ሙታን ይነሣሉን? (1ኛ ቆሮ. 15፡1-19)

ቆሮንቶስ የግሪክ ከተማ ነበረች፤ ግሪኮች ደግሞ በሙታን ትንሣኤ አያምኑም ነበር። ጳውሎስ በአቴና ሲሰብክና የክርስቶስን ትንሣኤ እውነታ ባወጀ ጊዜ፥ ከአድማጮቹ አንዳንዶቹ የምራቸውን ሳቁበት (የሐዋ. 17፡32)። አብዛኞቹ የግሪክ ፈላስፋዎች የሰውን አካል እንደ እስር ቤት ይቆጥሩ ስለነበር ሞትን ከባርነት መላቀቂያ አርነት እድርገው ተቀበሉት። 

ይህ የጥርጣሬ አመለካከት፥ በሆነ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ወርሮ ስለነበር ጳውሎስ ግንባር ለግንባር መግጠም ግድ ሆነበት። የትንሣኤ እውነት ችላ ለማለት የማያስችል ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆነ ዶክትሪናዊና ተግባራዊ አንድምታ ነበረው። ጳውሎስ አራት መሠረታዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ጉዳዩን አብራራው። 

ሙታን ይነሣሉን? (1ኛ ቆሮ. 15፡1-19) 

በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች/አማኞች በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ያምኑ እንደነበር ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው፤ በመሆኑም ጳውሎስ መሠረታዊውን እውነት አንተርሶ ማሳመኛውን ጀመረ። ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ከሞት መነሣቱን ለአንባቢያኑ ለማስረገጥ ሦስት ማረጋገጫዎችን አቀረበ። 

ማረጋገጫ ቁጥር 1- የእነርሱ ደኅንነት (15፡1-2)። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ መጥቶ የወንጌልን መልእክት ሰብኮኦል፤ በመሆኑም እምነታቸው ሕይወታቸውን ለውጦታል። ነገር ግን በጣም አስፈላጊው የወንጌል መልእክት ክፍል የክርስቶስ ትንሣኤ እውነታ ነበር። ለነገሩማ፥ ሙት አዳኝ እኮ ማንንም ማዳን አይችልም። የጳውሎስ አንባቢያን ቃሉን ተቀብለው፥ ክርስቶስን አምነው ድነው እና ለደኅንነታቸው ማረጋገጫ በቃሉ ላይ ቆመው ነበር። ጸንተው የመቆማቸው እውነታ እምነታቸው እውነተኛና ባዶ ላለመሆኑ ማረጋገጫ ነበር። 

ማረጋገጫ ቁጥር 2- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት (15፡3-4)። ከሁሉ በፊት ማለት «በተፈላጊነቱ የመጀመሪያ» ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን ከምታውጀው ሁሉ ወንጌል እጅግ አስፈላጊው መልእክት ነው። በማኅበራዊ ተግባርና የሰው ልጆችን መሻሻል በሚመለከት ነገር ውስጥ ተሳታፊ መሆን መልካም ሲሆን፥ እነዚህ አገልግሎቶች ግን ወንጌልን የሚከላከሉበት ምንም ምክንያት የለም። «ክርስቶስ ሞተ . . ተቀበረ . . . ተነሣ. . . ታየ» የሚሉት ወንጌል የሚቆምባቸው (ቁ. 3-5) መሠረታዊ የታሪክ እውነታዎች ናቸው። «ክርስቶስ ለኃጢአታችን ሞተ» የሚለው ለእነዚህ ታሪካዊ እውነታዎች ሥነ መለኮታዊ ማብራሪያ ነው። ብዙ ሰዎች በሮማውያን ተሰቅለዋል፤ ነገር ግን ለዓለም ኃጢአት የሞተ ቢኖር አንድ «ምስኪን» ብቻ ነው። 

ጳውሎስ «መጽሐፍ እንደሚለው» (ቁ. 3) ብሎ ሲጽፍ ያመለከተው የብሉይ ኪዳንን መጽሐፍ ነበር። በብሉይ ኪዳን የነበሩ ብዙዎች ሥርዓተ መሥዋዕቶች ክርስቶስ የእኛ ምትክና አዳኝ ሆኖ እንደሚሠዋ ያመለክቱ ነበር። ዓመታዊው የማስተሰሪያው ቀን (ዘሌዋ. 16) እና እንደ ኢሳይያስ 53 ያሉ ትንቢቶችም ትውስ ይላሉ። 

ነገር ግን ብሉይ ኪዳን የእርሱ ትንሣኤ በሦስተኛው ቀን እንደሚሆን የት ላይ ነው የሚናገረው? ኢየሱስ ወደ ዮናስ ልምምድ (ማቴ. 12፡38-41) አመለከተ። ጳውሎስ የክርስቶስን ትንሣኤ «ከመከር በኩራት» ጋር አነጻጸረ፤ የመከር በኩራት ደግሞ ለእግዚአብሔር የሚቀርቡት ከፋሲካ በኋላ ሰንበትን ተከትለው ነበር (ዘሌዋ. 23፡9-14፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡23)። ሰንበት ሁልጊዜ ሰባተኛ ቀን መሆን ስላለበት፥ ከሰንበት በኋላ ያለው ቀን የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፥ ወይም እሑድ የጌታችን ትንሣኤ ቀን ነው። ይህ በአይሁድ የቀን አቆጣጠር ሦስት ቀናትን ይሸፍናል። ከመከር በኩራት በዓል ሌላ፥ ስለ መሲሑ ትንሣኤ በብሉይ ኪዳን ሌሎች ትንቢቶችም ነበሩ። መዝ. 1(6)፡ 8-11፤ (የሐዋ. 2፡25-28ን ተመልከት)፤ መዝ. (22)፡22 (ዕብ. 2፡12ን ተመልከት)፤ ኢሳይያስ 53፡10-12፥ እና መዝ. 2፡7 (የሐዋ. 13፡32-33ን ተመልከት)። 

ማረጋገጫ ቁጥር 3- ክርስቶስ ለምስክሮች ታይቶአል (15፡5-11)። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በማያምኑ ሰዎች ዓይን ፊት ተጋልጦአል፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ፥ ስለ ትንሣኤው ምስክር ሊሆኑ በሚችሉ አማኞች ታይቶአል (የሐዋ. 1፡22፤ 2፡32፤ 3፡15፤ 5፡32)። ጴጥሮስ አየው፤ ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ በጋራ አዩት። ያዕቆብ ጌታ ከታየው በኋላ ያመነ በግማሽ ጎኑ የጌታ ወንድም የሆነ ሰው ነው (ዮሐ. 7፡5፤ የሐዋ. 1፡14)። አምስት መቶዎችና ወንድሞች ሁላቸውም በአንድ ጊዜ አዩት (ቁ 6)፤ በመሆኑም ቅዠት ወይም ማጭበርበር ሊሆን የሚችልበት መንገድ አልነበረውም። ይህ ሁኔታ ልክ ከማረጉ በፊት (ማቴ. 28፡16) ሳይሆን አይቀርም። 

ነገር ግን ከታላቅ ምስክሮች አንዱ ጳውሎስ ራሱ ነበር፤ ምክንያቱም አማኝ ባልነበረበት ወቅት ኢየሱስ ስለ መሞቱ እርግጠኛ ነበር። በሕይወቱ የተከሰተው ሥር ነቀል ለውጥ-ስደትና መከራን ያስከተለበት ይህ ለውጥ-በእርግጥ ጌታ ከሞት ለመነሣቱ የማያጠራጥር ማረጋገጫ ነበር። ጳውሎስ የእርሱ ደኅንነት የጠራ የእግዚአብሔር ጸጋ ሥራ መሆኑን ግልጽ አደረገ፤ ነገር ግን ጌታን በሚያገለግልበት ወቅት ይህ ጸጋ በእርሱ ውስጥና በእርሱ በኩል ሠርቷል። በትክክለኛ ጊዜ “ተወለደ” የሚለው ምናልባት እነርሱም እንደ ጳውሎስ መሢሑን በክብር የሚያዩበትን መጻኢ የእስራኤል ደኅንነት የሚያመለክት ይመስላል (ዘካ. 12፡10-13፡6፤ 1ኛ ጢሞ. 1፡16)። 

በዚህ ደረጃ ላይ፥ የጳውሎስ አንባቢያን «አዎን፥ ኢየሱስ ከሙታን እንደ ተነሣ እንስማማበታለን» ሳይሉ አልቀሩም። ጳውሎስም በበኩሉ፥ «ይህን ካመናችሁ፥ እንግዲያውስ የሞቱት ሁሉ ትንሣኤ እንደሚያገኙ ማመን አለባችሁ!» የሚል ምላሽ ሳይሰጣቸው አልቀረም። ክርስቶስ እንደ ሰው፥ እውነተኛ ሥጋ ለባሽ ሆኖ መጣ፤ እናም ኃጢአት ከመሥራት በቀር እኛ የተለማመድነውን በሙሉ ተለማምዷል። ተስማምቶአል። ትንሣኤ ከሌለ፥ እንግዲያስ ክርስቶስ አልተነሣም። እርሱ ካልተነሣ፥ የሚሰበክ ወንጌልም የለም። ወንጌልም ከሌለ፥ ያመናችሁት በከንቱ ነው፤ አሁንም በኃጢአታችሁ አላችሁ! ትንሣኤ ከሌለ፥ እንግዲያውስ የሞቱት አማኞች ተስፋ የላቸውም። ለዘላለም ዳግም አናያቸውም! 

ድምዳሜው ግልጽ ነው። በዚህ ሕይወት ሥቃይ ብቻ ከተረፈንና ለወደፊት የምንጠብቀው ክብር ከሌለን ለምን ክርስቲያን እንሆናለን? (ከ29-34 ባሉት ቁጥሮች፥ ጳውሎስ አሳቡን አስፋፋ።) ትንሣኤ አስፈላጊ ብቻ ላይሆን፤ የምናምነው ሁሉ በእርሱ ላይ የተተከለ ስለሆነ «የመጀመሪያ ተፈላጊነት» ያለው ነው።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: