ ሆኖ– ወደ መንግሥተ ሰማይ ወይም፥ አሊያም የፍርድ ትንሣኤን በመሳተፍ- ወደ ገሃነም ይሄዳል (ዮሐ 5፡28-29)። ለሞቱብን አማኞች እናለቅሳለን፥ ነገር ግን ለመዳን ዕድል ላላቸው ያላመኑ ሰዎችም ማልቀስ ይገባናል! ትንሣኤን እውነታ የሚያደርገው ለወንጌል የሚደረገው መነሣሣት ነው። 

መከራ (15፡30-32)። በየዕለቱ እሞታለሁ የሚለው በሮሜ እንዳለው «ለኃጢአት እንደሞታችሁ» የሚለውን የሚያመለክት ሳይሆን፥ ጳውሎስ የክርስቶስ አገልጋይ ሆኖ በሥጋው የገጠመውን አደጋ የሚያሳይ ነው (2ኛ ቆሮ. 4፡8-5፡10፤ 11፡23-28)። ከጠላቶቹ አቅጣጫ የሚያቋርጥ አደጋ ነበረበት፡ በመሆኑም ከአንድ ጊዜ በላይ ለሞት ተቃርቦ ነበር። ሞት ሁሉን ነገር የሚገላግል ከሆነ ለምን መከራን መታገሥ ያስፈልጋል? «ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ» (ኢሳ. 22፡13)። 

በዚህ ሕይወታችን በሥጋ የምናደርገው በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ሊታይ ይቀርባል (2ኛ ቆሮ. 5፡10)። እግዚአብሔር ሰውን የሚፈርደው ከምልዓተ ስብእናው አኳያ እንጂ «ነፍሱን» ብቻ አይደለም። ሥጋ በደኅንነት ተካፋይ ነው (ሮሜ 8፡18-23)። መከራን በሥጋ የታገሠ በትንሣኤ ጊዜ ክብርን ይቀዳጃል (2ኛ ቆሮ. 4፡7-18)። ለሥጋ ምንም መጻኢ ተስፋ ከሌለው፥ ስለ ክርስቶስ መሠቃየትና መሞት ለምን አስፈለገ? 

ከኃጢአት መለየት (15፡33-34)። ትንሣኤ ከሌለ በሥጋችን የምናደርገው ነገር በመጻኢ ዕድላችን ላይ ምንም ተጽዕኖ አይኖረውም። ዝሙት በቆሮንቶስ የተለመደ አኗኗር ነበር፥ በመሆኑም ከአማኞች አንዳንዶቹ ኃጢአታቸውን ትክክለኛ ለማድረግ ትንሣኤን ትተውት ነበር። «ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል» የሚለው ከግሪኩ ገጣሚ መንደር የተወሰደ ጥቅስ ነው፥ አባባሉ ለጳውሎስ አንባቢያንም እንግዳ አልነበረም። የአማኝ ሰውነት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለሆነ ከዓለም ኃጢአት የተለየ መሆን አለበት (2ኛ ቆሮ. 6፡14-7፡1)። «ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር» መተባበር (ኤፌ. 5፡6-17) የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ማርክስ ነው። 

ጊዜው ለቆሮንቶሳውያን የሚነቁበትና የሚነጹበት ነበር (1ኛ ተሰ. 5፡4-11ን ተመልከት።» ከኃጢአት ጋር ድርድር የሚመሠርት አማኝ በዙሪያው ላሉ ለሚጠፉት «የእግዚአብሔር እውቀት ለሌላቸው ሰዎች» ምስክርነት የለውም። ብዙዎች ያለ ክርስቶስ እየሞቱ በኃጢአት ውስጥ በራስ ወዳድነት መኖር ምንኛ አሳዛኝ ነገር ነው! 

ሞት (15፡49-57)። ሰማያዊ መንግሥት አሁን ለለበስነው ዓይነት የሥጋና ደም አካል የተሠራ አይደለም። ስለዚህ ኢየሱስ በሚመለስበት ጊዜ ሕያው የሆኑ አማኛች አካላት ከመቅጽበት ተለውጠው የእርሱን አካል ይመስላሉ (1ኛ ዮሐ 3፡1-3)፥ የሞቱት አማኞች በአዲስና በከበረ አካል ይነሣሉ። አዲሱ አካላችን የሚበሰብስና የሚሞት አይደለም። 

የሳይካይትሪ መሥራች የሆነው ሲግመንድ ፍሩድ እንዲህ ብሎ ጽፎአል። «በመጨረሻም እስካሁን ድረስ መድኃኒት ያልተገኘለትና ምናልባትም ለምን ጊዜውም የማይገኝለት፥ አሠቃቂው የሞት እንቆቅልሽ እንዳለ ነው።» ክርስቲያኖች በሞት ውስጥና በሞት ላይ ድል አድራጊነት አላቸው! ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ትንሣኤው ያገኘው ድል ስለሆነ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፥ «እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ» (ዮሐ 14፡19)። 

ኃጢአት፥ ሞት እና ሕግ አብረው ይሄዳሉ። ሕግ ኃጢአትን ይገልጣል፥ የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው» (ሮሜ 6፡23)። ኢየሱስ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ (1ኛ ጴጥ. 2፡24)፥ እንደዚሁም የሕግን መርገም ተሸከመ (ገላ 3፡13)። ይህ ድል ያለን በእርሱ በኩል ነው፤ ደግሞም ድሉን ዛሬ እንጋራዋለን። የቁጥር 57 ቀጥተኛ ትርጉም፥ «ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን» የሚል ነው። ለእርሱ በተሰጠን መጠን «የትንሣኤውን ኃይል በሕይወታችን እንለማመዳለን (ፊልጵ. 3፡10)። 

ቁጥር 58 የጳውሎስ የውዳሴ መዝሙርና ለቤተ ክርስቲያን የማሳረጊያ ምክሩ ነው። ክርስቶስ በሞት ላይ ከተቀዳጀው የድል ዋስትና የተነሣ፥ ለእርሱ ከምናደርገው አንዱም እንኳ እንደማይጠፋ እናውቃለን። ድካማችን ከንቱ አለመሆኑን ስለምናውቅ፥ በአገልግሎታችን የጸናን፥ በመከራ የማንናወጥ፥ ለሌሎች አገልግሎት የሚበዛልን ልንሆን እንችላለን። ሰሎሞን 38 ጊዜ ለተጠቀመበት ከንቱ የሚል አሳዛኝ የመክብብ ቃል ቁጥር 58 ምላሽ ነው። «የከንቱ ከንቱ፥ ሁሉም ከንቱ ነው!» ሲል ሰሎሞን አለቀሰ፤ ነገር ግን ጳውሎስ የድል መዝሙር ዘመረ!

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: