ማነጽ (1ኛ ቆሮ. 14፡1-5፥ 26)

ጳውሎስ ስለ መንፈስ ስጦታ፥ ስለ መንፈስ ስጦታዎች እና ስለ ጸጋ ስጦታዎች አውስቶአል። አሁን ደግሞ በማኅበር የአምልኮ ስብሰባዎች መንፈስን ስለ መግዛት በማውሳት ይህን ክፍል አጠቃለለ። አንዳንድ ቆሮንቶሳውያን ስጦታዎቻቸውን በሚጠቀሙበት ጊዜ ራሳቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው ይመስላል፤ በመሆኑም ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን የማኅበር ስብሰባዎች ሊገዙበት የሚገቡ መሠረታዊ መርሆችን እስቀመጠላቸው። እነዚህም ሦስት ናቸው-ማነጽ፥ ማስተዋል እና ሥርዓት። 

ማነጽ (1ኛ ቆሮ. 14፡1-5፥ 26) 

ይህ ጳውሎስ ከሕንጻ ጥበብ (አርክቴክቸር) የተዋሰው እና ከሚወዳቸው ቃላት አንዱ የሆነ ነው። ማነጽ ማለት «መገንባት» ማለት ነው። ይህ ጽንሰ ሃሳብ ቤተ ክርስቲያን እንደ «አካል» ከምትገለጽበት ምሳሌ የራቀ አይደለም። ዛሬም እንኳ ቢሆን ስለ አካል ገንቢ እንቅስቃሴዎች እንነጋገራለን። እዚህ ላይ የምሳሌዎችን መደራረብ እንመለከታለን፤ ምክንያቱም የክርስቶስ አካል የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ነው። ማነጽ የሚለውን ቃል ጳውሎስ መጠቀሙ የብልህነት አካሄድ ነበር። 

ቤተ ክርስቲያንን ችላ ብሎ ራስን ማነጽ ቆሮንቶሳውያን ተያይዘውት የነበረው ስሕተት ነው። ራሳቸውን እንጂ እማኝ ወገኖቻቸውን ለማነጽ አልፈቀዱም። ይህ አቋማቸው በእርግጥ የጎዳው ሌሎችን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን አድራጊዎቹንም ጭምር ነበር። ለነገሩ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ከሆንን፥ ከሌሎች ብልቶች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመጨረሻ እኛንም በግል ይነካናል። «ዓይን ለእጅ አታስፈልገኝም ሊል አይችልም» (12፡2)። የአካል አንድ ብልት የደከመ ወይም የታመመ ከሆነ ሁኔታው ሌሎችንም ብልቶች ይነካል። 

ቤተ ክርስቲያን ትንቢትን በመናቅ ትኩረቷን በልሳኖች ላይ ማድረጓን ጳውሎስ ደረሰበት። የአዲስ ኪዳንን ነቢይ መጻኢውን የሚናገር ሰው አድርገን ማሰብ የለብንም፤ የብሉይ ኪዳን ነቢያትም እንኳ ቢሆኑ ያደረጉት ከዚህ ያለፈ ነበር። ነቢያት የእግዚአብሔርን መልእክት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከመቅጽበት ተቀብለው፥ ሁልጊዜም ባይሆን ብዙ ጊዜ በልሳኖች ለቤተ ክርስቲያን ያስተላልፉ ነበር። ትንቢት ከዘመናችን «ስብከት» ጋር አንድ አልነበረም። ምክንያቱም የዛሬዎቹ ሰባኪያን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት መልእክቶቻቸውን የሚያዘጋጁ ናቸው። ማንም ሰባኪ ዛሬ ተነሥቶ ከእግዚአብሔር ቅጽበታዊ መሞላትን ተቀበልሁ ማለት አይገባውም። 

ጳውሎስ በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር እንደሚበልጥ ሁለቱን ስጦታዎች በማነጻጸር ያብራራል። 

ትንቢት ለሰዎች፥ ልሳኖች ደግሞ ለእግዚአብሔር ይናገራሉ (14፡1-3)። የጳውሎስ ምክር «ለመንፈሳዊ ስጦታዎች የምትጓጉ ከሆነ፥ ቢያንስ የሚበልጡትን ስጦታዎች ፈልጉ» የሚል ነበር። ትንቢት ቤተ ክርስቲያንን ስለሚያንጽ የበለጠ (የላቀ) ነበር። ሁሉም ሰው የሚፈልገውን -መበረታቻንና መጽናኛን ለአድማጮቹ ይሰጥ ነበር። 

ተርጓሚዎቻችን በቁጥር 2 ላይ ማንም የማያስተውለውን የሚለውን ማስገባታቸው የሚያሳዝን ነው። ምክንያቱም አዲስ ኪዳን «የማይታወቅ ልሳን» ብሎ ነገር አያውቅም። ከቤተ ክርስቲያን ጅማሬ አንሥቶ ልሳኖች የሚታወቁ፥ አድማጮቹ የሚያውቁአቸው ነበሩ (የሐዋ. 2፡4፡ 6፥8፥ 11)። ልሳኑ ለተናጋሪው ና ለአድማጮቹ ያልታወቀ ቢሆንም፥ ነገር ግን በዓለም ውስጥ ያልታወቀ አልነበረም (14፡10-11፡2)። 

ሰዎች ልሳኖች ለጠፉት ወንጌልን ለመስበክ ይጠቅማሉ ብለው ማሰባቸው አሳዛኝ ነገር ነው። እውነቱ ግን የዚህ ተቃራኒ ነበር። ጳውሎስ የሰጋው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመጠን ያለፈ የልሳኖች ንግግር እንዳይኖር ነበር። ምክንያቱም ያልዳኑ ሰዎች ክርስቲያኖች እብዶች ናቸው! (14፡23) ብለው ወደ ማመን እንዳይገፋፉ ነበር። በጴንጤቆላው ቀን፥ አማኞች «የእግዚብሔርን ድንቅ ሥራ» ያከበሩ ቢሆንም ጴጥሮስ ግን ወንጌልን የሰበከው ሁሉም አድማጮች በሚሰሙት በአራማይክ ቋንቋ ነበር። 

በልሳን የሚናገር አማኝ በውዳሴ እና በአምልኮ ለእግዚአብሔር ይናገራል፤ ነገር ግን ትንቢት የሚናገር እማኝ ቃሉን ለቤተ ክርስቲያን ያካፍላል፤ የሚሰሙትንም ይደግፋቸዋል። ይህ ደግሞ ወደ ሁለተኛው ንጽጽር ይመራል። 

ትንቢት ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል፥ ልሳን ተናጋሪውን ብቻ ያንጻል (14፡4-5)። ጳውሎስ ልሳን ለተናጋሪው ያለውን ዋጋ አልካደም። ነገር ግን እርሱ ከፍተኛ ዋጋ የሰጠው ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ ነው። «በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል» (ቁ 5)። ልሳኖቹ እስካልተተረጎሙ (12፡10፥30)፥ መልእክቱ ለቤተ ክርስቲያን ምንም አይጠቅምም። ጳውሎስ የልሳኖች ስጦታ ተግባራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ ተርጓሚ መኖር እንዳለበት ያመለክታል (14፡28)። 

የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአገልግሎት ወቅት መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ስጭናቸው ላይ አድርገው ይከታተሉ የነበረ እንዳይመስልህ። ምክንያቱም አዲስ ኪዳን ገና በመጻፍ ላይ ነበር፤ የብሉይ ኪዳን ጥቅሎችም ደግሞ ውድ ስለነበሩ በአብዛኛዎቹ አማኞች እጅ አልገቡም። በመሆኑም እግዚአብሔር ለሕዝቡ በቀጥታ በነቢያት በኩል ይናገር ነበር፤ መልእክቱም አንዳንዴ በልሳኖች ይሰጥ ነበር። ሦስቱም የእውቀት፥ የትንቢትና የልሳኖች ስጦታዎች እውነትን ለሕዝቡ ለማድረስ በጋራ ይሠሩ ነበር (13፡1-2፥ 8-11)። 

ጳውሎስ የዶክትሪን ትምህርት ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ስለመሆኑ አጽንኦት ሰጠ። አምልኮአችን በእውነት ላይ መመሥረት አለበት፤ አለበለዚያ መነሻው የማይታወቅ ጭፍን ስሜታዊነት ብቻ ሆኖ ይቀራል። ክርስቲያኖች የሚያምኑትን እና ለምንስ እንደሚያምኑት ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ነቢይ እውነትን ከቤተ ክርስቲያን ጋር አብሮ በመካፈል ያንጻታል። በልሳኖች የሚናገር ሰው (ተርጓሚ ከሌለ) እግዚአብሔርን በማምለክ ይደሰታል፣ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን እያንጻትም። 

በራሴ አገልግሎት፥ በበርካታ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ና ኮንፈረንሶች መልእክት አካፍዬአለሁ። እናም ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት ለሕዝቡ ለመናገር ጥረት አድርጌአለሁ። ታዲያ አንዳንድ ጊዜ ዝማሬው ሳያንጽ ሲቀር ሌላ ጊዜ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ኃይል ባለው ሁኔታ ሲያስተላልፍ ተመልክቼአለሁ። ሁላችንም እንደ አገልጋዮች ለመዝናኛ ሳይሆን ለእነጻ ስምናልምበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሲባርክ ሕዝቡም ረድኤት ሲያገኝ እናያለን። የማያንጽ አገልግሎት የቱንም ያህል «መንፈሳዊ» ቢመስልም ያፈራርሳል። የእግዚአብሔርን ቃል ለእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት ስናብራራ እና ስናዛምድ፥ ያኔ የማነጽ አገልግሎት አለን ማለት ነው።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading