ማሣው -ብዛት (1ኛ ቆሮ. 3፡5-9)

ጳውሎስ የእርሻ ምሳሌዎችን ይወድድ ነበር እናም ብዙ ጊዜ በደብዳቤዎቹ ይጠቀምባቸዋል። «እናንተ የእግዚአብሔር እርሻዎች ናችሁ» ማለት፥ «እናንተ የእግዚአብሔር የተዘጋጀ ማሣ ናችሁ፥ የእግዚአብሔር የአትክልት ስፍራ ናችሁ» ማለት ነው። በዘሪው ምሳሌ ላይ፥ ኢየሱስ የሰውን ልብ ከመሬት፥ ዘሩን ደግሞ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አነጻጽሮታል (ማቴ. 13፡1-9፥ 18-23)። ጳውሎስ ይህን ግላዊ ምሳሌ ወስዶ የጋራ አደረገው፥ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ፍሬ ማፍራት የሚገባት ማሣ ናት። የወንጌል አገልግሎት ሥራ መሬቱን ማዘጋጀት፥ ዘርን መዝራት፥ ቡቃያውን ውኃ ማጠጣት፥ እና ፍሬውን መሰብሰብ ነው። 

ይህ የ «ማሣነት» የቤተ ክርስቲያን ምስል ለቆሮንቶስ ልዩ ችግር ተግባራዊ የሚሆነው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ አጽንኦቱ መደረግ ያለበት በሠራተኞቹ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ነው። ጳውሎስ ና እጵሎስ የተመደበላቸውን ሥራ የሚሠሩ አገልጋዮች ብቻ ነበሩ። ለልፋታቸው ሕይወትን የሰጠው እግዚአብሔር ነበር። የአማኞቹ እምነትም እንኳ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው (ቁ 5)። አትኩሮትን በአገልጋዮቹ ላይ ማድረግ ስሕተት ነበር። ይልቅ የበረከት ሁሉ ምንጭ ወደሆነው ወደ መከሩ ጌታ ተመልከት። 

በዚህ አንቀጽ ብዛት ወይም እድገት ላይ የተደረገውን አጽንኦት ልብ በል። ለምን ሰባኪያንን ወይም ስታቲስቲኮችን እናወዳድራለን? የእድገቱ መንስኤ እግዚአብሔር ነው፤ ለዚህ ማንም ክብርን ሊቀበል አይችልም። በተጨማሪም፥ ማንም ሁሉንም ተፈላጊ ሥራዎች መሥራት አይችልም። ጳውሎስ ዘሩን ዘራው፥ እጵሎስ ውኃ አጠጣው፥ ነገር ግን ያሳደገው እግዚአብሔር ብቻ ነበር (ቁ. 6)። 

ከዚህ ምሳሌ ሦስት ዐበይት ትምህርቶች ይመነጫሉ። 

የመጀመሪያው፥ የወንጌል አገልግሎት ፈርጀ ብዙነት። አንዱ ሠራተኛ መሬቱን ያርሳል፥ ሌላኛው ዘሩን ይዘራል፥ ሦስተኛው ዘሩን ውኃ ያጠጣዋል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፥ ቡቃያው ያድጋል፥ ፍሬው ይደርሳል፥ ሌሎች ሠራተኞች ደግሞ መከሩን በመሰብሰብ ይደሰቱበታል። ይህ በፈርጀ ብዙነት ላይ የተደረገው አጽንኦት ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ብዙ ብልቶች ካሉት አካል ጋር በሚያነጻጽርበት ጊዜ ይነሣል። 

ሁለተኛ፥ የዓላማ አንድነት። አንድ ሰው ምንም ዓይነት ሥራ ለጌታ ይሥራ፥ የመከሩ ተካፋይ ነው። «የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው» (ቁ.8)። ጳውሎስ፥ አጵሎስና ጴጥሮስ እርስ በርስ እይወዳደሩም ነበር። በዚህ ፈንታ እያንዳንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነት ሥር የተመደበለትን ሥራ ይሠራ ነበር። ምንም እንኳ የአገልግሎት ፈርጀ ብዙነት ቢኖርም፥ የዓላማ አንድነት አለ፤ ደግሞም የመንፈስ አንድነትም ሊኖር ይገባል። 

ሦስተኛ፥ የትሕትና አስፈላጊነት። መከሩ እንዲደርስ የሚያደርጉት ሰብአዊ ሠራተኞች ሳይሆኑ የመከሩ ጌታ ነው። «እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር. . . የሚያሳድግ እግዚአብሔር» (ቁ 6-7)። እግዚአብሔር ሰዎች በምድር የእርሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ መወሰኑ የተረጋገጠ ነው፤ ሆኖም ግን የእነርሱ ጥረት ያለ እግዚአብሔር በረከት ውድቀት ነው። ቆሮንቶሳውያን በቤተ ክርስቲያናቸው ይኮሩ ነበር፤ በጉባኤው ያሉ ልዩ ልዩ ቡድኖች በመሪዎቻቸው ይመኩ ነበር። ይህ በትዕቢት «የመነፋት» ዝንባሌ እግዚአብሔር ክብርን እንዳይቀዳጅ ይከላከል ስለነበር ቤተ ክርስቲያንን ከፋፍሎአታል። 

ኢየሱስም በዮሐንስ 4፡34-38 በተዘገበው ይኸንኑ አሳብ ተናግሮአል። ዘሪና መከር ሰብሳቢ አንድ ላይ የሚሠሩ ብቻ ሳይሆኑ፥ ነገር ግን በአንድነት የሚደሰቱ እና የየድርሻቸውን ዋጋ የሚቀበሉ ናቸው። የብቻ አገልግሎት የሚባል ነገር የለም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሠራተኛ በሌሎቹ ሥራ ውስጥ መግባቱ ስለማይቀር ነው። እኔ ፍጹም እንግዶች የሆኑ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ የመምራት ዕድል ገጥሞኝ ያውቃል፤ ነገር ግን ሌሎች ዘሩን ዘርተው በፍቅራቸውና በጸሎታቸው አጠጥተውታል። 

«እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል» (1ኛ ቆሮ. 3፡8)። ሰዎች አላስፈላጊ አድርገው የሚቆጥሩትን አገልግሎታችንን እግዚአብሔር ታላቅ አድርጎ ይቆጥረዋል። ዋጋችን የሰዎች ውዳሴ ሳይሆን የመከሩ ጌታ «ጎሽታ» ሊሆን ይገባዋል። 

እግዚአብሔር ማሣው እንዲያድግ ይፈልጋል። እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ፍሬ (ገላ 5፡22-23)፥ ቅድስና (ሮሜ 6፡22)፥ ድሆችን መርዳት (ሮሜ 15፡26)፥ በጎ ሥራ (ቆላ. 1፡10)፥ ለእግዚአብሔር ምስጋና መሠዋት (ዕብ 13፡15)፥ እና ነፍሳትን ማፍራት (ሮሜ 1፡13) እንዲኖራት እግዚአብሔር ይፈልጋል። ከመንፈሳዊ እድገት ጋር አብሮ የሚቆጠር አኃዛዊ እድገት መኖር አለበት። አንድ ፍሬ በውስጡ ለብዙ ፍሬዎች የሚሆን ዘር ይይዛል። የአገልግሎታችን ፍሬ እውነተኛ ከሆነ፥ በመጨረሻ ለእግዚአብሔር ክብር «ብዙ ፍሬ…» ያፈራል (ዮሐ 15፡1-8)። 

በአገልግሎት የተሰማሩ ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን «መሬት» የማያቋርጥ ክብካቤ ማድረግ አለባቸው። አንድን መከር ለማግኘት በርትቶ መሥራትን ይጠይቃል። ሰነፉ ሰባኪ ወይም የሰንበት አስተማሪ ሰሎሞን በምሳሌ 24፡30-34 የጻፈውን ታካች ገበሬ ይመስላል። ሰይጣን አለመስማማትን፥ ውሸትን፥ እና ኃጢአትን ለመዝራት በመጣደፍ ላይ ነው፤ በመሆኑም መሬቱን በማዘጋጀት ና መልካሙን የእግዚአብሔር ቃል በመዝራት ሥራ የሚበዛብን መሆን እለብን።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: