ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው? (1ኛ ቆሮ. 15፡35-48)

ፈላስፋዎች እንደ መሆናቸው፥ ግሪኮች የሰው ሰውነት ትንሣኤ ጉዳይ የማይቻል ነው የሚል አቋም ነበራቸው። ለነገሩ፥ ሰውነት ወደ አፈር ከተለወጠ በኋላ፥ ሌሎች አካላት ምግብ የሚያገኙበት መሬት ይሆናል። በአጭሩ፥ የምንበላው ምግብ በጣም ከቀደሙ ትውልዶች አካል የተገኙ ንጥረ ነገሮችን ያካተተ ነው። የሮድ ደሴት መሥራች የሆነው ሮጀር ዊልያምስ ፍራሽ አካል በተቆፈረ ጊዜ፥ በአቅራቢያው የነበረው የፖም ዛፍ ሥር የሰቀለው በአስከሬኑ ሣጥን ውስጥ እንደሆነ ታየ። እስከተወሰነ ደረጃ ከዛፉ ፍሬ የበሉ ሰዎች ሥጋውን ተጋርተዋል ማለት ነው። እንግዲህ በትንሣኤ ቀን እነዚህን ልዩ ልዩ ንጥረ ነገሮች የእኔ ናቸው የሚል እርሱ ማን ነው? 

ለዚህ ዓይነቱ የምክንያት አሰጣጥ የጳውሎስ ምላሽ «አንተ ሞኝ!» የሚል የድፍረት አነጋገር ነበር። ከዚያም በጣም ጠቃሚ የሆነውን ነጥብ ማለትም ትንሣኤ እንደገና መገንባት አለመሆኑን ገለጸ። በትንሣኤ ወቅት፥ እግዚአብሔር የተበታተኑትን ክፍሎች ገጣጥሞ» የድሮውን አካላችንን እንደሚመልስልን መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ስፍራ አያስተምርም። ቀጣይነት ያለው (አካላችን ነውና)፥ ነገር ግን እንድ አይደለም (ከነበረን ጋር ተመሳሳይነት የለውም)። 

እንዲህ ያሉ ተአምራት ሊብራሩ እንደማይችሉ ጳውሎስ ስላወቀ፥ ዶክትሪኑን ግልጽ ለማድረግ ሦስት ንጽጽሮችን ተጠቀመ። 

ዘር (15፡35-38፥ 42-48)። ዘርን በምትዘራበት ጊዜ በመከር ወቅት ያው ዘር እራሱ እንደሚመለስ አትጠብቅም። ዘሩ ይሞታል፥ ነገር ግን ከሞቱ ሕይወት ይወጣል። (ጌታችን ይኸንኑ ንጽጽር ስለመጠቀሙ ዮሐ 12፡23-28ን ተመልከት።) የዘራኸው ጥቂት የስንዴ ዘር ሊሆን ይችላል፥ ነገር ግን ተክሉ በሚደርስበት ጊዜ ብዙ ፍሬ ታገኛለህ።

በተጨማሪም፥ በመከር ጊዜ የሚገኘው በአብዛኛው ከተዘራው ይልቅ የበለጠ ውብ ነው። ይህ በተለይ የቱሊፕ አበባን (የድንች አበባ ዓይነት) በተመለከተ እውነት ነው። እንደ ቱሊፕ ሥር የሚያስጠሉ ቢኖሩ ጥቂት ነገሮች ናቸው፥ እንዲህም ሆኖ በጣም የሚያምር አበባ ያወጣል። በትንሣኤ ጊዜ እግዚአብሔር እኛን መልሶ የሚገጣጥም ከሆነ ምንም መሻሻል አይኖርም። በተጨማሪ፥ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። በመንግሥተ ሰማይ ልንረካበት የምንችለው ብቸኛ መንገድ ለዚያ አካባቢ የሚስማማ አካል ማግኘታችን ነው። 

ከቁጥር 42-48 ባለው ጳውሎስ የዚህን ድንቅ ለውጥ ዝርዝር ነገር ያወሳል። ሥጋ የሚጠፋ ሆኖ (በመቅበር) ይዘራል፥ ምክንያቱም ይበሰብሳልና፤ ነገር ግን ሊበሰብስ በማይችል ተፈጥሮ ይነሣል። በመንግሥተ ሰማይ መበስበስ ወይም ሞት የለም። በውርደት ይቀበራል (ከአስከሬን ባለሙያው የማስዋብ ጥበብ ባሻገር)፤ ነገር ግን በትንሣኤ አካል ኃይል ይኖረዋል። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንሆናለን! 

ዛሬ ያለን አካል «ተፈጥሮአዊ አካል» ነው፥ ይህም ማለት ለምድራዊ አካባቢ የሚስማማ ማለት ነው። ይህን አካል የተቀበልነው ከመጀመሪያው ወላጃችን ከአዳም ነው። እርሱ የተበጀው ከአፈር ነበርና እኛም እንዲሁ ነን (ዘፍጥ. 2፡7)። ነገር ግን የትንሣኤ አካል የሚስማማው ለመንፈሳዊ አካባቢ ነው። ኢየሱስ በትንሣኤ አካሉ፥ ከቦታ ቦታ በፍጥነት መሄድ ይችል ነበር፥ ደግሞም በተቆለፈ በር ማለፍ ችሏል። እንዲህም ሆኖ ምግብ መብላት ይችል ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ነክተው ዳስሰው ሊያውቁት ይችሉ ነበር (ዮሐ 20፡19-29፤ ሉቃ. 24፡33-43)። 

ጳውሎስ ያሳይ የነበረው ነጥብ በቀላሉ ይህ ነው። የትንሣኤ አካል የቤዛነትን ሥራ የሚያጠናቅቅና የአዳኛችን መልክ የሚሰጠን ነው። ውስጠ ሰውነታችንን በተመለከተ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረናል፥ ነገር ግን ሥጋችንን በተመለከተ የተወለድነው ከአዳም ነው። አንድ ቀን ክብሩን በምንጋራበት ወቅት የአዳኛችን መልክ እንለብሳለን። 

ቁጥር 46 ጠቃሚ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህን ያስቀምጣል። መጀመሪያ «ፍጥረታዊው» (መሬታዊው)፥ ከዚያም «መንፈሳዊው» (ሰማያዊው)። የመጀመሪያው ልደት ተፈጥሮአዊውን፥ ነገር ግን ሁለተኛው ልደት መንፈሳዊውን ይሰጠናል። እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ልደት፥ ተፈጥሮአዊውን ውድቅ በማድረግ፥ «ዳግም ተወለዱ!» ይላል። ቃኤልን ትቶ አቤልን ተቀበለ። የአብርሃምን በኩር ልጅ እስማኤልን ትቶ፥ ሁለተኛውን ልጅ ይስሐቅን መረጠ። ኤሳውን ትቶ ያዕቆብን መረጠ። በመጀመሪያው ልደታችን ላይ ከተደገፍን፥ ለዘላለም እንኮነናለን፤ ነገር ግን አዲስ ልደትን ከተለማመድን፥ ለዘላለም እንባረካለን። 

ሥጋ (15፡39)። ጳውሎስ እዚህ ላይ የተለያዩ እንስሳት የሴል አወቃቀር የተለየ ነው የሚለውን ሳይንስ አስቀድሞ ደረሰበት፤ ስለዚህም የተለያዩ ዝርያዎችን በዘፈቀደ ማራባት አይቻልም። የሰው ሥጋ አንድ ዓይነት ተፈጥሮ አለው፤ እንስሳት፥ አዕዋፋት እና ዓሣዎች የራሳቸው የሆነ ልዩ ሥጋ አላቸው። ድምዳሜው ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተለያዩ ዓይነት ሥጋ ለሰው፥ ለእንስሳት፥ ለአዕዋፋት እና ለዓሣዎች መሥራት ከቻለ በትንሣኤ ጊዜ ለእኛስ የተለየ አካል መሥራት ምን ያቅተዋል? (መፍቀረ እንስሳት አስተውሉ፥ እዚህ ላይ ጳውሎስ እንስሳት ከሞት ይነሣሉ ማለቱ አይደለም። እንደ ምሳሌነት ብቻ ነው የተጠቀማቸው።) 

ሰማያዊ አካል (15፡40-41)። መሬታዊ አካላት ብቻ ሳይሆኑ ሰማያዊ አካላትም አሉ፤ እርስ በርስም የተለያዩ ናቸው። እንዲያውም፥ ሰማያዊ አካላት በሰብአዊ ዓይን ሲታዩ እርስ በርስ በክብር ይለያያሉ። ጳውሎስ እዚህ ላይ አሳብ የሚሰጠው ምንም እንኳ ሁሉም ክርስቲያኖች የከበሩ አካላት ቢኖሩአቸውም፥ እማኝ ከአማኝ በክብር ይለያል። በመንግሥተ ሰማይ ሁሉም ጽዋዎች የሞሉ ይሆናሉ፥ ቅዱሳኑ በምድር ላይ በነበሩ ጊዜ በፈጸሙት ታማኝነትና መሥዋዕትነት የተነሣ፥ የአንዳንዶቹ ጽዋዎች ከሌሎች ይበልጣሉ። 

እነዚህ ምሳሌዎች ስለ ትንሣኤ አካል ያሉንን ጥያቄዎች በሙሉ ላይመልሱ ይችላሉ፥ ሆኖም ግን የሚያስፈልጉንን ዋስትናዎች ይሰጡናል። እግዚአብሔር ለእኛ በመንግሥተ ሰማይ ለሚኖረን ሕይወት የሚስማማ የከበረ አካል ይሰጠናል። የፀሐይ ክብርና የእንጉዳይ ክብር አንድ እንዳልሆነ ሁሉ በጥራቱ አሁን እንደያዝነው ዓይነት አካል አይሆንም። ይህን አዲስ አካል ለዘላለም እግዚአብሔርን ለማክበርና ለማገልገል እንጠቀምበታለን። 

ይህ ሐተታ በጳውሎስ የተጻፈው የአማኞችን የማወቅ ጥማት እንዲያው ለማርካት እንዳይደለ ማስታወስ አለብን። የሚያስተላልፋቸው ተግባራዊ ነጥቦች ስለነበሩት ነው። እነዚህን ከ 29-34 ባሉት ቁጥሮች ግልጽ አድርጎአቸዋል። በአካል ትንሣኤ በእውነት ካመንን፥ ዛሬ አካሎቻችንን ለእግዚአብሔር ክብር እንጠቀምባቸዋለን (6፡9-14)። 

በመጨረሻ ም፥ የጠፉትም ለገሃነም ስፍራቸው የሚስማማ አካል ይሰጣቸዋል። በጨለማ ውስጥና በሕመም ለዘላለም ይሠቃያሉ (ማቴ. 25፡41፤ 2ኛ ተሰ. 1፡7-10፤ ራእይ 20፡11-15)። የዳንን ሁላችን ከፍርድ ልናስጥላቸው መፈለግ ይገባናል! «እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን» (2ኛ ቆሮ. 5፡1)። 

አዳኝህን አምነህ የማታውቅ ከሆንህ፥ ጊዜው ሳያልፍብህ አሁኑኑ እመን!

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading